የኪነ ህንፃ ባለሙያው ኃይሌ ታደሰ
ዓርብ፣ ሰኔ 9 2015የአርኪቴክቸር ወይም የኪነ ህንፃ ባለሙያ የሆነው ኃይሌ ታደሰ ከአራት አመታት በፊት ያቋቋመው የ ሉላ ኢንጂነሪንግ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ነው። « 22 ሰራተኞች አሉን። እነዚህ በቋሚነት የሚሰሩ ናቸው። በዋናነት በአርክቴክቸር እና ኢንጂነሪንግ የማማከር ስራ እንሰራለን። ከዛ ሌላ የግንባታ ስራ እንሰራለን። ከሌሎች ለምሳሌ መንገድ፤ ውኃ የመሳሰሉ የሚሰሩ አጋር ድርጅቶች ጋርም እንሰራለን»
በኪነ ህንፃ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ዲግሪ ያለው ይኼው ወጣት በተለይ ባለፉት ሶስት አመታት እንደ የሃላላ ኬላ ሪዞርት እና ጎርጎራ የመሳሰሉ ትላልቅ የግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ ተሳታፊ ለመሆን ችሏል። ለዚህ ዕድል በር የከፈተለት ደግሞ እርሱ እንደሚለው በአንድ አጋጣሚ አዲስ አበባ ወደ ሚገኘው የአንድነት ፓርክ ያደረገው ጉዞ ነው። « በስራ ከሚያቀኝ እና የፍሳሽ ማስወገጃ መሥመሮች ዲዛይን ከሚያደርግ ሰው ጋር የአንድነት ፓርክ ሲሰራ አብሬው እሄድ ነበር እና እነዚህ ከተለመደው ይልቅ ይበልጥ በኪነ ህንፃ መልኩ ቢሰራ የሚል ሀሳብ አቀርብለት ነበር እና ጥሩ ስራ ስለሰራን ከአንድ ሀገር በቀል ድርጅት ጋር አስተዋወቀኝ። በተደጋጋሚ ሄጄ ሀሳቦችን ሳነሳ ከገበታ ለሀገር አካል አንዱ የሆነው የኮንሻ ፕሮጀክት ጠቋሚ ዲዛይን እንዲሰራ የተለያየ ባለሙያ ይሄድ ነበር እና ወደ ስፍራው ከተላኩ ባለሙያዎች አንዱ ሆንኩ » ይላል። ኃይሌ እና አጋር ድርጅቱ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ አመላካች ዲዛይን ከሰሩ በኋላ ሌሎች ፕሮጀክቶች ለኃይሌ ተከታትለው መጡ። « የፅንሰ ሀሳብ ዲዛይኑን ለስድት ወራት ሰርተን ካስረከብን በኋላ የጎርጎራ ዲዛይን ወደ ኃላ ቀርቶ ነበርና ይህን የፅንሰ ሀሳብ ዲዛይን በነፃ አገልግሎት ሰራን ። ሶስተኛው ደግሞ የባሌ ዓለም አቀፍ ቱሪስት መዳረሻን ጽንሰ ሀሳብ ዲዛይን ሰራን። »
የሀላላ ኬላ ሪዞርት የቤቶቹን ጣሪያ አሰራር ያብራራልን ኃይሌ ምንም እንኳን ዲዛይኑን የሰራው የእሱ ድርጅት ባይሆንም የጣሪያ ዲዛይኑ ከዳውሮ ባህላዊ የቤት አሰራር ጣሪያ የወሰደ እንደነበር ገልፆልናል። ቤቶቹ በሰፉ ቁጥር ብርሃን በደንብ ስለማይገባ የጣሪያ ዲዛይኑ ላይ ጣሪያው ሳያልቅ ጣሪያው ተቆርጦ በዚያ በኩል ብርሃን ወደ ውስጥ እንዲገባ መደረጉንም ገልፆልናል። «ከዚህም በተጨማሪ የዳውሮ ህዝብ በ16ኛው ክፍለ ዘመን ከጠላት ለመከላከል የሰራው ግንብ ነበር። የዚህም የድንጋይ ካብ በግንባታው ፅንሰ ሀሳብ ውስጥ ተካቷል» ይላል ኃይሌ ። አብዛኛው ነገር የአካባቢው ማህበረሰብ ከሚጠቀምበት ቀለም፤ ባህላዊ የግንብ አሰራር፣ የጎጆ ቤቶች አሰራር የመሳሰሉ የተወሰዱ መሆናቸውንም ለዶይቸ ቬለ ገልጿል።
