1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የነሐሴ 22 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ነሐሴ 22 2015

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድን በዘንድሮ የቡዳፔስት የዓለም አትሌቲክስ ፉክክር ከኦሬገኑ ያነሰ ውጤት ይዞ አጠናቋል ። የ5000 ሜትር ተፎካካሪው የአትሌት ጥላሁን ኃይሌ ጉዳይም ፌዴሬሽኑን ለበርካታ ትችቶች አጋልጧል ። በዚሁ ኢትዮጵያ ከዓለም 6ኛ ደረጃ በያዘችበት ውድድር የጀርመን ቡድን በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ያለምንም ሜዳሊያ አጠናቋል ።

https://p.dw.com/p/4VfLw
በቡዳፔስት ውድድር ድል የተቀዳጁት ኢትዮጵያውያት አትሌቶች
በቅዳሜው ነሐሴ 13 እስከ 21 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የዐስር ሺህ ሜትር የሴቶች የሩጫ ፉክክር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ ርቀቱን በ31 ደቂቃ ከ27.18 ሰከንድ በማጠናቀቅ በአንደኛነት አሸንፋለች ። ኢትዮጵያውያቱ አትሌቶች ለተሰንበት ግደይ እና እጅጋየሁ ታዬም የሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ የውድድሩ የበላይ ሆነው ገነዋል ።ምስል Antonin Thuillier/AFP

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድን በዘንድሮ የቡዳፔስት የዓለም አትሌቲክስ ፉክክር ከኦሬገኑ ያነሰ ውጤት ይዞ አጠናቋል ። የ5000 ሜትር ተፎካካሪው የአትሌት ጥላሁን ኃይሌ ጉዳይም ፌዴሬሽኑን ለበርካታ ትችቶች አጋልጧል ። በዚሁ ኢትዮጵያ ከዓለም 6ኛ ደረጃ በያዘችበት ውድድር  የጀርመን ቡድን በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ያለምንም ሜዳሊያ አጠናቋል ። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ትናንት የኋላ መስመር ወሳኝ ተከላካዩ ገና በ28ኛው ደቂቃ ላይ በቀይ ካርድ የተሰናበተበት ሊቨርፑል ኒውካስልን በሜዳው የማታ ማታ ጉድ አድርጎታል ። በሜዳው ነጥብ የጣለው አርሰናል ደጋፊዎቹን አበሳጭቷል ። ሳምንት ማንቸስተር ዩናይትድ ይጠብቀዋል ። በጀርመን ቡንደስሊጋ ባየርን ሙይንሽን ድል ሲቀናው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ነጥብ ጥሏል ።

አትሌቲክስ

በቡዳፔስት የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሁለቱም ጾታ በመካከለኛ እና ረዥም ርቀቶች የተሳተፈችው ኢትዮጵያ ከዓለም 6ኛ ከአፍሪቃ ደግሞ ሁለተኛ ደረጃ ይዛ አጠናቃለች ። የቡዳፔስቱ ፉክክር ኢትዮጵያ ከረዥም ጊዜ በኋላ በወንዶች አንድም ወርቅ ያላገኘችበት ውድድር ሆኗል። ኢትዮጵያ ሁለቱን ወርቆች ያገኘችው፦ በ10 ሺ ሜትር የሴቶች የሩጫ ፉክክር በጉዳፍ ጸጋይ እንዲሁም በማራቶን ሩጫ በአማኔ በሪሶ ነው ።

ከፍተኛ የአሸናፊነት ግምት ተሰጥቶት የነበረው የ3ሺ ሜትር መሰናክል ሯጫ ለሜቻ ግርማ እንደተለመደው የብር ሜዳሊያ አሸናፊ ሆኗል። ሞሮኳዊው ኤልባላዲ ለተከታታይ አምስተኛ ጊዜ ለሜቻን በማሸነፍ ወርቁን ወደ ሀገሩ ወስዷል።

ኢትዮጵያ በድርቤ ወልተጂ ተጨማሪ የብር ሜዳሊያ አግኝታለች ።
በ1500 ሜeትርv የቡዳፔስቱ የሩቻ ፉክክር ኢትዮጵያ በድርቤ ወልተጂ ተጨማሪ የብር ሜዳሊያ አግኝታለች ። የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘችው ኬንያዊቷ ፋይዝ ኪፕዬገን ናት ። ምስል Martin Meissner/AP

