የጎርጎሪዮሳዊው 2023 የጀርመን አፍሪቃ ሽልማት ተሸላሚዎቹ ካሜሮናውያን ሴቶች
ዓርብ፣ ኅዳር 21 2016
ካሜሮን ውስጥ ትምህርት የሚጀመርበት አዲስ ዘመን ነው። በተለይ በሰሜን ካሜሮን ሞኮሎ በሚባለው መንደር ተማሪዎች ወደ ክፍል እየገቡ ነው። የሕግ ባለሙያ እና የሴቶች መብት ተሟጋቿ ማርቴ ዋንዱ በክፍሉ ውስጥ ንግግር ያደርጋሉ። ዋንዱ ካሜሮን ውስጥ ላለው ግጭት መፍትሄ የሚያፈላልገው በካሜሮን የመጀመሪያው ብሔራዊ የሴቶች ስብስብ አባል ናቸው። የካሜሮን ሴቶችን ያሰባሰበው ብሔራዊ ማኅበር ለዚህ ጥረቱ የጀርመንየአፍሪቃ ተቋም የዘንድሮውን የአፍሪቃ ሽልማት አሸናፊ ሆኗል። ይኽ ስብስብ 77 የሴቶች ድርጅቶች እና 10 ግዛቶችን እንዲሁም በካሜሮን ማኅበረሰብ ውስጥ የሚገኙ የሴቶች አጠቃላይ መድረክ ትስስሮችን ያካተተ ነው።
በሀገሪቱ ያሉት ዘርፈ ብዙ ቀውሶች
ካሜሮን በቀውስ ተከፋፍላለች። ከጎርጎሪዮሳዊው 2017 ጀምሮ ተገንጣይ ቡድኖች እንግሊዝኛ ተናጋሪውን ሰሜን ምዕራብ እና ደቡብ ምዕራቡን አካባቢ ይዘው ነጻ ለመውጣት ይታገላሉ። ዓለም አቀፉ የቀውስ ተመልካች ቡድን እንደሚለው በግጭቱ ምክንያት ቢያንስ ስድስት ሺህ ሰዎች አልቀዋል። ከ700 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ በሀገር ውስጥ ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን የተመድ ያመለክታል። ከዚህ በተጨማሪም የእስላማዊ ጽንፈኛው ቦኮ ሃራም ታጣቂዎች በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ጥቃት ያደርሳሉ፤ በጎረቤት ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፑብሊክ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ አማጽያንም በምሥራቅ ካሜሮን ጥቃት ይፈጽማሉ። በዚህም በርካታ ልጆች እና አዋቂ ሴቶች ለስቃይ ተዳርገዋል።
ብሔራዊው የካሜሮን ሴቶች ስብስብ አፋጣኝ የተኩስ አቁም እንዲደረግ እና ለመገንጠል በሚንቀሳቀሱት እና በመንግሥት መካከል ውይይት እንዲጀመር ጥሪ እያቀረበ ነው። በውይይቱም ሴቶችም መሳተፍ እንዳለባቸውም ያሳስባል። ለጦርነቱ ሰላባዎችም የስነልቡና ክብካቤ መደረግ እንደሚኖበትም እያመለከተ ነው። ከዚኽና መሰል ሥራዎቹ በተጨማሪ በብሔራዊው የሴቶች ስብስብ ውስጥ የሚንቀሳቀሱት ሴቶች፤ በማኅበረሰቡ ውስጥ በተለያዩ መስኮች ይሳተፋሉ። ከመካከላቸውም ሦስቱ ሽልማቱን በስብስቡ ስም ተቀብለዋል።
ማርቴ ዋንዱ በተለይ የተማሪዎች ነገር ያሳስባቸዋል፤ ካሜሮን ውስጥ ሁሉም ወላጆች አይደሉም ሴት ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት የሚልኩት። «እኔ የማልመው እያንዳንዷ ሴት ልጅም ሆነች ወልዶች ልጆች እስከፈለጉበት ደረጃ ድረስ መማር እንዲችሉ ትምህርት ቤት የመሄድ ዕድል እንዲኖራቸው ነው።» ይላሉ ዋንዱ።
