የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የወጪ ቅነሳ እና ቁጠባ ሥርዓት መመሪያ
ሐሙስ፣ መስከረም 26 2015የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሥራ ላይ ያዋለው የወጪ ቅነሳ እና ቁጠባ መመሪያ የደመወዝ አከፋፈል እና የሠራተኛ ቅጥርን ጨምሮ በመንግሥት ተቋማት በርካታ የበጀት አጠቃቀም ጉዳዮች ላይ ጠበቅ ያሉ ገደቦች እና ክልከላዎች ያስቀመጠ ነው። መመሪያው ክልሉ ያለውን "ውስን ገንዘብ" በቁጠባ በመጠቀም የተሻለ የልማት ሥራ ላይ ማዋል በማስፈለጉ የተዘጋጀ እንደሆነ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የገንዘብ እና ኤኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዚያድ አብዱላሒ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ኃላፊው እንደሚሉት በዚህ ልዩ የወጪ ቅነሳ እና ቁጠባ ሥርዓት መመሪያ ከክልሉ መንግሥት የ2015 ወጪ ከ20 በመቶ በላይ የሚሆነውን የማዳን ውጥን አለ።
መመሪያው አቶ ዚያድ በሚመሩት የገንዘብ እና ኤኮኖሚ ልማት ቢሮ ተዘጋጅቶ ለክልሉ ካቢኔ ከቀረበ በኋላ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሐሰን ፊርማ የጸደቀ ነው። ከዚህ ቀደም "በሕግ የሚፈቀዱ ነገር ግን ከፍተኛ ወጪ ሊያስወጡ የሚችሉ ጉዳዮች" ተለይተው በአዲሱ መመሪያ ገደብ አልያም ክልከላ እንደተደረገባቸው አቶ ዚያድ ያስረዳሉ።
መመሪያው ገደብ ከጣለባቸው ጉዳዮች መካከል የቋሚ እና የዉል ሠራተኛ ቅጥር ይገኝበታል። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከ48 ሺሕ በላይ ሠራተና መኖሩን ለዶይቼ ቬለ የተናገሩት አቶ ዚያድ "ለሥራ ማስኬጃ እና ለደመወዝ የምናውለው ከፍተኛ ወጪ እያስወጣን ነው" ሲሉ ጫናውን ገልጸዋል። በዚህም መሠረት "ቀደም ተብሎ በጀት እንዲያዝ ለገንዘብ እና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ፣ መምሪያ ወይም ጽህፈት ቤት ጥያቄ ቀርቦ" ፈቃድ ከተሰጠው በስተቀር አዲስ ሠራተኛ መቅጠር እንደማይቻል" መመሪያው ይደነግጋል። ከክልሉ መንግሥት ውሳኔ ውጪ አዲስ የሥራ መደብ መክፈት፣ ሠራተኛ መቅጠርም በመመሪያው ተከልክሏል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል "በየደረጃው ባለው መዋቅር በየበጀት ዓመቱ ለረጅም የትምህርት ዕድል የሚወጣ ወጪ ከፍተኛ" መሆኑን የጠቀሰው ይኸው መመሪያ በ2015 ግን የክልሉን የበጀት አቅም እና ወጪ ቅነሳና ቁጠባ ያማከለ መሆን" እንደሚገባው አስቀምጧል። በክልሉ የሚገኙ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች "ከተያዘላቸው በጀት በላይ ወጪ ማድረግ ወይም በጀት ሳይጸድቅ በታሳቢ እየተባለ ከፍተኛ ወጪ" መፈጸምን ከልክሏል። ለሥራ ማስኬጃ የተመደበ በጀት ወደ ደመወዝ ማዘዋወርም ተከልክሏል። ተቋማቱ መመሪያው ሥራ ላይ ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞችን በራሳቸው አጽድቀው ክፍያ መፈጸም አይችሉም።
