የ«አማራጭ ለጀርመን» ፓርቲ መጠናከርና ስጋቱ
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 2 2015በቅርቡ የተካሄዱ የህዝብ አስተያየት መመዘኛዎች፣ የጀርመን መራጭ ወደ ቀኝ ጽንፈኛው «አማራጭ ለጀርመን» በምህጻሩ AfD የተባለው ፓርቲ እያደላ መሆኑን ያመለክታሉ ትላለች የዶቼቬለዋ ዛቢነ ኪንካርትዝ። ባለፈው ሳምንት ምርጫ ቢካሄድ ተብሎ ለ1,297 ሕጋዊ መራጮች በተሰጠ የህዝብ አስተያየት መመዘኛ ውጤት መሠረት ፣ጽንፈኛው AfD 21 በመቶ ድምጽ ያገኝ ነበር ተብሏል። ይህም ከቀድሞዋ የጀርመን መራኄ መንግሥት ፓርቲ የክርስቲያን ዴሞክራቶች ኅብረት CDU ካገኘው ቀጥሎ ያለው ቦታ ነው CDU በመመዘኛው ከሁሉም ጠንካራ የተባለ 27 በመቶ ድምጽ ያገኝ ነበር እንደ ትንበያው። በአንጻሩ የመሀል ግራውን ጥምር መንግሥት የመሰረቱት ሦስት ፓርቲዎች ግን አብላጫ ድምጽ ሳያገኙ ቀርቷል።የመራኄ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ ፓርቲ SPD ባለፈው ምርጫ ካገኘው 25.7 በመቶ ድምጽ አሁን ወደ 17 በመቶ ዝቅ ሲል የፓርቲው መሪ የመራኄ መንግሥት ሾልዝ ድጋፍም በጣም እየቀነሰ ሄዷል። ከአንድ ዓመት በፊት በህዝብ አስተያየት መመዘኛ 25 በመቶ ድጋፍ የነበራቸው አረንጓዴዎቹ ወደ 15 በመቶ፣ የነጻ ዴሞክራቶቹ ፓርቲ በምህጻሩ FDP ደግሞ ከከዚህ ቀደሙ 11.5 በመቶ ወደ 7 በመቶ ወርዷል። ከሁሉ ከሁሉ የግራዎቹ ፓርቲ ተንሸራቶ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ ለመግባት የሚያስችለውን 5 በመቶ ድምጽ ማግኘት መቻሉም አጠራጥሯል። የቅርብ ጊዜው የህዝብ አስተያየት መመዘኛ ብቻ ሳይሆን ከዚህ ቀደም ያሉትም ተመሳሳይ ውጤት ማሳየታቸው የበርሊኑ ዘጋቢያችን ይልማ ኃይለ ሚካኤል እንደሚለው ብዙ አነጋግሯል።
እህትማማቾቹ CDU እና CSU ፓርቲዎች 80 ዓመታት ከተጠጋው ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወዲህ ከነፃ ዴሞክራት ፓርቲ FDP ወይም ከሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ SPD ጋር እየተጣመሩ የጀርመን ፌደራል መንግሥትን ለበርካታ ዓመታት መርተዋል።ሆኖም የአሁኑ የCDU መሪ ፍሬድሪሽ ሜርዝ በፓርቲያቸው አባላት ሳይቀር ያላቸው ድጋፍ አነስተኛ መሆን ፓርቲውን ወደ ፌደራል መንግሥት መሪነት ሊመለስ መቻሉን አጠራጣሪ አድርጎታል። በቅርብ ጊዜው አስተያየት መመዘኛ ከሦስት የፓርቲው ደጋፊዎች አንዱ ብቻ ናቸው ሜርዝ በበጎርጎሮሳዊው 2025 በሚካሄደው አጠቃላይ ምርጫ ቀጣዩ የጀርመን መራኄ መንግሥት እንዲሆኑ የሚፈልጉት። ከተቋቋመ ባለፈው ሚያዚያ አስር ዓመት የሞላው «አማራጭ ለጀርመን» በምሥራቅ ጀርመንዋ በማግደቡርግ ከተማ በሁለት የሳምንት መጨረሻዎች ባካሄደው ጉባኤ የተለያዩ ውሳኔዎች አሳልፏል። ከመላ ጀርመን የተሰባሰቡ 600 ያህል የፓርቲው አባላት የተገኙበት ይኽው ጉባኤ በሚቀጥለው ዓመት በጎርጎሮሳዊው ሰኔ 2024 ዓ.ም. በሚካሄደው የአውሮጳ ህብረት ምክር ቤት አባላት ምርጫ በሚወዳደሩ እጩዎች እንዲሁም በሚቀጥለው ዓመት በሀገር ውስጥ በተለያዩ ግዛቶች ምርጫዎች ተጨማሪ ድሎች የማግኘት ተስፋ ሰንቋል። ፓርቲው በሚቀጥለው ዓመት በአውሮጳ ኅብረት ምክርቤት ምርጫ የሚወዳደሩ 35 እጩዎችን ዝርዝርም አሳውቋል።ምርጫውን እንዲመሩም የኅብረቱ ፓርላማ አባል ማክሲሚላን ክራህንን መርጧል።
