1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ትምህርትአፍሪቃ

ወጣት ኢትዮጵያውያኑ በጀርመን ፤ከጥናት እና ምርምር ባሻገር

ዓርብ፣ ሰኔ 23 2015

« እንደሚመስለኝ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ችግር እና ጀርመን ያለው ችግር ልዩነት እንዳለው ሁሉ የምርምር አቅጣጫውም ልዩነት ይኖረዋል። አሁን የኢትዮጵያን ከወሰድክ ያለውን ምርት ለማሳደግ ነው ምርምሮች የሚሰሩት ፤ እዚህ የግብርና ሥራ ሲያከናውኑ በሰው ልጅ ጤና ላይ ፣ አካባቢ ላይ፣ የአየር ንብረት ለውጥ ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል የሚለውን ነው»

https://p.dw.com/p/4TGqs
Äthiopische Jungforscher in Bonn
ደረጀ ታምሩ፣ የሻምበል ምወድህ እና ዚያድ አብርሃ ምስል Dereje Tamiru

የወጣቶቹ ጥናት እና ምርምር በተስፋ እና ስጋት መካከል

ሰላም ጤና ይስጥልን የዝግጅታችን ተከታታዮች ለዛሬ ነጻ የትምህርት ዕድል አግኝተው እዚህ ጀርመን ሀገር መጥተው ለሶስተኛ ዲግሪ ወይም የዶክትሬት ዲግሪ ማሟያ የላቀ የግብርና የምርምር ሥራ እያከናወኑ የሚገኙ ሶስት ኢትዮጵያውያን ተመራማሪዎችን እንግዳ ያደረግንበትን መሰናዶ ነው ይዘን የቀረብነው ። ከዝግጅቱ ጋር ታምራት ዲንሳ ነኝ አብራችሁን እንድትቆዩ የአክብሮት ግብዛችን ነው ።

ደረጀ ታምሩ ትውልድ እና ዕድገቱ ኦሮሚያ ክልል ነው።  የሻምበል ምወድህ ከአማራ ክልል እንዲሁም ዚያድ አብርሃ ከትግራይ ክልል የመጡ ናቸው። ሶስቱም ተማሪዎች የነጻ የትምህርት ዕድሉን ከማግኘታቸው በፊት በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር የተለያዩ ማዕከላት ውስጥ መለስተኛ የግብርና የምርምር  ተግባራትን ያከናውኑ ነበር። ጀርመንን ጨምሮ አውሮጳ በሙሉ ማለት ይቻላል፤ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በታገዘ የግብርና ሥራ ውጤታማ በመሆን በጥቂት መሬት ላይ ከራስ አልፎ ተርፎ ለተቀረው ዓለም ገበያ የሚቀርብ ሁለገብ የግብርና ምርት የሚያጋብስ አቅም ፈጥረዋል። እንደ ኢትዮጵያ ካሉ የሶስተኛው ዓለም ምሁራን ወደዚህ ቴክኖሎጂ ጠገብ ምድር ሲመጡ ተጠባቂ የዕውቀት ሽግግር ይኖራል። ኢትዮጵያውያኑ ወጣት ተመራማሪዎች በጀርመን ቆይታቸው የሚያከናውኑት የምርምር ሥራዎች ከሀገር ቤቱ ጋር እያነጻጸሩ ሲገልጹ እንዲህ ይላሉ። የሻምበል ፤

Deutschland, Bonn | junge Äthiopische Forscher
ደረጀ ታምሩ እና የሻምበል ምወድህ ፤ ቦን ዩኒቨርሲቲ ጀርመንምስል Tamirat Dinssa/DW

«ከዚህ ሀገር ከመጣን በኋላ ያየሁት ልዩነት እዚህ የላቀ ቴክኖሎጂ ይጠቀማሉ፤ እና የምትፈልጋቸውን ነገሮች ፣ ለምርምር የሚያስፈጉህን ግብአቶች በቀላሉ ታገኛለህ ፣ የተሻለ ነው ፣ የተመቻቸ ነው። የተሻለ ግብአት እና የተሻለ ቴክኖሎጂ ስላለ የተሻለ ሥራ ልትሰራ ትችላለህ እዚህ። »

