የሊዮኔል ሜሲ አርጀንቲና የዓለም ዋንጫ አሸናፊ ሆነች
እሑድ፣ ታኅሣሥ 9 2015የ35 ዓመቱ ሊዮኔል ሜሲ እና አርጀንቲና የኳታሩ የዓለም ዋንጫ አሸናፊ ሆኑ። ስድስት ግቦች በተቆጠሩበት የ120 ደቂቃ ጨዋታ ፈረንሳይ ሁለት ጊዜ አቻ መሆን ብትችልም ሜሲ እና አርጀንቲን ከዓለም ዋንጫ ባለቤትነት ማቆም አልቻለችም።
ሊዮኔል ሜሲ በ23ኛው ደቂቃ በፍጹም ቅጣት ምት፤ አንጊል ዲ ማርያ በ36ኛው ደቂቃ በጨዋታ ባስቆጠሯቸው ግቦች አርጀንቲና የመጀመሪውን አጋማሽ 2 ለባዶ አጠናቃለች። ይሁንና ኪልያን ምባፔ በሁለተኛው አጋማሽ ከፍጹም ቅጣት ምት እና በጨዋታ ባስቆጠራቸው ሁለት ግቦች አቻ ሆነው ጨዋታው ወደ ተጨማሪ ሰዓት ተሸጋግሯል።
በተጨማሪ ሰዓት ሊዮኔል ሜሲ በጨዋታ ኪሊያን ምባፔ በፍጹም ቅጣት ምት ተጨማሪ ግቦች አስቆጥረው ሙሉ ጨዋታው 3-3 ተጠናቋል።
ጨዋታው 3-3 አቻ ከተጠናቀቀ በኋላ አርጀንቲና በመለያ ምት 4-2 አሸንፋለች። ኪንግስሌይ ኮማን የመታውን የመለያ ምት የአርጀንቲናው ግብ ጠባቂ ኢሚሊያኖ ማርቲኔዝ አድኖበታል። ሌላው ፈረንሳዊ ኦሬሊየን ቶካሜኒ የመለያ ምቱን ስቷል።
የኳታሩን የዓለም ዋንጫ በሳዑዲ አረቢያ የ2-1 ሽንፈት የጀመረችው አርጀንቲና ውድድሩን በበላይነት ለማጠናቀቅ የሊዮኔል ሜሲ ድንቅ ክህሎት አስፈልጓታል። ከፍጻሜ ጨዋታው ስድስት ግቦች አምስቱን ያስቆጠሩት ሊዮኔል ሜሲ እና ኪልያን ምፓፔ የኳታሩ የዓለም ዋንጫ ኮከብ ተጫዋች እና ኮከብ ግብ አግቢ ሆነው አጠናቀዋል።
አርጀንቲና ከኔዘርላንድስ እና በፍጻሜው ከፈረንሳይ ባደረገቻቸው ጨዋታዎች የመለያ ምቶች ያዳነው ኤሚ ማርቲኔዝ የዓለም ዋንጫ ኮከብ ግብ ጠባቂ ሆኖ ተመርጧል። የ21 ዓመቱ አርጀንቲናዊ የመሀል ሜዳ ተጫዋች ኤንዞ ፈርናንዴዝ የውድድሩ ወጣት ኮከብ ተጫዋች ለመሆን በቅቷል።
ሁለቱ ብሄራዊ ቡድኖች ቀደም ሲል ሁለት ሁለት ጊዜ የዓለም ዋንጫን አሸንፈዋል። አርጀንቲና በጎርጎርሳዊው 1978 እና በ1986 ፤ እንዲሁም ፈረንሳይ ደግሞ በ1998 እና በ2018 አሸናፊ መሆን የቻሉባቸው ጊዜያት ነበሩ።
አርጀንቲና ለፍጻሜ ስትደርስ ይኽኛው ስድስተኛዋ ነው። ከ36 ዓመታት በኋላ ያነሳችው የዛሬው ዋንጫ ደግሞ ሶስተኛው ሆኖ ተመዝግቦላታል። ሊዮኔል ሜሲ ኮከብ ተጫዋች ሆኖ ከመመረጡ ባሻገር በዚህ ዓለም ዋንጫ በምድብ፣ በጥሎ ማለፍ፣ በሩብ ፍፃሜ፣ በግማሽ ፍፃሜ እና የፍፃሜ ጨዋታዎች ላይ ግብ በማስቆጠር የዓለማችን ብቸኛው ተጫዋች ሆኖ አዲስ ታሪክ ጽፏል።
በዓለም ዋንጫው ትናንት ቅዳሜ ለሶስተኛ ደረጃ በክሮሽያ እና ሞሮኮ ብሄራዊ ቡድኖች መካከል በተደረገ ጫወታ ክሮሽያ ሞሮኮን 2 ለ 1 አሸንፋ የነሐስ ሜዳልያ ተሸላሚ መሆን ችላለች ። አፍሪካን ወክለው ከቀረቡት አምስት ቡድኖች ግማሽ ፍጻሜ መድረስ የቻለችው ሞሮኮ አራተኛ ሆና ስታጠናቅቅ ይህ ለአፍሪቃ አዲስ ታሪክ ነው።