በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ በአሜሪካ ምክር ቤት የተሰጠ ምስክርነት
ዓርብ፣ ኅዳር 21 2016ዩናይትድ ስቴትስ ኢትጵያ ላይ የምትከተለውን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በተመለከተ የወቅታዊ ጉዳዮች ዳሰሰ፣ ምስክርነትና ማብራሪያ በአሜሪካ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተካሄደ ። ምስክርነቱ ትናንት የተሰማው «ኢትዮጵያ፦ ተስፋ ወይንስ አደጋ፤ የዩናይትድ ስቴትስ ፖሊሲ» በሚል ዐቢይ ርእስ ነው ። የምክር ቤቱ የውጭ ጉዳይ ንዑስ ኮሚቴ ትናንት በጠራው በዚሁ ውይይት፤ በአፍሪቃ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር እና የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድዖ ድርጅት (USAID) ረዳት አስተዳዳሪ ታይለር ቤክልማን ቀርበው ምስክርነት ሰጥተዋል ። የምክር ቤቱ አባላትም የተለያዩ ጥያቄዎች አንስተው ምላሽ ተሰጥቷቸዋል ። በዐማራ ክልል ተጥሎ የሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ እና መገናኛ ብዙኃን ወደ ክልሉ እንዲገቡ እንዲሁም የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲጀመር ለኢትዮጵያ መንግስት ጥያቄ መቅረቡም ተብራርቷል ። ከአትላንታ ጆርጂያ ታሪኩ ኃይሉ ምስክርነቱን አድምጦ ቀጣዩን ዘገባ ልኮልናል ።
በኦሮሚያና ዐማራ የቀጠሉ ጦርነቶች
በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በአሜሪካ ምክር ቤት በተሰጠው በዚሁ ምስክርነት፣ የሰሜን ኢትዮጵያውያው ጦርነትና የሰላም ስምምነቱ ሁኔታ፣ በኦሮሚያና ዐማራ ክልሎች የቀጠለው ጦርነት፣ የሀገሪቱ ምጣኔ ሀብትና የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ፣ ከተነሱ ዋናዋና ጉዳዮች መኻከል ይገኙባቸዋል። በሰሜን ኢትዮጵያ የተካሄደውን ጦርነት ለማስቆም በፕሪቶሪያ ከተደረገው የሰላም ስምምነት አፈፃፀም ገና ብዙ እንደሚጠበቅ የጠቀሱት ልዩ መልእክተኛ ማይክ ሐመር፣ የሰላም ስምምነት መፈረሙ በራሱ ግን እፎይታ ማስገኘቱን ተናግረዋል።
አሜሪካ፣ በዐማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች የሚካሄዱት ግጭቶች በንግግርና ውይይት መፍትሔ እንዲገኝላቸው ጫና እያሳደረች መሆኑንም ማይክ ሐመር ዐስታውቀዋል። «በኦሮሚያና ዐማራ ለቀጠሉ ግጭቶች፣መፍትሔ ለማስገኘት፣የንግግርና መፍትሔ አስፈላጊነትን አስመልክቶ፣ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ጫና እያሳደርን ነው።» የኢትዮጵያ መንግስትና የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት፣ በቅርቡ ታንዛኒያ ውስጥ ባካሄዱት የሰላም ውይይት መሳተፋቸውን የተናገሩት ልዩ ልዑኩ፣ ችግሩ መፍትሔ እስኪገኝለት ድረስ፣ አገራቸው በቁርጠኝነት እንደምትሰራ አረጋግጠዋል። በዐማራ ክልል ተጥሎ የሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ እና መገናኛ ብዙኃን ወደ ክልሉ እንዲገቡ እንዲሁም የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲጀመር ለኢትዮጵያ መንግስት ጥያቄ መቅረቡንም አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት ይዞታ
ልዩ መልዕክተኛው፣ በዚሁ ምስክርነታቸው አሳሳቢ ነው ስላሉት፣ የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት ይዞታም አንስተዋል። «ኢትዮጵያ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ችግሮችን ተጋፍጣለች። የውጭ ምንዛሪ ክምችት በሁለት አስርት ዓመታት ውስጥ፣በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ባለፉት ሁለት ዓመታት የዋጋ ግሽበቱ በአማካይ 30 በመቶ በላይ ገደማ ነው። ስለዚህም ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት፣ በአሳሳቢው የሃገሪቱ ኢኮኖሚ ሁኔታ ላይ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር እየተወያየ ነው።» የህዳሴ ግድብን በተመለከተ፣ ኢትዮጵያ፣ ግብፅ፣ ሱዳንንና የተቀሩት የታችኛው የተፋሰሱን ሃገራት በሙሉ የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ መልኩ ስምምነት እንዲደረስ አሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል አምባሳደር ሐመር ጠቁመዋል።
የሰብአዊ ርዳታ
የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት (USAID) ረዳት አስተዳዳሪ ታይለር ቤክልማን በበኩላቸው በሰጡት ምስክርነት፣ የምግብ ዕርዳታ ለሌላ ዓላማ በመዋሉ ምክንያት ዕርዳታ ተቋርጦ መቆየቱን አውስተዋል። አሁን መስሪያ ቤታቸው የምግብ ዕርዳታውን ስለቀጠለበት ሁኔታ ሲያስረዱ፣ እንዲህ ብለዋል። «የኢትዮጵያ መንግስት በዚህ ወር መጀመሪያ፣በምግብ ድጋፍ ሥርጭቱ ላይ ከፍተኛ ለውጥ ለማድረግ በመስማማቱ፣ዩኤስኤይድ በመላው ሃገሪቱ ዕርዳታ እንዲቀጥል አድርጓል።»
ጥያቄና ምላሽ
ይህንን የሁለቱን ባለሥልጣናት ምስክርነት ተከትሎ፣ከምክር ቤቱ አባላት የተለያዩ ጥያቄዎች ቀርበው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል። በአሜሪካ ምክር ቤት የአፍሪቃ ጉዳዮች ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ ጆን ጀምስ፣ ከቀጠሉት ግጭትና ጦርነቶች ጋር ጋር በተገናኘ፣በኢትዮጵያ መንግስት ላይ የሰላ ሒስ በሰነዘሩበት አስተያየታቸው፣አሁን እየተነሳ ያለው የባህር በር ጥያቄ ቀጣይ ግጭት አያስከትልም ወይ የሚል ጥያቄ አስከትለዋል። አምባሳደር ማይክ ሐመር በሰጡት ምላሽም፣ጉዳዩ ለአሜሪካ ብቻ ሳይሆን ለአካባቢው ሃገሮች ጭምር፣ የስጋት ምንጭ መሆኑን አመልክተዋል። ይሁንና የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የባህር በር የማግኘት ጉዳይ በሰላማዊ መንገድ ብቻ የሚካሄድ መሆኑን በይፋ መናገራቸውን በመጥቀስ መልሰዋል።
ሰው አልባ አውሮፕላኖችን አስመልክቶ፣የአፍሪቃ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው ስራ በጀመሩበት ወቅት ወደ ቱርክ እና የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች በመጓዝ፣ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ለኢትዮጵያ መሰጠቱ፣ አሜሪካን የሚያሳስባት እንደሆነ፣ድሮኖቹም በሃገሪቱ ያለውን ሁኔታ እያወሳሰቡ ስለመሆኑ ስጋታቸውን እንደገለጹ ለምክር ቤቱ አባላት ገልጸዋል።
ታሪኩ ኃይሉ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ነጋሽ መሐመድ