የኮምፓክት ዊዝ አፍሪቃ ጉባኤና ስጋቶቹ
ቅዳሜ፣ ኅዳር 15 2016
የአፍሪቃ መሪዎች በዚህ ሳምንት ጀርመን ርዕሰ ከተማ በርሊን የተካሄደውን የቡድን ሀያ ኮምፓክት ዊዝ አፍሪቃ ጉባኤ በአፍሪቃ ብዙ መወረት አስፈላጊ መሆኑ ትኩረት እንዲያገኝ ተጠቅመውበታል ትላለች የዶጬቬለዋ ኬት ሄርሲን።በጉባኤው ላይ የተገኙት የአፍሪቃ ኅብረት የወቅቱ ሊቀ መንበር የኮሞሮሱ ፕሬዝዳንት አዛሊ ኦሱማኒ እንዳሉት በአሁኑ ጊዜ ባለጸጋዎቹ የቡድን 20 አባል ሀገራት በአፍሪቃ የሚወርቱት በኮቪድ ወቅት ከነበረው በመጠኑ ጨምሯል። ይሁንና ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት የተመዘገበው ከፍተኛ የሚባል ውረታ ላይ ግን ገና አልተጠጋም። ያኔ የቡድን ሀያ ሀገራት በአፍሪቃ የወረቱት 53 ቢሊዮን ዶላር ወይንም 48.4 ቢሊዮን ዩሮ ነበር ። ይህም በቡድኑ አባላት ባለሀብቶች እስከዛሬ ከተካሄደው ውረታ ከፍተኛው ነው።
የጀርመኑ «ኮምፓክት ዊዝ አፍሪካ» ጉባኤ እና ኢትዮጵያፕሬዝዳንት አሱማኒ ቻይና በብዛት በምትወርትበት በአፍሪቃ አውሮጶችም አዎንታዊ በሆነ ውድድር እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።ኮምፓክት ዊዝ አፍሪቃ፣ባለሀብቶች በአፍሪቃ በስፋት እንዲወርቱ የማበረታታት ዓላማ ይዞ በጎርጎሮሳዊው 2017 ዓም በጀርመን የቡድን ሀያ ፕሬዝዳንትነት ዘመን በመራኄ መንግሥት አንጌላ ሜርክል አመራር ወቅት የተጀመረ እንቅስቃሴ ነው። የቡድን ሀያ ኮምፓክት ዊዝ አፍሪቃ በምህጻሩ CwA 13 የአፍሪቃ ሀገራትን፣ የዓለም ዋና ዋና ኤኮኖሚዎችን የሚያንቀሳቅሱ የቡድን ሀያ ተወካዮችን የዓለም ባንክን የዓለም የገንዘብ ድርጅት እና የአፍሪቃ ልማት ባንክን ያቀፈ ነው። በአሁኑ ጉባኤ ከተገኙት 18 የአፍሪቃ ሀገራት መሪዎች መካከል የናይጀሪያውን ፕሬዝዳንት ቦላ ቲኑቡ፣ የኢትዮጵያውን ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ እና የሴኔጋሉ ፕሬዝዳንት ማኪ ሳሊ ይገኙበታል። በጀርመን የተካሄደ የመጀመሪያው ትልቁ የኤኮኖሚው ጉባኤ የተባለው የዚህ ሳምንቱ ስብሰባ ከቀድሞው ለውጥ የታየበት ነው ሲሉ የአፍሪቃ ኤኮኖሚ አዋቂ ሮበርት ካፔል ለዶቼቬለ ተናግረዋል።
« 800 የሚሆኑ ኩባንያዎች ተሳትፈዋል። አስር ፕሬዝዳንቶችና 30 ሚኒስትሮችም ነበሩ። የአውሮጳ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርዙላ ፎን ዴል ላየን የፈረንሳዩ ፕሬዝዳን ኢማኑኤል ማክሮና የጀርመኑ መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝም ተገኝተዋል።