1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኦስካር ማርቲኔዝ የ2023 የዶይቼ ቬለ የመናገር ነጻነት ሽልማትን አሸነፈ

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 25 2015

ኤልሳልባዶራዊው ጋዜጠኛ ኦስካር ማርቲኔዝ የ2023 የዶይቼ ቬለ የመናገር ነጻነት ሽልማትን አሸነፈ ። የ40 ዓመቱ ማርቲኔዝ የዓመቱን ሽልማት ያሸነፈው በደቡባዊ አሜሪካ ያለፍራቻ በሚሰራቸው የምርመራ ዘገባዎቹ ከተመረጠ በኋላ መሆኑን ዶይቼ ቬለ ዐስታውቋል።

https://p.dw.com/p/4QrHY
Oscar Martinez | Chefredakteur von El Faro in El Salvador
ምስል Alba Amaya/DW

የዓመቱ የዴይቼ ቬለ የመናገር ነጻነት አሸናፊ ኤልሳልቫዶራዊ ጋዜጠኛ

ኤልሳልባዶራዊው ጋዜጠኛ ኦስካር ማርቲኔዝ የ2023 የዶይቼ ቬለ የመናገር ነጻነት ሽልማትን አሸነፈ ። የ40 ዓመቱ ማርቲኔዝ የዓመቱን ሽልማት ያሸነፈው በደቡባዊ አሜሪካ ያለፍራቻ በሚሰራቸው የምርመራ ዘገባዎቹ ከተመረጠ በኋላ መሆኑን ዶይቼ ቬለ ዐስታውቋል። 
ትውልደ ኤልሳልባዶራዊው ማርቲኔዝ ዶይቼ ቬለ በየዓመቱ ለሚያዘጋጀው ዓለማቀፍ የመናገር ነጻነት ሽልማት ሲታጭ ድምጽ አልባ ለነበሩት ድምጽ በመሆኑ ነው ይላል ፤ የዓለማቀፉ የመገናኛ ብዙኃን ድርጅ ዶይቼ ቬለ። ጋዜጠኛውን ለዚሁ ሽልማት የበቃው ደግሞ 25 ዓመታትን ወደ ኋላ ተመልሶ በጎርጎርሳውያኑ 1998 የተመሰረተው እና በሂደት በደቡባዊ አሜሪካ ቀዳሚ የምርመራ ዘገባ ተነባቢው ጋዜጣ ኤል ፋሮ ወይም የብርሃን ቤት ተብሎ የሚታወቀው የህትመት ውጤት ነው። 
ማርቲኔዝ በዚሁ (አሁን) የዲጂታል ተነባቢ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ እና በኤልሳልቫዶር እና በቀጣናው ሃገራት ደግሞ የነጻ ጋዜጠኝነት ተምሳሌት ተደርጎም ይወሰዳል። ለድምጽ አልባዎች ድምጽ መሆንን መርህ አድርጎ የተነሳው ጋዜጠኛው ወደ ጋዜጠንነት ዓለም ለመምጣቱም በምክንያትነት ያነሳል። 
«ጋዜጠኝነት ሁለት አስፈላጊ ተግባራትን ማከናወን አለበት ብለን እናምናለን። በመጀመሪያ ኃይል እና ኃያላንን መለየት ፤ ከዚያም የእነርሱን የቁጥጥር ስልት መግለጽ ፤ ሁለተኛው በሚደርስባቸው ከፍተኛ ጫና ምክንያት በጣም ተጋላጭ የሆኑ እና ለስቃይ የተጋለጡት የህብረተሰብ ክፍሎች ህይወት እንዲገለጥ ማድረግ ነው። አሁን በመካከለኛው አሜሪካ ክፍል  የግለሰቦችን ነጻነት የሚጋፋ አዲስ  ማዕበል እያጋጠመ በመሆኑ ይህ የበለጠ አስፈላጊ ነው ብለን እናምናለን።»
ማርቲኔዝ በምርመራ ጋዜጠኝነቱ የኤልሳልቫዶርን ዝነኛ ወንጀለኞች እና የወሮበሎች እና መሪዎቻቸውን አሰራር መዘገቡ ይነገርለታል። በተጨማሪም የኤልሳልቫዶር ፖሊስ እና የመንግስት ባለስልጣናት ከተደራጁ ወንጀሎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት ጨምሮ በሀገሪቱ ከህግ አግባብ ውጭ የተፈጸሙ ግድያዎችንም  አጋልጧል።
በሌላ በኩል ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር ለማበር ፈቃደኛ አለመሆኑ ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ናይብ ቡኬሌ ላይ ለመነሳቱ ምክንያት ሳይሆን እንዳልቀረም ነው ዘገባዎች የሚያመለክቱት።  