ደረጀም በየሻምበልን ሃሳብ ይጋራል።

«የኢትዮጵያን ግብርና እና የጀርመንን ግብርና በተለይ በምርምር ደረጃ ስናነጻጽረው በጣም ሰፊ ልዩነት አለው። ይህ ተጠባቂ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ አሁንም ድረስ በአብዛኛው የነበረው ባህል ወይም እዚህ ሀገር ከዛሬ መቶ ዓመት በፊት ሲጠቀሙ የነበረውን ስልት ነው አሁንም ድረስ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር የምንጠቀመው ። አሁን እኛ ለምርምር የምንጠቀመው እና እዚህ ሀገር ለአጠቃላይ የግብርናው ምርት የሚጠቀሙት በጣም የራቀ እና  የላቀ ነው።»

የእዚህ ቦን የዶክትሬት ዲግር መርሃ ግብር ከሚከታተሉት መካከል  ከትግራይ ክልል የመጣው ዚያድ አብረሃ አንዱ ነው። ዚያድ ከጥቂት ዓመታት በፊት በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ አስተማሪ ነበር ። ልክ እንደ ደረጀ እና የሻምበል ሁሉ በግል ጥረቱ ከቦን ዩኒቨርሲቲ ጋር ተጻጽፎ ባገኘው የትምህርት ዕድል  ነው ወዲህ የመጣው። የምርምር ሥራውን እየሠራ ያለውም በቤት እንስሳት በተለይ በሚያመነዥጉ እንስሳቶች የአመጋገብ ስረዓት ላይ በማተኮር ነው። ዚያድ ወደ ጀርመን ከመጣ በኋላ በጥናት እና ምርምሩ ዘርፍ እንደው ምን የተለየ ነገር አግኝቶ ይሆን ?

Äthiopische Wissenschaftler in Deutschland
ዚያድ አብርሃ በምርምር ስራ ላይምስል Dereje Tamiru

«ሁሌ ምርምር ሲሰራ ያለውን ችግር ለመፍታት ብሎ ነው የሚነሳው ። እና እኔ እንደሚመስለኝ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ችግር እና ጀርመን  ያለው ችግር ልዩነት እንዳለው ሁሉ የምርምር አቅጣጫውም ልዩነት ይኖረዋል። አሁን የኢትዮጵያን ከወሰድክ ያለውን ምርት ለማሳደግ ነው ምርምሮች የሚሰሩት ፤ ምርት ከፍ ለማድረግ።  እዚህ ሀገር ግን የምርት ችግር አይደለም ያለባቸው ። የግብርና ሥራ ሲያከናውኑ በሰውልጅ ጤና ላይ ፣ አካባቢ ላይ፣ የአየር ንብረት ለውጥ ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል የሚለውን ነው ቅድሚያ የሚሰጡት ። እና የምርምር አቅጣጫ ልዩነት ያለው ይመስለኛል።»

ወጣት ተመራማሪዎቹ ያገኙትን  ዕድል ውጤታማ ለማድረግ ደፋ ቀና እያሉ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ሊታሰቡ የማይችሉ እና የሰው ልጆችን ተክተው ሊሰሩ የሚችሉ ሮቦቶችን የመፈብረክ  የምርምር ስራዎች ጭምር  ላይ ተሳታፊ እየሆኑ ነው። ለዚህ በጥሩ ምሳሌነት  ደረጀ ታምሩ የሚሳተፍበት ፕሮጀክት ተጠቃሽ ነው።

Äthiopische Wissenschaftler in Deutschland
ደረጃ ታምሩ በመስክ የምርምር ስራ ላይ ምስል Dereje Tamiru

