1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የነሐሴ 29 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ነሐሴ 29 2015

ጀርመን ቤርሊን ከተማ ውስጥ ለድል የበቃችው አትሌት ለተሰንበት ግደይ የራሷን ክብረ ወሰን ለጥቂት ሳትሰብር ቀርታለች ። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቸስተር ዩናይትድ ባለቀ ሰአት በአርሰናል ብርቱ በትር ቀምሷል ። ሊቨርፑል በአንፊልድ ሜዳው ተጋጣሚው አስቶን ቪላን ዘና ብሎ አሸንፏል ። የቡንደስሊጋ፤ የላሊጋና የሴሪኣ ጨዋታዎችንም ቃኝተናል ።

https://p.dw.com/p/4VwKq
የጀርመን ቡንደስሊጋ ባየርን ሙይንሽን ከአውግስቡርግ ፤ ፎቶ ከማኅደር ።
በጀርመን ቡንደስሊጋ የእግር ኳስ ግጥሚያ ሔሪ ኬን በፍጹም ቅጣት ምት መለያ ለባየርን ሙይንሽን ቡድኑ አውግስቡርግ ላይ ግብ ሲያስቆጥር ። ፎቶ ከማኅደር ።ምስል ActionPictures/IMAGO

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

ጀርመን ቤርሊን ከተማ ውስጥ ትናንት ለድል የበቃችው አትሌት ለተሰንበት ግደይ የራሷን ክብረ ወሰን ለጥቂት ሳትሰብር ቀርታለች ። በቡዳፔስት የዓለም አትሌቲክስ ፉክክር ውጤት ላስመዘገቡ አትሌቶች ትናንንት በቤተመንግሥት የገንዘብ ሽልማት ስነስርዓት ተከናውኗል ። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቸስተር ዩናይትድ ባለቀ ሰአት በአርሰናል ብርቱ በትር ቀምሷል ። ሊቨርፑል በአንፊልድ ሜዳው ተጋጣሚው አስቶን ቪላን ዘና ብሎ አሸንፏል ። ዳርምሽታድትን በሰፊ የግብ ልዩነት ድል ያደረገው ባየር ሌቨርኩሰን በጀርመን ቡንደስሊጋ የደረጃ ሰንጠረዥ ቀዳሚ ሆኗል ።  ከባየር ሙይንሽን ጋር የሚለያዩት በግብ ክፍያ ብቻ ነው ። በስፔን ላሊጋ ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ ለባርሴሎና የማሸነፊያዋን ግብ በፍጹም ቅጣት ምት አስቆጥሯል ።  

አትሌቲክስ

በጀርመን ቤርሊን ከተማ ትናንት በተደረገው የ5,000 ሜትር የሩጫ ፉክክር ያሸነፈችው ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ለተሰንበት ግደይ ለጥቂት ክብረ ወሰን ሳትሰብር ቀረች ። ለተሰንበት በርቀቱ በራሷ የተያዘውን ክብረወሰን ለመስበር ሦስት ነጥብ ከግማሽ ሰከንድ ብቻ ነበር የቀራት ። ኦሎምፒያ ስታዲየም ውስጥ ትናንት 14 ደቂቃ ከ08 ሰከንድ ከ79 ማይክሮ ሰከንድ  ሮጣ በማጠናቀቅ በርቀቱ  4ኛውን ፈጣን ሰዓት አስመዝግባለች ።

በተያያዘ ዜና፦ በቡዳፔስት 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ፉክክርላይ በማሸነፍ ሜዳልያ ላስገኙ አትሌቶች  ትናንት  በቤተ መንግስት በተከናወነ መርኃ ግብር የገንዘብ ሽልማት ተሰጥቷል ። የወርቅ ሜዳልያ ላመጡ 2 አትሌቶች በኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ሣኅለ-ወርቅ ዘውዴ እጅ ለእያንዳንዳቸው 1.5 ሚሊዮን ብር መሰጠቱን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዐስታውቋል ። የብር ሜዳልያ ላመጡ 4 አትሌቶች ለእያንዳንዳቸው 1 ሚሊዮን ብር፤ እንዲሁም የነሐስ ሜዳልያ ላስገኙ 3 አትሌቶች ለእያንዳንዳቸው 700ሺ ብር መበርከቱም ተገልጿል ። ከዚህ በተጨማሪ የወርቅ፤ የብር እና የነሐስ ሜዳሊያዎች እንዲገኝ ላስቻሉ አሰልጣኞችም እንደየ ደረጃው 750ሺ ብር፤ 500ሺ ብር፤ 350ሺ ብር መሰጠቱ ተዘግቧል ። ዲፕሎማ ላስመዘገቡ፤  ለተሳታፊዎችና ለቡድኑ አመራር የገንዘብ ሽልማት መበርከቱን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ቢገልጽም የገንዘብ መጠኑን ግን አልጠቀሰም ።

እግር ኳስ

አርሰናል ትናንት በአስደማሚ የእግር ኳስ አጨዋወት እና አጨራረስ ባለቀ ሰአት ማንቸስተር ዩናይትድን ጉድ አድርጎታል ። በአጠቃላይ ጨዋታ ብልጫ ያሳየው አርሰናል የማታ ማታ መደበኛው 90 ደቂቃ ከተጠናቀቀ በኋላ በዴልካን ሪስ እና ጋብሪየል ጄሱስ ግቦች 2 ለ1 አሸንፎ ወሳኝ ሦስት ነጥቡን ሰብስቧል ።

ጨዋታው በአቻ ተጠናቆ ቡድናቸው በሜዳው ነጥብ የሚጥል የመሰላቸው አንዳንድ ችኩል የአርሰናል ደጋፊዎች ተስፋ በመቁረጥ ከሜዳ ወጥተው ነበር ። ሁለተኛው ግብ ሲቆጠርና ስታዲየሙ በሆታ ሲናጥ ግን ግራ በመጋባት ወደ ስታዲየሙ መመለስ ጀምረውም ነበር ። የማሸነፊያውንም ሆነ ሦስተኛውን ግብ ተመልክተው ጮቤ ለመርገጥ የታደሉት ግን ቡድናቸውን እስከመጨረሻው በትእግስት እዛው ስታዲየም ውስጥ ሆነው በታማኝነት ሲደግፉ የቆዩት ናቸው ። ሌሎቹ  መንገድ ላይ እንዳሉ ጥለው ወደወጡት ስታዲየምም ሳይደርሱ ቡድናቸው ድል አድርጓል ።

የነሐሴ 22 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የስፖርት ዘገባለማንቸስተር ዩናይትድ ቀዳሚዋን ግቭ በ27ኛ ደቂቃ ላይ ያስቆጠረው ማርኩስ ራሽፎርድ ነበር ። የማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊዎችም ሆኑ አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሐግ ግን ደስታቸውን ለማጣጣም ከግማሽ ደቂቃ በላይ መቆየት አልታደሉም ። ወዲያውኑ በግሩም የኳስ ቅብብሎሽ ቅንብር አርሰናሎች ተጋጣሚያቸውን ግራ አጋብተው በማርቲን ኦዴጋርድ አቻ የምታደርገውን ኳስ ከመረብ አሳርፈዋል ።

በዚህ ጨዋታ የማንቸስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሐግ በስልጠና ወቅት ደካማ ነበር ያሉትን የእንግሊዙ የክንፍ ተጨዋች ጄደን ሳንቾን አላሰለፉም ። እንደውም የ23 ዓመቱ ጄደን ወደ ኤሚሬት ስታዲየም ከማንቸስተር ጋር አልተጓዘም ነበር። ጄደን ሳንቾ በዘንድሮ የፕሬሚየር ሊግ ያለፉት ሦስት ጨዋታዎች የተሰለፈው ከአግዳሚ ወንበር እየተቀየረ ነበር ። ከ2 ዓመት በፊት ከጀርመኑ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ወደ ማንቸስተር ዩናይትድ በ83 ሚሊዮን ዩሮ የተዘዋወረው ሳንቾ በኦልድትራፎርድ  ብዙም አልተመቸውም ።ከኤሪክ ቴን ሐግ ቀደም ብለው በነበሩት አሰልጣኞች፦ በኦሌ ጉናር ሶልስካየርም ሆነ በራልፍ ራንኚክ እምብዛም ቦታ አላገኘም ። የዛሬ ሁለት ወር ገደማ ሲነገር እንደነበረው የቀድሞው ቡድኑ ቦሩስያ ዶርትሙንድ በውሰት መልሶ ወደ ጀርመን እንዳይወስደውም ማንቸስተር ዩናይትድ የዶርትሙንድ ፍላጎትን ውድቅ አድርጓል ። ጄደን ሳንቾ በአሁኑ ወቅት ምን እንደሚያስብ ባይታወቅም በማንቸስተር ዩናይትድ ግን በዚህ መልኩ የሚቀጥል አይመስልም ።

