የጀርመን ገበሬዎች የአንድ ሣምንት ተቃውሞ ለምን ተቀሰቀሰ?
ረቡዕ፣ ጥር 1 2016የጀርመን መንግሥት ለግብርና ሥራዎች ይሰጥ የነበረውን ድጎማ ለማቋረጥ በደረሰበት ውሳኔ የተበሳጩ ገበሬዎች የአንድ ሣምንት ተቃውሟቸውን ባለፈው ሰኞ ጀምረዋል። በተቃውሞው መንገዶች፣ የፍጥነት አውራ ጎዳናዎች በአንዳንድ ቦታዎች የባቡር መስመሮች ጭምር እስከ መዘጋት ደርሰው ነበር። ተቃውሟቸውን እስከ አካባቢያዊ ምክር ቤቶች ደጃፍ የወሰዱ ገበሬዎችም ነበሩ።
በርሊን፣ ሐምቡርግ፣ ኮሎኝ እና ብሬመንን በመሳሰሉ ከተሞች በተካሔዱ ተቃውሞዎች በእያንዳንዳቸው እስከ 2,000 የሚደርሱ ትራክተሮች መሳተፋቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል። በባደን ቩርተንበርግ ግዛት በተደረጉ 270 ተቃውሞዎች 25,000 ገደማ ተሽከርካሪዎች መሳተፋቸውን በሽቱትጋርት የሚገኘው የግዛቲቱ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
የጀርመን ገበሬዎች መንግሥትን በመቃወም አድማ መቱ
የጀርመን ገበሬዎች ለግብርና ሥራ ናፍጣ ሲሸምቱ ለሚከፍሉት ታክስ ከመንግሥት ማካካሻ ይሰጣቸዋል። የእርሻ ተሽከርካሪዎች ሲገዙም ግብር አይከፍሉም። ትራክተር እያሽከረከሩ ለተቃውሞ ከወጡ ገበሬዎች አንዱ ፒተር ካይም ናቸው። ከበርሊን በስተምዕራብ በሐፈላንድ በሚገኘው እርሻቸው ፒተር ካይም የሚጠቀሙባቸው ማሽኖች በሙሉ በናፍጣ የሚሰሩ ናቸው።
ካይም እና ሠራተኞቻቸው የሚያስተዳድሩት የቤተሰብ የእርሻ ሥራ በ1,000 ሔክታር መሬት ላይ የሚከወን ነው። 170 የወተት ላሞችም ያረባሉ። ካይም እንደሚሉት አምስት ትራክተሮቻቸውን ናፍጣ ለመሙላት የሚያወጡት ወጪ በጣም ውድ ነው። ትራክተሮቻቸው እያንዳንዳቸው 480 ሊትር ናፍጣ የሚጭን ታንከር አላቸው። እስካሁን በነበረው አሠራር አንድ ሊትር ናፍጣ ሲሸምቱ ከመንግሥት 21 ሣንቲም ተመላሽ ይደረግላቸዋል።
ፒተር ካይም “በዓመት 120,000 ሊትር ናፍጣ ለግብርና ሥራ እንጠቀማለን። ለግብርና ሥራዎች ጥቅም ላይ ለሚውለው ናፍጣ በሊትር 21 ሣንቲም ይመለሳል ማለት እኛ 25,000 ዩሮ እናገኛለን” ሲሉ ተናግረዋል።
ይህ እስካሁን ገቢራዊ ሲሆን የቆየ አሰራር ግን ቀስ በቀስ እንዲቋረጥ የጀርመን መንግሥት ወስኗል። ኦላፍ ሾልስ የሚመሩት ጥምር መንግሥት ድጎማዎቹን በአንድ ጊዜ የማንሳት ዕቅድ የነበረው ቢሆንም ባለፈው ወር ከታዩ የገበሬ ተቃውሞች በኋላ ውሳኔውን ለማጠፍ ተገድዷል።
የነዳጅ ድጎማ ማሻሻያ ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሐብት ምን ይዞ ይመጣል?