ኢትዮጵያ በለተሰንበት ግደይ፣ ጎይተቶም ገብረሥላሴ እና ድርቤ ወልተጂ ተጨማሪ የብር ሜዳሊያዎችን ስታገኝ ፤ በእጅጋየሁ ታዬ ፣ ሰለሞን ባረጋ እና ልዑል ገብረሥላሴ ሦስት የነሐስ ሜዳሊያዎችን አሰባስባ በድምሩ 9 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ነው ከዓለም በስድስተኛነት ያጠናቀቀችው። ዉጤቱ ካለፈው ዓመት በአሜሪካ በኦሬገኑ ከተገኘው እጅጉን ያነሰ ሆኖም ተመዝግቧል።

የአትሌት ጥላሁን ጉዳይ

በዚሁ 19ኛው የቡዳፔስት የዓለም አትሌቲክስ ፉክክር የብዙዎችን ትኩረት የሳበ ድርጊትም ተከስቷል ። ለአምስት ሺህ ሜትር የሩጫ ፉክክር ቀደም ሲል ባሟላው ሰአት መሰረት በሦስተኛ ደረጃ እንደሚሰለፍ የተነገረው አትሌት ጥላሁን ኃይሌ በድንገት እንደማይወዳደር መደረጉን እያለቀሰ በማኅበራዊ የመገናኛ አውታር በቪዲዮ መልእክት የደረሰብኝን በደሌን ስሙኝ ብሏል ። በተጠባባቂነት ተመዝግቦ የነበረው ሌላኛው አትሌት በሪሁ አረጋዊ መተካቱን እና አትሌት ጥላሁን እንደማይሰለፍ ይፋ ከሆነ በኋላ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በጋዜጣዊ መግለጫው ስለ አትሌት ጥላሁን ጉዳይ ምላሽ ሰጥቷል ።

የፌዴሬሽኑ ፕሬዚደንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ፦ አትሌቱ በማዘኑ እና በማልቀሱ ይቅርታ ጠይቃለች ። ሆኖም የአትሌት ጥላሁን መብት ግን እንዳልተነካ ገልጻለች ።   «እሱን አስወጥተን ማንንም አላስገባንም ።  ሁሉም ባላቸው ሰአት እና በብቃታቸው ነው የገቡት»ም ስትል አክላለች ። በትናንቱ የ5 ሺህ የፍጻሜ ውድድር ዮሚፍ ቀጄልቻ ፣ ሀጎስ ገብረ ሕይወት እና በሪሁ አረጋዊ በቅደም ተከተል 5ኛ፣ 6ኛ እና 8ኛ በመሆን አጠናቀው ከሜዳሊያ ውጪ ሆነዋል ።

ፌዴሬሽኑ የአትሌት ጥላሁን በድንገት መቀነስን አስመልክቶ የሰጠው ድንገተኛ መግለጫ ብዙዎችን ለብዥታ ቢዳርግም ፤ አንዳንድ የወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከሆነ ግን አትሌት ጥላሁን በውድድሩ ሊሳተፍ የመግቢያ ባጅ ሁሉ ወጥቶለት ነበር ።  በተፎካካሪዎች ዝርዝር ውስጥም 3ኛ ተፎካካሪ ተብሎ ተመዝግቦ እንደነበር ተገልጿል ።

