1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተገን ጠያቂዎች ጥረዛ

ማክሰኞ፣ የካቲት 14 2009

የጀርመን መንግሥት ማመለከቻቸው ተቀባይነት ያላገኘ ተገን ጠያቂዎች በግዳጅ ወደ ሀገራቸው የሚባረሩበትን ሂደት እያፋጠነ ነው ።ሆኖም ከመካከላቸው በተለይ እንደ አፍጋኒስታን ያሉ አስተማማኝ ሰላም የላቸውም ወደሚባሉ አገራት የሚካሄደው ጥረዛ እያወዛገበ ነው ።

https://p.dw.com/p/2Y0PD
Rückführung von Flüchtlingen
ምስል picture alliance/dpa/P. Seeger

Europa 2100217(Debatte über Afghanistan Abschiebung) - MP3-Stereo

ከጀርመን እንዲወጡ ውሳኔ የተላለፈባቸውን ተገን ጠያቂዎችን ወደ መጡበት የማባረሩ ሂደት ካለፉት ጥቂት ወራት አንስቶ እንዲፋጠን መደረጉ ማነጋገሩ ቀጥሏል ። እርምጃው የተፋጠነው በተለይ ከጀርመን እንዲባረር ተወስኖበት የነበረው ተገን ጠያቂ ቱኒዝያዊው አኒስ አምሪ ባለፈው ታህሳስ በበርሊኑ የገና ገበያ በከባድ የጭነት መኪና የ12 ሰዎች ህይወት ካጠፋ በኋላ ነበር ።  አኒስ አምሪ ጥቃቱን ከማድረሱ ከወራት አስቀድሞ ወደ ሀገሩ እንዲባረር የመጨረሻ ውሳኔ ተስጥቶ ነበር ይሁን እና ፣ እርሱን ወደ ሀገሩ ለመመለስ የሚያስፈልገው የጉዞ ሰነድ ባለመሟላቱ የጀርመን መንግሥት ወደ ሀገሩ ሊልከው አልቻለም ነበር  ። ከአደጋው በኋላ የጉዞ ሰነዶቻቸውን የተሟሉ ሌሎች ጀርመን ያልተቀበለቻቸው ተገን ጠያቂዎችን  በግዳጅ የማባረሩን ሂደት መንግሥት አፋጥኗል ። ይህንኑ ሥራ ይበልጥ ያቀላጥፋል የተባለ እቅድም ተዘጋጅቷል ። በሚቀጥለው ዓመት መስከረም ምርጫ የሚጠብቃቸው የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ማመልከቻቸው ውድቅ የተደረገ ተገን ጠያቂዎችን  በአፋጣኝ መጠረዝ ያስችላል ያሉትን ባለ 16 ነጥብ እቅድ አቅርበዋል ። ከእቅዱ ውስጥ አንዱ በግዳጅ የሚመለሱ ተገን ጠያቂዎችን ጉዳይ የሚያስተባብር እና የ16 ቱ የጀርመን ፌደራል ክፍለ ግዛቶች ተወካዮች የሚገኙበት ማዕከል በርሊን ውስጥ ማቋቋም ነው ። እቅዱ ፌደራል ግዛቶችም በርከት ያሉ ሰዎችን በአንዴ ለማጓጓዝ እንዲረዳ በአውሮፕላን ማረፊያዎች አቅራቢያ  ይህንኑ ሥራ የሚያካሂዱ ማዕከላትን እንዲያቋቁሙ ይጠይቃል ።  