ለአፍሪቃ የተነደፈው የልማት እቅድ
ማክሰኞ፣ ግንቦት 29 2009ቡድን ሀያ የሚባለው የበለጸጉ ሀገራት ስብስብ ለአፍሪቃ ልማት የነደፈው እቅድ በሚቀጥለው ሳምንት በርሊን ጀርመን ውስጥ በይፋ ይቀርባል። ለሁለት ቀናት በሚካሄደው የቡድን ሀያ እና የአፍሪቃ ጉባኤ ላይ የሚቀርበው የዚህ እቅድ ምንነት አተገባበሩ እና ፈተናዎቹ የዛሬው አውሮጳ እና ጀርመን ዝግጅታችን ትኩረት ነው። ለቅንብሩ ኂሩት መለሰ።
የዘንድሮው የቡድን ሀያ ጉባኤ አስተናጋጅ ጀርመን፣ ትኩረት ሰጥታ ከምትንቀሳቀስባቸው ጉዳዮች አንዱ እና ዋነኛው ለአፍሪቃ ልማት እገዛ ማድረግ ነው። በዚሁ መሠረት በጀርመን በቡድን ሀያ የፕሬዝዳንትነት ዘመን ባለፈው መጋቢት የቡድን ሀያ የገንዘብ ሚኒስትሮች የዓለም ባንክ የዓለም የገንዘብ ድርጅት እና የአፍሪቃ ልማት ባንክ በጋራ ለአፍሪቃ ልማት ይበጃል ያሉትን «ኮምፓክት ዊዝ አፍሪካ» የተሰኘ እቅድ ደቡባዊ ጀርመን ውስጥ ነድፈዋል። በመጪው ሳምንት ሰኞ እና ማክሰኞ በርሊን ውስጥ የሚካሄደው የቡድን ሀያ እና የአፍሪቃ ጉባኤ በክፍለ ዓለሙ የውጭ የግል መዋዕለ ንዋይ ፍሰትን ለማበረታታት እና የሥራ እድሎችንም ለመፍጠር ያስችላል በተባለው በዚህ እቅድ ላይ ይነጋገራል። አብዛኛዎቹ የአፍሪቃ ሀገራት የውጭ ባለሀብቶችን የሚስብ መሠረተ ልማት የላቸውም። ባለሀብቶች በአፍሪቃ እንዳይወርቱ እንቅፋት የሆነውን ይህን ችግር መፍታት የ«ኮምፓክት ዊዝ አፍሪካ» ሀሳብ ቅድሚያ ትኩረት መሆኑን በርሊን የሚኖሩት እና የሚሰሩት የኤኮኖሚ እድገት መምህርና ተመራማሪ እንዲሁም የኤኮኖሚ ጉዳዮች አማካሪ እና ደራሲ ዶክተር ፈቃደ በቀለ ያስረዳሉ።
በዚህ እቅድ ውስጥ ኮት ዲቯር፣ሞሮኮ ፣ሩዋንዳ ፣ሴኔጋል እና ቱኒዝያ ይሳተፋሉ። ወደፊት ሌሎች የአፍሪቃ ሀገራትም በእቅዱ እንደሚታቀፉ ተገልጿል። በእቅዱ ውስጥ የሚካፈሉት ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ከሚያበረክቱት የቴክኒክ አስተዋጽኦ በተጨማሪ የእቅዱ ተካፋይ የአፍሪቃ ሀገራትን ሁኔታ ለውጭ ባለሀብቶች በማስተዋወቅም ይሳተፋሉ። እንደ ዶክተር ፈቃዱ የዚህ እቅድ አተገባበር ሦስት መሠረታዊ ጉዳዮችን መሠረት ያደርጋል። በርካታ የውጭ ባለሀብቶች፣ሙስና በተስፋፋባቸው እና የፖለቲካ አለመረጋጋት በተከሰተባቸው የአፍሪቃ ሐገራት መዋዕለ ንዋያቸውን ከማፍሰስ እየተቆጠቡ ነው። በጎርጎሮሳውያኑ 2016 ዓም የውጭ ባለሀብቶች በአፍሪቃ ሥራ ላይ ያዋሉት ቀጥተኛ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት በ51 ቢሊዮን ዩሮ ተገቷል። ይህ በዓመቱ በሌላው ክፍለ ዓለም ከነበረው ውረታ ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ ነው። ይህ እንዲሻሻልም «ኮምፓክት ዊዝ አፍሪቃ» በተባለው እቅድ ውስጥ የሚታቀፉ የአፍሪቃ ሀገራት የውጭ ባለሀብቶችን ለመሳብ መሠረታዊ ማሻሻያዎች እና ለውጦች ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ይሁን እና የአፍሪቃ መሪዎች ለዚህ ተዘጋጅተዋል ወይ ነው ጥያቄው?
የአፍሪቃ ሀገራት የሚጠበቁባቸውን ማሻሻያዎች ተግባራዊ ማድረግ አለማድረጋቸው በጀርመን አማካይነት ለአፍሪቃ የተነደፈው የቡድን ሀያ እቅድ አተገባበር አንዱ ፈተና መሆኑ አይቀርም። ከዚህ ሌላ ዶክተር ፈቃደ እንደሚሉት እቅዱ በደንብ ያላጤናቸው ሌሎች ጉዳዮችም አሉ።
ከዚሁ ጋር ጀርመንም ሆነ የቡንድ ሀያ ሀገራት ለአፍሪቃ የነደፉት እቅድ ትኩረት የራሳቸውን ችግር ማቃለል ላይ እንጂ ለአፍሪቃ ያሰበ አይደለም ሲሉም የሚተቹ አልጠፉም።
በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ «African Predicaments & the Method of solving them effectively» ወደ አማርኛ ሲመለስ «የአፍሪቃ መሠረታዊ ችግሮች እና መፍትሄዎቻቸው»በሚል ርዕስ መጸሐፍ ያሳተሙት ዶክተር ፈቃደ በቀለ ለአፍሪቃ ልማት ዘላቂ መፍትሄ ካሏቸው መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል። የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን ሙሉውን ዝግጅት ማዳመጥ ይችላሉ።
ኂሩት መለሰ
ሸዋዬ ለገሠ