1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የነሐሴ 8 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ነሐሴ 8 2015

ብራዚሊያዊው ኔይማር የእነ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ተቀናቃኝ ቡድንን በሳዑዲ አረቢያ ሊቀላቀል ጫፍ ደርሷል ። ክርስቲያኖ ሮናልዶ ከአል ናስር ቡድን ጋር ዋንጫ ማንሳት ችሏል ። የባየር ሙይንሽን ሽንፈት ደጋፊዎቹን አስቆጥቷል ። በሴቶች የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ስፔን ከስዊድን፤ እንግሊዝ ከአውስትራሊያ ለግማሽ ፍጻሜ ነገ እና ከነገ በስትያ ይጋጠማሉ ።

https://p.dw.com/p/4V9OS
የሴቶች የዓለም ዋንጫ
አውስትራሊያ ከእንግሊዝ ጋር የምታደርገው ውድድር ከስታዲየሙ ውጪ ቱምባሎንግ አፀድ ውስጥ በሚገኘው የሕዝብ መመልከቻም ከ200 ሺህ በላይ ታዳሚያንን ለማስተናገድ ዝግጅት መጠናቀቁ ተዘግቧልምስል Mathias Bergeld/Bildbyran/IMAGO

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

ለረዥም ጊዜ ሲያወዛግብ የቆየው የቡዳፔስት የዓለም አትሌቲክስ ፉክክር ተሳታፊ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ምርጫ ተጠናቆ ሽኝት ተደርጓል ። ከባለሞያ ጋር የተደረገ ቃለ መጠይቅ ይኖረናል ። የሳዑዲ አረቢያ እግር ኳስ ሊግ በርካታ የዓለም ምርጥ ተጨዋቾችን እየሳበ ነው ። ብራዚሊያዊው ኔይማር የእነ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ተቀናቃን ቡድንን በሳዑዲ አረቢያ ሊቀላቀል ጫፍ መድረሱ ተዘግቧል ። ክርስቲያኖ ሮናልዶ  ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ከአል ናስር  ቡድን ጋር ዋንጫ ማንሳት ችሏል ። የባየር ሙይንሽን ሽንፈት ደጋፊዎቹን አስቆጥቷል ። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ቶትንሀም ከብሬንትፎርድ እንዲሁምሊቨርፑል ከቸልሲ ጋር ትናንት አቻ ወጥተዋል ። የሊቨርፑሉ አጥቂ ሞሐመድ ሳላህ 77ኛ ደቂቃ ላይ ሲቀየር እጅግ ተበሳጭቷል ። አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ ሞሐመድ ሳላህ በትናንቱ ጨዋታ የግብ ክብረወሰን ለመስበር ማለሙን ዐላውቅም ነበር ብለዋል ። በሴቶች የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ስፔን ከስዊድን፤ እንግሊዝ ከአውስትራሊያ  ለግማሽ ፍጻሜ ነገ እና ከነገ በስትያ ይጋጠማሉ ።

አትሌቲክስ

በ19ኛው የቡዳፔስት የዓለም አትሌቲክስ ፉክክር ላይ ተሳታፊ ለሚሆነው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ልኡካን ቡድን ትናንት ደማቅ አሸኛኘት መደረጉ ተዘገበ ። ስማቸው ይፋ ሆኖ ልምምድ ሲያደርጉ ከቆዩ 31 አትሌቶች መካከል የመጨረሻዎቹን መምረጡ ሲያወዛግብ ቆይቶም ነበር ።   የቡዳፔስቱ ፉክክር የሚካሄደው ከነሐሴ 13 እስከ 21 ቀን፣ 2015 ዓ.ም ድረስ ነው ።  በኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮ ስፖርት መርኃ ግብር ዋና አዘጋጅ ምስጋናው ታደሰ በሽኝት መርኃ ግብሩ ላይ ተሳታፊ ነበር ።  

