1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጀርመን ብዝኃነት ውስጥ የአፍሪቃውያን ሞያተኞች ሚና

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 16 2015

ዛሬ ዛሬ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ አፍሪቃውያን ስደተኞች እንደ ጀርመን ባሉ የአውሮጳ ሀገራት የላቀ ሞያ በሚጠይቁ ስራዎች ተሰማርተው መገኘታቸው እንግዳ አይደለም። ይልቅ በቁጥር እና ካሁን ቀደም ነጮች ብቻ ይታዩባቸው በነበሩ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ ጭምር ውክልና እስከማግኘትም ደርሰዋል።

https://p.dw.com/p/4VQ3T
Selamawit Getachew - Wissenschaftlerin
ምስል Privat

አፍሪቃውያን ሞያተኞች በጀርመን በእርግጥ ቦታ እያገኙ ይሆን ?

ዛሬ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ አፍሪቃውያን ስደተኞች እንደ ጀርመን ባሉ የአውሮጳ ሀገራት የላቀ ሞያ በሚጠይቁ ስራዎች ተሰማርተው መገኘታቸው እንግዳ አይደለም። ይልቅ በቁጥር እና ካሁን ቀደም ነጮች ብቻ ይታዩባቸው በነበሩ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ ጭምር ውክልና እስከማግኘትም ደርሰዋል። አፍሪቃውያኑ የቆዳ ቀለማቸው ለብቻው ጫና በሚያሳድርባቸው ዓለም በዕውቀት እና ክህሎት ብዙ ከእነርሱ ርቀው ከሚገኙት ተወዳዳሪ ሆነው ፤ ብሎም የተሻለ ቦታ እስከመድረስ መቻላቸው በተለይ በጀርመን ብዝኃነት እየተስተናገደ ስለመምጣቱ እየተሰማ ነው ።
ዶ/ር ጸጋዬ ደግነህ አሁን በጀርመን የመርሴዲስ ቤንዝ ኩባንያ ውስጥ የምጣኔ ኃብት ባለሞያ ናቸው ። ወደ ጀርመን የመጡት ያኔ ገና ሁለቱ ጀርመኖች ሳይዋሃዱ በምስራቅ ጀርመን ባገኙት የየነጻ ትምህርት ዕድል አማካኝነት ነበር ። የመጀመሪያ  ፣ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ብሎም የሶስተኛ ወይም የዶክትሬት ዲግሪአቸውን በተከታታይ ባገኙት የትምህርት ዕድል ተጠቅመው እዚሁ ጀርመን መማር ችለዋል። በተለያየ መንገድ ወደ ጀርመን እንደመጡ እና ያገኙትን ዕድል በአግባቡ እንደተጠቀሙት ሌሎች አፍሪቃውያን ሁሉ ዶ/ር ጸጋዬ በተማሩበት የትምህርት መስክ የስራ ዓለምን አንድ ብለው ሲጀምሩ መማራቸው እንደጠቀማቸው ይናገራሉ።አፍሪቃውያን ጀርመናውያን በጀርመን እውቅና ለማግኘት የሚያደርጉት ትግል
« መጀመሪያ የስራ ልምዴን አንድ ኦልስቴት በሚባል የኢንሹራንስ ኩባንያ እዚያ የቢዝነስ አናሊስት ሆኜ ጀመርኩኝ እዚያም ብዙ ሳልቆይ ወደ መርሴዴስ ቤንዝ ኩባንያ  በአይ ቲ ላይ ፕሮጀክት ፖርት ፎሊዮ ቦታ አግኝቼ ገባሁኝ ፤ ከዚህ በተጨማሪ ፒኤች ዲ እየሰራሁ በሰመር ስኩል በዚያው በፕሮጀክት ማኔጅመንት ኳሊፋይ አድርጌ ነበር ጠቅሞኛል ማለት እችላለሁ »