«በትንሹ እኔ የምስራበት ፕሮጀክት phenotypic rhobotics for sustainbale crop production ይባላል። እንዴት ግብርናው የሚመጣውን ትውልድ በማይጎዳ መልኩ እናስቀጥላለን የሚል ነው። ያንን ለማድረግ እንዴት አድርገን የላቀ ቴክኖ  ሎጂ እንጠቀማለን ነው። አንዱ ለምሳሌ መስክ ሂዶ ራሱ የሚሰራ ሮቦት የሚሰራበት ነው ።   እኔ ያለሁበት ፕሮጀክቱ ራሱ ሮቦት ራሱ ተቆጣጥሮ ፣ በራሱ የሚዘራ ፣ በራሱ ማጨድ የሚችል ፤ በተለይ አረምን ራሱ ለይቶ መግደል የሚችል ሮቦት መስራት ነው።»

ወጣቱ ተመራማሪ የሻምበልም ከዚሁ የዕጽዋት የምርምር መስክ ሳይርቅ እንዲሁ አንድ እርምጃ ሊያራምደው የሚችል የምርምር ዕውቀት ለመጨበጥ ይታትራል።

«በምርምሩ የሆነ የዕጽዋት ትንሽዬ ክፍል ቆርጠህ ኪው ፒሲ አር በሚባል መንገድ ናሙና በመውሰድ የአርሶአደሩ ማሳ የትኛው ንጥረ ነገር እንዳነሰው የምታውቅበት ስልት ስለሆነ ባጣም ጠቃሚ ነው።»

ወጣት ኢትዮጵያውያኑ ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ የተለያየ ህልም እንዳላቸው ይናገራሉ። ትናንት ተወልደው ባደጉበት ማኅበረሰብ ውስጥ የነበሩ የመስኩ ችግሮችን ለመቅረፍ የራሳቸውን ጠጠር ለመወርወር የልብ ዝግጁነት አለን ባይ ናቸው ።  ዚያድ ከጀርመን የቀሰመውን ዕውቀት ይዞ  ወደ ሀገር ቤት መመለስን ሲያስብ ይከፋዋል። እርሱ የወጣበት የትግራይ ክልል በከፋ ጦርነት ውስጥ ማለፉ ከግብርና ምርት ዕድገት ይልቅ የመኖር አለመኖር የህልውና ትግል ውስጥ ይገኛሉ ይላል ። ይህ ደግሞ ለእርሱ እንቅልፍ የሚያስወስድ አይደለም ።   በእርግጥ ትልቅ ተስፋ ነበረው ፤ በሀገር ቤት የፖለቲካዊ አለመረጋጋት የፈጠረው ቀውስ የወደፊት መዳረሻውን ገና ከወዲሁ እንዳይወስን ቢገታውም ።የኪነ ህንፃ ባለሙያው ኃይሌ ታደሰ እና ትላልቅ ስራዎቹ

«በምርምር ብዙ ለውጥ ለራስ ዕድገትም ይሁን ያለውን ተጨባጭ ችግር ለመፍታት ብዙ መስራት ዕድሉ እንዳለ እና ከእነዚህ ተምረህ ማገዝ ከምትችል ሰዎች አንዱ አድርገህ ራስህን ስታስብ ዕድሎች እንዳለ በደንብ ያሳይሃል። ከተጨባች ሁኔታ ጋር ስታየው ደግሞ የፖለቲካው አለመረጋጋት ስታየው ደግሞ ተስፋ ያስቆርጥሃል። በተለይ የመጣሁበትን ክልል ሳስብ ሰው የሚበላ አጥቶ በረሃብ የሚሞትበት ጊዜ ከመሆኑ አንጻር ስለ ግብርና ዕድገት ማውራት ትንሽ ይከብደኛል »

ደረጀ ታምሩ እንደሚለው ደግሞ  እያከናወነ ካለው የምርምር መስክ ላይ ተመስርቶ ኢትዮጵያ በመስኩ ክፍተት ያለባትን ለመሙላት የበኩሉን አስተዋጽዖ በምን መልኩ እንደሚያሳካ ከወዲሁ እያሳሰበው ነው ።

