የግንቦት 5 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ ግንቦት 5 2016ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በዶሀ ዳይመን ሊግ ለድል በቅተዋል ። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቸስተር ሲቲ እና አርሰናል ዘንድሮ ዋንጫውን ለማንሳት አንገት ለአንገት ተናንቀዋል ። በጀርመን ቡንደስሊጋ፦ የዋንጫ ባለድሉ ባዬርን ሌቨርኩሰን አመርቂ ድል እየተደጋጋመ ነው ። ሁለት ተጨማሪ የዋንጫ ግጥሚያዎች ይጠብቁታል ። በሻምፒዮንስ ሊግ ደግሞ የጀርመኑ ቦሩስያ ዶርትሙንድ እና የስፔኑ ሪያል ማድሪድ ዋንጫውን ለማንሳት ከሁለት ሳምንታት በኋላ በፍጻሜው ይፋለማሉ ።
አትሌቲክስ
በዶሀ ዳይመን ሊግ በ3000 ሜትር መሠናከል በወንዶች ፉክክር እና በ1500 ሜትር የሴትቶች ሩጫ ውድድር ኢትዮጵያን አትሌቶች በሳምንቱ መጨረሻ ላይ አሸናፊ ሆነዋል ። በ3000 ሜትር መሠናከል የወንዶች ፉክክር የግሉን ሰአት በማሻሻል ለድል የበቃው አትሌት ሳሙኤል ፍሬው ነው (8:07.25 1ኛ)። በዚህ ውድድር አትሌት ጌትነት ዋሌ (በ 8:09.69) 3ኛ ደረጃ አግኝቷል ።
በ1500 ሜትር ሴቶች ፉክክር ደግሞ አትሌት ፍሬወይኒ ኃይሉ (4:00.42) 1ኛ ወጥታለች ። ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ወርቅነሽ መሰለ(4:01.25) 4ኛ ደረጃ አግኝታ አጠናቃለች ። በ5000 ሜትር ሴቶች ሩጫም አትሌት እጅጋየሁ ታዬ (14:29.26) 2ኛ ስትወጣ፥ መዲና ኢሳ(14:34.11) የ3ኛ፤ መልክናት ውዱ (14:44.17) የ4ኛ ደረጃን አግኝተዋል ። በ800 ሜትር ሴቶች ፉክክር አትሌት ሀብታም ዓለሙ (1:59.08) 4ኛ ደረጃ አግኝታ አጠናቃለች ።
እግር ኳስ
የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን የሦስተኛ ዙር የመጀመራያ ጨዋታውን ከኬንያ ጋ ዐርብ በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም አድርጎ ያለምንም ግብ ተለያይቷል ። የመልሱ ጨዋታ የፊታችን እሁድ ኬንያ ውስጥ ይከናወናል። እስካሁን በተደረጉ ግጥሚያዎች፦ ጅቡቲ በቡሩንዲ ቡድን ትናንት የ18 ለ0 ብርቱ ሽንፈትን በማስተናገድ የግብ ጎተራ ሆናለች ። ትናንት በነበረ ሌላ ግጥሚያ ዛምቢያ ዩጋንዳን 2 ለ0 አሸንፋለች ። ቅዳሜ ዕለት፦ ሴኔጋል ላይቤሪያን 3 ለ1 ስታሸንፍ፤ ቡርኪናፋሶ እና ናይጄሪያ አንድ እኩል ተለያይተዋል ። ዐርብ ዕለት ከኢትዮጵያ እና ኬንያ ግጥሚያ በተጨማሪ በነበረ ጨዋታ፦ ሞሮኮ አልጄሪያን 4 ለ0 ረትታለች ።
ከ17 ዓመት በታች የሴቶች የዓለም ዋንጫ የሚያልፉ ሃገራት የሚታወቁት ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ በሚከናወኑት አራተኛ ዙር ግጥሚያዎች ይሆናል ። የዘንድሮውን የዓለም ዋንጫ ከሕዳር መገባደጃ አንስቶ የምታስተናግደው የዶሚኒክ ሪፐብሊክ ናት ።
ፕሬሚየር ሊግ
በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ትናንት ማንቸስተር ዩናይትድን አንድ ለዜሮ ያሸነፈው አርሰናል አንድ የመጨረሻ ጨዋታ እየቀረው በ86 ነጥብ አንደኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች የሚቀሩት ማንቸስተር ሲቲ በአርሰናል የሚበለጠው በአንድ ነጥብ ብቻ ነው ። ማንቸስተር ሲቲ ነገ በቶትንሀም ሆትስፐር ስታዲየም ቶትንሀምን ካሸነፈ የመሪነቱን ስፍራ ከአርሰናል ይረከባል፥ በሁለት ነጥብ ልዩነትም ይበልጣል ማለት ነው ። አቻ ከወጣ በነጥብ ከአርሰናል ጋ ተስተካክሎ በግብ ክፍያ ግን የሁለተኛ ደረጃው ላይ ይቆያል ። ያም በመሆኑ የነገውን የማንቸስተር ሲቲ ግጥሚያ የአርሰናል ደጋፊዎች እጅግ በተለየ ሁናቴ ነው የሚከታተሉት ። ምናልባትም ማንቸስተር ሲቲ እንዲሸነፍ በመጸለይ ጭምር ።
