የጳጉሜ 6 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ ጳጉሜን 6 2015የጀርመን ብሔራዊ ቡድን በገዛ ሜዳው የገጠመው ሽንፈት አሰልጣኙን እንዲሰናበቱ አድርጓል ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ለአፍሪቃ የማጣሪያ የመጨረሻ ጨዋታውን በግብጽ ተሸንፏል ። ሞ ፋራህ አራተኛ ወጥቶ ከሩጫው ዓለም በተሰናበተበው የኒውካስል የግማሽ ማራቶን ፉክክር ኢትዮጵያዊው አትሌት ታምራት ቶላ አሸናፊ ሆኗል ። በሜዳ ቴኒስ የዩ ኤስ ፍጻሜ አሜሪካዊቷ ኮኮ ጋውፍ የመጀመሪያ ድሏን ተጎናጽፋ ዋንጫ አንስታለች ። በሴሬና ዊሊያምስ ድል የስምንት ዓመት ልጅ ሆና ስታዲየም ውስጥ በመገኘት በዳንስ ደስታዋን ስትገልጽ ለነበረችው ኮኮ የትናንቱ ድል የበርካታ ስፖርት አፍቃሪዎች መነጋገሪያ ሆኗል።
አትሌቲክስ
እንግሊዛዊው ሯጭ ሞ ፋራህ ከሩጫው ዓለም በተሰናበተበት የታላቁ የሰሜን ሩጫ በኒውካስል ከተማ የግማሽ ማራቶን የትናንቱ ውድድር ኢትዮጵያዊው አትሌት ታምራት ቶላ አሸናፊ ሆነ ። ታምራት ቶላ ውድሩን በአንደኛነት ለማጠናቀቅ የፈጀበት ጊዜ 59 ደቂቃ ከ58 ሰከንድ ነው ። ለቤልጂየም የሚሮጠው ሌላኛው ትውልደ ሶማሊያ አትሌት ባሺር አብዲ 61:20 በመሮጥ የሁለተኛ ደረጃ አግኝቷል ። ኢትዮጵያዊው አትሌት ሙክታር እድሪስ 61:54 ሰከንድ በመሮጥ 3ኛ ወጥቷል ።
ስድሳ ሺህ ግድም ተሳታፊዎች በነበሩበት በዚህ ታላቅ የሩጫ ውድድር ሞ ፋራህ አራተኛ ደረጃ ይዞ አጠናቋል ። የገባበት ሰአትም ከሙክታር አንድ ደቂቃ ከሰላሳ ሰከንድ በመዘግየት 63:24 ሰከንድ ሆኖ ተመዝግቧል ። በዚህም ውድድር ሞ ፋራህ በጡረታ መሰናበቱ ይፋ ሆኗል ።
በኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያዎች ባለድሉ፤ ትውልደ ሶማሊያዊው የብሪታንያ ሯጭ ሞ ፋራህ በለንደን ከተማ ውስጥ ከእሁዱ ውድድር በኋላ በጡረታ እንደሚሰናበት ቀደም ሲል ተናግሮ ነበር ።
«ለመናገር ይከብዳል፤ ግን በቃ ሲመስለን ውድድሩ ላይ ማተኮር ከዚያም እንደተጠናቀቀ ከቤተሰቦች ጋር ደስታውን ማጣጣም ። ከዚያም አዎ፤ የሚሆነው የሁላችንንም ስሜት የሚነካ ይመስለኛል ። ግን ደግሞ እዚያ የምንገኘው ቅጽበቱን ለማጣጣምም ነው ። ያለ ሕዝብና ድጋፍ አሁን የደረስሁበት የአትሌት ደረጃ ላይ አልደርስም ነበር። »
የሞ ፋራህ ስንብት
የ40 ዓመቱ ሞ ፋራህ በብሪታንያ ከፍተና ግምት የሚሰጠውን «ሰር» የሚል ማእረግ የተጎናጸፈ ነው ። ሞ ፋራህ የእርስ በእርስ ጦርነት ባዳቀቃት ሶማሊያ ተወልዶ የልጅነት ጊዜውን ያሳለፈው እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ነበር ። ለብሪታንያ ተሰልፎ በሮጠበት የሩጫ ዘመኑ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2012 እና 2016 በኦሎምፒክ ውድድር በአምስት እና በዐሥር ሺህ ሜትር ርቀቶች በሁለቱም ዘርፍ በተከታታይ የወርቅ ሜዳሊያዎችን ሰብስቧል ። ከዚያ ቀደም ብሎ ለስድስት ጊዜያት የዓለም እንዲሁም ለአምስት ጊዜያት የአውሮጳ ባለድል ለመሆን የበቃም ታላቅ አትሌት ነው ።