የ«ኮምፓክት ዊዝ አፍሪቃ »የአንድ ዓመት ጉዞ ስለዚህ በከፍተኛ ባለሥልጣናት ደረጃ ነው ጉባኤው የተካሄደው። ንግድ ላያ ያተኮሩ ሌሎች ንዑስ ዝግጅቶችም ነበሩ። ከዚህ በመነሳት ጉባኤው ከአፍሪቃ ጋር ለተጠናከረ ትብብር አዲስ ጅማሮ ነው ማለት እንችላለን።አሁን የሚቀረው ጀርመንን ጨምሮ ሌሎች የቡድን አባል ሀያ ሀገራት በአፍሪቃ ውረታቸውን ለማሳደግ በጉባኤው ላይ የተነጋገሩባቸውንና የተስማሙባቸውን ጉዳዮች ገቢራዊ ማድረግ ነው።»
የአፍሪቃ ኤኮኖሚ ጉዳዮች አዋቂው ሮበርት ካፔል እንደሚሉት የእስካሁኑ የቡድን ሀያ አባል ሀገራት ውረታ በተለይ የጀርመን በተወሰኑ የአፍሪቃ ሀገርት ላይ ብቻ ያተኮረ ነው።
«እስካሁን ጀርመን በአፍሪቃ ያን ያህል እየተንቀሳቀሰች አይደለም።የጀርመን ኩባንያዎች በንቃት የሚሳተፉት ጥቂት የአፍሪቃ ሀገራት ውስጥ ነው። ይኽውም ደቡብ አፍሪቃ እና በተለይ ሞሮኮና ቱኒዝያን በመሳሰሉ የሰሜን አፍሪቃ ሀገራት ነው። በማዕከላዊ አፍሪቃ ግን ጥቂት የጀርመን ኩባንያዎች ናቸው የሚወርቱት ።ለምሳሌ ናይጀሪያ ውስጥ 30 የጀርመን ኩባንያዎች ይገኛሉ። በደቡብ አፍሪቃ ግን ቢያንስ 400 በሀገሪቱ የወረቱ የጀርመን ኩባንያዎች አሉ። »
ቡድን ሀያ እና አፍሪቃ መቀመጫውን ለንደን ያደረገው የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ተንታኙ የቻተም ሀውስ የአፍሪቃ ፕሮግራም ክፍል ሃላፊ አሌክስ ቪነስም ይህንኑ ያጠናክራሉ።
«ጀርመን በውጭ ቀጥተኛ ውረታ ወደ አፍሪቃ ያፈሰሰችው መዋዕለ ንዋይ በጎርጎሮሳዊው 2016 እና 2020 መካከል 9.7 ቢሊዮንዶላር ነው። ይህ ከሌሎች የአውሮጳ ኅብረት አባel hg,ራትጋር ሲነጻጸር በጣም አነስተኛ ነው። ይህ ውረታ ፈረንሳይ ካፈሰሰችው መዋዕለ ንዋይ በግምሽ የሚያንስ ከብሪታንያ ጋር ሲነጻጸር ደግሞ በሦስት አምስተኛ ያነሰ ነው። አብዛኛው ትኩረት አንድ ሀገር ላይ ብቻ ነው፤ ደቡብ አፍሪቃ »
በቪነስ ግምገማ ባለፉት አስር ዓመታት የጀርመን ኩባንያዎች በአፍሪቃ የፈጠሩት የስራ እድል 30 ሺህ ብቻ ነው። ይህም በዓመት 3 ሺህ ማለት ነው።በርሳቸው እምነት የአፍሪቃ ሀገራት የአውሮጳ ተቋማት ከተፈጥሮ ሀብት በተጨማሪ በኢንዱስትሪ፣በምግብ፣በእርሻ በቱሪዝም እና በአገልግሎት ዘርፍ ኢንዱስትሪ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ እድል ይሰጡዋቸዋል። የጀርመን መራኄ መንግሥት ሾልዝ በአሁኑ ጉባኤ በአፍሪቃ ለታዳሽ ኃይል ማመንጫ ፕሪጀክቶች እስከ ጎርጎሮሳዊው 2030 አራት ቢሊዮን ዩሮ ወይም 4.4 ቢሊዮን ዶላር ለመወረት ቃል ገብተዋል።
ኬት ሄርሲን
ኂሩት መለሰ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር