የመስከረም 7 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ መስከረም 7 2016ባሕርዳር ከነማ የእግር ኳስ ቡድን የቱኒዝያ ተጋጣሚውን ድል አድርጓል ። ወደ ቀጣይ ዙር የማለፍ እድሉ ከፍተኛ ነው ። ቃለ መጠይቅ ይኖረናል ። አትሌት ጉዳፍ ጸጋዬ ዩጂን በተከናወነው የዳያመንድ ሊግ የ5 ሺህ ሜትር የሩጫ ፉክክር ክብረ ወሰን ሰብራለች ። ከተደጋጋሚ ሽንፈቶች በኋላ አጣብቂኝ ውስጥ የገባው የጀርመን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ግብረ ኃይል ሁለት አባላት ከኃላፊነታቸው በገዛ ፈቃዳቸው መነሳታቸውን ትናንት ይፋ አድርገዋል ። የፌዴሬሽኑ አሠራር ግልጽነት ይጎለዋል ሲሉም ከሰዋል ። በቡንደስ ሊጋው ሐይደንሀይም የመጀመሪያውን ድል አስመዝግቧል ። በፕሬሚየር ሊጉ ፉክክሩ እጅግ ተጠናክሯል ።
አትሌቲክስ
ዩጂን ኦሬጎን ውስጥ በተከናወነው የዋንዳ ዳያመንድ ሊግ ውድድር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ጉዳፍ ጸጋዬ በ5000 ሜትር ርቀት የሩጫ ፉክክር ትናንት ክብረወሰን ሰብራ አሸንፋለች ። ትናንት እና ከትናንት በስትያ በተከናወኑ ዘርፈ ብዙ የአትሌቲክስ ፉክክሮች መካከል ከተሰበሩት ሁለት ክብረ ወሰኖች አንዱ የጉዳፍ መሆን ችሏል ። ገና ከመጀመሪያው ብርቱ ፉክክር ያሳየችው ጉዳፍ ለድል የበቃችው ርቀቱን በ14 ሜትር ከ00.21 ሰከንድ በመሮጥ ነው ። በዚህ እጅግ አመርቂ ውጤቷም ጉዳፍ በኬኒያዊቷ ፋይዝ ኪፕዬገን ተይዞ የቆየውን ክብረወሰን በአምስት ሰከንዶች ግድም አሻሽላ መስበር ተሳክቶላታል ።
በዩጂን ኦሬጋኑ ፉክክር ሁለት ክብረወሰኖች የተሰበሩ ሲሆን ከኢትዮጵያዊቷ ድል በተጨማሪ ሌላኛው ክብረወሰን የተሰበረው በምርኩዝ ድጋፍ የከፍታ ዝላይ ተወዳዳሪው ስዊድናዊ አትሌት ነው ። አርማንድ ዱፕላንቲስ የገዛ ክብረወሰኑን የሰበረው፦ 6 ሜትር ከ23ሣንቲ ሜትር ከፍታ በመዝለል ነው ። በዚህም ባለፈው ዓመት በኦሎምፒክ ክብረወሰን የያዘበትን ከፍታ በአንድ ሴንቲ ሜትር ማሻሻል ችሏል ።
የባሕር ዳር ከነማማ ድል
ለአፍሪቃ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ትናንት በተኪያሄዱ ጨዋታዎች፦ የኢትዮጵያው የባሕር ዳር ከነማ ቡድን ድል ቀንቶታል ። ባህር ዳር ከነማ በትናንቱ ግጥሚያ የቱኒዝያው ክለብ አፍሪካ ቡድንን አበበ ቢቂላ ስታዲየም ውስጥ 2 ለ 0 በማሸነፍ ወደ ቀጣይ ዙር የማለፍ እድሉን እጅግ አለምልሟል ። የመልስ ጨዋታው የፊታችን እሁድ ሳምንት ቱኒዝያ ውስጥ ይካሄዳል ። ባህርዳር ከነማ በደርሶ መልስ ውጤት የሚያሸንፍ ከሆነ በአፍሪቃ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳታፊ ይሆናል ። በአማራ ክልል ካለው ጦርነት አንጻር ቡድኑ በስነ ልቦናም ተዘጋጅቶ ማሸነፉ እጅግ የሚያስደንቅ ነው ። ለመሆኑ ቡድኑ በመቀጠል የሚጠብቀው ምንድን ነው? የስፖርት ተንታኙ ጋዜጠኛ ዖምና ታደለ ።
ባህር ዳር ከነማ ወደዚህ ዙር ያለፈው በቅድመ ማጣሪያ ግጥሚያ የታንዛኒያውን አዛም በደርሶ መልስ ጨዋታ አሸንፎ ነው ። ያኔ የነበረውን ጨዋታ ከትናንቱ ጋር ስታነጻጽረው ቡድኑ አቋሙ ምን ይመስላል? ምንስ ላይ ሊያተኩር ይገባል ትላልህ?