ከቸልሲ ወደ አርሰናል በጥሩ ክፍያ የቀየረው ጀርመናዊው ካይ ሐቫርትስም በቡንደስ ሊጋ እንደነበረው በፕሬሚየር ሊጉ ብቃቱን ዘንድሮ ማሳየት አልቻለም ። በትናንትናው ግጥሚያ ግብ ሊሆን የሚችል ኳስ አግኝቶ አልፈስፍሶ በመምታት መክኖበታል ። በቪዲዮ ረዳት ዳኛ (VAR)ታይቶ ተሻረ እንጂ ፍጹም ቅጣት ምት ክልል ውስጥም እንደተጠለፈ መስሎ ወድቆ ነበር ። በአርሰናል ውስጥ ከፍተኛ ተከፋይ ለሆነው የ24 ዓመቱ ካይ ሐቫርትስ የትናንቱ ቀን ድክመቱ ጎልቶ የታየበት ነበር ። ካይ ሐቫርትስ በአርሰናል በየወሩ የ1,6 ሚሊዮን ዩሮ ተከፋይ ነው ። በሳምንት 400,000 ግድም ዩሮ ማለት ነው ።

ቀደም ብሎ በነበረው ግጥሚያ ሊቨርፑል አንፊልድ ሜዳው ላይ አስቶን ቪላን 3 ለ0 ድል አድርጓል ። ሊቨርፑል ቀዳሚዋን ግብ በዶሚኒክ ሶቦስላይ ያስቆጠረው ጨዋታው ከተጀመረ ሦስት ደቂቃም ሳይሞላ ነበር ። ከጀርመን ላይፕትሲሽ ለተዘዋወረው አጥቂ 2 ደቂቃ ከ20 ሰከንድ ላይ ከመረብ ያሳረፈው ኳስ በዲስ ቡድኑ ሊቨርፑል የመጀመሪው ሆኖ ተመዝግቦለታል ። ሁለተኛው ግብ ተከላካይ ኳሷን በጨረፍታ ቢነካም በዳርዊን ኑኔዝ ተቆጥሯል ። ወደ ሳዑዲ ፕሮ እንደሚያቀና ለሚወራለት ሞሐመድ ሣላኅ ምናልባትም በሊቨርፑል ቆይታው የመጨረሻው ልትሆን የምትችለውን ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው 3 ለ0 ተጠናቋል ።

የነሐሴ 15 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የስፖርት ዘገባየትናንቱ የሊቨርፑል ድል ማንቸስተር ሲቲ በጥፍሮቹ እንዲቆም ያደረገ ነው ። ምንም እንኳን ማንቸስተር ሲቲ ቅዳሜ ዕለት ፉልሀምን እጅግ በሰፋ የግብ ልዩነት 5 ለ1 ድል ቢያደርግም በደረጃ ሰንጠረዡ ቶትንሀም፤ ሊቨርፑል፤ ዌስትሀም እና አርሰናል 10 ነጥብ ይዘው በግብ ልዩነት ብቻ እስከ አምስተኛ ደረጃ ተደርድረው በቅርብ ርቀት ይከተሉታል ። ስድስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ብራይተንም ቢሆን እስካሁን ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች 9 ነጥብ ሰብስቦ ከመሪው ማንቸስተር ሲቲ የሚበለጠው በ3 ነጥብ ብቻ ነው ።

ማንቸስተር ሲቲ ኢትሐድ ስታዲየም ውስጥ በደጋፊዎቹ ፊት ድል ባደረገበት የቅዳሜው ግጥሚያ ኖርዌጂያዊው አጥቂ ኧርሊንግ ኦላንድ ሔትትሪክ ሠርቷል ። ሶን ሆይንግ ሚን ሦስት ግቦችን በማስቆጠር ሔትትሪክ በሠራበት ግጥሚያም ቶትንሀም ሆትስፐር በርንሌይን በድንቅ ጨዋታ በገዛ ሜዳው 5 ለ2 ጉድ አድርጎታል ።