አትሌቶች ለውድድር ተሰናድተው
አትሌቶች ለውድድር ተሰናድተውምስል Sven Hoppe/dpa/picture alliance

እግር ኳስ

እጅግ ዝነኛ የአውሮጳ ተጨዋቾችን እያስፈረመ የሚገኘው የሳዑዲ አረቢያ እግር ኳስ ሊግ የበርካቶችን ትኩረት እየሳበ ነው ። በተለይ ደግሞ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ለአል-ናስር ቡድን ፈርሞ መጫወቱ ለበርካታ ተጨዋቾች በር ከፍቷል ። የ38 ዓመቱ ፖርቹጋላዊው አጥቂ ክርስቲያኖ ሮናልዶ በዓረብ ቡድኖች የዋንጫ ግጥሚያ ሁለት ኳሶችን ከመረብ በማሳረፍ ቡድኑ አል-ናስር የመጀመሪያ ዋንጫ እንዲያነሳ አስችሏል ። ንጉሥ ፋህድ ስታዲየም ውስጥ በጭማሪ ሰአት በተጠናቀቀው ግጥሚያ አል- ናስር ተጋጣሚው አል -ሒላልን ያሸነፈው 2 ለ1 ነው ። በዓረብ ሊግ ውድድር ሣዑዲ አረቢያ፣ ካታር፣ የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች፣ ኢራቅ፣ ሞሮኮ፣ ቱኒዝያ እና አልጀሪያ ውስጥ ያሉ ቡድኖች ይሳተፉበታል።

ናይጀርያ ድል አልቀናዉም፤ እንግሊዝ ሩብ ፍፃሜ ደርሷል

እስካሁን ድረስ በሳዑዲ ዓረቢያ ሊግ ፦ ከክርስቲያኖ ሮናልዶ፣ ካሪም ቤንዜማ፣ ንጎሎ ካንቴ፣ ሮቤርቶ ፊርሚኖ፣ ሳዲዮ ማኔ፣ ሪያድ ማኅሬዝ፣ ሠርጂዮ ሚሊንኮቮች ሳቪችን ጨምሮ የተለያዩ ዝነኛ ተጨዋቾች ለሊጉ ፈርመዋል ። ትናንት ደግሞ ብራዚሊያዊው ኔይማር ጁኒዬር በ90 ሚሊዮን ዩሮ ግድም ለሳዑዲ አረቢያው አል ሒላል የእግር ኳስ ቡድን መፈረሙ ተዘግቧል ። ኔይማር ከስድስት ዓመታት በፊት ለፈረንሳዩ ፓሪ ሳን ጃርሞ ሲፈርም የተከፈለው 222 ሚሊዮን ዩሮ በዓለም የእግር ኳስ ተጨዋች ክፍያ ታሪክ ከፍተኛውን ክብረወሰን የሰበረ ነበር ። ኔይማር ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ሲያቀና ሌላኛው ኮከብ ኬሊያን እምባፔ ግን በፓሪ ሳንጃርሞ መቆየቱ ተረጋግጧል ።

ፖርቹጋላዊው አጥቂ ክርስቲያኖ ሮናልዶ በሳዑዲ ዓረቢያ ሊግ ገንኗል
ፖርቹጋላዊው አጥቂ ክርስቲያኖ ሮናልዶ በሳዑዲ ዓረቢያ ሊግ ገንኗል ምስል FAYEZ NURELDINE/AFP/Getty Images

ከዚሁ የዝውውር እና ከፍተኛ ክፍያ ዘገባ ሳንወጣ፦ ሊቨርፑል ሞይሰስ ካይሴዶን ሊያስፈርም ጫፍ ደርሶ በስተመጨረሻ ቸልሲ በፕሬሚየር ሊግ ታሪክ ከፍተኛ በተባለ ክፍያ  አማካይ ተጨዋቹን ከሊቨርፑል መንትፎ ከእጁ አስገብቷል ። የሊቨርፑል አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ ሞይሰስ ካይሴዶን ለማስፈረም ከብራይተን አልቢዮን ጋር ተስማምተው እንደነበር ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ቅሬታና ግርታ በተሞላበት መልኩ ተናግረዋል ። ቸልሲ ጥር ወር ላይ ኤንዞ ፈርናንዴዝን ከቤኔፊካ ሲያስፈርም ያወጣው 121 ሚሊዮን ዩሮ በቡድኑ የክፍያ ታሪክ ክብረወሰን የሰበረ ተብሎ ነበር ። በዚህ የጨዋታ ዘመን ቸልሲ ያን ለመድገም አሳምኝ ምክንያት አለው ። ወሳኝ አማካዮቹ ሜሰን ማውንት፣ ካይ ሐቫርትስ፣ ማቲዮ ኮቫቺች፤ እና ኢንጎሎ ካንቴን ያጣው ቸልሲ በዚህም አለ በዚያ ሞይሰስ ካይሴዶን ማስፈረሙ ግድ ነበር

የሐምሌ 24 ቀን 2015 ዓ/ም የስፖርት ዝግጅት

ቸልሲ ሞይሰስ ካይሴዶን በ133 ሚሊዮን ዩሮ ነው ያስፈረመው ። ያም ብቻ አይደለም ለብራይተን አልቢዮን ተጨማሪ ድጎማም እንደሚከፍል ተዘግቧል ። ሊቨርፑል ለዚህ ብዙ ለተነገለት አማካይ የመደበው 127 ሚሊዮን ዩሮ ነበር ።

ብራይተን አልቢዮን ይህን ብዙ የተነገረለት አማካይ ሞይሰስ ካይሴዶን የዛሬ ሁለት ዓመት ወደ ቡድኑ ያስመጣው በ5, 2 ሚሊዮን ፓውንድ ብቻ ነበር ። አንድ የጨዋታ ዘመን ብቻ አጫውቶ ከፍተኛ ትርፍ አግኝቶ ተጨዋቹን ለቸልሲ በማስፈረም ካዝናውን ሞልቷል ። ባለፈው የጨዋታ ዘመን ሊቨርፑልን ተከትሎ ለአውሮጳ ሊግ ኮንፈረስን ማለፉን ላረጋገጠው ብራይተን አልቢዮን በዚህ ተጨዋች የዝውውር ክፍያ ያገኘው ገቢ ቡድኑን ይበልጥ እንደሚያጠናክረው ይጠበቃል ።

ብራይተን አልቢዮን በፕሬሚየር ሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታ ዘንድሮ ከታች ያደገው ሉቶን ታውንን ቅዳሜ ዕለት 4 ለ1 አደባይቷል ። በአማካዩ ሞይሰስ ካይሴዶን የተወዛገቡት ሊቨርፑል እና ቸልሲ በስታምፎርድ ብሪጅ ሜዳ ትናንት ተጋጥመው አንድ እኩል ተለያይተዋል ። ቶትንሀም ከብሬንትፎርድ ጋር ትናንት ተጫውቶ ሁለት እኩል ወጥቷል ። ዛሬ ማታ ማንቸስተር ዩናይትድ ከዎልቨርሀምፕተን ጋር ይጋጠማል

የኢትዮጵያዊያን ስፖርት እና ባሕል ፌዴሬሽን በአውሮፖ ፌስቲቫል

በ77ኛው ደቂቃ ላይ የተቀየረው ሞሀመድ ሳላህ
በ77ኛው ደቂቃ ላይ የተቀየረው ሞሀመድ ሳላህ ምስል DW

ሊቨርፑል በቸልሲ ሜዳ ነጥብ በተጋራበት በትናንቱ ግጥሚያ በ77ኛው ደቂቃ ላይ የተቀየረው ሞሀመድ ሳላህ ከሜዳ ሲወጣ እጅግ ተበሳጭቶ ነበር ። በትናንቱ ግጥሚያ ከጨዋታ ውጪ ግቡ የተሻረበት እና ቀዳሚዋን ግብ እንድትቆጠር ለሉዊስ ዲያዝ ኳስ በግሩም ሁኔታ ያመቻቸው ሞሀመድ ሳላህ የተበሳጨው አቅዶ ወደ ሜዳ የገባውን ሳያሳካ በመውጣቱ ነው ። ሞሐመድ ሳላህ በስምንት የፕሬሚየር ሊግ የመክፈቻ ጨዋታዎች በተከታታይ በሁሉም አንድ አንድ ግቦችን በማስቆጠር ክብረወሰን ለመስበር ዓልሞ ነበር ። የሊቨርፑል አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ ተጨዋቻቸው ይህን አልሞ ሜዳ ስለመግባቱ እንደማያውቁ ተናግረዋል ። አዳዲስ ተጨዋቾችን እድል የመስጠት ኃላፊነቱም አለብኝ ብለዋል ። በእርግጥም ተቀይረው የገቡት አዳጊ ተጨዋቾች የ17 ዓመቱ ቤን ዶዋክ እና የ20 ዓመቱ ሐርቬይ ኤሊዮት የቸልሲ የበላይነት የተኢ,በት የሁለተና አጋማሽ ጨዋታ ስልት መቀየር ችለዋል ።