ለመሆኑ መጀመሪያውኑ ለአትሌቱ እንደማይሰለፍ አስቀድሞ ለምን አልተነገረውም? ቡዳፔስት ድረስ እንዲጓዝ ተደርጎም በአግባቡ ሳይነገረው መቀነሱን በድንገት ማወቁ ከአሠራር ዝርክርክነት ባሻገር ለአትሌቱም ሆነ ለሌሎች አትሌቶች ሞራል ተገቢ ነው ወይ? በፌዴሬሽኑ አሠራር እንዲህ ያለ ነገር እጅግ የሚያስተች አይደለም ወይ? የሚሉ ጥያቄዎች አጭሯል ። አትሌት ጥላሁን በደሉን ገልጾ ሳይወዳደር ወደ ሀገሩ ተመለሰ እንጂ እሱ እንዳለውም ሆነ ሌሎች ውስጥ አዋቂዎች እንደሚናገሩት ፌዴሬሽኑ በብዙ ችግሮች መተብተቡ ይነገራል ። ራሱን ሊፈትሽም ይገባዋል ተብሏል ።  የስፖርት ጋዜጠኛ እና ተንታኝ ዖምና ታደለ ለፓሪሱ ዖሎምፒክ ከወዲሁ ዝርክርክነትን አስወግዶ መዘጋጀት ያስፈልጋል ብሏል ።  

የፓሪስ ኦሎምፒክን በ2024 የምታዘጋጀው ፓሪስ ከተማ ከፊል ገጽታ ።
ፓሪስ ዖሎምፒክ መሰል ውዝግብ ሳይከሰት ኢትዮጵያ እንደ ቡድን የተሻለ ውጤት እንድታገኝ ምን መደረግ አለበት? የፓሪስ ኦሎምፒክን በ2024 የምታዘጋጀው ፓሪስ ከተማ ከፊል ገጽታ ። የአይፍል ታወር ከወንዙ ባሻገር ።ምስል Kyodo/picture alliance

19ኛው የቡዳፔስት የዓለም አትሌቲክስ ፉክክር

ሐንጋሪ ውስጥ በ19ኛው የቡዳፔስት የዓለም አትሌቲክስ ፉክክሩን አጠናቆ ለተመለሰው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ዛሬ አቀባበል ማድረጉም ተዘግቧል ። በተገኘው ውጤት ዙሪያም መግለጫ መሰጠቱ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል ። ስለዚህ ምስቅልቅል ሁኔታ ምን የተባለ ነገር አለ? አትሌት ጥላሁንስ አሁን ያለበት ሁኔታ ምን ይመስላል?

እንግዲህ አሁን የፓሪስ ዖሎምፒክ መዳረሻ ላይ ነን ። በቡዳፔስት ያገኘነው ውጤት በኦሬገኑ ከተገኘው እጅጉን ያነሰ ነው ። በፓሪስ ዖሎምፒክ መሰል ውዝግብ ሳይከሰት ኢትዮጵያ እንደ ቡድን የተሻለ ውጤት እንድታገኝ ምን መደረግ አለበት? የስፖርት ጋዜጠኛ እና ተንታኝ ዖምና ታደለ ። የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ባልደረቦችን ለማነጋገር በስልክ ሞክረን ነበር፤ ሆኖም የቡድኑ ተሳታፊዎች በጉዞ ላይ በመሆናቸው ሳይሆን አይቀርም በስልክ elnag,ናቸው አልቻልንም ። ወደፊት አግኝተን በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር እንሞክራለን ። 

ከዚሁ ከአትሌቲክስ ዜና ሳንወጣ፦ የጀርመን ብሔራዊ ቡድን በዓለም የአትሌቲክስ ፉክክር ያለምንም ሜዳሊያ ሲያጠናቅቅ የቡዳፔስቱ የመጀመሪያው ሆኖ ተመዝግቧል ። በተለይ የፓሪስ ዖሎምፒክ ከመቃረቡ አንጻር የጀርመን ውጤት በስፖርት አፍቃሪው ዘንድ ከፈተኛ መነጋገሪያ ሆኗል ።

የጀርመን ቡድን  ባለፈው የኦሬጎን ውድድር ቢያንስ ሁለት ሜዳሊያዎችን አግኝቶ ነበር ። በርዝመት ዝላይ በማላይካ ሚሃምቦ ወርቅ እንዲሁም በሴቶች የ100 ሜትር የዱላ ቅብብል የነሐስ ሜዳሊያ ።  ከሩጫው ባሻገር፤ እንደ የአሎሎ ውርወራ፤ የዲስክ ውርወራ፤ የጦር ውርወራ፤ የከፍታ፣ የምርኩዝ እና የርቀትን የመሳሰሉ የተለያዩ ዝላዮች፤ እንዲሁም በሌሎች ዘርፈ ብዙ የስፖርት አይነቶች ላይ በርካታ ተፎካካሪዎች ለምታሰልፈው ጀርመን ዘንድሮ አንድም ሜዳሊያ አለማግኘቱ አስደማሚ ነው ።

