16ኛው ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን መድረክ
ሰኞ፣ ሰኔ 12 2015
ዶይቼ ቬለ (DW) በየዓመቱ የሚያስተናግደው ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን መድረክ በጎርጎሪያኑ ዛሬ ሰኞ፤ ሰኔ 19 ቀን 2023 ጀምሮ ለሁለት ቀናት ይካሄዳል። በጀርመኗ ቦን ከተማ እየተካሄደ የሚገኘው ይህ ታላቅ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን መድረክ «መከፋፈልን ማሸነፍ» የሚል መሪቃል አለው ።
በአሁኑ ወቅት በተለያዩ አመለካከቶች መከፋፈል በበዛባት ዓለማችን ፤ክርክሮች በተለይ በማህበራዊ ድረ-ገጾች ይበልጥ አወዛጋቢ እና አስቸጋሪ እየሆኑ መጥተዋል። በህብረተብ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ቃላት ከ"ባህል ግጭት" እስከ "ስርዓት ግጭት" እያስከተሉ ነው።ከዚህ አኳያ የመገናኛ ብዙኃን እና አዘጋጆቹ ልዩ ኃላፊነት አለባቸው ይላሉ የዶቼ ቬለ ዋና ስራ አስኪያጅ ፒተር ሊምቡርግ።«በብዙ የዓለማችን ክፍሎች እየጨመረ የመጣውን ማኅበራዊ መከፋፈል በመመልከት የመገናኛ ብዙኃን እና አዘጋጆቹ ልዩ ኃላፊነት አለባቸው።የተሳሳቱ መረጃዎች፣ የሴራ ፅንሰ-ሀሳቦች እና ህዝባዊነት ለኢንዱስትሪው ዋና ተግዳሮቶች ናቸው። ምናልባትም ጋዜጠኞች የራሳቸውን ድርጊት በጥልቅ ማጤን ከምንጊዜውም ጊዜ በላይ አስፈላጊ ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ ይህንን ማድረግ የመድረኩ ተግባር ነው። ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን መድረክ ልምድና አመለካከት የሚለዋወጡበት፣ አንዱ ከሌላው የሚማርበት፣ አንድ ሰው በጥያቄዎቹ እና በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ብቻውን እንዳልሆነ እና ከሌሎች ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ የሚገነዘብበት መድረክ ነው። እና በጉባኤው ተሳታፊ የሆነ ሁሉ ከዚህ የልምድ ልውውጥ ይጠቀማል።»
ዶይቸ ቬለ ለ16ኛ ጊዜ በሚያዘጋጀው በዚህ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን መድረክ ከ 120 በላይ ሀገራት የመጡ ከ 2000 በላይ ተሳታፊዎች ታድመዋል።
ከነዚህም ውስጥ እንደ ፎቶግራፍ አንሺው ሮን ሃቪቭ ያሉ ታዋቂ የጦርሜዳ ዘጋቢዎች በመድረኩ ይገኛሉ። እንደ ፌደራል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክ ያሉ የጀርመን ፖለቲከኞችም በቪዲዮም ቢሆን ንግግር ያደርጋሉ። መርማሪ ጋዜጠኛ ኦስካር ማቲኒዝ የ2023 የንግግር ነፃነት ሽልማትን ለመቀበል ከኤል ሳልቫዶር መጥቷል። የላይቤሪያ የሰላም እና የሴቶች አንቂ እንዲሁም የኖቤል ሽልማት አሸናፊ ሌይማህ ግቦዌ በመጀመሪያ ረድፍ ይቀመጣሉ።
በዾቼቬለ የመድረኩ አዘጋጅ ቬሪካ ስፓሶቭስካ እንዳሉት በዚህ መድረክ መክፈቻ ላይ ቮልኒ የተባለ በስደት ፖላንድ የሚገኝ የሙዚቃ ቡድንም የቤላሮስን መንግስት በመቃወም ፊታቸውን ሸፍነው ሙዚቃ አቅርበዋል።
ከ140 በላይ ታዋቂ ንግግር አድራጊዎችም በመድረኩ የሚገኙ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል በጎርጎሪያኑ 2021 ዓ/ም የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊው ሩሲያዊው ጋዜጠኛ ዲሚትሪ ሙራቶው ይገኝበታል። የሙራቶቭ መታደም በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ከዩክሬን ወገን የተለየ ትችት አስነስቷል።የዶቼቬለው ዋና ስራ አስፈፃሚ ፒተር ሊምቡርግ ግን መድረኩ ከልዩነት ይልቅ የውይይት ነው ይላሉ።
«ሩሲያ በዩክሬን ላይ በከፈተችው ጦርነት ሁለተኛው ዓመት ላይ ነን። ዩክሬናውያን ከሩሲያውያን ጋር መነጋገር እንደማይፈልጉ እያየን ነው። እና በአንፃሩ እንዲህ ዓይነቱ አለመነጋገር በሌሎች የዓለም ክፍሎች ግጭቶች በሚካሄዱባቸው አካባቢዎችም አሉ። ዓለም አቀፉ የመገናኛ ብዙሃን ጉባኤ ከዚህ ቀደም የነበሩ ስንጥቆችን በማስወገድ ወደ ውይይት መግባት የሚቻልበት መድረክ ነው።የዘንድሮው ጉባኤም ይህንኑ ያደርጋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።»
የመድረኩ አስተባባሪ ስፓሶቭስካ በበኩላቸው «ባለፈው አመት የሩሲያ እና የዩክሬን ጋዜጠኞች በውይይቱ አንድ ላይ ተቀምጠው ነበር» በማለት ያስታውሳሉ።ባለፉት አመታት የተካሄዱት መድረኮችም የመወያየትን ሚና ማረጋገጣቸውን ይገልፃሉ።
«ዓለም አቀፉ የመገናኛ ብዙሃን ጉባኤ የገለልተኝነት መሰረት ነው። ጠላት የምትላቸውን ወይም ከጠላት ሀገር መጡ የምትላቸውን እና ሀገርህ ውስጥ የማታገኛቸውን ሰዎች እዚህ ማግኘት ትችላለህ። ለምሳሌ ዩክሬን ፣ ሩሲያ ፣ ፍልስጤም ፣ እስራኤል ፣ ጥቂቶቹን መጥቀስ ይቻላል። ይህ የማይታመን፣ አደናቂ እና አስገራሚ ሁኔታ ነው። »
በዓለም አቀፉ የመገናኛ ብዙሃን መድረክ ምስሎችን እና ቪዲዮዎችን ከአውታረ መረብ ስለማጣራት፣ ስለ ፖድካስቶች የድምፅ ጥራት እንዲሁም ሰው ሰራሽ አስተውሎት እና ጋዜጠኝነት ላይ አውደ ጥናቶች ይደረጋሉ። የጀማሪ ቴክኖሎጅ ኩባንያዎች ውድድርም የመድረኩ አካል ነው።በዘንድሮው ውድድር ከሁሉም አህጉራት የተውጣጡ ከ90 በላይ ጀማሪ የቴክኖሎጅ ኩባንያዎች የፈጠራ ሀሳቦቻቸውን አቅርበዋል።ሶስቱ የመጨረሻ እጩዎችም ወደ ቦን አቅንተዋል።
ፀሀይ ጫኔ
ታምራት ዲንሳ