ጀርመን ተቀባይነት ያላገኙ ተገን ጠያቂዎችን በፍጥነት ለማስወጣት ሕግ አፀደቀች
ማክሰኞ፣ ጥር 14 2016ቡንደስታግ እየተባለ የሚጠራው የጀርመን ፓርላማ ጥያቄያቸው ተቀባይነት ያላገኙ ተገን ጠያቂዎችን በፍጥነት ከጀርመን ማስወጣትን የሚፈቅድ ረቂቅ አዋጅን ያለፈው ሳምንት መጨረሻ በጎርጎሪያኑ ጥር 19 ቀን 2024 ዓ/ም አጽድቋል። ርምጃው የተወሰደው የመራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልስ ጥምር መንግስት መደበኛ ያልሆነ ስደትን እና ተያያዥ ጉዳዮችን ለመፍታት ማቀዱን ተከትሎ ነው።
ህጉ ከገና በፊት በነበረው አንድ ሳምንት በአጭር ጊዜ የተነሳ አጀንዳ ሲሆን፤ ምክንያቱ ደግሞ ከጥምር አጋሮቹ አንዱ የሆነው አረንጓዴው ፓርቲ ለውጥ እንዲደረግ በመጠየቁ ነው።
የሶስቱ የጥምር መንግስቱ መስራቾች ገዥ ፓርቲዎች ህጉን ደግፈው ድምጽ ሰጥተዋል። በጣት የሚቆጠሩ የአረንጓዴው ፓርቲ አባላት እና የተቃዋሚው የክርስቲያን ዴሞክራቶች ፓርቲ እና አማራጭ ለጀርመን የተባሉ ፓርቲዎችም ውጤታማ የማይሆን ሲሉ ርምጃውን ተቃውመው መንግስትን ተችተዋል።ህጉ ያለፈው ሀሙስ ክርክር የተደረገበት ሲሆን በማግስቱ አርብ በጀርመን ፓርላማ እንዲፀድቅ መደረጉን በጀርመን ሀገር የህግ ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ለማ ይፍራሸዋ ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል።የተገን ጠያቂዎች ጥረዛ በጀርመን
ከሕጉ አንዳንድ ድንጋጌዎች መካከል ወደ አገር ቤት የመመለሻ ማሻሻያ ህግ ተብሎ የሚጠራው ሲሆን፤ ይህም ከስደት በፊት ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ጥበቃ ሲሆን ይህም አንድ ግለሰብ ጀርመንንን ከመልቀቁ በፊት ሂደቱን ማጠናቀቅ እንዲችል ለባለሥልጣናት ተጨማሪ ጊዜ የሚሰጥ ነው።
ዶክተር ለማ ይፍራሸዋ እንደሚሉት ጥገኝነት ጠያቂዎቹ ከሀገር ከመባረራቸው በፊት ከዚህ በፊት የነበረው ከፍተኛው የእስር ጊዜ 10 ቀን ሲሆን በአዲሱ ህግ ግን ወደ 28 ቀናት ይራዘማል።
ይህ ድንጋጌ ባለስልጣናት ፍተሻዎችን በሚያደርጉበት ጊዜ ተጨማሪ ስልጣን ይሰጣል።ይህም ከዚህ በፊት ባለስልጣናት ወደ ሀገር ቤት የሚላከው ግለሰብ ክፍል ብቻ ለፍተሻ እንዲገቡ ይፈቀድ የነበረ ሲሆን፤ በአዲሱ ህግ የጋራ ክፍሎችን ጭምር ገብተው እንዲፈትሹ ይፈቀድላቸዋል።
ይህም ተባባሪዎችን ጭምር በማግኘት ተገን ጠያቂዎችን በቀላሉ ከጀርመን ለማስወጣት እና አንዳንድ ጊዜም ወደ ሀገራቸው ላለመመለስ የመታወቂያ ወረቀቶችን መስጠት በማይፈልጉ ስደተኞች ሂደቱ እንዳይዘገይ ወይም እንዳይደናቀፍ የባለስልጣናትን ስራ ያቀላል ተብሏል። ከዚህ በተጨማሪ የተደራጁ ወንጀሎችን የሚፈፅሙ እና በህገወጥ የሰዎች ዝውውር የሚሳተፉ ሰዎችን ለመያዝም ህጉ ለባለሥልጣናት ያግዛል።
የህግ ባለሙያው እንደሚሉት ከኢትዮጵያውያን ስደተኞች አንፃር ህጉ ከዚህ ቀደም ከነበረው የተለዬ ነገር የለውም።
የጀርመን የስደተኞች ጉዳይ ረቂቅ ህግ
ህጉን፤ እንደ ጀርመን የህግ ባለሙያዎች ማህበር ያሉ የመብት ተሟጋቾች ነቅፈውታል። ማህበሩ አያይዞም የሰላማዊ ሰዎችን ጥበቃ እና ደህንነት ላለማደናቀፍ በጥምረት ስምምነቱ የገቡትን ቃል አጥፈዋል።ሲል ወቅሷል።
በባህር ላይ የስደተኞችን ህይወት የሚታደገው ሲ ረስኪዩ የተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት በበኩሉ ህጉን «አስፈሪ»ሲል ገልጾታል። ህጉ ስደተኞችን እና የሰብአዊ እርዳታ የሚሰጧቸውን ሰዎች ጭምር ለእስር ቅጣት የሚዳርግ በመሆኑ ማዘናቸውን የረዴት ድርጅቱ ሰብዓዊ እርዳታ ቡድን ተናግሯል።
በአንዳንድ ሁኔታዎች አዲሱ ህግ በጎ ፈቃደኞችን ጭምር ለእስር ሊዳርግ የሚችል ነው።ብሏል ድርጅቱ።ዶክተር ለማ ይፍራሸዋ ግን የድርጅቶቹ ወቀሳው ህጉን ስራ ላይ ከመዋል አያግደውም ብለዋል።
ሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ናንሲ ፌዘር «የመቆየት መብት የሌላቸው ሰዎች አገራችንን በፍጥነት ለቀው እንዲወጡ እናደርጋለን» ሲሉ።ያለፈው ሐሙስ አመሻሽ ላይ በጀርመን ፓርላማ በተደረገው ክርክር ህጉን ደግፈዋል።
ቀደም ሲል በተወሰዱ እርምጃዎች ወደ ሀገራቸው የሚመለሱ ሰዎች ቁጥር በ2023 ዓ/ም በ27 በመቶ ማለትም ወደ 16,430 ከፍ ማለቱን ፌዘር አመልክተዋል።ከዓዲሱ ህግ በኋላም ከጀርመንን የሚባረሩ ምክንያታቸው ተቀባይነት ያላገኙ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ተገልጿል።
ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።
ፀሀይ ጫኔ
ታምራት ዲንሳ