መመሪያው በተሽከርካሪ ጥገና፣ የመኪና ፣ የነዳጅ፣ የቅባት አጠቃቀሞች ላይ ገደቦች አበጅቷል። የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እና ምክትል ርዕሰ መስተዳድርን ጨምሮ "ኮር" የተባሉ አመራሮች፣ የጸጥታ እና የፖሊስ ኮሚሽን የስራ ኃላፊዎች፤ በከተማ ውስጥ ለሚኖራቸው እንቅስቃሴ እስከ 150 ሊትር ነዳጅ እንዲጠቀሙ በመመሪያው ተፈቅዶላቸዋል። ሌሎች የበላይ ኃላፊዎች ለሚያደርጓቸው ተመሳሳይ ጉዞዎች በወር 70 ሊትር ነዳጅ መፈቀዱን የሚገልጸው መመሪያው፤ ከዚያ በላይ ለሚደረግ እንቅስቃሴ ግን ኃላፊዎች ወጪውን ራሳቸው እንደሚሸፍኑ ደንግጓል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እና ምክትል ርዕሰ መስተዳድርን ጨምሮ ኮር ተብለው በመመሪያ ከተጠቀሱት አመራሮች ውጪ ያሉ ሹማምንት ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዉጪ ሲጓዙ አውሮፕላን እና የመንግሥት ተሽከርካሪ በጥምረት መጠቀም ተከልክለዋል። በክልሉ የሚካሔዱ ሥልጠናዎች በየመንግሥት ተቋማቱ የመሰብሰቢያ አዳራሾች እና ማዕከላት ብቻ እንዲካሔዱ በማድረግ የኪራይ ክፍያ መቅረት እንዳለበትም መመሪያው ይደነግጋል።
በመደበኛ በጀትም ሆነ ከልማት አጋሮች ወይም ባለድርሻ አካላት ጋር ለሚካሔዱ ስብሰባዎች እና ክብረ በዓላት ለተሳታፊዎች የሚሰጡ ቦርሳዎች፣ ቲ-ሸርቶች፣ ኮፍያዎች እና ሻርፖች መግዛትን የክልሉ መንግሥት መመሪያ ከልክሏል። በመመሪያው እንደሰፈረው "የክህሎት ስልጠና ካልሆነ በስተቀር ከሶስት ቀናት በታች ለሆኑ ስልጠናዎች እና የውይይት መድረኮች የማስታወሻ ደብተር እና ስክሪብቶ ግዥ ማከናወን አይቻልም።"
የቢሮ ኪራይ ሌላው የክልሉን መንግሥት ለከፍተኛ ወጪ የዳረገ ጉዳይ እንደሆነ በመመሪያው ሰፍሯል። "በቀላል ወጪ ተጠግኖ አገልግሎት መስጠት የሚችሉ የመንግሥት ተቋማትን ማፈላለግ፤ ካልሆነ በሒደት በቀላል ወጪ ማለቅ የሚችሉ ግንባታዎች በመንግሥት ግዢ ሥርዓት መሠረት ማከናወን" እንደሚገባ መመሪያው ያሳስባል። አዲስ ከሚሾሙ እና በልዩ ሁኔታ ከሚፈቀድላቸው በስተቀር በመመሪያው እንደሰፈረው በ2015 በክልሉ ላፕቶፕ፣ ሞባይል እንዲሁም ተንቀሳቃሽ የኢንተርኔት ራውተር መግዛት አይቻልም። አቶ ዚያድ አብዱላሒ የክልሉ ተቋማት ወርኃዊ ወጪ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የገንዘብ እና ኤኮኖሚ ልማት ቢሮ ሲለቀቅ ከዚህ በኋላ ከመመሪያው ጋር እየተመሳከረ እንደሚሆን ገልጸዋል።
ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የገንዘብ እና ኤኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዚያድ አብዱላሒ ጋር የተደረገውን ቃለመጠይቅ ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ
እሸቴ በቀለ