1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የነዳጅ ድጎማ ማሻሻያ ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሐብት ምን ይዞ ይመጣል?

እሑድ፣ ሐምሌ 10 2014

የነዳጅ ድጎማ ብቻውን ኢትዮጵያን ከ146.6 ቢሊዮን ብር በላይ ለሆነ የበጀት ጉድለት እንደዳረጋት መንግሥት አስታውቋል። የነዳጅ ድጎማውን በሒደት የሚያነሳ ማሻሻያ መንግሥት ገቢራዊ እያደረገ ነው። ማሻሻያው ጦርነት፣ ድርቅና የዋጋ ግሽበት ለተጫነው ምጣኔ ሐብት ምን ይዞ ይመጣል? ደሐውን የማኅበረሰብ ክፍል ከዳፋው እንዴት መታደግ ይቻላል?

https://p.dw.com/p/4EDc7
Dschibuti Tankwagen
ምስል Getty Images/S. Gallup

እንወያይ፦ የነዳጅ ድጎማ ማሻሻያ ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሐብት ምን ይዞ ይመጣል?

የኢትዮጵያ መንግሥት የነዳጅ ድጎማ ማሻሻያ ከዚህ ወር ጀምሮ ተግባራዊ ሲያደርግ አንድ ሊትር ቤንዚን ከሰኔ 1 እስከ ሰኔ 30 ቀን 2014 ከሚሸጥበት 36 ብር ከ87 ሳንቲም ወደ 47 ብር ከ83 ሳንቲም አሻቅቧል። ልዩነቱ 10 ብር ከ96 ሳንቲም ነው። የኢትዮጵያ ንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር እንደሚለው በሰኔ 2014 ነዳጅ በዓለም ገበያ በሚሸጥበት ዋጋ ተሰልቶ ለኢትዮጵያ ሸማቾች ቢቀርብ ኖሮ አንድ ሊትር ቤንዚን 82 ብር በደረሰ ነበር። በአዲሱ የዋጋ ተመን ነጭ ናፍጣ እና ኬሮሲን ከአስራ ሶስት ብር በላይ ጭማሪ አሳይተው በሊትር ወደ 49 ብር ገብተዋል። 

ማሻሻያው ተግባራዊ ሲሆን ኢትዮጵያ "ያለችበትን ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ" በዓለም ገበያ ነዳጅ በሚሸጥበት ተመን እና በአገሪቱ የችርቻሮ መሸጫ መካከል ካለው ልዩነት 75 በመቶውን መንግሥት ሲሸፍን 25 በመቶው ለተጠቃሚው መተላለፉን የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ደብዳቤ ያሳያል። 

ኢትዮጵያ በዘርፉ የድጎማ ፖሊሲ ባይኖራትም በነዳጅ ዋጋ ማረጋጊያ ፈንድ በኩል "በዓለም ገበያ በሚከሰተው የነዳጅ ዋጋ ማደግ ምክንያት የሚያስፈልገውን ወጪ በመደጎም" የማረጋጋት ሥራ ስታከናውን ቆይታለች። የነዳጅ ዋጋ ማረጋጊያ ፈንድ ዋንኛ የገቢ ምንጭ "በዓለም ገበያ የነዳጅ ዋጋ በመቀነሱ ምክንያት ከሚገኝ ተራፊ ሂሣብ" ነበር። ይሁንና በዓለም ገበያ የነዳጅ ዋጋ በመጨመሩ "በነዳጅ ማረጋጊያ ፈንድ ላይ በወር በአማካይ ወደ ተጠቃሚው መተላለፍ የነበረበት 10 ቢሊዮን ብር ጉድለት" እንደገጠመው የኢትዮጵያ የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቋል። በመሥሪያ ቤቱ መረጃ መሠረት በዚህ የዋጋ ልዩነት ምክንያት የዕዳው መጠን ከ146 ቢሊዮን 624 ሚሊዮን ብር በላይ ሆኗል። 

ይኸ የውይይት መሰናዶ የኢትዮጵያ መንግሥት ተግባራዊ ማድረግ የጀመረውን የነዳጅ ድጎማ ማሻሻያ እና በገበያው የሚኖረውን አንድምታ ይፈትሻል። የኢትዮጵያን ኤኮኖሚ በቅርበት የሚከታተሉት የፋይናንስ ባለሙያው አቶ አብዱልመናን መሐመድ፣ በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የኤኮኖሚክስ መምህሩ አቶ ሐብታሙ ግርማ እና በብሪታኒያው የልማት ጥናት ኢንስቲትዩት ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ቀልቤሳ መገርሳ በውይይቱ ተሳትፈዋል። የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴርን ጨምሮ ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው የኢትዮጵያ ተቋማት ተወካዮች ለመጋበዝ የተደረገው ጥረት አልተሳካም። 

ሙሉ ውይይቱን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ 

እሸቴ በቀለ