የማንቸስተር ሲቲ አሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ ቶትንሀምን በሜዳው ለማሸነፍ «ለየት ያለ» ያሉትን «ነገር» እንደሚሞክሩ ዛሬ ተናግረዋል ። ያ የተለየው ነገር ምን እንደሚሆንም በርካቶች በልዩ ትኩረት የሚጠብቁት ነው ። ቡድናቸው በቶትንሀም ሜዳ ከዚህ ቀደም ተጫውቶ «ግብ ማስቆጠርም ሆነ ማሸነፍ» እንዳልቻለ የተናገሩት ፔፕ ጓርዲዮላ፦ ነገ የተለየ ነገር ካላደረጉ ዋንጫው የአርሰናል ይሆናል ብለዋል ። እናስ አሰልጣኙ የተለየ ያሉት ነገር ሳይሳካ ቶትንሀም አርሰናል ይታደግ ይሆን?
አርሰናል አንድ ቀሪ 38ኛ ጨዋታውን የፊታችን እሁድ ከኤቨርተን ጋ ያደርጋል ። ማንቸስተር ሲቲ ደግሞ የመጨረሻ ግጥሚያውን በተመሳሳይ ቀን እና ሰአት የሚያደርገው ከዌስትሀም ዩናይትድ ጋ ነው ።
በሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሊቨርፑል ዛሬ ማታ ቪላ ፓርክ ስታዲየም ውስጥ አስቶን ቪላን ይገጥማል ፥ 38ኛ እና የመጨረሻ ጨዋታውን ደግሞ እሁድ ከዎልቭስ ጋ ያደርጋል ። ሁለቱንም ቀሪ ጨዋታዎቹን ቢያሸንፍ እንኳ አሁን ማንቸስተር ሲቲ ካለው 85 ነጥብ በአንድ መበለጡ አይቀርም ። ቀሪ ሁለት ጨዋታዎቹ የአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ ቦታውን ላረጋገጠው ሊቨርፑል የሚፈይዱት ነገር የለም ።
ባይሆን 67 ነጥብ ሰብስቦ 4ኛ ደረጃ ላይ ለሚገኘው አስቶን ቪላ ቀሪ ሁለት ግጥሚያዎች የሞት ሽረት ናቸው ። የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ አራተኛ ቡድንነቱን በአስተማማኝ መልኩ ለማረጋገጥ ቀሪ ሁለት ጨዋታዎቹን ማሸነፍ ይጠበቅበታል ። ዛሬ ከሊቨርፑል ጋ ከሚያደርገው ግጥሚያ ባሻገር እሁድ ከክሪስታል ፓላስ ጋ ያለው ጨዋታንም ካላሸነፈ ቶትንሀም ሆትስፐር ያሰጋዋል ። ቶትንሀም በ63 ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። በዚሁ ካጠናቀቀ የአውሮጳ ሊግ የምድብ ተጋጣሚነቱን እንደተጠበቀ ይቆያል ። የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ ለመሆን ግን ቀሪ ሁለት ጨዋታዎቹን አሸንፎ የአስቶን ቪላን ሽንፈት አለያም አቻ መሆን መማጸን ይኖርበታል ። ከሊቨርፑልም ሆነ ከክሪስታል ፓላስ ጋ ቀሪ ጨዋታዎቹን የሚያደርገው አስቶን ቪላ በሁለቱም ነጥብ ይጥላል ማለት ግን ይከብዳል ።
ቡንደስ ሊጋ
የጀርመን ቡንደስሊጋ የዘንድሮ ዋንጫን ቀደም ሲል መውሰዱን ያረጋገጠው ባዬርን ሌቨርኩሰን ትናንት ቦሁምን 5 ለ0 ድባቅ መትቶ አሸንፏል ። ባዬርን ሌቨርኩሰን ከሳምንት በፊትም አይንትራኅት ፍራንክፉርትን በቡንደስሊጋው ያደባየው 5 ለ1 ነበር ። በሚቀጥለው ሳምንት ቅዳሜ ከካይዘርስላውተርን ጋ የጀርመን እግር ኳስ ማኅበር (DFB) ፍጻሜ ይጠብቀዋል ። የፍጻሜ ተጋጣሚው ካይዘርስላውተርን በቡንደስሊጋ ሁለተኛ ዲቪዚዮን 15ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ቡድን ነው ። በሚቀጥለው ሳምንት ረቡዕ ደግሞ በአውሮጳ ሊግ የዋንጫ ፍልሚያ አታላንታ ይጠብቀዋል ። ለበርካታ ዓመታት የቡንደስሊጋ ዋንጫን እየተቁለጨለጨ ዘንድሮ የተሳካለት ባዬርን ሌቨርኩሰን በዣቪ አሎንሶ የአሰልጣኝነት ዘመን ሦስት ዋንጫዎችን ሰብስቦ በርካቶችን ያስደምም ይሆን?