ፕሬሚየር ሊግ
በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያ ትናንት አርሰናል በሌያንድሮ ትሮሳርድ ብቸኛ ግብ ኤቨርተንን 1 ለ0 አሸንፎ ወሳኝ ነጥብ ሰብስቧል ። አርሰናል በትናንቱ ድል በደረጃ ሰንጠረዡ ከበላዩ ከሚገኙት ሊቨርፑል እና ቶትንሀም እኩል 13 ነጥብ ይዞ በግብ ክፍያ ብቻ ይበለጣል ። ሊቨርፑል ቅዳሜ ዕለት በጨዋታ ብልጫ ዎልቨርሀምፕተንን በሜዳው 3 ለ1 አሸንፏል ። ከሁለተኛ ደረጃ ከሚገኘው ቶትንሀም ጋር እንደ ነጥቡ ሁሉ በግብ ክፍያም ተስተካክለው የሚበላለጡት ብዙ ባገባ በሚለው ነው ። ቶትንሀም ቅዳሜ ዕለት ሼፊልድ ዩናይትድን 2 ለ1 አሸንፏል።
የነሐሴ 8 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የስፖርት ዘገባበ15 ነጥብ በመሪነት የሰፈረው ማንቸስተር ሲቲ ዌስትሀም ዩናይትድን ከትናንት በስትያ 3 ለ1 ድል አድርጓል ። እስካሁን ያደረጋቸውን አምስቱንም ጨዋታዎች በድል በማጠናቀቅ ዘንድሮም ብርቱነቱን አስመስክሯል ። በሌሎች ግጥሚያዎች ቅዳሜ ዕለት ማንቸስተር ዩናይትድ በብራይተን የ3 ለ1 ሽንፈት በገዛ ሜዳው ገጥሞታል ። አስቶን ቪላ ክሪስታል ፓላስን 3 ለ1 እንዲሁም ኒውካስል ብሬንትፎርድን 1 ለ0 አሸንፈዋል ። ቶትንሀም ሆትስፐር ሼፊልድ ዩናይትድን 2 ለ1 ፤ ፉልሀም ሉቶን ታውንን 1 ለ0 አሸንፈዋል ።
ቸልሲ ከበርመስ ትናንት ያለምንም ግብ ተለያይቷል ። ዛሬ ማታ ኖቲንግሀም ፎረስት ከበርንሌይ ጋር ይጋጠማል ።
ቡንደስሊጋ
በጀርመን ቡንደስሊጋ ሀይደንሀይም የመጀመሪያ ድሉን ትናንት አስመዝግቧል ። በሜዳው ባደረገው ግጥሚያ ቬርደር ብሬመንን 4 ለ2 ማሸነፍ ችሏል ። ትናንት ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ ከዳርምሽታድት ጋር ሦስት እኩል ተለያይቷል ። ቅዳሜ ዕለት በነበሩ ግጥሚያዎች አንድ ተጨዋቹ በቀይ ካርድ ከሜዳ የተሰናበተበት ኮሎኝ በሆፈንሀይም የ3 ለ1 ሽንፈት በሜዳው አስተናግዷል። ላይፕትሲሽ አውግስቡርግን 3 ለ0 አሸንፎ ደጋፊዎቹን አስቦርቋል ።
በደረጃ ሰንጠረዡም በ9 ነጥብ ሦስተኛ ላይ ይገኛል ። ቅዳሜ ዕለት ሁለት እኩል የተለያዩት ባየርን ሙይንሽን በ10 እንዲሁም ባዬርን ሌቨርኩሰን በተመሳሳይ ነጥብ ግን በግብ ክፍያ ልዩነት አንደኛ እና ሁለተኛ ሆነው ተደርድረዋል ። ፍራይቡርግን በሜዳው 4 ለ2 ያሸነፈው ቦሩስያ ዶርትሙንድ በስምንት ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ።
ከቡንደስሊጋው ስንቀጣ፦ የባየርን ሙይንሽን ቦርድ አባል ካርል-ሐይንትስ ሩሜኒገ እና የላይፕትሲሽ ባልደረባው ኦሊቨር ሚንትስላፍ ከጀርምን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ግብረ-ኃይል አባልነታቸው በፈቃዳቸው መሰነናበታቸውን ዐስታወቁ ። ሁለቱ ስመጥር የኳስ ባለሞያዎች ለጀርመን እግር ኳስ ፌዴሬሽን አዲስ ፕሬዚደንት ሲሾም ማንም አላመማከረንም እኛም ያወቅነው ከመገናኛ አውታር ነው ብለዋል ከግብረ ኃይሉ መውጣታቸውን ትናንት ይፋ ሲያደርጉ ። ለጀርመን እግር ኳስ ፌዴሬሽን የኮሎኝ ስፖርት ኃላፊ የነበሩት አንድሪያስ ሬቲንግ አዲስ ፕሬዚደንት ሆነው ተሹመዋል ።