መንግሥት መጀመሪያ ከነበረው ዕቅድ ቢያፈገፍግም እንደ ፒተር ካይም ያሉ ገበሬዎች ግን ደስተኛ አይደሉም። “ተፅዕኖው በጣም ከባድ ስለሆነ መቃወም አለብኝ። የታቀደው ሕግ ተግባራዊ ከሆነ የድጎማው መነሳት በእውነት ለእኛ ከባድ ይሆንብናል” ሲሉ ገልጸዋል።
ጀርመን በአጠቃላይ 250,000 ገደማ ገበሬዎች አሏት። የሐፈላንድ ገበሬዎች አብዛኞቹ በዚህ አንድ ሣምንት ውስጥ ተቃውሟቸውን እንደሚቀጥሉ ተስፋ ያደርጋሉ። ለተቃውሞ አደባባይ የወጡት አንጀ ሹልዝ “ሥራችንን ለማካሔድ ምን ያክል ከባድ እንደሆነ በቤተሰባችን አይቼዋለሁ። ጎን ለጎን ተጨማሪ ገቢ ካልተገኘ በጣም ከባድ ሆኗል” ብለዋል።
የጀርመን ገበሬዎች በዓመት በአንድ ሔክታር 300 ዩሮ ገደማ የቀጥታ ክፍያ ከአውሮፓ ኅብረት ያገኛሉ። የግብርና ድጎማ ቢነሳ እንኳ አልፎንስ ባልማን እንደሚሉት የጀርመን ገበሬዎች የሚቀርባቸው ከአጠቃላይ ድጎማ 5 በመቶ ብቻ ነው። በሌይቢኒትዝ ኢንስቲትዩት የግብርና ኤኮኖሚ ተመራማሪው አልፎንስ ባልማን በግብርናው ዘርፍ ለናፍጣ የሚደረገው ድጎማ ጊዜው ያለፈበት ነው የሚል አቋም አላቸው።
አልፎንስ ባልማን “የድጎማውን መነሳት የግብርና ሥራዎች ሊቋቋሙት የሚችሉት ነው። ባለፉት ዓመታት ገበሬዎች ጥሩ ገቢ አግኝተዋል። ከዚህ በተጨማሪ በሐብታቸውን ጠንካሮች ናቸው። ስለዚህ የሚገጥማቸውን ተግዳሮት ሊቋቋሙት ይችላሉ” ብለዋል።
ኦላፍ ሾልስ የሚመሩት ጥምር መንግሥት ለግብርና ሥራዎች የሚሰጠውን ድጎማ ለማንሳት የወሰነው በ2014 በጀት ውስጥ በተፈጠረ 17 ቢሊዮን ዩሮ ጉድለት ምክንያት ነው። ይኸ ድጎማ ማቋረጥን የሚጨምር የበጀት ማሻሻያ የጀርመን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባሳለፈው ውሳኔ ምክንያት የተፈጠረ ነው።
የኦላፍ ሾልስ መንግሥት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያሳደረውን ተጽዕኖ ለመቋቋም የተመደበ 60 ቢሊዮን ዩሮ የከባቢ አየር ለውጥን ለመቋቋም እና ሀገሪቱን ለማዘመን ሥራዎች የመጠቀም ፍላጎት የነበረው ቢሆንም ዕቅዱ በጀርመን ሕገ-መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ውድቅ ሆኖበታል።
ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ያስተላለፈው ጀርመን የበጀት ጉድለትን ለመቆጣጠር በምትከተለው ጥብቅ መርኅ ምክንያት ነው። በሕጉ መሠረት የበጀት ጉድለቱ ከ0.35 በመቶ መብለጥ አይችልም። በሀገሪቱ ሕገ-መንግሥት መሠረት መንግሥት ሥራውን በሚያገኘው ገቢ ማከናወን አለበት። በመንግሥት ላይ የተጣለው የበጀት ጉድለት ገደብ ሊነሳ የሚችለው እጅግ አስገዳጅ ሁኔታ ሲፈጠር ብቻ ነው።
ፍርድ ቤቱ ካሳለፈው ውሳኔ በኋላ የተፈጠረው 17 ቢሊዮን ዩሮ ወይም 19 ቢሊዮን ዶላር የበጀት ክፍተት እንዴት መሙላት ይቻላል የሚለው ክርክር አወዛጋቢ ሆኖ ቆይቷል። እንዲያም ሆኖ የሀገሪቱ በጀት ባለፈው ሳምንት መጽደቁን የመንግሥት ቃል አቀባይ ተናግረዋል።
አዲስ የጸደቀው በጀት ለግብርናው ዘርፍ ይደረግ የነበረውን ድጎማ በሒደት እንዲቋረጥ የሚያደርግ ነው። በዚህም መሠረት በተያዘው የጎርጎሮሳዊው 2024 በጀት ዓመት ድጎማው በ40 በመቶ ይቀንሳል። በሚቀጥለው ዓመት በ30 በመቶ ሊቀነስ የታቀደ ሲሆን በጎርጎሮሳዊው 2026 ሙሉ በሙሉ ይነሳል።
ለግብርና ሥራዎች ይሰጥ የነበረው ድጎማ መቋረጥ በቀጥታ በገበሬዎች ላይ ተጽዕኖ ማሳደር የሚጀምረው በጎርጎሮሳዊው 2025 ነበር። ምክንያቱም ገበሬዎች ናፍጣ ሲገዙ ለከፈሉት ታክስ የሚሰጠው ድጎማ የሚደርሳቸው ሁልጊዜም በሚቀጥለው ዓመት ነው።
የጀርመን የፋይናንስ ሚኒስቴር በ2025 በድጎማው መቋረጥ 142 ሚሊዮን ዩሮ ተጨማሪ ገቢ ይገኛል ብሎ ይጠብቃል። የገቢ መጠኑ በ2026 ወደ 285 ሚሊዮን ዩሮ እንዲሁም በ2027 ደግሞ ወደ 419 ሚሊዮን ዩሮ ከፍ ይላል። ከ2028 በኋላ በየዓመቱ 453 ሚሊዮን ዩሮ ተጨማሪ ገቢ ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።
