በጀርመን ማመልከቻቸው ተቀባይነት ያላገኘ ተገን ጠያቂዎች እጣ ፈንታ
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 27 2016የጀርመን መንግሥት ካቢኔ ከጀርመን እንዲባረሩ የተወሰነባቸውን ተገን ጠያቂዎች በተቻለ ፍጥነት ከሀገሪቱ ለማስወጣት መወሰኑን በቅርቡ አስታውቋል። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ጀርመን የሚገቡ ፍልሰተኞችና ስደተኞች ቁጥር እየጨመረ መሄዱ ማነጋገሩ መቀጠሉ፣ መንግሥት ይህን እቅድ እንዲያወጣ ምክንያት ሆኗል ።በአሁኑ ጊዜ ከጀርመን እንዲወጡ ከተወሰነባቸው ስደተኞች ጥቂቱ ብቻ መባረራቸው በመንግሥት ላይ ጫና ፈጥሯልም ይባላል። ቀኝ ጽንፈኛ ፖለቲከኞችም ብዙውን ጊዜ ይህን ጉዳይ የህዝብ ድጋፍ እንዲጨምርላቸው ይጠቀሙበታል።
ጀርመን ባለፈው ዓመት በሩስያ ዩክሬን ጦርነት ምክንያት ከለላ የሚያስፈልጋቸው የተባሉትን ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ የዩክሬን ስደተኞችን ያለ ተገን ይሰጠን ማመልከቻ ተቀብላለች። ከዛ ውጭ በዚሁ ባለፈው ዓመት 244 ሺህ ሰዎች ጀርመን ከለላ እንድትሰጣቸው ማመልከቻ አስገብተዋል። በዚህ ዓመት ደግሞ ይህ ቁጥር ወደ 300 ሺህ ከፍ ሊል እንደሚችል የመስኩ ባለሞያዎች ገምተዋል።
የጀርመን ፌደራል መንግሥት የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደሚለው እስካለፈው መስከረም መጨረሻ ድረስ 12 ሺህ ተገን ጠያቂዎች ወደ መጡበት እንዲባረሩ ተደርጓል። አሁን ደግሞ የጀርመን ሶሻል ዴሞክራት ፓርቲ ፖለቲከኛ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ናንሲ ፌዘር ጉዳያቸው ተቀባይነት ያላገኘ ተገን ጠያቂዎችን ከጀርመን በጥድፍያ ለማስወጣት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።
ፌዘር ጀርመን የመቆየት መብት የሌላቸው ያሏቸው ተገን ጠያቂዎች ከጀርመን መውጣት አለባቸው ብለዋል።« ተገን የማግኘት መሠረታዊ መብትን ለማስጠበቅ ሕገ ወጥ ስደትን በእጅጉ መገደብ አለብን። በድጋሚ እዚህ የመቆየት መብት የሌላቸው ሀገራችንን ለቀው መውጣት አለባቸው። በዚህ ዓመት ከሀገራችን የሄዱት ቁጥር ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ጊዜ ከተመለሱት ጋር ሲነጻጸር በ27 በመቶ ከፍ ያለ ነው። ያም ሆኖ ተግባራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ከፍተኛ ፍላጎት አለ።»
ከርሳቸው ቀደም ሲልም መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ ጀርመን የመቆየት መብት ያላገኙት ተገን ጠያቂዎች በስተመጨረሻ መጠረዝ አለባቸው ሲሉ ሽፒግል ለተባለው ታዋቂ የጀርመን መጽሔት በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ ተናግረዋል። ፌዘር የአዲሱ የጀርመን ካቢኔ እቅድ እዚህ የመቆየት መብት የላቸውም የሚባሉትን ስደተኞች ለማስወጣት ብቻ ሳይሆን በተለይ በሕገ ወጥ መንገድ ሰዎችን ማሸጋገርን ለመከላከልም ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል ።
