1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመናገር ነጻነት አሁንም አደጋ ላይ ነው

ሐሙስ፣ ሰኔ 15 2015

ዶይቸ ቬለ በየዓመቱ የሚያካሂደው ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን መድረክ ማክሰኞ ሰኔ 13 ቀን፣ 2015 ዓ.ም ተጠናቋል ። በሁለት ቀናቱ መድረክ ስለመናገርና ፕሬስ ነጻነት ብሎም የተለያዩ የመገናኛ አውታርን የሚዳስሱ ጉዳዮች ለውይይት ቀርበዋል ። የዶይቸ ቬለ የመናገር ነጻነት የዘንድሮ ሽልማት ለኤልሣልቫዶራዊው ጋዜጠኛ ኦስካር ማርቲኔዝ ተሰጥቷል ።

https://p.dw.com/p/4StoM
GMF 2023 | Plenarsaal
ምስል Florian Goerner/DW

ኤልሣልቫዶራዊው ጋዜጠኛ ኦስካር ማርቲኔዝ ቦን ከተማ ተገኝቶ ሽልማቱን ወስዷል

እንደ ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን ዘገባ ከሆነ በዓለማችን ዘንድሮ ከምንጊዜውም በላይ በርካታ ጋዜጠኞች እስር ቤት ውስጥ ይገኛሉ ። እንዲያም ሆኖ ግን ጋዜጠኞች በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ራሳቸውን ለአደጋ አጋልጠው ለመገናኛ ብዙኃን ነጻነት ይፋለማሉ ። ከእነዚህ ደፋር ጋዜጠኞች መካከል አንዱ የመናገር ነጻነት ሽልማትን በዶይቸ ቬለ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን መድረክ ላይ ተገኝቶ ተቀብሏል ።

የዶይቸ ቬለ የመናገር ነጻነት የዘንድሮ ሽልማት
የዶይቸ ቬለ የመናገር ነጻነት የዘንድሮ ሽልማትምስል Bjorn Kietzmann/DW

የዶይቸ ቬለ የመናገር ነጻነት የዘንድሮ ሽልማት ለኤል ፋሮ ድረገጽ ዋና አርታኢ ኤልሣልቫዶራዊው ጋዜጠኛ ኦስካር ማርቲኔዝሰኞ ሰኔ 12 ቀን፣ 2015 ዓ.ም ቦን ከተማ ውስጥ ተሰጥቷል ። ኦስካር ማርቲኔዝ በዶይቸ ቬለ 16ኛዉ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን መድረክ ላይ ለመናገር ነጻነት 9ኛው ሽልማት የበቃው በሰብአዊ መብቶች በተለይም በመናገር ነጻነት ላይ ላበረከተው አስተዋጽኦ ነው ተብሏል ። የምርምር ጋዜጠኛው ኦስካር የጋዜጠኝነት ጉዞው በሀገሩ እጅግ አስቸጋሪ መሆኑን ሽልማቱን በተቀበለበት ወቅት ተናግሯል ።

«ወደዚህ የመጣሁባት እና ይህን ሽልማትም ተቀብዬ የምሄድባት ኤልሣልቫዶር ሙሉ ለሙሉ ወደ አምባገነን አመራር እያመራች ነው ። ዴሞክራሲ የሚባል የለም ። በኤል ፋሮ የዜና ድረገጼ ላይ ብቻ እኔን ጨምሮ 22 ሰዎች ፕሬዚደንቱ ከወንጀለኛ ቡድኖች ጋር ምሥጢራዊ ስምምነት ስለማድረጋቸው መረጃዎችን በምናሰባስብበት ወቅት ዒላማ ውስጥ ገብተን ነበር ። »

የዶይቸ ቬለ ዋና ኃላፊ ኢንቴንዳንት ፒተር ሊምቡርግ በበኩላቸው፦ «የመናገር ነጻነት ኤል ሣልቫዶር ውስጥ አደጋ ተጋርጦበታል ። ጋዜጠኝነትን ተአማኒ ማድረግ ከምንም በላይ ጠቃሚ ነው» ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል ። 