ስጋት ናቸው ተብለው የተፈረጁ ሰዎችን በቀላሉ ለማባረር ያስችላል በተባለው በዚህ እቅድ ማመልከቻቸው ውሳኔ ሳይሰጥበት በፈቃዳቸው ለሚመለሱ ደግሞ ማበረታቻ ይሰጣል ።ከ0 ቀናት በፊት ለ16 ቱ የጀርመን ፌደራል ክፍላተ ሀገር እቅዳቸውን ያቀረቡት የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል  በወቅቱ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ጀርመን መኖር የተከለከለ ማንኛውም ሰው ሀገሪቱን ለቆ መውጣት አለበት ብለዋል ።
«ከህግ የበላይነት ጋር ተያይዞ እዚህ የመኖር መብት ለተሰጣቸው በራችን ክፍት ነው ።ይህ ያልተሳካላቸው ደግሞ ህጋዊ ይግባኝ ማቅረብ ይችላሉ ።ያንንም አድርገው እዚህ መኖር ያልተፈቀደላቸው ሰዎች ሀገራችንን ለቀው መውጣት አለባቸው ።»
ማመልከቻቸው ተቀባይነት ያላገኘ ተገን ጠያቂዎችን ከጀርመን ወደ መጡበት የማባረሩ ሥልጣን እና ሃላፊነት የጀርመን ፌደራል ክፍለ ግዛቶች ቢሆንም የፌደራል መንግሥቱ በዚህ በኩል የበኩሉን ሚና ከፍ ማድረግ ይፈልጋል ። 
ሰዎችን ከመጠረዙ በተጨማሪ በፈቃዳቸው መመለስ የሚፈልጉትን ጉዳያቸው ያላለቀ ተገን ጠያቂዎችንም የጀርመን መንግሥት ከኪስ ገንዘብ ጋር ወደ መጡበት እየላከ ነው ።  በፈቃደኝነት ወደ ሀገራችን እንመለሳለን ለሚሉ እስከ 1200 ዩሮ የሚደርስ ገንዘብ የሚሰጥባቸው የተገን ጠያቂዎች መመለሻ መርሃ ግብሮችም አሉ ። በአሁኑ ጊዜ ጀርመን ተገን የጠየቁ በርካታ አፍጋናውያን ጊዜም ሳይሰጠን ወደ ሀገራችን እንባረራለን በሚል ፍርሃት ውስጥ መሆናቸውን ቩፐርታል በተባለው ከተማ ውስጥ በሚገኝ አንድ የበጎ አድራጎት ድርጅት ውስጥ ለተገን ጠያቂዎች ምክር የሚሰጡት ማርያ ሻኩራ ይናገራሉ ።
«ተገን ጠያቂዎቹ ምናልባትም መውጣት በማይችሉበት እና ከሰዎች ጋርም በማይገናኙበት  በአንድ ማዕከል እንዲሰባሰቡ የሚደረግ ከሆነ  ምንም ዓይነት ህጋዊ ድጋፍ ስለሌላቸው ፍትሀዊ  ባልሆነ መንገድ በግዳጅ እንባረራለን የሚል ከፍተኛ ፍርሃት ውስጥ ናቸው ። »