ፌዘር እንደሚሉት እርምጃው ደላሎችን ለማባረርም ያስችላል። «ሕገ ወጥ ፍልሰትን መገደቡ አስፈላጊ የሆነበት ዋነኛው ምክንያት በሕገ ወጥ መንገድ የሚካሄድ አረመኔያዊ ጭካኔ የተሞላበትና አጸያፊ፣ ሰዎችን ከአገር አገር ማሻገርን መከላከልን ለማጠናከር ነው። ይህ የዛሬው ውሳኔ ወደፊት እንድንራመድ ያደርገናል። ወደፊት ሕገ ወጥ የሰዎች አሻጋሪዎችን በቀላሉ ለማባረር እንችላለን። ከዚህ በተጨማሪም ህጻናትን በሕገ ወጥ መንገድ ማሸጋገር ወደፊት በሕግ የሚያስቀጣ ይሆናል።»
ዶቼቬለ በጉዳዩ ላይ ያነጋገራቸው ጀራልድ ክላውስ የተባሉ የፍልሰት ጉዳዮች አጥኚ አዲሱ እቅድ፣ ማመልከቻቸው ውድቅ የተደረገባቸውን ተገን ጠያቂዎች ብቻ ሳይሆን ማመልከቻ ያላስገቡትንም ጭምር ይመለከታል ። የጀርመን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደሚለው እስካለፈው መስከረም መጨረሻ ድረስ ከጀርመን መባረር ነበረባቸው የሚባሉ 255 ሺህ ሰዎች አሁን በሀገሪቱ ይገኛሉ። ሆኖም ከመካከላቸው 205 ሺሁ በጀርመንኛ ዱልዱንግ የሚባለው ጊዜያዊ የመኖሪያ ፈቃድ አላቸው።
ማመልከቻቸው ውድቅ የተደረገባቸው ተገን ጠያቂዎች ከጀርመን መባረር አለባቸው ቢባልም በሕጋዊ ምክንያቶች ግን ከሀገሪቱ እንዲወጡ አይገደዱም። ይህ የሚሰራው ደግሞ ለምሳሌ የመጡበት ሀገር ለደኅንነታቸው አስጊ ለሆነባቸው ፣ የጤና ችግር ላለባቸው ፣ የሙያ ስልጠና ለጀመሩ ወይም ደግሞ ሰነዶች ለጎደሉባቸው ነው። የትውልድ ሀገራቸው አልቀበልም ካለም ማባረር አይቻልም ። በዚህ የተነሳም የጀርመን መንግሥት እነዚህን ተገን ጠያቂዎች አግዛለሁ ቢልም ይህ ሊሳካ አይችልም ሲሉ ባለሞያው ክናውስ ጥርጣሪያቸውን ገልጸዋል።
የእቅዱ አተገባበር እያነጋገረ ባለበት በአሁኑ ጊዜ ማመልከቻቸው በሂደት ላይ ያለና በጊዜያዊ ፈቃድ ጀርመን የሚገኙ ተገን ጠያቂዎች ስጋት አድሮባቸዋል።ከመካከላቸው አንዱ ጀርመንና ኔዘርላንድ ጠረፍ አካባቢ በሚገኘው በምዕራብ ጀርመኑ ክሌቨ ከተማ ውስጥ ባለ አካባቢ የሚኖረው ወጣት ተገን ጠያቂ አንዱ ነው። ወጣቱ ለዶቼቬለ እንደተናገረው ከአሁኑ የመንግሥት ውሳኔ ሁለት ነገሮችን ይጠብቃል።ተገን ጠያቂው ከባለቤቱ ጋር ነው ጀርመን የመጣው። እዚህ ከመጣ በኋላ የተወለደች የ4 ዓመት ልጅም አለችው።
ተገን ጠያቂው እንደሚለው በጀርመን የርሱና ቤተሰቡ አያያዝም ሆነ የተገን ጥያቄአቸው ሂደት በተግዳሮቶች የየተሞላና ተስፋም የሚያስቆርጥ ሆኖበታል። እርሱና ቤተሰቡ በየ3 ወር በሚታደስ ጊዜያዊ የመኖሪያ ፈቃድ እንደሚኖሩ የተናገረው ወጣቱ እነርሱ በሚኖርበት አካባቢ ከነበሩ ሌሎች ተገን ጠያቂዎች አብዛኛዎቹ ተስፋ በመቁረጥ አካባቢውን ለቀው ወደ ሌሎች ሀገራት ተሰደዋል ብሏል። አምስት ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ በጀርመን ቢሮክራሲ ብዙ ውጣ ውረድ ያሳለፈው ወጣቱ ተገን ጠያቂ የጀርመን መንግስት የተገን ጠያቂዎችን ችግር በቅጡ እንዲያጤን ተማጽኗል።
ይሁንና የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ናንሲ ፌዘር መንግሥት የተገን ጥያቄአቸው ተቀባይነት ያላገኘ ሰዎችን ማጋዙ አስፈላጊ ነው ብለዋል።« ሆኖም እነዚህ እርምጃዎች አስፈላጊ ናቸው። በዚህ ዓመት በአሁኑ ወቅት በኛ ሀገር ከፍተኛ ሕገ ወጥ ስደት እየተካሄደ ነው። ለዚህም ነው እንደ መንግሥት እርምጃ መውሰድ ያለብን።» የጀርመን መንግሥት በቅርቡ ተቀባይነት ያላገኙ ተገን ጠያቂዎችን በአስቸኳይ ወደመጡበት ለመመለስ ያወጣው አዲስ እቅድ ስራ ላይ እንዲውል በጀርመን ፓርላማ መጽደቅ አለበት ።
ኂሩት መለሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