የነሐሴ 15 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የስፖርት ዘገባበአጠቃላይ ውድድሩ ዩናይትድ ስቴትስ 12 የወርቅ፤ 8 የብርና 9 የነሐስ በድምሩ 29 ሜዳሊያዎችን ሰብስባ 1ኛ ወጥታለች ። ካናዳ በ4 የወርቅ እና በ2 የብር በድምሩ 6 ሜዳሊያዎች ሁለተኛ ወጥታለች ። ስፔን በ4 ወርቅ፤ እና በ1 ብር ሦስተኛ ደረጃ አግኝታለች ። ጄማይካ በ3 የወርቅ፤ በ5 የብር እንዲሁም በ4 የነሐስ በድምሩ 12 ሜዳሊያ አራተኛ ደረጃ ስታገኝ፤ ጎረቤት ኬንያ በ10 ሜዳሊያ አራተኛ ደረጃ ይዛለች ። ኬንያ 3 የወርቅ፤ 3 የብር እና 4 የነሐስ ሜዳሊያዎችን ሰብስባ ነው ከአፍሪቃ ኢትዮጵያን አስከትላ አንደኛ የወጣችው ። ብሪታንያ፤ ኔዘርላንድ፣ ኖርዌይ፤ ስዊድን እና ኡጋንዳ እያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት የወርቅ ሜዳሊያ በማግኘት በብር እና በነሐስ ሜዳሊያ ብዛት ተበላልጠው ከ7ኛ እስከ 11ኛ ደረጃ ተደርድረዋል ።

የጀርመን ቡንደስሊጋ
የጀርመን ቡንደስሊጋ የአውግስቡርግ እና ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ ግጥሚያ ። ፎቶ ከማኅደር ። ምስል Bernd Feil/M.i.S./IMAGO

እግር ኳስ

የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ እና የጀርመን ቡንደስሊጋ ውጤቶችን ከማሰማታችን በፊት የኢትዮጵያ የተለያዩ የእግር ኳስ ቡኖች ያስመዘገቧቸውን ውጤቶች እንቃኛለን ። በምስራቅ አፍሪቃ የሻምፒየንስ ሊግ ማጣሪያ ውድድር የግማሽ ፍፃሜ ግጥሚያ የኬንያውን ቪጋ ኩዊንስን የገጠመው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች ቡድን 2 ለ1 በማሸነፍ ለፍፃሜ ማለፉን አረጋግጧል ። ንግድ ባንክ በፍጻሜው የሚፋለመው ከታንዛኒያው ጄ ቲ ኬ ኩዊንስ ጋር ነው ።

በአፍሪቃ ኮንፌዴሬሽን ካፕ የመጀመሪያ ዙር የመልስ ግጥሚያ ባለፈው ዐርብ የታንዛኒያው አዛምን በሜዳው የገጠመው ባህርዳር ከተማ በመለያ ምት 4 ለ3 በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፉን አረጋግጧል ። ባህር ዳር ከተማ ከሳምንት በፊት አዛምን አዲስ አበባ ከተማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ውስጥ አስተናግዶ 2 ለ1 ማሸነፉ አይዘነጋም ።

በአፍሪቃ ሻምፒየንስ ሊግ ውድድር ደግሞ፦ ቀደም ሲል ከሜዳው ውጭ 2 ለ1 አሸንፎ የነበረው ቅዱስ ጊዮርጊስም ድል ቀንቶታል ። አበበ ቢቂላ ስታዲየም ውስጥ የዛንዚባሩን ኬ ኤም ኤም የእግርኳስ ቡድንን 3 ለ1 በደርሶ መልስ 5 ለ 2 በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር አልፏል ። ፈረሰኞቹን በቀጣዩ ዙር የግብፁ አል አህሊ ቡድን ይጠብቃቸዋል ።

