ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ሽልማታቸዉን ተቀበሉ
ዓርብ፣ ኅዳር 10 2014የሰብአዊ መብት ተሟጋች ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ትናንት በርሊን ብራንድቡርግ፤ ላይ ትናንት ሃሙስ ምሽት በተዘጋጀው የእራት ግብዣ ላይ የ2021 የጀርመን አፍሪቃ ሽልማት ተቀበሉ። ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ሽልማቱን ያገኙት በህይወት ዘመናቸው ለሰብአዊ መብት መከበር ባደረጉት ከፍተኛ ትግል ነው። ሽልማቱን የጀርመን አፍሪቃ ፋውንዴሽን ፕሬዝዳንት ኡሺ አይድ እና የጀርመን አፍሪቃ ፋዉንዴሽን ዳኞች ፕሬዝዳንት ክላዉስ ሽቴከር በጋራ ለዶ/ር ዳንኤል በቀለ አበርክተዉላቸወዋል። በክብረ በዓሉ ላይ ወደ 50 የሚሆኑ ከፖለቲካ፣ ከንግድ እና ከህብረተሰብ የተውጣጡ ጀርመናዉያን እንግዶች የኮሮና ተኅዋሲ ጥንቃቄ በተሞላበት ሂደት ተገኝተዋል። የቀድሞው የጀርመን ፕሬዝዳንት ዮአሂም ጋውክ በሥነ-ስርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተዋል።
የጀርመን አፍሪቃ ፋውንዴሽን ፕሬዝዳንት ኡሺ አይድ በኢትዮጵያ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በመጥቀስ «ሽልማቱ ለምሳሌ ኦሮሞ፣ አማራ፣ ትግሬ፣ ሶማሌ ወይም አፋር ዉስጥ ያሉና ሳይፈሩ ለሰብአዊ መብት መከበር ለሚቆሙ ሁሉ ማበረታቻ ሊሆን ይገባል» ሲሉ አሳስበዋል።
የጀርመን አፍሪቃ ፋዉንዴሽን ዳኞች ፕሬዝዳንት ክላዉስ ሽቴከር በበኩላቸዉ «ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት አስቸጋሪ ሁኔታ የኃላፊነት እና ድፍረት ምሳሌ ሲሉ ዶክተር ዳንኤል በቀለን አሞግሰዋቸዋል። ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ምን ያህል በአስቸጋሪ ሁኔታ ዉስጥ ሆነዉ ስራቸዉን እያከናወኑ እንደሆነም ሽቴከር አዉስተዋል። ዶ/ር ዳንኤል « ሰዎች ወዳጅ ወይም ጠላት ብቻ ተብልዉ በሚፈረጁበት ሁኔታ እርሶን የመሰለ የመብት ተሟጋች እንዴት የሞራል ግዴታዉን እና ስብዕናዉን ጠብቆ በአመነበት ጉዳይ ሊሰራ ይችላል? » ሲሉም የጀርመን አፍሪቃ ፋዉንዴሽን ዳኞች ፕሬዝዳንት ክላዉስ ሽቴከር ጠይቀዋል።»
የሽልማቱ አሸናፊ ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በበኩላቸዉ «ሽልማቱ ለሰብአዊ መብቶች መከበር በየቀኑ ለሚሰሩ እና በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ እንዲሁም በፖለቲካዊ ተቃውሞ ውስጥ እንኳን ሆነዉ የእኩልነት መርህን ለሚጠብቁ ባልደረቦቻቸዉ ሁሉ ይሁን» ሲሉ ተናግረዋል።
አዜብ ታደሰ
ኂሩት መለሰ