ዶ/ር ጸጋዬ በዓለም አቀፍ ደረጃ  ከባድ ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ ቅንጡ የቤት ተሽከርካሪዎችን በማምረት በሚታወቀው የሜርሴዴስ ኩባንያ ውስጥ በመስራት ብቻ አልተገደቡም ። በሀገረ ጀርመን ስም እና ዝና ብቻ ሳይሆን ከሀገሪቱ መንግስት ሽልማት እስከማግኘት ባደረሳቸው የማህበራዊ አገልግሎት እና የማርሻል አርት ስፖርት የነቃ ተሳትፎ ያደርጋሉ ።
« በዚህ ሆቢዬ በሆነ ስፖርት በጁዶ ጁጂትሱ ወደ ሰላሳ ዓመት ያህል ሰርቻለሁ ከዚያም በዓለም አቀፍ ፌዴሬሽን ውስጥ የስነ ምግባር ኮሚሽን ውስጥ ምክትል ፕሬዚዳንት ነኝ። የተለያዩ ኮሚሽኖች ውስጥም አለሁበት ።»
እንደ ዶ/ር ጸጋዬ ያሉ አፍሪካዊ መሰረት ያላቸው በተወለዱበት ሀገር ዜግነት አልያም የጀርመን ዜጋ ሆነው የላቀ ሞያ እና ክህሎትን ጨምሮ በተለያዩ የስራ መስኮች ተሰማርተው ይገኛሉ ። በእርግጥ ነው ጀርመን ከአፍሪቃውያን በተጨማሪ ከመላው ዓለም ከተለያየ ባህል ፣ እምነት፣ ቋንቋ ፣ የቆዳ ቀለም እና  እና ማህበራዊ መሰረት ለመጡ ሰዎች በሯን መክፈቷ ለበርካቶች የህይወት መለወጥ ምክንያት መሆኑ ይነገርለታል።የቀኝ ጽንፈኛው «አማራጭ ለጀርመን» ፓርቲ መጠናከርና ስጋቱ
ዶ/ር ደረጀ በለው ተወልደው ያደጉት ኢትዮጵያ ውስጥ ቢሆንም በወቅቱ የፖለቲካ አመለካከታቸው ወደ ዩኒቨርሲቲ ገብተው እንዳይማሩ እንቅፋት ፈጥሮባቸው እንደነበር ይናገራሉ ። በጎርጎርሳውያኑ 1985 ወደ አውሮጳ የተሰደዱው የያኔው ወጣቱ ደረጀ ጀርመን ያቀረበችለትን  ገጸ በረከት በአግባቡ በመጠቀሙ ለዛሬው ዶ/ር ደረጀ መሰረት ጥሏል። በአንድ የመንግስታዊ ተቋም ውስጥ በፋይናንስ አስተዳደር የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አማካሪነት የሚያገለግሉት ዶ/ር ደረጀ በአገልግሎታቸው ኩባንያቸው ደስተኛ ነው። እርሳቸውም ቢሆኑ በስራቸው የተሻለ ክፍያ ያገኛሉ ።  ከዶ/ር ደረጀ ንግግር መረዳት የቻልነው አፍሪቃውያን በጀርመኖች እየተፈለጉ ስለመምጣታቸው ነው ።
«በዚህ ኩባንያ ውስጥ ተቀጥሬ ኩባንያው በጣም ደስተኛ ነው። እኔም በኩባንያው በጣም ደስተኛነኝ ። ጥሩ ተከፋይ ነኝ ። እና እኔ ለኩባንያው የማበረክተው አስተዋጽዖ በጣም ከፍተኛ ነው። የፕሮጀክት ኃላፊ ነኝ ፕሮጀክቶች አንቀሳቅሳለሁ። በአሁኑ ሰዓት ለምሳሌ ትልልቅ ሁለት ፕሮጀክቶችን በኃላፊነት እያሰራሁ ነው። ሶስተኛ ፕሮጀክት ነው ፤ ይኸኛው ደግሞ በሚሊዮን የሚቆጠር ፕሮጀክት ነው ። እና ለጀርመን ለመግለጽም ደግሞ ለመናገር ከተፈለገ የኛ ስራ በጣም ተፈላጊ ነው ይፈልጉታል።» 
በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ትልልቅ ስም እና ዝናን ያተረፉ የእግር ኳስ ተጫዋቾችን ጨምሮ ፤ በህክምና ፣ ሕግ ፣ ምህንድስና ፣ በጥበባዊ ኢንዱስትሪ በስራቸው አንቱታን ያተረፉ አፍሪቃውያን በርካቶች ናቸው ።ጀርመን፤ ዶ/ር እሌኒ ገብረ መድኅን የግሎባል ኢኮኖሚ ሽልማትን አሸነፉ ቀደም ሲል አልፎ አልፎ ብቻ ይታዩ የነበሩ አፍሪቃውያን አሁን አሁን በአንድ የስራ መስሪያ ቤት በርከት ብለው እንደሚታዩ ነው ዶ/ር ደረጀ የነገሩን ።
« የአይ ቲ ስፔሻሊስት ኢትዮጵያውያን አሉ የማውቃቸው ፤ ከካሜሩን ፣ ሞሮኮ አሉ አሁን የኔ መስሪያ ቤት የሚሰሩ እዚህ ኩባንያ ብቻ እና ጠቀሜታው ትልቅ ነው ለማለት ነው ። 
አዎ ይህንኑ ተከትሎ ነው እንግዲህ ጀርመን ለብዝኃነት በሯን መክፈቷ በማሳያነት የሚጠቀሰው ። በዓለም 4ኛዋ የኤኮኖሚ ባለቤት ጀርመን ባለፈው የሰኔ ወር በርካታ የተማረ የሰው ኃይል መቀበል የሚያስችላትን ሕግ በላይኛው ምክር ቤት ማጽደቋ ይታወሳል ። ዶ/ር ጸጋዬ ደግነህ እንደሚሉት በጀርመኖቹ የትውልድ ቅብብሎሽ መካከል ክፍተት መፈጠሩ ሀገሪቱ ካሁን ቀደም ተቀራራቢ ኤኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ መሰረት ካላቸው ሀገራት ብቻ የተማረ የሰው ኃይል የመቀበል አሰራሯን ለማሻሻሏ በምክንያትነት ይጠቅሳሉ።
«አሁን የጡረታ ስረዓቱ እድሜያቸው በጣም እየገፋ ስለመጣ የእነርሱን ጡረታ የሚከፍልላቸው ሰው ያስፈልጋቸዋል። አብዛኛው በጣም ወጣት ነው ፤ ወይም ዕድሜው በጣም የገፋ ነው። በዚያ መካከል ክፍተት ስላለ የተማረ ሰው ይፈልጋሉ ። እና ባለሞያዎች መግባት አለባቸው ብለው ነው የሚያስቡት እና መጀመሪያ ሃሳባቸው የነበረው መሰል ከሆኑ ሃገራት ያስቀድሙ ነበር ከአውሮጳ ወይ ከአሜሪካ ወይ ከእንደዚህ አይነት አካባቢ ቢመጡልን ብለው ነበር የሚያስቡት ከዚያ ቀጥለው ወደ ህንድ ፤ እና አሁን አሁን ግን ያ ሁሉ ተነስቶ ከአፍሪቃም ቢመጡልን የሚል አይነት ነገር በሃሳብ እና በድርጊትም እያየን ነው።  »
አፍሪቃውያኑ በጀርመን ኤኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ከአነስተኛ የስራ መደቦች ጀምሮ እስከ በከፍተኛ ደረጃ ተከፋይ እስከ ሚያደርጉ የሞያ መስኮች ሚናቸው እየታየ ነው ። ለዚህም ነው የሃገሪቱ ምክር ቤት በሕግ ማዕቀፍ የተማሩ ሰዎችን ለመቀበል የሚያስችል ህግ እስከ ማውጣት የደረሰው ። ዶ/ር ደረጀ በለውም የዶ/ር ጸጋዬን ሃሳብ ያጠናክራሉ ።ወጣት ኢትዮጵያውያኑ በጀርመን ፤ከጥናት እና ምርምር ባሻገር
« ትልቅ ተሳትፎ  ነው ምንም ጥያቄ የለውም ። አሁን ራሱ በቅርብ ሰምተኸው ከሆነ አዲስ ሕግ የስራ የጉልበት ወይም ደግሞ በከፍተኛ ደረጃ እጥረት ስላለባቸው ከፍተኛ አስተዋጽዖ ነው ያለው ። ሐኪሞችን በጠቀስከው መሰረት ብዙ ኢትዮጵያውያን ጓደኞቼ እኔ እዚህ ምኖርበት ከተማ እንኳ ከአምስት ከስድስት በላይ ሀኪሞች አሉ። ትልቅ ሆስፒታል ኃላፊነት ይዘው የሚያንቀሳቅሱ ፣ በኃላፊነት ደረጃ ዳይሬክተር ሆነው የሚሰሩ ሼፍ አርትስ ይባላል በጀርመን ፤ ሼፍ አርትስ ማለት ትልቅ ስራ ነው።   »