ፓርቲው ከአንድ ሳምንት በፊት በርካታ ደጋፊዎቹ በሚገኙበት በማግድቡርግ ከተማ ጉባኤውን በጀመረበት እለት አንድ ሺህ እንደሚሆኑ የተገመቱ ሰዎች ጉባኤው በሚካሄድበት ቦታ ፊት ለፊት ተቃውሞአቸውን ሲያሰሙ ነበር ።በቀድሞዋ ኮምኒስት ምሥራቅ ጀርመን፣ ዛክሰን አንሀልት ፌደራዊ ክፍለ ሀገር ዋና ከተማ ማግድቡርግ አደባባይ የወጡት ሰልፈኞቹ ከሁሉም በላይ በየጊዜው በሚካሄዱ የህዝብ አስተያየት መመዘኛዎች ፓርቲው የሚያገኘው ድጋፍ እየጨመረ መሄዱ በጣም አሳስቧቸዋል። ከመካከላቸው ተማሪና የግራዎቹ ፓርቲ አባል ሌና ራይንሃርት አንዷ ናቸው።
«እርግጥ ነው የቅርብ ጊዜው የህዝብ አስተያየት መመዘኛ ውጤት ሁላችንንም በጣም አሳስቦናል። እዚህ ምን እየሆነ ነው?በጀርመን ወደ ቀኝ ጽንፈኞች ማዘንበሉ እንዴት በግልጽ ሊሆን ቻለ? ከምንም በላይ ዓይኔ ስር በግልጽ ብሔራዊ ሶሻሊስት ፓርቲ በፍጥነት ድጋፍ እያገኘ ነው? »ሌላው ለተቃውሞ የወጣው ሰልፈኛ ሉቃስ እንደሚለው የፓርቲው መጠናከር ያሰጋዋል። «ዛሬ እዚህ የመጣሁት አማራጭ ለጀርመን በምህፃሩ AFD በጀርመን በእጅጉ ለዴሞክራሲ አደጋ ነው ብዬ ስለማስብና ያልተለመደ ስሜት ለፈጠረብኝ ለኔ በከፍተኛ ደረጃ ስለሚያሰጋኝ ነው።»
የአውሮጳ የጋራ መገበያያ ገንዘብ ዩሮን በመቃወም የተመሰረተው «አማራጭ ለጀርመን» በሂደት ወደ ፀረ-እስልምናና ፀረ-ስደተኞች ፓርቲነት ተቀየረ። በመራኄ መንግሥት አንጌላ ሜርክል የስልጣን ዘመን በ2015 ዓ.ም. ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ስደተኞች ጀርመን የገቡበትን አጋጣሚ ለፕሮፓጋንዳው በመጠቀም ፓርቲው ከክስተቱ አትራፊ ለመሆን በቃ።ከጊዜ ወደ ጊዜ የደጋፊዎቹ ቁጥር እየጨመረ ሄዶ በጎርጎሮሳዊው 2017ቱ አጠቃላይ ምርጫ በጀርመን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች አገኝቶ ዋነኛ የተቃዋሚ ፓርቲ ሆነ ። በ2021ዱ ምርጫም ባገኘው ውጤት ከከዚህ ቀደም የላቀ ቁጥር ያላቸው አባላቱ የምክር ቤት መቀመጫ ይዘዋል። ከጥቂት ሳምንታት በፊት ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ቱሪንገን በተባለችው በቀድሞዋ የምሥራቅ ጀርመን ግዛት በምትገኘው የ56 ሺህ ህዝብ መኖሪያ ዞነንበርግ ከተማ የፓርቲው እጩ የከተማይቱ ከከንቲባ ማዕረግ ሆነው ተመርጠዋል። የፓርቲው እጩ ሮበርት ሴሰልማን የተቃዋሚውን የክርስቲያን ዴሞክራት ፓርቲ እጩ ዩርገን ኮፐርን አሸንፈው ነው ከንቲባ የሆኑት። አንድ የፓርቲው እጩ በዚህ ደረጃ ሲያሸንፍ የዞነንበርጉ ምርጫ የመጀመሪያው ነው። በሶሻል ዴሞክራቱ መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ በሚመራው ጥምር መንግሥት ፖሊሲዎችና በጀርመን ምጣኔ ሀብት መዳከም ያልተደሰቱ ጀርመናውያን ለ«አማራጭ ለጀርመን» ድጋፋቸውን አጠናክረዋል።