በእርግጥ ሞ ፋራህ የሩጫ ዘመኑ ሁሉ በስኬት ብቻ የተሞላ ነበር ማለት አይቻልም ። በአሰልጣኙ አልቤርቶ ሣላዛር የተነሳ በኃይል ሰጪ አበረታች ንጥረ ነገር በተደጋጋሚም ተጠርጥሮ ያውቃል ። በእርግጥ ይህ ነው የሚባል ማረጋገጫ ባይገኝበትም ማለት ነው ።
የነሐሴ 29 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የስፖርት ዘገባኒውካስል ከተማ ውስጥ በተከናወነው የትናንቱ የግማሽ ማራቶን የሴቶች የሩጫ ፉክክር ደግሞ፦ ኬንያዊቷ አትሌት ፔሬስ ጄፕቺርቺር አሸናፊ ሆናለች። የኦሎምፒክ ባለድሏ ፔሬስ ውድድሩን በአንደኛነት ለማጠናቀቅ የፈጀባት 66 ደቂቃ ከ45 ሰከንድ ነው ። የሀገሯ ልጅ ሻሮን ሎኬዲ በ58 ሰከንዶች ብቻ ተበልጣ ለጥቂት የሁለተኛ ደረጃ አግኝታለች። ሦስተኛ ሆና ያጠናቀቀችው የብሪታንያዋ ሯጭ ሻርሎቴ ፑርዱ ናት ። 69 ደቂቃ ከ36 ሰከንድ ውድድሩን ያጠናቀቀችበት ጊዜ ነው ።
የአፍሪቃ እግር ኳስ
የነሐሴ 8 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ የማጣሪያ ግጥሚያዎች ዛሬ እና ነገም ይቀጥላሉ ። ዛሬ ማታ ጊኒ ቢሳዎ ከሴራሊዮን ጋር ትጋጠማለች ። በነገው ዕለት ደግሞ ካሜሩን ቡሩንዲን ታስተናግዳለች ። ምድቡን አጠቃላይ አራት ጨዋታዎችን አከናውና አምስት ነጥብ የሰበሰበችው ናሚቢያ ትመራለች ። በሦስት ጨዋታዎች አራት ነጥብ የሰበሰቡት ካሜሩን እና ቡሩንዲ ሩምዴ አድጃ ስታዲየም ውስጥ በሚከናወነው በነገው የመጨረሻ ግጥሚያ ሁለቱም የማለፍ እድል አላቸው ። ሦስቱም ቡድኖች ምንም የግብ እዳ የለባቸውም ። ውድድሩ ከመጀመሩ በፊት በአፍሪቃ የእግር ኳስ ኮንፈደሬሽን (CAF) እገዳ የተጣለባት ኬንያ በምድቡ ውስጥ ብትገኝም አንድም ጨዋታ ስላላደረገች በዜሮ ነጥብ የመጨረሻ ደረጃ ላይ ትገኛለች ። ኬንያ እንደ ዚምባብዌ ሁሉ በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበር ፌዴሬሽን (FIFA) በፖለቲካ የተነሳ የተጣለባቸው ማእቀብ ባለመነሳቱ በውድድሩ መሳተፍ አልቻሉም ። የአፍሪቃ እግር ኳስ ኮንፈደሬሽን ምናልባት ሁለቱ ሃገራት ላይ የተጣለው እገዳ ሃገራቱ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ከማከናወናቸው ሁለት ሳምንታት በፊት ከተነሳ በሚል በምድብ ዝርዝር ውስጥ አስገብቷቸው ነበር ። እገዳው ስላልተነሳላቸው ግን መወዳደር አልቻሉም።
ከምድቡ በአምስት ግጥሚያዎች ዐሥር ነጥብ ሰብስባ በሁለተኛ ደረጃ ማለፏን ያረጋገጠችው ጊኒ ቢሳው ዛሬ ማታ ሴራሊዮንን ታስተናግዳለች ። ሴራሊዮን አምስት ነጥብ ነው ያላት ። ናይጄሪያ በስድስት ጨዋታዎች ዐሥራ አምስት ነጥቦችን ሰብስባ በመሪነት ለቀጣዩ የአፍሪቃ ዋንጫ አልፋለች ። በናይጄሪያ የደርሶ መልስ ጨዋታዎች 16 ለ0 የተሸነፈችው ንዑሷ ሳዎ ቶሜ እና ፕሪንሲፔ በአጠቃላይ 23 የግብ እዳ ተሸክማ በአንድ ነጥብ የምድቡ መጨረሻ ላይ ትገኛለች ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ደካማ ውጤትና ስንብት