ቅዳሜ ዕለት በነበሩ የፕሬሚየር ሊግ ግጥሚያዎች፦ ቶትንሀም ወደ ብሬንትፎርድ አቅንቶ ሁለት እኩል ተለያይቷል ። አስቶን ቪላ በኒውካስል 5 ለ1 ተሸንፏል ። እንደ ኒውካስል አያያዝ አስቶን ቪላ ከዚያም በላይ በርካታ ግቦች ሊቆጠሩበት ይችሉ ነበር ። ሁለት ኳሶችን ከመረብ ያሳረፈው አሌክሳንደር ኢሳቅ ለጥቂት ሦስት ግቦችን አስቆጥሮ ሔትሪክ ሳይሠራ ቀርቷል ። በጨዋታው ግን በፍጥነት ኳሶችን ተቀብሎ ለግብ በማብቃት ብርቱ አጥቂ መሆኑን አስመስክሯል ።

በ100 ሚሊዮን ዩሮ ግድም የዝውውር ክፍያ ከእንግሊዙ ቶትንሀም ሆትስፐር ወደ ባየርን ሙይንሽን የተዘዋወረው ሐሪ ኬን
በ100 ሚሊዮን ዩሮ ግድም የዝውውር ክፍያ ከእንግሊዙ ቶትንሀም ሆትስፐር ወደ ባየርን ሙይንሽን የተዘዋወረው ሐሪ ኬን ምስል Matthias Schrader/AP/picture alliance

በጀርመን ሱፐር ካፕ የእግር ኳስ ግጥሚያ የባየር ሙይንሽን በሜዳው የገጠመው ሽንፈት ደጋፊዎቹን አስቆጥቷል ። ቅዳሜ ዕለት በነበረው ግጥሚያ ባየርን ሙይንሽን በጨዋታ ቢበልጥም በኤር ቤ ላይፕትሲሽ ግን የ3 ለ0 ሽንፈት ገጥሞታል ። ከፍተኛ በተባለለት የ100 ሚሊዮን ዩሮ ግድም የዝውውር ክፍያ ያለፈው ዐርብ ከእንግሊዙ ቶትንሀም ሆትስፐር ወደ ባየርን ሙይንሽን የተዘዋወረው ሐሪ ኬን በቅዳሜው ጨዋታ 64ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ ቢገባም ለቡድኑ የፈየደው ነገር የለም ። ይልቁንስ የምሽቱ ኮከብ የነበረው የላይፕትሲሹ ዳኒ ዖልሞ ነበር ። ሦስት ግቦችን በማስቆጠር ሔትትሪክ ሠርቷል ። በተለይ ሁለተኛው ግብ የዳኒ ዖልሞ ብቃት የታየበት ነበር ።

በሴቶች የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ የስፔን ቡድን
በሴቶች የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ፉክክር ነገ ስፔን ከስዊድን ከነገ በስትያ ደግሞ እንግሊዝ ከአውስትራሊያ ጋር የግማሽ ፍጻሜ ውድድር ያከናውናሉ ። ምስል Alessandra Tarantino/AP/picture alliance

በሴቶች የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ፉክክር ነገ ስፔን ከስዊድን ከነገ በስትያ ደግሞ እንግሊዝ ከአውስትራሊያ ጋር የግማሽ ፍጻሜ ውድድር ያከናውናሉ ። በተለይ የባለፈው ውድድር ዋንጫን ያሸነፉት የእንግሊዝ አናብስቱ ዘንድሮ ለሦስተኛ ጊዜ ግማሽ ፍጻሜ ደርሰዋል። ከኒውዚላንድ ጋር ተባባሪ አስተናጋጇ አውስትራሊያ እንደ ስፔን ሁሉ ግማሽ ፍጻሜ ስትደርስ ለመጀመሪያ ጊዜዋ ነው ። የረቡዕ ዕለት ግጥሚያን የሚያስተናግደው እና ሲድኒ ውስጥ የሚገኘው ስታዲየሟ ከ81 ሺህ በላይ ታዳሚዎች የማስተናገድ አቅም አለው ። አውስትራሊያ ከእንግሊዝ ጋር የምታደርገው ውድድር ከስታዲየሙ ውጪ ቱምባሎንግ አፀድ ውስጥ በሚገኘው የሕዝብ መመልከቻም ከ200 ሺህ በላይ ታዳሚያንን ለማስተናገድ ዝግጅት መጠናቀቁ ተዘግቧል ። የሁለቱ ግጥሚያ በተለይ በበርካቶች ዘንድ በከፍተኛ ደረጃ የሚጠበቅ ነው ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሠ