በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አማኔ በሪሶ እና ጐተይቶም ገብረሥላሴ በማራቶን አሸንፈዋል
ቅዳሜ፣ ነሐሴ 20 2015በሐንጋሪ ዋና ከተማ ቡዳፔስት በመካሔድ ላይ በሚገኘው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያውያን ሴት አትሌቶች በማራቶን ውድድር የወርቅ እና የብር ሜዳሊያ አሸንፈዋል። ዛሬ ጠዋት የተካሔደውን የማራቶን ውድድር አማኔ በሪሶ በ2 ሰዓት ከ24 ደቂቃ ከ23 ሰከንድ በማጠናቀቅ አንደኛ ወጥታለች። ሌላዋ ኢትዮጵያዊት ጐተይቶም ገብረ ሥላሴ በ2 ሰዓት ከ24 ደቂቃ 34 ሰከንድ ሁለተኛ ሆና ጨርሳለች።
ያለምዘርፍ የኋላው ውድድሩን አምስተኛ ሆና አጠናቃለች። ሞሮኳዊቷ ፋጢማ ኢዛህራ እና እስራኤላዊቷ ሎናህ ቼማቲ ሦስተኛ እና አራተኛ ደረጃን ይዘው ጨርሰዋል። ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች በትብብር በመሥራት ውድድሩን ለሌሎች ሯጮች አስቸጋሪ እንዳደረጉባቸው የ31 ዓመቷ አማኔ በሪሶ ተናግራለች
ኢትዮጵያውያን የደመቁበት የኦሪጎን አትሌቲክስ ሻምፒዮና
ኢትዮጵያውያኑ ከሌሎቹ አትሌቶች ተለይተው ከወጡ በኋላ ፉክክሩ እርስ በርስ እንደሆነ አማኔ ገልጻለች። በተለይ በኦሬጎን በተካሔደው የዓለም ሻምፒዮና አሸናፊ ከነበረችው ጐተይቶም ገብረ ሥላሴ ጋር የነበራት ጠንካራ ፉክክር እንደነበር አማኔ አንስታለች። ጐተይቶም "ጠንካራ አትሌት ናት" ያለችው አማኔ በቡዳፔስት ጎዳናዎች የተካሔደውን የማራቶን ውድድር በአሸናፊነት የማጠናቀቅ ፍላጎት እንደነበራት ተናግራለች።
በውድድሩ ከተሳተፉ 77 ሯጮች መካከል ማጠናቀቅ የቻሉት 65 ናቸው። ውድድሩ ሲጀመር 23 ዲግሪ ሴልሺየስ የነበረው ሙቀት በመጨረሻ ወደ 29 ዲግሪ ሴልሺየስ ከፍ ብሏል። አማኔ "እጅግ ሞቃት እንደሆነ አውቃለሁ። ነገር ግን ለእኔ አስቸጋሪ አልነበረም" ስትል ተናግራለች። የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት የሆነችው አማኔ ውድድሩ ቀደም ብሎ ቢጀመር ኖሮ በተሻለ ፈጣን ሰዓት መሮጥ ይቻል እንደነበር እምነቷን ተናግራለች።
ጐተይቶም ገብረ ሥላሴ ውድድሩን ያጠናቀቀችው ከአማኔ በሪሶ 11 ሰከንዶች ዘግይታ ነው። ዋናው ዓላማ ወርቅ ማሸነፍ እንደነበር የተናገረችው ጎተይቶም ያቀዱት በመሳካቱ ኩራት እንደሚሰማት ገልጻለች። ጎተይቶም ባለፈው ዓመት በአሜሪካዋ ኦሬጎን ርቀቱን በ2 ሰዓት ከ18 ደቂቃ ከ11 ሰከንድ በማጠናቀቅ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሪከርድ አስመዝግባ ነበር። "በኦሬጎን በጣም ቀዝቃዛ ነበር። በቡዳፔስት በጣም ሞቃት ነው" ያለችው ጎተይቶም "ነገር ግን ሁኔታዎቹ ከባድ እንደሚሆኑ እናውቅ ነበር" ብላለች።
የአሜሪካ ኦሪጎን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ውጤታማ ጉዞ
በቡዳፔስት የዓለም ሻምፒዮና ስምንተኛ ቀን የሴቶች የ5000 ሜትር ውድድር አራት ኢትዮጵያውያን ይሳተፋሉ። ዛሬ ቅዳሜ ከምሽቱ 3:30 ውድድሩ ሲጀመር ጉዳፍ ጸጋይ፣ እጅጋየሁ ታዬ፣ መዲና ኢሳ እና ፍሬወይኒ ኃይሉ ኢትዮጵያን ወክለው የሚሮጡ አትሌቶች ናቸው።
በሪሁ አረጋዊ፣ ሐጎስ ገብረ ሕይወት እና ዮሚፍ ቀጀልቻ ኢትዮጵያን ወክለው የሚሳተፉበት የወንዶች የ5000 ሜትር ውድድር ነገ እሁድ ይካሔዳል። በሴቶች 3000 ሜትር የፍጻሜ ውድድር ሎሚ ሙለታ፣ ሰምቦ ዓለማየሁ እና ዘርፌ ወንድማገኝ ይሳተፋሉ።
በቡዳፔስት በመካሔድ ላይ በሚገኘው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እስካሁን ኢትዮጵያ ስምንት ሜዳልያዎች በማግኘት በደረጃ ሰንጠረዡ አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። ጉዳፍ ጸጋይ በ10000 ሜትር፤ አማኔ በሪሶ በማራቶን ለኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያ ያሸነፉ አትሌቶች ናቸው። ለሜቻ ግርማ፣ ድርቤ ወልተጂ፣ ለተሰንበት ግደይ እና ጎተይቶም ገብረሥላሴ የብር ሜዳሊያዎች አሸንፈዋል። ሰለሞን ባረጋ እና እጅጋየሁ ታዬ የነሐስ ሜዳሊያ ያሸነፉ አትሌቶች ናቸው። አሜሪካ፣ ስፔን እና ጃማይካ የሜዳሊያ ሰንጠረዡን ከአንድ እስከ ሦስተኛ ደረጃ በመያዝ ይመራሉ።