ዋናኛው ችግር ግን በልጅነት መዳር ነው። የተባበሩት መንግሥታት የባህል እና የሳይንስ ድርጅት UNICEF እንደሚለው ከ30 በመቶ በላይ የሚሆኑት የካሜሮን ሴት ልጆች 18 ዓመት ሳይሞላቸው ይዳራሉ። ማርቴ ዋንዱ ግን ሴት ልጆች እና አዋቂዎቹ ሴቶች ወደ ትምህርት ቤት ተመልሰው እንዲገቡ ወይም ንግድ እንዲማሩ ለማግባባት እየሞከሩ ነው። ሆኖም ግን አስቀድመው ቤተሰቦቻቸውን ማሳመን ይኖርባቸዋል። ዋንዱ «ይህን ችግር በራሴም መንደር ተመልክቼዋለሁ። በባህል ምክንያት ሰዎች የተማረች ልጅ ጥሩ ሴት መሆን አትችልም ይላሉ። የሚያገባት አታገኝም እንዲሁ ታረግዛለች። ዛሬም ከ40 ዓመታት በኋላ እንዲህ ያለው ፍረጃ እና ማግለል በመንደሪቱ በመቀጠሉ በጣም አዝናለሁ። አስከፊ በሆኑ ነው ቤተሰቦችን ማስተማራችንን የገፋንበት።» ይላሉ።
ከቦኮ ሃራም ጋር የሚደረገው ፍልሚያ
ባህል እና የሃይማኖት እሴቶች ብቻም አይደሉም ሴቶችን የሚገድቡት፤ የቦኮሃራም ስጋትም ሌላው ምክንያት ነው። የ21 ዓመቷ አይሻ እና መላ ቤተሰቧ በጎርጎሪዮሳዊው 2016 ዓ.ም. በእስላማዊው አሸባሪ ቡድን ታግተው የቡድኑን ተዋጊ በግዳጅ እንድታገባ ተደርጓል።
«ሴቶች ካለምንም ምክንያት ይደበደባሉ እንዲሁም በየጊዜው በግዳጅ ይደፈራሉ።» ነው የምትለው አይሻ። አንዳንዶች መጠነኛ ከለላ ለማግኘት በሚል ያገባሉ። እንዲያም ሆኖ በሌላው ዓለም እንዳለው የእውነት ትዳር ጋር የሚመሳሰል ጋብቻ አይደለም እዚህ ያለው። የቦኮ ሃራም ተዋጊዎች በሙሉ በጦር ሰፈራቸው ከየትኛዋም ሴት ጋር ወሲብ የመፈጸም መብት አላቸው። ሴቶችም መራመድ እስኪያቅታቸው ነው የግዳጅ ወሲብ የሚፈጸምባቸው። ባላቸው ከሞተ እና በ24 ሰዓት ውስጥ ሌላ ባል ለማግባት ካልፈለጉ ወዲያው አንገታቸው ይቀላል።»
አይሻ ልጇን ይዛ ከጦር ሰፈሩ ማምለጥ ችላለች። ዕድሜ ለዋንዱ የስነአእምሮ ክብካቤ እና የራሷን ንግድ እንድታንቀሳቅስም የፋይናንስ ድጋፍ አግኝታለች።
«አንዳንዴ ባስከፊ ነገሮች ውስጥ ልናልፍ እንችላለን፤ ሆኖም ግን አስቸጋሪ ገጠመኞቻችንን ወደ ኋላ በመተው ተስፋ እና ሕይወታችንን በራሳችን ለመምራት ድፍረት ማግኘት አስፈላጊ ነው።» ይላሉ ለሀገራቸው ሴቶች የሚታገሉት ዋንዱ።
የተጽዕኖን ሰንሰለት ሰባሪዋ ኤስተር ኦማም
በደቡብ ምዕራብ ካሜሮን ኤስተር ኦማም ተንቀሳቃሹን ክሊኒክ በዓሣ አጥማጆቹ መንደር ደቡብድቻ ላይ ለአንድ ቀን ከፍተው ያክማሉ። እሳቸው እና ያቋቋሙት መንግሥታዊ ያልሆነው ድርጅት «ሪች አውት ካሜሮን» ነጻ የህክምና አገልግሎትን ለበርካታ ሺህ ሰዎች በየሳምንቱ በመስጠት ላይ ይገኛሉ። ለብዙዎቹ ታካሚዎቻቸው ይኽ ብቸኛው የጤና ክብካቤ የሚያገኙበት ዕድል ነው። በተገንጣዮች እና በመንግሥት ጦር መካከል የሚካሄደው ውጊያ የህክምና ማዕከላትን አውድሟል። የዘንድሮውን የጀርመን አፍሪቃ ሽልማት ከተቀበሉት አንዷ የሆኑት ኦማም ስላለው ችግር ለዶቼ ቬለ ሲገልጹም።
«ከኤችአይቪ ተሀዋሲ ጋር ለሚኖሩ ሰዎች የሚያስፈልገው መድኃኒት አቅርቦት ሙሉ በሙሉ ተቋርጧል። ወደ ህክምና ማዕከላት ለመሄድ ሰዎች በቀላሉ ኢላማ ልሆን እችል ይሆናል ከሚለው ስጋት መላቀቅ አይችሉም።» ነው ያሉት።