Deutschland Abschiebungen abgelehnter Asylbewerber in Leipzig
ምስል picture-alliance/dpa/S. Willnow

 በጎርጎሮሳዊው 2015 በፈቃዳቸው ጀርመንን ለቀው የወጡ ተገን ጠያቂዎች ቁጥር 37,220 ነበር በዚሁ ዓመት በግዳጅ የተወሰዱት ደግሞ 20,914 ናቸው ። በፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘገባ መሠረት በ2016 ጀርመን ከገቡት 280 ሺህ ተገን ጠያቂዎች መካከል 80 ሺህ ያህሉ ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ተደርጓል ። እንደዘገባው ከመካከላቸው 54 ሺህ ያህሉ በፈቃዳቸው ወደ የሀገራቸው ሲመለሱ የተቀሩት ደግሞ በአየር በየብስ እና በባህር በግዳጅ ተባረዋል ። ሻኩራ ከሚያማክሯቸው አፍጋናውያን አንዱ ከነቤተሰቡ እባረራለሁ የሚል ስጋት ውስጥ ነው ያለው ። ወደ ሀገሩ ከሚባረር የራሱን ህይወት አጥፍቶ ቤተሰቦቹ እዚህ እንዲቆዩለት ማድረግ እንደሚመርጥ ነግሯቸዋል ።
«የአንድ ወጣት አፍጋናዊ አባወራ አማካሪ ነበርኩ ።በ20 ዎቹ እድሜ ላይ የሚገኘው የዚህ ወጣት ባለቤት  4ተኛ ልጃቸውን አርግዛለች ። ብቻቸውን ልጅ የሚያሳድጉ ሴቶች ወደ አፍጋኒስታን በግዳጅ አይላኩም ሲባል ስለሰማ ቢያንስ ባለቤቱ እና ልጆቹ እዚህ የመኖር እድል እንዲያገኙ የራሱን ህይወት እንደሚያጠፋ ይነግረን ነበር ። »
ባለፉት ሳምንታት በርካታ የአፍጋኒስታን ዜጎች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ተደርጓል ። በቅርቡ ከተባረሩት መካከል ባለፈው ሳምንት ወደ ሀገራቸው የተላኩት 34 አፋጋናውያን ይገኙበታል ። የአፍጋኒስታንን መንግሥት እና እዚያ የዘመቱ አጋሮቹን የሚወጋው አማጺው ታሊባን ጥቃቱን ባጠናከረበት በአሁኑ ጊዜ እነዚህ ጥያቄአቸው ተቀባይነት ያላገኘ ተገን ጠያቂዎች አፍጋኒስታን መላካቸው ከጀርመን ተቃዋሚ ፖለቲከኞች በኩል ጠንካራ ተቃውሞ አስነስቷል ። ከተቃዋሚዎቹ አንዱ የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ ነው ። የፓርቲው ተባባሪ መሪ ሴም ኦዝዴሚር የአፍጋኒስታን የፀጥታ ሁኔታ ከመሻሻል ይልቅ በባሰበት በአሁኑ ጊዜ አፍጋናውያን መባረር የለባቸውም ብለዋል ። የግራዎቹ ፓርቲ ተባባሪ መሪ ካትያ ኪፒንግ ደግሞ ውሳኔውን የሰብዓዊ መብቶችን የሚጥስ ሲሉ ተቃውመውታል ። የጀርመን መንግሥት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ሳይቀሩ በአፍጋኒስታን ደህንነቱ አስተማማኝ ነው የተባለ አካባቢ ስለመኖሩ የሚናገር ዘገባ አይቼ አላውቅም ሲሉ ጥርጣሬአቸውን ገልፀዋል ። በሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ የሚመሩ አንዳንድ የየጀርመን ፌደራል ክፍለ ግዛቶች አፍጋናውያን ከጀርመን በመባረራቸው አይስማሙም  ። በነርሱ አስተያየት በአፍጋኒስታን አስተማማኝ ደህንነት ስለሌለ ተገን ጠያቂዎች ወደ ዚያ መላክ የለባቸውም ። የሰሜን ጀርመኑ ሽሌስቪክ ሆልሽታይን ፌደራዊ ክፍለ ሀገር ለጊዜውም ቢሆን በተለይ በአፍጋኒስታን ዜጎች ላይ ተግባራዊ እንደማያደርግ አስታውቋል ። የግዛቱ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስርትር ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ፣በሰብዓዊ ምክንያቶች አፍጋናውያን ለሦስት ወራት ከጀርመን እንደማይባረሩ አስታውቀዋል ። ጀርመን ከካቡል መንግሥት ጋር የአፍጋኒስታን ስደተኞችን ለመመለስ ከ5 ወር በፊት በተስማማችው መሠረት ነው ተቀባይነት ያላገኙ አፍጋናውያን ተገን ጠያቂዎችን የምታባርረው ። ስምምነቱም ለአፍጋኒስታን እርዳታ ማሰባሰቢያ ዓለም ዓቀፍ ጉባኤ ከመካሄዱ ከጥቂት ቀናት አስቀድሞ ነበር የተፈረመው ። ጀርመን ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት ተገን ጠያቂዎች ሶርያውያን ናቸው አፍጋኒስታውያን ደግሞ ሁለተኛውን ደረጃ ይይዛሉ። በ2015 ጀርመን ከገቡት ተገን ጠያቂዎች 154,000 ሺሁ አፍጋናውያን ነበሩ ። የጀርመን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ቶማስ ደ ሚዜር ሀገራቸው ከቀደሙት ዓመታት ጋር ሲነፃጸር አሁን ለበርካታ ስደተኞች ተገን መስጠቷን  በዚያ መጠን ደግሞ በርካታ ማመልከቻቸው ተቀባይነት ያላገኘ ተገን ጠያቂዎች እንደሚባረሩም ተናግረዋል ። የስደተኞች አማካሪዋ ሻኩራ እንደሚሉት መንግሥት ለመጀመሪያ ጊዜ የተገን ማመልከቻ ጥያቄን ውድቅ ሲያደርግ ተገን ጠያቂው ወዲያውኑ ይባረራሉ ማለት አይደለም ። ይግባኝ ማለት የሚቻልባቸው እድሎች አሉ። ሆኖም አፍጋናውያኑ ይህን እውነት አይመስላቸውም ።
«በቅርቡ ሳማክራቸው ከነበሩ 22 ተገን ጠያቂዎች መካከል ሰባቱ ማመልከቻቸው ተቀባይነት አላገኘም ። የሚረብሽ ፍርሃት ውስጥ ነው የሚወድቁት ። ተገን ጠያቂዎች ከጀርመን ፌደራል የኢሚግሬሽን እና የስደተኞች ጉዳይ መሥሪያ ቤት ማመልከቻቸው ተቀባይነት እንዳላገኘ ከተገለፀላቸው በኋላ ወዲያውኑ አይባረሩም ። ከዚያ ይልቅ ውሳኔው እንዲቀየርላቸው የሚጠይቅ የፅሁፍ ማመልከቻ የሚያቀርቡበት ወይም አቤት የሚሉበት የ14 ቀናት ጊዜ ይሰጣቸዋል ።ከዚያ በኋላም ጉዳያቸው ፍርድ ቤት ሊቀርብ የሚችልበት ሁለተኛ እድል ይኖራቸዋል ።ይሁን እና ብዙዎች ይህን አያምኑም ። »
ተገን ጠያቂዎቹ የአገራቸው ሰዎች በየጊዜው ወደ አፍጋኒስታን ሲላኩ እያዩ ይህን ባያምኑ አያስደንቅም 
በአሁኑ ጊዜ ከጀርመን የመባረር ስጋት የሌለባቸው ሶሪያውያን እና ኤርትራውያን ተገን ጠያቂዎች ናቸው ። ኢራቃውያን እንኳን አሁን ማመልከቻቸው ውድቅ እየተደረገ ነው ። አማካሪ ሻካራ ተገን ጠያቂዎች የሰው ልጅ ህይወት ለአደጋ ወደተጋለጠበት ወደ አፍጋኒስታን መላክ የለባቸውም የሚል አቋም ነው ያላቸው ።ሰዎች በተደጋጋሚ ወደ ሚገደሉባት ኢራቅም እንዲሁ ።የእነዚህ ሀገራት ደህንነት አስተማማኝ ነው የሚል ፣ እዚያ ሄዶ ራሱን ማረጋገጥ ሲችል ሃሳቡን ወዲያውኑ መቀየሩ አይቀርም የሚል እምነት አላቸው ።

Mexiko Protest gegen Trump
ምስል Getty Images/AFP/R. Schemidt
Deutschland Abschiebung in Schönefeld
ምስል DW/N. Jolkver

ኂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