ገና በአማራ ክልል የግጭት ድባብ እና የዋጋ ንረት ተጭኖታል
ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 27 2016የዘንድሮው የገና በዓል በአማራ ክልል በጦርነት ድባብ ለማክበር ህብረተሰቡ የተዘጋጀ ቢሆንም የአለው ወቅታዊ የክልሉ ፀጥታ ሁኔታ እንደበፊቶቹ ዳማቅ አያደርገውም ሲሉ የአነጋገርናቸው የአንዳንድ ከተሞች ነዋሪዎች አመልክተዋል፡፡ በሰሜን ወሎ ላሊበላ ከተማ ደግሞ በዓሉን በተሻለ ሁኔታ ለማክበር ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን የዞኑ አስተዳደር አስታውቋል፣ ምዕመናን ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ ከተማዋ እየገቡ እንደሆነም ተገልጧል፡፡
ዛሬ በባሕር ዳር ሰባት አሚት የእንስሳት ግብይት በሚደረግበት ቦታ እንደተመለከትነው ሻጭና ገዥ እንደወትሮው በቦታው ተገኝተዋል፡ ምንም እንኳ በዚህ ዓመት በክልሉ ያለው የሰላም ሁኔታ የበዓሉን ድባብ የቀዘቀዘ ቢያደርገውም ህብረተሰቡ እንደ አቅሙ የእርድ እንስሳትን ሲገዛና ሲሸጥ ተመልክተናል፡፡
የአማራ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች ምክር ቤት የሰላም ጥሪ
በስፍራው ያገኘናቸው አንድ ሻጭ የእንስሳት ዋጋ ወርዷል ቢሉም የባህር ዳር ከተማ ሸማች ግን እንስሳት ወደ ገበያ ብዙ አልገቡም፣ የገቡትም ቢሆን ዋጋቸው እጅግ ውድ እንደሆ ገልጠዋል ፣ በ62 ሺህ ብር አንድ የእርድ በሬ መግዛታቸውን ጠቅሰው፣ ከዚህ በፊት ግን ከ50 ሺህ ብር የበለጠ ወጪ እንዳላወጡ አስረድተዋል፡፡ ዛሬ በሰባት አሚት በነበረው ገበያ ግን አንድ የእርድ በሬ እስከ 110 ሺህ የሚጠራ ሰንጋ መኖሩንም ነግረውናል፡፡
በምስራቅ ጎጃም ዞን የቢቸና ከተማ አስተያየት ሰጪ ደግሞ በክልሉ ያለው ጦርነት በፈጠረው አውድ ሆኖ ሰው በዓሉን ለማክበር የሚያሳየው ነገር የለም ነው ያሉት፣ የመንገዶች መዘጋጋት የስጋ እንስሳቱን ጨምሮ ሌሎች ሸቀጦች መግብታ ባለመቻላቸው ኑሮ በእጅጉ ከባድ አድርጎታል ሲሉ ነው የገለጡት፡፡
በምዕራብ ጎጃም ዞን የቡሬ ከተማ ነዋሪም ቢሆኑ ህብረተሰቡ በዓሉን ለማክበር ጥረት እያደረገ ቢሆንም ስጋት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ “ሁለቱም ኃይሎች በቅርብ እርቀት ስለሚገኙ ከአሁን አሁን ምን ይፈጠር ይሆን የሚል ከፍተኛ ስጋት ባለበት ሁኔታ ነው ህብረተሰቡ በዓሉን ለማክበር እያሰበ ያለው፡፡” ብለዋል፡፡
ተፈናቃዮችን የማቋቋም ውጥንና የተፈናቃዮች ሥጋት
በደቡብ ወሎ ዞን የደሴ ከተማ ነዋሪ የእንስሳቱ ዋጋ የቀነሰ ቢሆንም የሌሎች ሸቀጦች ዋጋ ካለው የሰላም እጦት ጋር የበዓሉን አከባበር ጥላ ጥሎበታል ሲሉ ነው አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬሌ የተናገሩት፣ ከሰሞኑ ከደብረ ብርሀን እስከ ደሴ ያለው መስመር የፀጥታ ችግር ያለበት በመሆኑ በበዓሉ አከባበር ላይ ተፅዕኖ ፈጥሯል ነው ያሉ፡፡
በሰሜን ወሎ ዞን የቆቦ ከተማ ነዋሪ የገናን በዓል በታሻለ ሁኔታ ለማክበር በዓሉ ሀይማኖታዊ ይዘቱን ይዞ እንዲከበር የማክበሪያ ሰፊ ቦታ እንደተሰጠው አመልክተዋል፣ ነዋሪውም ምንም እንኳ ኑሮ ከባድ ቢሆንም ሰንጋዎችን ለመግዛት መዘጋጀቱን ገልጠዋል።
የሰሜን ወሎ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ፀሐይነው ሲሳይ በስልክ እንደነገሩን የገና በየዓመቱ በድምቀት በሚከበርበት የላሊበላ ከተማ በድምቅት ለማክበር ዝግጅቶች ተጠናቅቀው ምዕመናን ወደ ከተማዋ በመግባት ላይ ናቸው፡፡ ከ40 በላይ ሆቴሎች በዓሉን ምክንያት በማድረግ የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን ያመለከቱት አቶ ፀሐይነው የየብስና የአየር ትራንስፖርትም ዝግጁ ሆነዋል ብለዋል፡፡
በአብዛኛዎቹ የአማራ ክልል አካባቢዎች በዓሉን ለማክበር ዝግጅቶች እየተደረጉ ቢሆንም የጦርነቱ ድባብና የኑሮ ውድነቱ የህብረተሰቡን ደስታ እንዳደበዘዘው ነዋሪዎቹ አመልክተዋል።
ዓለምነው መኮንን
እሸቴ በቀለ