ኦማም ከ20 ዓመታት በላይ ካሜሮን ውስጥ ሰብአዊ እርዳታ ሲያቀርቡ ኖረዋል። አነስተኛ የንግድ ሥራዎችን በማስጀመርም የመብት ተቆርቋሪዋ ኤስተር ኦማም የድህነት እና የጭቆና አዙሪቱን ለመበጠስ አልመው ሴቶችን በመርዳት ሥራ ተጠምደዋል።
«ሴቶቹ ንጹሕ ውኃ እና ከስጋት ነጻ የሆነ ትምህርት ማግኘት እንደሚፈልጉ ይነግሩኛል። እኔም ተመሳሳይ ችግር አሳልፌያለሁ። ስለዚህ የሰዎችን ልብ በመንካት በሕይወታቸው ላይ ለውጥ ማምጣት መቻል ለእኔ እርካታ ነው።» ይላሉ ኦማም።
ለስነተዋልዶ ጤና መብት የሚታገሉት ሳሊ ማቡሚኒ
በሰሜናዊ ካሜሮን ሳሊ ማቡሚኒ እና «የጋራ እርምጃ ለጾታ ልማት» በተሰኘው ድርጅት ሥር የተሰባሰበው የሴቶች ቡድን አዋቂ እና ሴት ልጆች በወሲብ እና በስነተዋልዶ ጤና መብት እንዲኖራቸው ዘመቻ ያካሂዳሉ። ባሜንዳ በተባለችው ከተማ የካሜሮን ብሔራዊ የሴቶች ስብስብ አባል የሆኑት ማቡሚኒ የጾታ ጥቃት ሰለባዎችን ያማክራሉ፤ ይረዳሉ። ያደጉበት አካባቢ እንደመሆኑም ማቡሚኒ ያሉትን ተግዳሮቶች ጠንቅቀው ያውቃሉ።
«ሌላው ቀርቶ ይህን የሚመለከት የጤና አገልግሎት እንኳን ማግኘት ቢሟገቱም ማግኘት አልቻሉም። ሴቶቹን በሚመለከቱ ጊዜም በኤኮኖሚ ሲታለሉ እንደኖሩ ያስባሉ፤ ለደህንነታቸውም ቢሆን እንዲሁ፤ በራሳቸው አካል ነጻነት የላቸውም፤ የመሪነት ሚናም አግኝተው አያውቁም። የዘርፈ ብዙ ጥቃቶች እና አለአግባብ የሚፈጸሙ ድርጊቶች ሰለባዎች ናቸው።»
የካሜሮን ሴቶች ከፍ ወዳለው ደረጃ መድረስ
ከጎርጎሪዮሳዊው 2015 ጀምሮ ማቡሚኒ ሴቶች በማኅበረሰባቸው ውስጥ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው በማስተማር እና በማነቃቃት ላይ ይገኛሉ። ዶሪን ናክዋይም ወጣት አንቂ ናት።
«በአሁኑ ጊዜ ሴቶችን በመሪነት ቦታ ላይ ማግኘት አስቸጋሪ ነው። ሌላው ቀርቶ አስፈላጊውን አሟልታ እንዲህ ላለው ዕድል ብታመለክትን እኳን፤ አይቻልም ሴት ልጅ አንቀጥርም ነው የሚሉት። ለምን ቢባል፤ ባገባች ጊዜ የወሊድ ፈቃድ ትወጣለች እና የመሳሰሉትን ምክንያቶች ይሰጣሉ።»
ማቡሚኒ እንደሚሉት የካሜሮንን ቀውስ ከሚፈልቱ መፍትሄዎች አንዱ አዋቂ እና ወጣት ሴቶችን በከፍተኛ ደረጃዎች ላይ ማስቀመጥ ነው።
የጀርመን አፍሪቃ ሽልማት በዳኞቹ ዕይታ ለዴሞክራሲ፤ ለሰላም፤ ለሰብአዊ መብቶች፤ ለኪነጥበብ ፤ ለባህል፤ ለልማት፤ ለሳይንስ እና ማኅበረሰብ በቁጥርጠኝነት አስተዋጽኦ ላበረከቱ አፍሪቃውያን የሚሰጥ ትልቅ ሽልማት ነው። ቀደም ሲልም የቦስትስዋና የድሮ ፕሬዝደንት ኬቱሚሊ ማሲሬ፤ የሶማሊያ ሴቶች መብት ተሟጋች ዋሪስ ዲሪ፤ ከደቡብ አፍሪቃ የባዮኢንፎርማቲክ ፕሮፌሰር ቱሊዮ ደ ኦሊቪራ፤ እንዲሁም የተሀዋስን ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ሲኩሊሊ ሞዮ ከቦትስዋና ይህን የጀርመን አፍሪቃ ሽልማት ወስደዋል።
ሲሊያ ፍሮህሊሽ/ ቤላይስ ኤሊዮን
ሸዋዬ ለገሠ
ነጋሽ መሐመድ