ከቡንደስሊጋው ዳርምሽታድት ወደ ታችኛው ዲቪዚዮን መውረዱን አረጋግጧል ። በአጠቃላይ ከ14ኛ እስከ 17ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት፦ ቦሁም፤ ማይንትስ፤ ዑኒዮን ቤርሊን እና ኮሎኝ የመውረድ እና የመዋዠቅ ሥጋት ገጥሟቸዋል ።
17ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ኮሎኝ ቀጣዩን ግጥሚያ አሸንፎ ዑኒዮን ቤርሊን ከተሸነፈ ከቡንደስሊጋው ከመሰናበት ለጊዜው ይተርፋል። ሆኖም ከታችኛው ዲቪዚዮን ሦስተኛ ደረጃ ይዞ ካጠናቀቀው ፎርቱና ዱይስልዶርፍ ቡድን ጋ ተጋጥሞ በሚኖረው ውጤት ይሆናል በቡንደስሊጋው መቆየት አለያም መሰናበቱን ወደፊት የሚያረጋግጠው ። በቡንደስሊጋው የዘንድሮ የመጨረሻ ግጥሚያ ቅዳሜ በሐይደንሀይም ከተሸነፈ አለያም ዑኒዮን ቤርሊን ፍራይቡርግን ማሸነፍ ከቻለ ግን ኮሎኝ ያበቃለታል ። ኮሎኝ ወደ ቡንደስሊጋ ሁለተኛ ዲቪዚዮን መሰናበቱ አይቀርም ።የሚያዝያ 14 ቀን 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ከዑኒዮን ቤርሊን በሁለት ነጥብ በልጦ 15ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ማይንትስም በቡንደስሊጋው ለመቆየት ቮልፍስቡርግን ማሸነፍ ይጠበቅበታል ። አቻ ከወጣ ግን 30 ነጥብ ያለው ዑኒዮን ቤርሊንን ውጤትን ማየት አለበት ። 33 ነጥብ ያለው ቦሁም ራሱ ቬርደር ብሬመንን ማሸነፍ አለያም አቻ መውጣት ካልቻለ የሌሎቹን ውጤት ጠብቆ ሊዋዥቅም ይችላል ። ያም ማለት፦ ማይንትስ እና ዑኒዮን ቤርሊን ካሸነፉ ቦሁም በቡንደስሊጋው ለመቆየት ከታችኛው ዲቪዚዮን ሦስተኛ ደረጃ ይዞ ካጠናቀቀ ቡድን ጋ መጋጠም ግድ ሊሆንበት ነው ።
ቡንደስሊጋ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ውስጥ እነማን ቀልጠው ቀሩ?