የጀርመን መንግሥት ከግብርና በተጨማሪ ከአየር ትራፊክ ታክስ እና በማኅበራዊ ድጎማ ላይ በሚደረግ ጥብቅ ቁጥጥር ተጨማሪ ገቢ የማግኘት ዕቅድ አለው። በጎርጎሮሳዊው 2024 ብቻ ከከፍተኛ የአየር ትራፊክ ታክስ 445 ሚሊዮን ዩሮ ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል። በማኅበራዊ ድጎማ ላይ በሚደረግ ጥብቅ ቁጥጥር 170 ሚሊዮን ዩሮ ለማዳን መታቀዱን ሬውተርስ የመንግሥትን ሰነድ ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
ለአንድ ሣምንት የሚዘልቀውን ተቃውሞ የጠራው የጀርመን የገበሬዎች ማኅበር መንግሥት ባደረገው ማሻሻያ ደስተኛ አይደለም። ማኅበሩ ድጎማ የሚያስቀረው የበጀት ማሻሻያ ሙሉ በሙሉ እንዲቀር ይሻል።
“በወጪ ጫና ምክንያት እኛ የጀርመን መንግሥት ለገበሬዎች መልካም ፈቃዳችንን አሳይተናል። ውይይት የተደረገባቸው የድጎማው አስፈላጊ ክፍሎች ማለትም የግብርና ተሽከርካሪዎች የታክስ እፎይታ እና የግብርና ናፍጣ ድጎማ ቀስ በቀስ የማንሳቱ ሒደት ባሉበት እንዲቆዩ እናደርጋለን። በዚህ መንገድ የተሻለ ፍትኃዊ ይሆናል” ሲሉ የጀርመን የኤኮኖሚ ሚኒስትር ሮበርት ሐቤክ ተናግረዋል።
ዕዳ መክፈል ከተሳናቸው ሀገራት ጎራ የተመደበችው ኢትዮጵያ ከቦንድ ባለቤቶች እየተደራደረች ነው
“ይሁንና ሁሉንም መተው አንችልም” ያሉት ሐቤክ “በሕገ-መንግሥታዊው ፍርድ ቤት ውሳኔ ምክንያት የወጪ ቁጠባ ጫናው አለ። በቢሊዮን ዩሮዎች ለመቆጠብ ተገደናል” በማለት የማሻሻያውን አስፈላጊነት አስረድተዋል።
የገበሬዎቹ ተቃውሞ ግን በአክራሪዎች ሊጠለፍ ይችላል የሚል ሥጋት በጀርመን ባለሥልጣናት ዘንድ አለ። የጀርመን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ናንሲ ፌዘር ቃል አቀባይ “ቀኝ አክራሪዎች እና ሌሎች የዴሞክራሲ ጠላቶች ተቃውሞዎቹን ሰርስሮ ለመግባት እና መሳሪያ ለማድረግ እየሞከሩ ነው” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ቀኝ ክራሪ ቡድኖች አጠቃላይ የሥራ ማቆም አድማ እንዲደረግ የማነሳሳት ፍላጎት አላቸው የሚል ዕምነት በሀገሪቱ የፌድራል ፖሊስ ዘንድ እንዳለ የገለጹት የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ መንግሥትን ለመገልበጥ ግርግር መፍጠር እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የወጪ ቅነሳ እና ቁጠባ ሥርዓት መመሪያ
በሰሜን ጀርመን ለመዝናናት ይጓዙበት ከነበረ ጀልባ እንዳይወርዱ ከ250 እስከ 300 በሚሆኑ ተቃዋሚዎች የተከለከሉት ምክትል መራኄ መንግሥት ሮበርት ሐቤክም ተመሳሳይ ሥጋታቸውን ገልጸዋል። የጀርመን የኤኮኖሚ ሚኒስትር ጭምር የሆኑት ሐቤክ የደረሰባቸው ኩነት በሀገሪቱ ፖለቲካዊ ክርክር ፈር ለቋል የሚል ሥጋት አጭሯል። ከተቃዋሚዎቹ እስካሁን አንድም ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር ባይውልም ፖሊስ በጉዳዩ ላይ ምርመራ መጀመሩን አስታውቋል።
የጀርመን ምክትል መራኄ መንግሥት እና የኤኮኖሚ ሚኒስትሩ ሮበርት ሐቤክ "የመፈንቅለ-መንግሥት ናፋቂዎች ጥሪ እየተዘዋወረ ነው። አክራሪ ቡድኖች እየተመሠረቱ የብሔርተኞች ምልክቶችም በአደባባይ እየታዩ ነው” በማለት በይፋ አስጠንቅቀዋል። “የሕጋዊ፣ ዴሞክራሲያዊ ተቃውሞ እና ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት ድንበሮች ባለፉት ዓመታት ተሸርሽረው ከዚህ ቀደም የማይነገር የነበረው ትክክል ሆኖ መታየት የጀመረ ይመስላል” ሲሉ ሮበርት ሐቤክ ሥጋታቸውን ገልጸዋል።
እሸቴ በቀለ
ማንተጋፍቶት ስለሺ