የነሐሴ 29 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የስፖርት ዘገባከዚህም ባሻገር ግብረ ኃይሉ በፌዴሬሽኑ ውስጥ ሥራውን በተሳካ መልኩ እንዳያካሂድ ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይ አንዳችም ጊዜ አልተሳተፈም ብሏል ሩሜኒጋ ። ግብረ ኃይሉ የተቋቋመው የጀርመን እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን ከዓለም ዋንጫ የጥሎ ማለፍ ውድድር ከተሰናበተ በኋላ ነበር ። ከዚያን ጊዜ አንስቶም የጀርመን ወጣቶች ቡድን ብዙም ውጤት አላስመዘገበም ። የሴቶቹም ቡድን ቢሆን ከዓለም ዋንጫ ከምድብ ውድድር ሳይዘል ነው የተሰናበተው ። የጀርመን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን እጅግ አጣብቂኝ ውስጥ ነው ያለው ።
የወንዶች አሰልጣኝ ዲተር ሐንሲ ፍሊክ በአምስት ተከታታይ ጨዋታዎች አራቱን ከተሸነፉ በኋላ ከብሔራዊ ቡድኑ ተሰናብተዋል። አሰልጣኝ ዲተር ሐንሲ ፍሊክ ከተሰናበቱ በኋላ እንደ አሰልጣኝ ቡድኑን ይዞ ባለፈው ሳምንት ከፈረንሳይ ጋር የነበረውን ጨዋታ ያሸነፈው የብሔራዊ ቡድኑ ኃላፊ ሩዲ ፎይለርም የግብረ ኃይሉ አባል ነው ። የቀድሞ የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ተጨዋች እና የቦሩስያ ዶርትሙንድ ኃላፊ ሐንስ-ዮአሂም ቫትስከም ከግብረ ኃይሉ አባላት አንዱ ነው ።
ቡጢ
በ57 ኪሎ ግራም ዘርፍ ኢትዮጵያ በፓሪሱ ኦሎምፒክ ተሳታፊ ለመሆን ለጥቂት ሳይሳካ ቀርቷል ። በዚህ የቡጢ ዘርፍ ኢትዮጵያዊው «ጊችሮ ነብሮ» በሚለው ቅጽል ስሙ የሚታወቀው ኢትዮጵያዊው ቡጢኝ ፍቅረማሪያም ያደሳ ለኦሊምፒክ ማጣሪያ ከናይጀሪያዊው ቡጢኛ ዶላፖ ጆሹዋ ጋር ባደረገው የፍጻሜ ጨዋታ ዳካር ሴኔጋል ውስጥ ሳይሳካለት ቀርቷል ። ፍቅረማሪያም ለፍጻሜ የበቃው አራት ግጥሚያዎችን በተከታታይ በማሸነፍ ነበር ። ባለፈው ሳምንት ዐርብ በነበረው ግጥሚያ ፍቅረማሪያም አሸናፊ ሆኖ ኢትዮጵያን በፓሪስ ኦሎምፒክ ይወክላል የሚል ተስፋ በብዙዎች ዘንድ ነበር ። ፈረንሳይ በምታሰናዳው የፓሪስ ኦሎምፒክ የቡጢ ፉክክር ተሳታፊ ለመሆን አልመው በአፍሪቃ የቡጢ ፉክክር የመጨረሻው ጫፍ በመድረስ ፍቅረማሪያም ያስመዘገበው ውጤት ይበል የሚያሰኝ ነው ። ወደፊት በቡጢው ዘርፍ ብዙ ከተሠራ ውጤት ሊኖር እንደሚችልም አመላክቷል ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ኂሩት መለሰ