ዛሬ በአርአያነታቸው ስማቸውን በዚህ ዝግጅት የምናነሳቸው ኢትዮ አፍሪቃውያን ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ ሆኖላቸውም እዚህ አልደረሱም ። ዛሬም ድረስ አንዳንዶች እንደሚሉት ፊት ለፊት ባይገለጽም በላቀ ሞያ ፤ ሃብት ፈጥረው አልያም በማንኛውም ሁኔታ የተሻለ ቦታ ላይ የሚደርሱ የቆዳ ቀለማቸው ጥቁር ስለሆነ ብቻ እንዴት እዚህ ደረሰ አይነት እና ለጥላቻ አመለካከት ሲጋለጡ ይሰማል ። ዶ/ር ደረጀ በለው በአንድ አጋጣሚ ስራቸውን እስከ መልቀቅ ያደረሳቸውን ተመሳሳይ የዘረኝነት ጥቃት ወደ ኋላ ተመልሰው ያስታውሳሉ ።
« የቆዳ ቀለም የሚለው በትክክል አይገለጽም።  ግን በተዘዋዋሪ መንገድ ፤ ሁለት መስሪያ ቤቶች ለምሳሌ አሁን ከሰራሁበት ወይም መጀመሪያ በራሴ አማካሪ ሆኜ ከመስራቴ በፊት ሁለት መስሪያ ቤቶች ድሮ ምስራቅ ጀርመን ከተገናኙ በኋላ ጥሩ ደሞዝ እየከፈሉኝ ግን መስሪያ ቤቱ ውስጥ ከእኛ የበለጠ እንዴት ሊከፈለው ይችላል ? እንዴትስ ደግሞ ትምህርት እንዲህ አይነት ውጤት ልታመጣ ትችላለህ የሚሉ አንዳንድ ጥያቄዎች ይቀርቡ ነበር ያ ማለት እንግዲህ በተዘዋዋሪ የቅናት ወይም ደግሞ ጥቁሩ ከእኛ የተሻለ እንዴት ሊሆን ይችላል የሚል አመለካከት እንዳላቸው ይገባኛል።» ። ጀርመን የታንዛንያ ቅኝ ግዛት ዘመን የተፈጸሙ በደሎች
በእርግጥ የፈተና አይነት እና መልኩ ይለያይ እንጂ አፍሪቃውያን በትውልድ ሃገራቸውም ቢሆን አይቀርላቸውም ፤ ፖለቲካው ይሁን ማህበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ችግሩ ዘርፈ ብዙ ነው። በዚህ ሁሉ መሃል ግን ለዘመናት አንጡራ የተፈጥሮ ሃብቷን ስትቦጠቦጥ የኖረችው አፍሪቃ ለዓመታት ያስተማረቻቸው ልጆቿን ሳትወድ አሳልፋ ለመስጠት መገደዷን እንመለከታለን ። ምዕራባውያኑ ያደገውን ኤኮኖሚያቸውን የበለጠ ለማጎለበት «ብዝኃነትን ለማስተናገድ» ይሁን የስራ ዕድል ፈጠራ በአንዱ ልፋት የተፈጠረውን የትውልድ ክፍተት ለመሙላት ሕግ እስከማውጣትም ይደርሳሉ ። አፍሪቃውያኑ በጀርመንም ይሁን በተቀረው ዓለም ያላቸውን ዕውቀት እና ክህሎት ተጠቅመው  ራሳቸውን ለመለወጥ ከሚያደርጉት ጥረት ጎን ለጎን የተነሱበትን አንድ አፍታ መለስ ብሎ መመልከትም ተገቢ ሳይሆን አይቀርም ። 

Ausstellung The Cube Eschborn | “Ernest Cole. House of Bondage"
አፍሪቃውያን ወደ አውሮጳ ለመግባት ከአሁን በፊት የሚጋፈጡት ፈተና ቀላል አልነበረም ምስል Ernest Cole/Magnum Photos