ፕሬሚየር ሊግ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ በኒውካስል ሜዳ 1 ለ0 ሲመራ የቆየው ሊቨርፑል የማታ ማታ በዳርዊን ኑኔዝ ሁለት ድንቅ ግቦች አሸናፊ ሆኖ ደጋፊዎቹን አስቦርቋል ። ሁለተኛዋ ግብ የሞሐመድ ሳላኅ በግሩም ሁኔታ ኳስ አቀባበሉ እና የዳርዊን ከጨዋታ ውጪ ላለመሆን ሰከንዷን ጠብቆ የማፈትለኩ ድምር ውጤት ናት ።

28ኛው ደቂቃ ላይ የኋላ መስመር ተከላካዩ ቪርጂል ቫንጃይክ በቀይ ካርድ የተሰናበተበት ሊቨርፑል ጨዋታውን ከመቆጣጠር አልፎ የበላይነቱን አስጠብቆ መውጣቱ ለቡድኑ ስነ ልቦና ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ።

በዩናይትድ ስቴትስ ዋናው የእግር ኳስ ሊግ (MLS)
በዩናይትድ ስቴትስ ዋናው የእግር ኳስ ሊግ (MLS) ዓርማ የሚታይበት የእግር ኳስ ። ዋናው የእግር ኳስ ሊግ በተለይ አርጀንቲናዊው አጥቂ ሊዮኔል ሜሲን ካገኘ በኋላ ይበልጥ ትኩረት ስቧል ።ምስል Gia Quilap/Sports Press/picture-alliance/dpa

የሊቨርፑል አሰልጣኝ ጀርመናዊው ዬርገን ክሎፕ ከመመራት ተነስቶ ለድል ስለበቃው ቡድናቸው ሲናገሩ «እንደ አሰልጣኝነቴ ከ1000 በላይ ጨዋታዎች እንዲህ ያለውን ዐይቼ ዐላውቅም» ብለዋል ። ኒውካስል ዩናይትድ ባለፈው ሳምንት በማንቸስተር ሲቲ የ1 ለ0 ሽንፈት አስተናግዶ ነበር ።

ትናንት በርንሌይን 3 ለ1 በገዛ ሜዳው ያሸነፈው አስቶን ቪላ እሁድን ሊቨርፑልን አንፊልድ ውስጥ ይገጥማል ። ማንቸስተር ሲቲም ሼፊልድ ዩናይትድን ትናንት 2 ለ1 በማሸነፍ እስካሁን የተደረጉ ሦስት ጨዋታዎችን ሁሉንም በማሸነፍ ብቸኛው ሆኗል ። ዌስትሀም ብራይተንን 3ለ1፤ ዎልቨርሀምፕተን ኤቨርተንንን 1 ለ0፤ ቶትንሀም ቦርመስን 2 ለ0 እንዲሁም ቸልሲ ሉቶን ታውንን 3 ለ0 አሸንፈዋል ። ክሪስታል ፓላስ ከብሬንትፎርድ፤ እንዲሁም አርሰናል በሜዳው ከፉልሀም ጋር ሁለት እኩል በመውጣት ነጥብ ተጋርተዋል ።

ቡንደስሊጋ

በጀርመን ቡንደስሊጋ፦  ባየርን ሙይንሽን ትናንት አውግስቡርግን 3 ለ1 ድል አድርጓል ። አይንትራኅት ፍራንክፉርት ከማይንትስ ጋር አንድ እኩል ወጥቷል ። ቅዳሜ ዕለት  ባየርን ሌቨርኩሰን ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅን 3 ለ0፤ ፍራይቡርግ ቬርደር ብሬመንን 1 ለ0 አሸንፈዋል ። ዑኒዮን ቤርሊን ዳርምሽታድትን 4 ለ1 ሲያደባይ፤ ቮልፍስቡርግ ኮሎኝን 2 ለ1፤ ሆፈንሀይም ሐይደንሀይምን 3 ለ2 አሸንፈዋል ። ቦሩስያ ዶርትሙንድ በዶኒዬል ማሌን ብቸኛ ግብ ከቦሑም ጋር አቻ ወጥቷል ። ሽቱትጋርት በላይፕትሲሽ የ5 ለ1 ብርቱ ሽንፈት አስተናግዷል ።