የነሐሴ 22 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የስፖርት ዘገባኢትዮጵያ ባለችበት ምድብ ግብፅ በ15 ነጥብ ቀዳሚ ሆና ጊኒ በ10 ነጥብ ተከታትለው ማለፋቸውን አረጋግጠዋል ። ምንም እንኳን ከአፍሪቃ ዋንጫ ውድድር መሰናበቱን ቀደም ብሎ ያረጋገጠው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ከግብፅ አቻው ጋር ዐርብ እለት ካይሮ ከተማ ውስጥ ባደረገው የመጨረሻ ጨዋታው 1 ለ0 ተሸንፏል ። የኢትዮጵያ ቡድን በአጠቃላይ ውጤት ከማላዊ በአንድ ነጥብ ተበልጦ በአራት ነጥቡ የምድቡ መጨረሻ ሆኖ አጠናቋል። ዋሊያዎቹ በአጠቃላይ ግጥሚያቸው በአራት ጨዋታዎች ተሸንፈው አንድ በማሸነፍ እና አንድ አቻ ወጥተዋል ።
በሌሉቹ ምድቦች እስካሁን ማለፋቸውን ካረጋገጡ ቡድኖች መካከል፦ ቡርኪና ፋሶ እና ኬፕ ቬርዴ፤ ጋና እና አንጎላ፤ አልጄሪያ እና ታንዛኒያ፤ ማሊ እና ጋምቢያ፤ ዛምቢያ እና አይቮሪ ኮስት፣ የኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እና ማውሪታንያ፣ ቱኒዝያ እና ኤኳቶሪያል ጊኒ፣ ደቡብ አፍሪቃ እና ሞሮኮ፣ እንዲሁም ሴኔጋል እና ሞዛምቢክ ይገኙበታል።
ለማጣሪያ ከተደለደሉት ከ12ቱም ምድቦች ውስጥ በነጥብ ልዩነት አንደኛ እና ሁለተኛ የወጡ 24 ሃገራት ከጥር 4 ቀን፣ እስከ የካቲት 3 ቀን፣ 2016 ዓ.ም አይቮሪ ኮስት በምታዘጋጀው የአፍሪቃ ዋንጫ የእግር ኳስ ውድድር ላይ በቀጥታ ተሳታፊ ይሆናሉ ።
እስካሁን 10 ኳሶችን ከመረብ በማሳረፍ ለጣሊያኑ ናፖሊ በአጥቂ መስመር ተሰላፊው የናይጄሪያው ቪክቶር ኦሲምሄን ቀዳሚ ነው ። የሴኔጋሉ አጥቂ እና የክንፍ ተጨዋች ሳዲዮ ማኔ፤ የመካከለኛው አፍሪቃ አጥቂ ሉዊ ማውፎታ፤ የሞሮኮው የክንፍ አለያም የአጥቂ መስመር ተጨዋች ዩሱፍ ምሳክኒ እንዲሁም በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የላይሰተር ሲቲ ቡድን ተሰላፊው የዛምቢያው አጥቂ ፓስቶን ዳካ እያንዳንዳቸው አምስት ግቦችን በማስቆጠር ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ ። የቡርኪና ፋሶው ዳንጎ ኦታራ አራት ኳሶችን ከመረብ በማሳረፍ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ሰፍሯል ።
በባሎን ደ ኦር 4 አፍሪቃውያን አሉበት
በነገራችን ላይ በአፍሪቃ የእግር ኳስ ማጣሪያ ግጥሚያዎች ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ ያሸነፈው ናይጄሪያዊው አጥቂ ቪክቶር ኦሲምሄን በባሎን ደ ኦር ኮከብ ተጨዋች እጩ ውስጥ ይገኛል ። በዓለም ምርጥ የእግር ኳስ 30 ተጨዋቾች የሽልማት ዝርዝር እጩዎች ውስጥ ቪክቶርን ጨምሮ አራት ተጨዋቾች ተካተዋል ። እነሱም የሊቨርፑሉ አጥቂ ግብጻዊው ሞሐመድ ሣላኅ እንዲሁም ሁለት ግብ ጠባቂዎች፦ ናይጄሪያዊው አንደሬ ኦናና እና ሞሮኮዋዊው ያሲን ቦውኑ ይገኙበታል ። ሁለቱ አፍሪቃውያን ግብ ጠባቂዎች የፈረንሣይ ያሺኔ መጽሄት ለሚያዘጋጀው ሽልማትም እጩ ሆነዋል ። የአምስት ጊዜ አሸናፊው ክርስቲያኖ ሮናልዶ ካለፉት ዐሥር ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ የሽልማት ዝርዝር እጩ ውስጥ አልተካተተም ። የ7 ጊዜያት የባሎን ደ ኦር አሸናፊው የ36 ዓመቱ አርጀንቲናዊ አጥቂሊዮኔል ሜሲ ዘንድሮም እጩ ውስጥ ከተካተቱት 30 የዓለማችን ተጨዋቾች መካከል ይገኛል ።