አፍሪቃውያን ስደተኞች በኮለን የእግር ኳስ ክለቦችን ለመቀላቀል ጥረት ያደርጋሉ
አፍሪቃውያን ወጣት ስደተኞች በእግር ኳሱ ዓለም ስም እና ዝና እያተረፉ መጥተዋል።ምስል DW/A.-Bakarr Jalloh
Modelabel Noh Nee Marie Darouche und Rahmee Wetterich
አፍሪቃውያን መሰረት ያላቸው ጀርመናውያን በጀርመን የስራ ዓለም ብዝኃነትን እያጠናከሩ መሆኑ ተገልጿል።ምስል Christoph Stache/AFP/Getty Images
ዶ/ር ደረጀ በለው የፋይናንስ አስተዳደር የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አማካሪ
ዶ/ር ደረጀ በለው የፋይናንስ አስተዳደር የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አማካሪ ምስል privat
ዶ/ር ጸጋዬ ደግነህ
ዶ/ር ጸጋዬ ደግነህ በተለያዩ መድረኮች ንግግሮች እንዲያደርጉ ይጋበዛሉምስል privat
ሳንድራ ኩያላ የዶይቼ ቬለ ጋዜጠኛ
ሳንድራ ኩያላ በዶይቼ ቬለ የፖርቱጋል ቋንቋ ዘጋቢ ጋዜጠኛምስል Philipp Böll/DW
ሰላማዊት ጌታቸው የዶክትሬት ዲግሪ ተማሪ እና
ፎቶ ማህደር ፤ ሰላማዊት ጌታቸው በሎንዶን የዶክትሬት ዲግሪ ተማሪ እና በወጣት አፍሪቃውያን የሳይንስ ክህሎት የውድድር መድረክ ተካፋይ ነበረች ምስል Privat
ዶ/ር ደረጀ በለው በጀርመን በአንድ የመንግስት መስሪያ ቤት የፋይናንስ አስተዳደር የአይቲ አማካሪ
ዶ/ር ደረጀ በለው በጀርመን በአንድ የመንግስት መስሪያ ቤት የፋይናንስ አስተዳደር የአይ ቲ አማካሪ ናቸውምስል privat
ዶ/ር ጸጋዬ ደግነው የጁዶ ስፖርት ላይ
ፎቶ ማህደር፤ ዶ/ር ጸጋዬ ደግነው በጀርመን በጁዶ ስፖርት ታላቅ ስም እና ዝናን ማትረፍ ችለዋል። በጁዶ ስፖርት ለሰላሳ ዓመታት የዘለቀ ልምድ እና እስk ከፍተኛ የስፖርቱ ማዕረግ መዝለቅ ችለዋል።ምስል privat
ዶ/ር በጋዬ ደግነው  ከቀድሞዋ በጀርመን የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙሉ ሰሎሞን ጋር
ፎቶ ከማህደር ፤ ዶ/ር በጋዬ ደግነው በጀርመን ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር ተቀራርበው እንደሚሰሩ ይነገርላቸዋል። በዚህም የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ በጀርመን በማስተባበርም ሚናቸው ጎልቶ ይሰማል።ምስል Biruk Andarge Seifegebreal
ዶ/ር ጸጋዬ ደግነህ ከጀርመን መንግስት የእውቅና ሽልማት ሲቀበሉ
ዶ/ር ጸጋዬ ደግነህ በጀርመን ህይወታቸው ላበረኩቷቸው ማህበራዊ አስተዋጽዖዎች ከጀርመን መንግስት እውቅና እና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።ምስል Biruk Andarge Seifegebreal


ማንተጋፍቶት ስለሺ 
ታምራት ዲንሳ