ጋዜጠኞች አፍሪቃ፤ አውሮጳ፤ እስያ ብሎም አሜሪካን ጨምሮ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች አሁንም ለእስር እና እንግልት እየተዳረጉ ነው ። ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን ዘንድሮ ይፋ ባደረገው የዓለም የፕሬስ ነጻነት ዘገባ መሠረት ከ180 ሃገራት መካከል 21ኛ ደረጃ ላይ በምትገኘው ጀርመን ሳይቀር ጋዜጠኞች ለተለያዩ እንግልቶች እና እስር እንደሚዳረጉ ይነገራል ። የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚንሥትር አናሌና ባኤርቦክ በዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን መድረኩ ላይ በተንቀሳቃሽ ምስል ባስተላለፉት መልእክት ይህንኑ አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል ። 

የዶይቸ ቬለ የመናገር ነጻነት የዘንድሮ ሽልማትን ኤልሣልቫዶራዊው ጋዜጠኛ ኦስካር ማርቲኔዝ ቦን ከተማ ውስጥ ተቀብሎ
የዶይቸ ቬለ የመናገር ነጻነት የዘንድሮ ሽልማትን ኤልሣልቫዶራዊው ጋዜጠኛ ኦስካር ማርቲኔዝ ቦን ከተማ ውስጥ ተቀብሎምስል Florian Goerner/DW

«እንዳለመታደል ሆኖ በሀገራችን ጥቂት የማይባሉ ዘጋቢዎችን የሚተናኮሉ ድርጊቶችን ተመልክተናል ። በተለይ ደግሞ በሰላማዊ ሰልፎች ወቅት ።»

የዶይቸ ቬለ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን መድረክ የፕሬስ እና የመናገር ነጻነት በመላው ዓለም እንዲጎለብት ጥናቶች የሚቀርቡበት፤ ውይይቶችም የሚስተናገዱበትም ነው ።

ለሁለት ቀናት በቆየውየዶይቸ ቬለ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን መድረክ ከሁለት ሺህ በላይ ታዳሚዎች ተገኝተውበታል ። ከ140 በላይ ተናጋሪዎች ሐሳባቸውን መድረኩ ላይ አንጸባርቀዋል ። ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ120 በላይ ሃገራት ተወካዮች በጉባኤው ታድመዋል ። መሰል የውይይት መድረክ በዘንድሮው የድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን የፕሬስ ነጻነት ደረጃ ሲንጋፖርን ከፊት አስቀድማ ርዋንዳን ከኋላ አስከትላ 130ኛ ደረጃ ላይ ለምትገኘው ኢትዮጵያ እንዲሁም ለበርካታ ሃገራት ጠቀሜታው የጎላ ነው ።

የዶይቸ ቬለ ዋና ኃላፊ ኢንቴንዳንት ፒተር ሊምቡርግ (ከመሀል) ለተሸላሚው ጋዜጠኛ እያጨበጨቡ
የዶይቸ ቬለ ዋና ኃላፊ ኢንቴንዳንት ፒተር ሊምቡርግ (ከመሀል) ለተሸላሚው ጋዜጠኛ እያጨበጨቡምስል Rosa Muñoz/DW

በዶይቸ ቬለ ዋና ኃላፊ ፒተር ሊምቡርግ ንግግር ሰኞ ጠዋት ተከፍቶ ለሁለት ቀናት የቆየው መድረክ ማክሰኞ ከሰአት ተጠናቋል ። ማምሻውንም በራይን ወንዝ ላይ በምትቀዝፍ መርከብ ላይ ለታዳሚዎች በተደረገ የእራት እና የሙዚቃ ግብዣ ታዳሚዎች የዓመት ሰው ይበለን ብለው ተለያይተዋል ። የዶይቸ ቬለ 17ኛዉ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን መድረክ የሚቀጥለው ዓመት ከሰኔ 10 እስከ 11 ይካሄዳል ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

እሸቴ በቀለ