« እኔ የአርሶ አደር ልጅ ነኝ፤ ማሳ ላይ ነው ያደኩት በጣም አስታውሳለሁ ማኛ ጤፍ በደብረዘይት የግብርና ምርምር ማዕከል ሲለቀቅ የኅብረተሰቡን ኑሮ ምንያህል እንደጨመረ፤ የጅማ ምርምር ማዕከል ብዙ የቡና ዝርያዎችን ለቆ ምዕራብ እና ደቡባዊ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክፍልን ምን ያህል ተጠቃሚ እንዳደረገ ፤ አሁን ሰፊ ክፍተት ያለበት የቴክኖሎጂ ክፍተት ነው። እና እኔ አሁን እያሰብኩ ያለሁት  ዜሮ ላይ ያለውን ቴክኖሎጂ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዴት መጠቀም እንችላለን ነው።»

ኢትዮጵያ ያላት ዕምቅ የተፈጥሮ ሀብት እና ሰፊ የሰው ኃይል ጅምር የግብርና የምርምር ሥራዎች ከዳር እንዲደርሱ ተስፋ እንዳሳደሩበት የነገረን የሻምበል ነው። ነገር ግን እንደዚያም ሆኖ ጎን ለጎን ለእነዚሁ የምርምር ሥራዎችም ሆነ ለአጠቃላዩ የግብርና ሥራ ስኬታማነት ስጋት የሚያጭሩ ነገሮች መኖራችውን ተናግሯል።  ይህ ስጋት ከወቅታዊ ተጨባች የሀገሪቱ ሁኔታ አንጻር ወጣቶቹ የቀሰሙትን ዕውቀት ይዘው ወደ ሀገር ቤት ለመመለስ እስኪያዳግት ድረስ የሚያደርስ ስጋት እንዳለም አልሸሸገም።

« እኔ ተስፋ የማደርገው ብዙ ወጣት የሰው ኃይል አለ። ከሠራን እንለወጣለን ብዬ አስባለሁ ። እንደ ችግር የማየው በተለይ  ባለፉት ሶስት ዓመታት አካባቢ ያለን የእርስ በእርስ ግንኙነት ፤ ያለው አለመረጋጋት እና ከጸጥታ ጋር ተያይዞ ያለው ችግር በራሱ ትልቅ ስጋት ነው። እና ምናልባትም ይኸ የጸጥታ ችግር ካልተቀረፈ ብዙ ሰው ምናልባት ወደ ሀገሩ ተመልሶ ለመስራት ምናልባት አዳጋች ሊሆንበት ይችላል የሚል ስጋት አለኝ ።»«አፍሪቃን ማስተዋወቅ ነው ዓላማችን»: አቤኔዘር ታደሰ

የተጀመሩ ሁለንተናዊ የምርምር ሥራዎች ከግብ እንዲደርሱ የግለሰቦች ጥረት እንዳለ ሆኖ መንግሥት ለዘርፉ የሚሰጠው ትኩረት ግን ወሳኝነት እንዳለው ነው ደረጀ የሚገልጸው 80 ከመቶ በላይ የሆነው የማኅበረሰብ ክፍል በግብርና የሚተዳደርባት ሀገር ከዚህ የምታስቀድመው ነገር እንደሌላት በማከል ። 

«የጀርመን እዚህ የቦን ከተማ ተማሪዎች ስለ ግብርና በደንብ ያውቃሉ። ገና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ሆነው የግብርና ሥራዎችን ይጎበኛሉ። የአዲስ አበባ ልጆች እንደዚያ ያደርጋሉ ወይ? ጥያቄ ነው ። ምክንያቱም ትኩረት ይፈልጋል። መንግሥት የሀገሪቱ የኤኮኖሚ ምሶሶ የሆነውን የበለጠ ትኩረት መስጠት ይኖርበታል። የመናፈሻ ፓርክ ከመገንባት ቴክኖሎጂዎችን ማስገባት ቅድሚያ ማግኘት አለበት እላለሁ።»

እንግዲህ አድማጮቻችን እዚህ ቦን ከተማ በሚገኘው ቦን ዩኒቨርሲ የ3ኛ ዲግሪ መርሃ ግብር በመከታተል ላይ ከሚገኙ ሶስት ኢትዮጵያውያን ወጣት ተመራማሪዎች ጋር የነበረን ቆይታ ይህን ይመስል ነበር ሳምንት በሌላ ዝግጅት እንጠብቃችኋለን ጤና ይስጥልን።

ታምራት ዲንሳ

ሸዋዬ ለገሠ