በቅርቡ በተካሄደ የህዝብ አስተያየት መመዘኛ ፓርቲው በብሔራዊ ደረጃ ከሾልዝ የጀርመን ሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ የሚቀድመውንና ከዋነኛው ተቃዋሚ ፓርቲ ከክርስቲያን ዴሞክራቶች ኅብረት ቀጥሉ ያለውን ቦታ መያዙ አሁን እንዳስገረመ ቀጥሏል። ከጀርመን የምርጫ ጥናት ተቋም ቡድን ማትያስ ዩንግ ለፈረንሳይ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት የአማራጭ ለጀርመን ፓርቲ ደጋፊዎች ስለ ዓለም ጠባብ አመለካከት ካላቸው አንስቶ እስከ ቀኝ ጽንፈኞች፣ እምብዛም የፖለቲካ ፍላጎት የሌላቸው ፣በወቅቱ የጀርመን ፖሊሲ የተበሳጩ እንዲሁም የጀርመን ወግ አጥባቂ ፓርቲዎችን እንደ ታማኝ አማራጭ የማያያዩ ናቸው። ከበርሊኑ የሽርቲ የአስተዳደር ትምህርት ቤት አንድሪያ ሮመለ ደግሞ የጀርመን መንግሥት አባላት ስለ ፓርቲው ሲከራከሩ AFD ግን ደጋፊዎቹን ያስፈሩ የነበሩትን የውስጥ ጠቦች ጥሎ አልፏል ብለዋል። ፓርቲው በተለይ በጎርጎሮሳዊው 1990 ከተካሄደው የጀርመን ውኅደት በኋላ ተረስተናል የሚል ስሜት ያላቸው በርካቶች በሚገኙባት በምሥራቅ ጀርመን ውጤታማ ነው።በአስተያየት መመዘኛዎች መሠረት በጎርጎሮሳዊው መስከረም 2024 የአካባቢ ምክር ቤቶች ምርጫ በሚካሄድባቸው በምሥራቅ ጀርመኖቹ ግዛቶች በትዩሪንገን፣በዛክሰን እና በብራንድቡርግ ግዛቶች ወደ 30 በመቶ የሚደርሱ ደጋፊዎች አሉት።ከወዲሁ እንደተገመተው AfD ከሶስቱ ግዛቶች ምክር ቤቶች ቢያንስ በአንዱ አብላጫ መቀመጫ ሊያገኝ ይችላል። ሆኖም በመጪው ጥቅምት ምርጫ በሚያካሂዱት በባቫሪያና በሄሰን ግዛቶች መጠነኛ ድጋፍ ቢኖረውም በአስተያየት መመዘኛዎች ግን ድጋፉ እየዋዠቀ ነው ተብሏል።
በ2025 ዓ.ም. በሚካሄደው የጀርመን አጠቃላይ ምርጫ የሚወዳደር ዕጩ እንደሚሰይም ያሳወቀው ፓርቲው በአሁኑ ጉባኤው ቀድሞም የሚቃወመውን የአውሮጳ ኅብረት «የከሰረ ፕሮጀክት» ሲል አጣጥሎታል። ፓርቲው ባወጣው መግለጫ «የአውሮጳ ኅብረት» ፍልሰትና የአየር ንብረት ለውጥን ጨምሮ በሁሉም አስፈላጊ በሚባሉ ጉዳዮች ላይ ሙሉ በሙሉ አልተሳካለትም ያለው ፓርቲው አሁንም ዩሮ መገበያያ ገንዘብ መሆኑን እቃወማለሁ ብሏል።የአውሮፓ ኅብረት የአውሮፓ ሀገራት ፌደሬሽን ሆኖ እንደገና እንዲመሰረትም ጥሪ አቅርቧል። ዋና ዋና ተግባራቱ ተግባራቱም ሊሆኑ ይገባሉ ካላቸው መካከልም የውጭ ድንበርን ከፍልሰተኞች መጠበቅ እና በአውሮጳ የተለያዩ ማንነቶችን ጠብቆ ማቆየት የሚሉት ይገኙበታል ።ሆኖም ፓርቲው ጀርመን ከኅብረቱ ትውጣ አላለም። ይልቁንም አዲሱ የAfD ፕሮግራም የአባት ሀገሮች አውሮጳ እና የሉዓላዊና ዴሞክራሲያዊ ሀገራት የአውሮጳ ማኅበረሰብ ከዚህ ቀደም አንዳንድ የፓርቲው ባለሥልጣናት ጀርመን ከኅብረቱ ትውጣ የሚለውን አቋማቸውን ያስተጋቡ ነበር።
ኂሩት መለሰ
እሸቴ በቀለ