በሌላ ግጥሚያ ቅዳሜ እለት ኖቲንግሀም ፎረስት ቸልሲን በገዛ ሜዳው ስታምፎርድ ብሪጅ 1 ለ0 በማሸነፍ ኩም አድርጎታል ። ብራይተን ኒውካስልን 3 ለ1 አሸንፎ ባስደመመበት ግጥሚያም ኤቫን ፌርጉሰን ሦስት ኳሶችን ከመረብ በማሳረፍ ሔትትሪክ ሠርቷል ። ለኒውካስልን ብቸኛዋን ግብ ያስቆጠረው ካሉም ዊልሰን ነው ። ሼፊልድ ዩናይትድ ከኤቨርተን፥ ብሬንትፎርድ ከበርመስ ጋር ሁለት እኩል በመውጣት ነጥብ ተጋርተዋል ።  ዌስትሀም ዩናይትድ ሉቶን ታውንን 2 ለ1፤ ክሪስታል ፓላስ ዎልቨርሀምፕተንን 3 ለ2 አሸንፈዋል ። እስካሁን በተደረጉ አራት ግጥሚያዎች አንድ ተሸንፎ አንድ አቻ ወጥቶ በቅዳሜው ግጥሚያ ኖቲንግሀም ፎረስትን 1 ለ0 ያሸነፈው ቸልሲ 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ።

በጀርመን ቡንደስሊጋ ኤር ቤ ላይፕትሲሽ ዑኒዮን ቤርሊንን 3 ለ0 አሸንፏል ።
በጀርመን ቡንደስሊጋ የኤር ቤ ላይፕትሲሹ ቤንጃሚን ሴስኮ ሁለተኛ ግብ አስቆጥሮ ደስታውን ሲገ።ልጽ ።በዚህ ጨዋታ ላይፕትሲሽ ተጋጣሚው ዑኒዮን ቤርሊንን 3 ለ0 አሸንፏል ።ምስል LISI NIESNER/REUTERS

ቡንደስሊጋ  

በጀርመን ቡንደስሊጋ ኤር ቤ ላይፕትሲሽ ትናንት ዑኒዮን ቤርሊንን 3 ለ0 አሸንፏል ። አይንትራኅት ፍራንክፉርት ከኮሎኝ ጋር አንድ  እኩል ወጥቷል ። ቅዳሜ እለት በነበሩ ስድስት ግጥሚያዎች፦ ባየርን ሙይንሽን ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅን 2 ለ1 እንዲሁም ፤ ሽቱትጋርት ፍራይቡርግን 5 ለ0 አሸንፈዋል ። ቬርደር ብሬመን ማይንትስን 4 ለ0 ሸኝቷል ። ቮልፍስቡርግ በሆፈንሀይም የ3 ለ1 እንዲሁም ዳርምሽታድት በባየር ሌቨርኩሰን የ5 ለ1 ሽንፈት ገጥሟቸዋል ። አውግስቡርግ ከቦሁም ቅዳሜ ዕለት እንዲሁም ቦሩስያ ዶርትሙን ከሐይደንሀይም ዐርብ እለት በተመሳሳይ ሁለት እኩል ወጥተዋል ።

የነሐሴ 8 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የስፖርት ዘገባእስካሁን በነበሩ የቡንደስሊጋ ሦስት ግጥሚያዎች፦ ባየር ሌቨርኩሰን ከባየርን ሙይንሽን ጋር ተመሳሳይ ዘጠኝ ነጥብ ይዞ በአንድ የግብ ክፍያ በልጦ አንደኛ ደረጃ ላይ ሰፍሯል ።  ሽቱትጋርት፤ ኤር ቤ ላይፕትሲሽ፤ ዑኒዮን ቤርሊን፤ ሆፈንሀይም፤ ቮልፍስቡርግ እና ፍራይቡርግ እያንዳንዳቸው ስድስት ነጥብ በመሰብሰብ ከሦስተኛ እስከ ስምንተኛ ደረጃ ላይ ተደርድረዋል ። እስካሁን በነበሩ ሦስት ግጥሚያዎች አንዱንም ጨዋታ ሳያሸንፍ አለያም አቻ ሳይወጣ ሁለት ግብ ብቻ አስቆጥሮ በስምንት የግብ እዳ የመጨረሻ 18ኛ ደረጃ ላይ ለሚገኘው ዳርምሽታድት በቡንደስሊጋው አደጋ ውስጥ ለመሆኑ አመላካች ነው ።

ላሊጋ

በስፔን ላሊጋ፦ ትናንት በቀይ ካርድ አንድ ተጨዋቹ ከሜዳ የተሰናበተበት ኦሳሱና በሜዳው በባርሴሎና የ2 ለ1 ሽንፈት አስተናግዷል ። ለባርሴሎና የማሸነፊያዋን ግብ 85ኛው ደቂቃ ላይ በፍጹም ቅጣት ምት ያስቆጠረው ሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ ነው ። ትናንት እና ከትናንት በስትያ  በነበሩ ሌሎች ግጥሚያዎች፦ ጂሮና ላ ፓልማን፤ ቤቲስ ራዮ ባሌካኖን እንዲሁም አላቬስ ቫሌንሺያን እያንዳንዳቸው 1 ለ0 አሸንፈዋል ። ሪያል ማድሪድ በጁድ ቤሊንግሀም 95ኛ ደቂቃ ላይ በተቆጠረ ግብ ጌታፌን 2 ለ1 ሲያሸንፍ፤ ሪያል ሶሴዳድ ግራናዳን 5 ለ3 ድል አድርጓል ። አልሜሪያ በሴልታ የ3 ለ2 እንዲሁም ቪላሪያል በካዲዝ የ3 ለ1 ሽንፈት አስተናግደዋል ።

እስካሁን በተደረጉ አራት ግጥሚያዎች ሪያል ማድሪድ በ12 ነጥብ ይመራል ። ባርሴሎና በተመሳሳይ 10 ነጥብ ሆኖም በግብ ክፍያ ልዩነት ጂሮናን ተከትሎ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ነው ። አትሌቲኮ ማድሪድ፤ አትሌቲኮ ቢልባዎ እና ካዲዝ እስከ ስድስተኛ ደረጃ ተከታትለው ይገኛሉ ። 7ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቤቲስን ጨምሮ ሁሉም 7 ነጥብ አላቸው።  

ሴሪኣ

የነሐሴ 1 ቀን 2015 ዓ/ም የስፖርት ዝግጅትበጣሊያን ሴሪኣ፦ ትናንት ፊዮሬንቲናን 4 ለ0 ኩም ያደረገው ኢንተር ሚላን 9 ነጥብ  ሰብስቦ መሪነቱን አስጠብቋል ። ዐርብ ዕለት በሮማ ሜዳ አንድ ተጨዋቹን በቀይ ካርድ አጥቶም  2 ለ1 ያሸነፈው ኤሲ ሚላንም እስካሁን ባደረጋቸው ሦስት ጨዋታዎች 9 ነጥብ ሰብስቧል ። ከኢንተር ሚላን በሁለት የግብ ክፍያ ልዩነት ብቻ ይበለጣል ። ተጋጣሚዎቻቸው ኤምፖሊ እና ሳሌርኒታናን ትናንት 2 ለ0 ያሸነፉት ጁቬንቱስ እና ኡኤስ ሌቼ 7 ነጥብ ይዘው በግብ ክፍያ ልዩነት 3ኛ እና 4ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ ።  አታላንታ፤ ናፖሊ እና ቬሮና ስድስት ነጥብ ይዘው ከአምስተኛ እስከ ሰባተኛ ደረጃ ተደርድረዋል።  ኤፍ ሴ ቱሪን ጄኑዋን ትናንት 1 ለ0 አሸንፏል ። በ4 ነጥብ ብቻ ግን 11ኛ ደረጃ ላይ ሰፍሯል ።

የሳኡዲ ፕሮ ሊግ

ክርስቲያኖ ሮናልዶ አል ናስር ቡድኑ በሳኡዲ ፕሮ ሊግ አል ሐዛምን 5 ለ1 ባሸነፈበት ግጥሚያ በእግር ኳስ የጨዋታ ዘመኑ 850ኛ ግቡን አስቆጥሯል ። ለአል ናስር ቡድን በተሰለፈበት ሦስት ግጥሚያዎች ስድስት ግብ ሲያስቆጥር ቡድኑም በየከታተይ ሦስት ጨዋታዎችን ድል አድርጓል ። የቀድሞው የሊቨርፑል አጥቂ ሳዲዮ ማኔም ለአል ናስር አምስት ግቦችን በማስቆጠር ከ38 ዐመቱ ፖርቹጋላዊ አጥቂ በርካታ ግብ በማስቆጠር ይከተላል ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