በእርግጥ ነው፤ ወጣቱ የኤልሳልቫዶር መሪ በወንጀለኛ ቡድኖች ላይ የሚያደርገው ጦርነት በኤሳልቫዶራውያን ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነትን አ,ትርፎለታል። ቡኬሌ የጠንካራ መስመር ፖሊሲዎቹን  በማስታወቂያ ቪዲዮዎች በመታገዝ ያስተዋውቃሉ። ነገር ግን እንደዚያም ሆኖ  በእርሳቸው አስተዳደር ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት እየተፈፀመ ነው ሲሉ ተቺዎች ይናገራሉ።
 ኦስካር ማርቲኔዝ እና የምርመራ ዘገባ ቡድኑ ደግሞ ፕሬዚዳንት  ቡኬ እታገላቸዋለሁ ከሚሏቸው  ቡድኖች ጋር ግንኙነት እንዳላቸው እና ለፖለቲካዊ አላማቸው ሲሉም ከወሮበላ መሪዎች ጋር ስምምነት እስከማድረግ መድረሳቸውን አጋልጠዋል።
«የፖሊስን ጭፍጨፋ፣ የፖለቲከኛውን ሙስና እና ከወንጀለኞች ጋር ያለውን ስምምነት ባናጋልጥ ኖሮ ምን ይፈጠር ነበር? እንደሚመስለኝ የሙስና ህይወት በጣም ቀላል ይሆን ነበር ። እና እኛ ደግሞ ያ እንዲሆን አንፈልግም ።»
የፕሬዚዳንት ቡኬሌ አስተዳደር ማርቲኔዝን ጨምሮ በጥብቅ የምርመራ ዘገባ ላይ የተሰማሩ ጋዜጠኞችን ዒላማ ማድረጉ ነው የሚነገረው ።
ማርቲኔዝ እና የኤል ፋሮ ቡድን በመንግስት ሰዎች ስለላ እና ክትትል ሲደረግባቸው ቆይቷል።  እሱ እና ቤተሰቡ በቁጥጥር ስር ሊውሉ እንደሚችሉ በመፍራት በተደጋጋሚ ከሀገር እስከ መውጣትም ደርሰዋል። ስለቤተሰቦቹ ደህንነት አጥብቆ እንደሚጨነቅ የሚናገረው ጋዜጠኛው እርሱ እና ሌሎች በርካታ የአካባቢው ሃገራት ጋዜጠኞች የሚያጋጥሟቸውን ስጋቶች ጠንቅቆ እንደሚረዳ ይገልጻል።  
«አካላዊ ጥቃት፣ ከፖለቲከኞች እና ነጋዴዎች የሚደርስብን ስም ማጥፋት፣ቤተሰቦቻችንን ማዋከብ፣ስደት፣ሞት፣እስር ቤት ኸረ ስንቱ..»
ነገር ግን እንደዚያም ሆኖ ትልቅ ግላዊ ስጋቶች ቢኖሩም ኦስካር ማርቲኔዝ መጻፉን ለመቀጠል እና ስልጣን ላይ ያሉትን ተጠያቂ ለማድረግ መቁረጡን ይናገራል። ለዚህ ነው  እንግዲህ ዶይቼ ቬለ 75ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በሚያከብርበት ወቅት ኦስካር ማርቲኔዝ የዓመቱ የመናገር ነጻነት ሽልማት አሸናፊ መሆኑን ይፋ ያደረገው ። 
የዶይቼ ቬለ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፒተር ሊምቡርግ የማርቲኔዝ ለሽልማት መታጨት በተመለከተ ሲናገሩ ።
«ኦስካር ማርቲኔዝ ለፕሬስ ነፃነት እና ለሃሳብ ነፃነት የሚታገል ደፋር ጋዜጠኛ ነው፣ መፅሄት እና የሚዲያ ማሰራጫው በርግጥም ለአመለካከቱ ለሆነ እና ለጥቅም የሚታገል አካልን የሚያነብ እና የደፋር ሰው ተምሳሌት ነው»
ኦስካር ማርቲኔዝ ዶይቼ ቬለ በሚያዘጋጀው የሽልማት ስነስረዓት ላይ ቀርቦ ሽልማቱን እንደሚወስድ ይጠበቃል። 

Peter Limbourg
ፒተር ሊምቡርግ ፤ የዶይቼ ቬለ ዋና ስራ አስፈጻሚምስል DW
DW Freedom of Speech Award 2023
ዶይቼ ቬለ የሚያዘጋጀው የመናገር ነጻነት ሽልማት
Oscar Martinez | Chefredakteur von El Faro in El Salvador
ኦስካር ማርቲኔዝምስል Alba Amaya/DW

ታምራት ዲንሳ 

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር