1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአማራ ክልል ግጭትና የወባ በሽታ ስርጭት

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 10 2016

በአማራ ክልል ከተፈጠረው የፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ ከ270 በላይ የጤና ተቋማት ከአግልሎት ውጪ መሆናቸውና ከ10 ሺህ በላይ የቀዶ ህክምና ቀጠሮ የነበራቸው ህሙማን ህክምናውን ማግኘት እንዳልቻሉ ቀደም ሲል የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልከሪም መንግስቱ መግለፃቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

https://p.dw.com/p/4aP5G
የአማራ ክልል የሕብረተሰብ ጤና ተቋም
የአማራ ክልል የሕብረተ ሰብ ጤና ተቋም ምስል Alemnew Mekonnen/DW

በአማራ ክልል የወባ በሽታ አለቅጥ ተዛምቷል

በአማራ ክልል በወባ በሽታ የሚያዘዉ ሰዉ ቁጥር ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነፃፀር በእጥፍ መጨመሩን የክልሉ የህብረተሰብ ጤና ተቋም አስታወቀ።የጤና ተቋሙ እንደሚለዉ ዘንድሮ በወባ በሽታ የተያዘዉ ሰዉ ቁጥር ከ670 ሺሕ በልጧል።የሕሙማኑ ቁጥር ከአምናዉ ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነፃፀር ከ50 ከመቶ ይበልጣል። የጤና ተቋሙ እንደሚለዉ ለበሽታዉ መዛመት በክልሉ የሚደረገዉ ዉጊያ፣ የመድሐኒትና የሌሎች የግብዓቶች እጥረትና በአግባቡ አለመጠቀም፣ የክትትልና ቁጥጥር  መቀነስ ዋና ምክንያቶች ናቸዉ።በወባ በሽታ ባለፉት  ስድስት ወራት  15 ሰዎች ሞተዋል፡፡
የወባ ስርጭት መጨመር በአማራ ክልል

በአማራ ክልል በተለይም በምዕራብ የክልሉ ዞኖች የወባ በሽታ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን የክልሉ ህብረተሰብ ጤና ተቋም አስታውቋል፡፡ የወባን ሳምንት ምክንያት በማድረግ ትናንት በክልሉ ጤና ቢሮና በአማራ ህብረተሰብ ጤና ተቋም  በተዘጋጀ የምክክር መድረክ ላይ የተገኙት የአማራ ህብረተሰብ ጤና ተቋም የወባ ፕሮግራሞች አስተባባሪ አቶ ዳምጤ ላንከር እንዳሉት ከአለፈው ሐምሌ 2015 ዓ ም ጀምሮ በክልሉ በወባ በሽታ  የተያዙ ሰዎች ቁጥር ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 50 በመቶ ጨምሯል፡፡
“በ2016 በጀት ዓመት 671 ሺህ የሚሆኑ ህሙማን ናቸው በወባ የተያዙት፣ ከአለፈው ዓመት ሐምሌ እስከ ታህሳስ ካለው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ስናነፀጽር 50 ከመቶ ነው ጭማሪው፡፡ ከ671 ሺህ ህሙማን ውስጥ 15 ሰዎች በወባ ህይወታቸው አልፏል፡፡”

ባሕርዳር ዉስጥ የተደረገዉ የወባ ጉዳይ ስብሰባ
በአማራ ክልል ስላለዉ የወባ በሽታ ስርጭት የተነጋገረዉ ስብሰባምስል Alemnew Mekonnen/DW

ለስርጭቱ መጨመር ምክንያቶች

ለበሽታው ስርጭት ዋና ዋና ምክንቶቹ የዝናብ እትረት፣ የቁጥጥር ማነስ፣ የእርጭት መቀነስ፣ የአልጋ አጎበርን ለሌላ ዓላማ ማዋልና በክልሉ ያለው የፀጥታ ሁኔታ ተጠቃሾች ናቸው ብለዋል፡፡ ከ650 በላይ ቀበሌዎችን የፀረ ወባ ትንኝ ኬሚካል ርጭት ለማድረግ ቢሞከርም አፈፃፀሙ ከግማሽ በታች እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
“በፀረ ወባ ትንኝ ኬሚካል እርጭት መሸፈን የነበረባቸው ቀበሌዎችንም መሸፈን አልቻልንም፡፡ 651 ቀበሌዎችን የፀረ ወባ ትንኝ ኬሚካል ርጭት ለማድረግ ቢታቀድም አፈፀፀሙ ከ37 ከመቶ አልበለጠም፡፡ ” ብለዋል፡፡
 

ለወባ ስርጭቱ የጨመረባቸው አካባቢዎች

የበሽታው ስርጭት በምዕራብ የአማራ ክልል ዞኖች በ30 ወረዳዎች የበረታ እንደሆነ ገልጠዋል፡፡ በዋናነትም ምዕራብና ምስራቅ ጎጃም ዞኖች፣ አዊ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ ባህር ዳር ከተማ አስተዳደር፣ ደቡብና ሰሜን ጎንደር ዞኖች፣ ማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች ተጠቃሾች እንደሆኑ ነው የገለጡት፣ እነዚህ ዞኖች አጠቃላይ 91 ከመቶ የሚሆነውን የወባ በሽታ ስርጭት እንደሚሸፍኑ ነው ያስረዱት፡፡ በነዚህ ዞኖች የሚገኙ 30 ወረዳዎች ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ በወባ በሽታ ስርጭት ቀዳሚውን ሲይዙ አጠቃላይ በተጠቀሱ ዞኖች ከሚገኘው 91 ከመቶው የወባ ስርጭት ካለባቸው ዞኖች መካከል ከ73 ከመቶ በላይ የሚሆኑት  በነዚህ ወረዳዎች ይገኛሉ ብለዋል፡፡ ከነዚህ ወረዳዎች መካከል ባህር ዳር፣ ምስራቅና ምዕራብ ደንቢያ፣ ፎገራ፣ሊቦ ከምከምና በለሳ ወረዳዎች ይጠቀሳሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት በቂ መድኃኒት ቢኖርም በመንገድ መዘጋጋትና በሌሎች ምክንቶች መድኃኒቶችን ማሰራጨት እንዳልተቻለም አብራርተዋል፡፡

የመድኃኒት አቅርቦትና ተግዳሮቱ

“...አሁን ላይ ከ200ሺህ በላይ ህሙማንን ማከም የሚችል የወባ ማከሚያ መድኃኒት አለን፣ ሆኖም መድኃኒቱ ቢኖርም በመንገድ መዘጋጋትና በሌሎች ምክንያቶች በወቅቱ ማድረስ አልተቻለም፣ ሆኖም እስከ ሁለት ወራት ማገልገል የሚችል መድኃኒት አለ” ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የአማራ ክልላዊ መንግስት አርማ
የአማራ ክልልላዊ መንግስት አርማምስል Amhara National Regional State


በውይይቱ ላይ ከተገኙት ተሳታፊዎች መካከል ከደቡብ ጎንደርዞን  ጤና መምሪ ተወክለው የመጡ ተሳታፊ እንዳሉት የወባ ስርጭት በዚህ ዓመት  ወባማ ባልሆኑ አካባቢዎች ጭምር ተስፋፍቷል፡፡ ከጸጥታ ጋር በተያያዘም በርከት ያሉ ጤና ተቋማት በስራ ላይ አይደሉም ነው ያሉት፡፡
በምዕራብ ጎጃም አንድ የጢስ ዓባይ ከተማ ነዋሪ በአንድ ጤና ጣቢያ ብቻ እስከ 150 ሰዎች የወባ ህክምናለመውሰድ እንደሚሰባሰቡ አመልክተዋል፣ በሽታቸው ወባ መሆኑ የሚነገራቸው ህሙማን መድኃኒት በቀላሉ ማግኘት ስለማይችሉ በበሽታው እየተሰቃዩ ነውም ብለዋል፡፡

በምስራቅ ጎጃም ዞን የየጁቤ ሆስፒታል ሀኪም ዶ/ር ፀሐይ ስፍር ለዶቼ ቬሌ እንገለፁት የወባ በሽታ በእጅጉ ጨምሯል፣ በሆስፒታላቸው ከሚመረመሩ ሰዎች መካከል ግማሾቹ የወባ ህመምተኞች እንደሆኑ ተናግረዋል፣ ባለው የፀጥታ ችግር ምክንትም ሰራተኞች ቆላማ ወደ ሆኑ አካባቢዎች ሄደው የኬሚካል ስርጭት ማካሄድ እንዳልቻሉ አመልክተዋል፡፡፡፡
በምዕራብ ጎጃም ዞን የደንበጫ ወረዳ ጤና ጽ/ቤት የወባና ሌሎች ቬክተር ወለድ በሽታዎች ቁጥጥር ባለሙያ አቶ  ኃይለማሪያም ታደሰ የፀጥታ አለመኖር፣ የባጀት እጥረት፣ አንዳንድ ጤና ተቋማት ከፀጥታ ጋር በተያያዘ ወደ ስራ አለመመለስ የበሽታውን ስርጭት ጨምሮታል ብለዋል፡፡

ጦርነቱ በጤና ተቋማት ላይ ያደረሰው ተፅዕኖ

በአማራ ክልል ከተፈጠረው የፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ ከ270 በላይ የጤና ተቋማት ከአግልሎት ውጪ መሆናቸውና ከ10 ሺህ በላይ የቀዶ ህክምና ቀጠሮ የነበራቸው ህሙማን ህክምናውን ማግኘት እንዳልቻሉ ቀደም ሲል የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልከሪም መንግስቱ መግለፃቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ዓለምነው መኮንን

ነጋሽ መሐመድ

እሸቴ በቀለ