አርጀንቲናዊው ሊዮኔል ሜሲ በዩናይትድ ስቴትስ ዋናው የእግር ኳስ ሊግ (MLS) የመጀመሪያው ግቡን አስቆጥሯል ።
አርጀንቲናዊው ሊዮኔል ሜሲ በዩናይትድ ስቴትስ ዋናው የእግር ኳስ ሊግ (MLS) የመጀመሪያው ግቡን አስቆጥሯል ። የ36 ዓመቱ የኢንተር ሚያሚ አጥቂ 89ኛው ደቂቃ ላይ ነው ኒው ዮርክ ቡልስ ላይ ሁለተኛዋን ግብ ያስቆጠረው ። ምስል Twitter/La Nacion/ZUMAPRESS/picture alliance

በሌላ የእግር ኳስ ዜና አርጀንቲናዊው ሊዮኔል ሜሲ በዩናይትድ ስቴትስ ዋናው የእግር ኳስ ሊግ (MLS) የመጀመሪያው ግቡን አስቆጥሯል ። የ36 ዓመቱ የኢንተር ሚያሚ አጥቂ 89ኛው ደቂቃ ላይ ነው ኒው ዮርክ ቡልስ ላይ ሁለተኛዋን ግብ ያስቆጠረው ። ሊዮኔል ሜሲ ከሳምንት በፊት የሊግ ዋንጫን ካነሱበት ጊዜ በኋላ በዋናው የእግር ኳስ ሊግ ግብ ያስቆጠረው 60ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ ገብቶ ነው ። ግቧም በኢንተር ሚያሚ ቆይታው 11ኛ ሆና ተመዝግባለች ። ሠርጂዮ ቡስኬትም ተቀይሮ ገብቶ በዋናው የእግር ኳስ ሊግ ተሳትፎውን ሀ ብሎ ጀምሯል ።

የከባድ ሚዛን የቡጢ ፍልሚያ

ዩክሬናዊው የከባድ ሚዛን ቡጢኛ አሌክሳንደር ኡዚክ የዓለም ከባድ ሚዛን ቡጢ ቀበቶውን  አስጠብቋል ። ፖላንድ ብሬስላው ውስጥ በ45.000 ታዳሚያን ፊት ትናንት በተደረገው ግጥሚያ አሌክሳንደር ዘጠነኛው ዙር ላይ በዝረራ ያሸነፈው የብሪታኒያውን ቡጢኛ ዳንኤል ዱቢዮስን ነው ። በዚህም አሌክሳንደር ከ21 ግጥሚያዎች 21ኛ ድሉን ትናንት አክብሯል ።

የመኪና ሽቅድምድም

የሐምሌ 24 ቀን 2015 ዓ/ም የስፖርት ዝግጅትሌዊስ ሐሚልተን  ስምንተኛ ደረጃ ይዞ ባጠናቀቀበት የትናንቱ የሰሜን ሆላንድ የፎርሙላ  አንድ የመኪና ሽቅድምድምን ማክስ ፈርሽታፐን አሸነፈ ። በዚህም የሬድ ቡል አሽከርካሪው ማክስ የመሪነቱን ቦታ በ339 ነጥብ ማስጠበቅ ችሏል ። የመርሴዲሱ አሽከርካሪ ሌዊስ እስካሁን በተከናወኑ ሽቅድምድሞች የሰበሰበው156 ነጥቡ ብቻ ነው ። እስካሁን 201 ነጥብ ሰብስቦ 2ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሌላኛው የሬድ ቡል አሽከርካሪ ሠርጂዮ ፔሬዝ ትናንት በ4ኛነት ነው ያጠናቀቀው። ትናንት በአስቶን ማርቲን መኪናው 2ኛ ደረጃ ያገኘው ፈርናንዶ አሎንሶ በ168 ነጥብ የ3ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። በአጠቃላይ እስካሁን 37 ነጥብ ብቻ ይዞ 10ኛ ደረጃ ላይ ለሰፈረው የአልፓይን አሽከርካሪው ፒዬር ጋስሌይ ትናንት 3ኛ ደረጃ ይዞ ማጠናቀቁ ልዩ ደስታ ነው የፈጠረለት ። በትናንቱ ውድድር ብቻ 15 ነጥብ ሰብስቧል ።  

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