ኃይሌ ተወልዶ ያደገው በምዕራብ ሸዋ ዞን ግንደ በረት ወረዳ ሲሆን አካባቢውም «ገጠራማ ነው» ይላል። ይሁንና እዛ አካባቢ ያያቸው ቤቶች ዛሬ ላይ የኪነ ህንፃ ባለሙያ እንዲሆን ትልቅ ሚና ነበራቸው። « ያደኩበት አካባቢ በ1950ዎቹ የተገነቡ የሚሲዮናውያን መኖሪያ ቤቶች ነበሩ። እነዚህ ቤቶች ከአካባቢያችን ቤቶች ይለዩ ስለነበር ይህ ለምን ሆነ ብዬ አባቴን እጠይቅ ነበር። » አባቱም ቤቶቹ በኪነ ህንፃ ባለሙያዎች እንደተሰሩ እና ኃይሌ ይህንን ሙያ መማር ከፈለገ በሂሳብ እና ፊዚክስ ትምህርት ጎበዝ ተማሪ መሆን እንዳለበት ይነግሩት ነበር። « ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነው ለኪነ ህንፃ ያለኝ ፍቅር ያደገው።»
ፍላጎቱን የተረዱት አባቱ ኃይሌ የ7 ዓመት ልጅ ሳለ ጀምሮ ወደ አዲስ አበባ በሚሄዱበት ጊዜ ትላልቅ ተቋማትን እና ህንፃዎችን እያስፈቀዱ ያስጎበኙት እንደነበር የነገረን ኃይሌ ከልጅነቱ አንስቶ የነበረው ዝንባሌ እንዲያድግ የቤተሰቦቹ ሚና ትልቅ ነበር። ሌላው ደግሞ በግል ጥረቱ ያገኘው ነው። « ዩንቨርስቲ ተማሪ ከሆንኩ በኋላ ለልምድ ልውውጥ እንዲሆነኝ እና ሙያውን ለማሳደግ ወደ ዱባይ፣ ቱርክ፣ ግሪክ ፣ ታንዛኒያ እና ኬንያ ሀገራት ሄጃለሁ።»
ኃይሌ አሁን የደረሰበትን ሁኔታ የአካባቢው ሰዎች ሲያዩ ብዙም አይደነቁም ይላል። « በቅርበት የሚያውቁኝ ሰዎችን ብዙ አይገርማቸውም ምክንያቱም የሆነ ቀን ተምሬ፤ በኪነ ህንፃ ብዙ ዕውቀት ኖሮኝ፤ የእኛን አካባቢ ህብረተሰብ አኗኗር ቀይሬ እላቸው ነበር እና ገና ጅማሬ ላይ እንዳለው ነው የሚሰማቸው። » ለሌሎች ሰዎች ግን ጥሩ «ብርታት ሆኛለሁ» የሚል ዕምነት አለው።
«በኪነ ህንፃ ለመካን ወይም ለመማር ተፈጥሮዊ ተሰጥዎ እና ዝንባሌ ይፈልጋል» የሚለው ኃይሌ የአባቱን ምክር በተግባር ላይ አውሏል። የራሱን ምክር በተግባር ላይ ማዋል ለሚፈልጉ ወጣቶችስ ኪነ ህንፃ ለመማር ምን ያስፈልጋቸዋል ይላል? «በጣም ጉዳዮን መውደድ ፣ ሙያውን መፈለግ ያስፈልጋል፣ ከዛ ቀጥሎ ደግሞ ሁሉም የትምህርት ዘርፎች ላይ የሚረዳ እና የሚገነዘብ አይነት መሆን ይፈልጋል። » ይላል እንደ ኮይሻ እና ጎርጎራ ባሉ ትላልቅ ፕሮጀክቶች የተሳተፈው የኪነ ህንፃ ባለሙያ ኃይሌ ታደሰ።
ልደት አበበ
ታምራት ዲንሳ