የጀርመን ብሔራዊ የእግር ኳስ
የነሐሴ 15 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የስፖርት ዘገባየጀርመን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ቅዳሜ ዕለት እንግዳው ባደረገው የጃፓን ቡድን የደረሰበት የ4 ለ1 ሽንፈት በርካታ የቡድኑ ደጋፊዎችን እጅግ አበሳጭቷል ። የ58 ዓመቱ የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ሐንሲ ፍሊክንም በጀርመን የእግር ኳስ ታሪክ የመጀመሪያው ተሰናባች አሰልጣን አድርጓቸዋል ። ከቅዳሜው ብርቱ ሽንፈት በኋላ የጀርመን እግር ኳስ ፌዴሬሽን አሰልጣኝ ሐንሲ ፍሊክን በነጋታው ማሰናበቱ ታውቋል። አሁን የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ማን ይሆናል የሚለው ነው የበርካቶች መነጋገሪያ ።
ምናልባትም ሐንሲ ፍሊክን በመተካት የ36 ዓመቱ የቀድሞው የባየርን ሙይንሽን አሰልጣኝ ዩሊያን ናግልስማን ብሔራዊ ቡድኑን ይረከባሉ ተብሎም ይገመታል ። ነገ የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ከፈረንሳዩ አቻው ጋር ዶርትሙንድ ውስጥ ለሚያደርገው የወዳጅነት ግጥሚያ ግን ሌሎች ሰዎች ተመድበዋል ። ብሔራዊ ቡድኑን የታዳጊዎች ስልጠና እና እድገት ኃላፊ የ42 ዓመቱ ሐንስ ቮልፍ በአሰልጣኝነት እንዲሁም የ35 ዓመቱ ዛንድሮ ቫግነር በረዳት አሰልጣኝነት ወደ ሜዳ ይዘው እንደሚገቡ ተዘግቧል ።
የሜዳ ቴኒስ
በዩኤስ የሜዳ ቴኒስ ፍጻሜ ሠርቢያዊው የዓለማችን ድንቅ የሜዳ ቴኒስ ተጨዋች ኖቫክ ጄኮቪች 24ኛ የፍጻሜ ድሉን አጣጥሟል ። ኖቫክ ጄኮቪች ኒው ዮርክ ከተማ ውስጥ ትናንት በተደረገው የፍጻሜ ግጥሚያ የሩሲያው ተፎካካሪው ዳኒል ሜድቬዴቭን 6 ለ3 7 ለ6 (7:5) እና 6 ለ3 አሸንፏል ። በሜዳ ቴኒስ ምርጥ ተፎካካሪዎች መካከል በእድሜ ትልቁ እና የ36 ዓመቱ ኖቫክ የትናንት ድሉ ልዩ ትርጉም ያለው ነው ። ከዛሬ ሦስት ዓመት በፊት ለሦስት ሰአት ከ17 ደቂቃ በፈጀ የፍጻሜ ፍልሚያ በዳኒል ሜድቬዴቭ ሽንፈት ገጥሞት ነበር ። ያ ድል ለዳኒል ብቸኛው የፍጻሜ ድሉ ተደርጎ ተመዝግቦለታል ። ያን ኖቫክ ጊዜ ጠብቆ አሁን ተበቅሏል ።
ከዚያ ቀደም ብሎ ቅዳሜ ዕለት በነበረ የፍጻሜ ግጥሚያ አሜሪካዊቷ ኮኮ ጋውፍ የመጀመሪያ ድሏን አጣጥማለች ። ኮኮ ጋውፍ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2012 በሴሬና ዊሊያምስ ድል የስምንት ዓመት ልጅ ሆና ስትቦርቅ ትታወሳለች ። ኮኮ የዛሬ 11 ዓመት ስታዲየም ውስጥ በመገኘት በዳንስ ደስታዋን ስትገልጽ የሚታይበት ተንቀሳቃሽ ምስልን መለስ ብሎ በማስታወስ የቅዳሜ ድሏ በበርካታ ስፖርት አፍቃሪዎች ዘንድ መነጋገሪያ ሆኗል ። ኮኮ ዋንጫ ያነሳችው የቤላሩሷ ተጨዋች አሪና ሳባሌንካን 6 ለ3 እና 6 ለ2 በማሸነፍ ነው ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ታምራት ዲንሳ