በነገራችን ላይ ከታችኛው ዲቪዚዮን ሳንክት ፓውሊ እና ሆልሽታይን ኪል ቡድኖች አንደኛ እና ሁለተኛ በመሆን ወደ ዋናው ቡንደስ ሊጋ ማለፋቸውን አረጋግጠዋል ። በሁለተኛው ዲቪዚዮን እንደ ሐምቡርግ፤ ሻልከ፤ ኑይርንበርግ፤ ሔርታ ቤርሊን እና ሐኖቨር ያሉ የቀድሞ የቡንደስሊጋ ተፎካካሪ ቡድኖች ቀልጠው ቀርተዋል ።
አይንትራኅት ፍራንክፉርት የቀጣይ የአውሮጳ ሊግ የምድብ ተጋጣሚነት ቦታውን ላለማጣት ቅዳሜ ዕለት ላይፕትሲሽን ማሸነፍ አለያም አቻ መውጣት ይጠበቅበታል ። ሆፈንሀይም በበኩሉ፦ የአይንትራኅት ፍራንክፉርትን ቦታ ለመውሰድ ወይንም የአውሮጳ ሊግ ኮንፈረንስ የማጣሪያ ተወዳዳሪነት ቦታውን በፍራይቡርግ ላለመነጠቅ ከባዬርን ሙይንሽን ጋ የሞት ሽረት ግጥሚያ ያደርጋል ። የቅዳሜው ግጥሚያ በአንጻሩ ለባዬርን ሙይንሽን የሚቀይረው ነገር የለም ። እንደ መሪው ባዬርን ሌቨርኩሰን፤ ሽቱትጋርት፤ ላይፕትሲሽ እና ቦሩስያ ዶርትሙንድ የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊነቱ እንደተጠበቀ ነው ። ይህም በመሆኑ ቅዳሜ የሚጠናቀቀው ቡንደስሊጋ ግጥሚያዎች በመውረድ እና በመዋዠቅ መካከል የሚደረጉ በመሆናቸው እጅግ አጓጊ ናቸው ።
በሴቶች የጀርመን እግር ኳስ ፍጻሜ ቮልፍስቡርግ ባዬርን ሙይንሽንን አሸንፎ ዋንጫቻውን ለዐሥረኛ ጊዜ መውሰድ ችሏል ። ቮልፍስቡርግ ባዬርን ሙይንሽንን 2 ለ0 አሸንፎ ዋንጫውን የወሰደው ሐሙስ ዕለት ነው ። ትናንት በነበረው የቡንደስሊጋ የወንዶች ግጥሚያ በተቃራኒው ባዬርን ሙይንሽን ቮልፍስቡርግን 2 ለ0 አሸንፏል ። ተሰናባቹ ዳርምሽታድት ትናንት በሆፈንሀይም እንደማይሆን ሆኖ ተሸንፏል፥ 6 ለ0 ።
ኬሊያን ምባፔ
የፓሪ ሳንሳንጃርሞ አጥቂ ኬሊያን ምባፔ ወደ ስፔኑ ሪያል ማድሪድ ሊዛወር እንደሆነ እየተነገረ ነው ። ኬሊያን ምባፔ ባለፈው ዐርብ ከፓሪ ሳንጃርሞ እንደሚለቅቅ ካሳወቀ በኋላ ወደ የትኛው ቡድን እንደሚሄድ የታወቀ ነገር አልነበረም ። አሁን ግን ፈረንሣዊው አጥቂ ወደ ስፔኑ ሪያል ማድሪድ ማቅናቱ የማይቀር መሆኑ ተዘግቧል፥ የሚጠበቀው መቼ የሚለው ነው ።
በፈረንሣይ ሊግ አንድ ፓሪ ሳንጃርሞ እሁድ ከቱሉዝ ጋ በተጫወተበት ወቅት የቡድኑ ደጋፊዎች ለኬሊያን ምባፔ አድናቆታቸውን ገልጠውለታል ። «ከፓሪስ ከተማ መዳረሻ ልጅነት የፓሪ ሳንጃርሞ ዝነኛው ወሳኝ ሰው ሆነሀል» ሲሉም አወድሰውታል ። ያደነቁትን ያህልም ትናንት ጨዋታው ሲጀመር እና የኬሊያን ምባፔ ስም ሲጠራ በፉጨት ተቃውሟቸውን የገለጡም ነበሩ ። በትናንቱ ግጥሚያ ምንም እንኳን ኬሊያን ምባፔ ጨዋታው በተጀመረ በስምንተኛው ደቂቃ ላይ ብቸኛዋን ግብ ለፒኤስጂ ቢያስቆጥርም፥ ቱሉዝ ሦስት ለአንድ ማሸነፍ ችሏል ።
በፈረንሣይ ሊግ በ70 ነጥብ እየመራ ዋንጫውን መውሰዱን ቀደም ሲል ያረጋገጠው ፓሪ ሳንጃርሞ፥ ባለፈው ሳምንት ከአውሮጳ ሻፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ መሰናበቱ ይታወሳል ። በግማሽ ፍጻሜ ውድድሩ የፈረንሣዩ ፓሪ ሳን ጃርሞን 1 ለ0 አሸንፎ በደርሶ መልስ የ2 ለ0 ውጤት ያሰናበተው የጀርመኑ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ነው ።
ቦሩስያ ዶርትሙንድ እንግሊዝ ዌብሌይ ስታዲየም ውስጥ ግንቦት 24 በሚካሄደው የፍጻሜ ውድድር የስፔኑ ሪያል ማድሪድን ይገጥማል ። ኬሊያን ምባፔን ሊወስድ ነው የተባለው ሪያል በሜዳው ሳንቲያጎ ቤርናቤዉ ባዬርን ሙይንሽንን ገጥሞ ሁለት ለአንድ በማሸነፍ ነው ለፍጻሜ የበቃው ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ታምራት ዲንሳ