አምባሳደር ማይክ ሐመር ሎስ አንጀለስ ከሚኖሩ ኢትዮጵያ አሜሪካውያን ጋር ተወያዩ
ማክሰኞ፣ ግንቦት 8 2015አምባሳደር ሐመር፣ከኢትዮጵያ አሜሪካውያን ማህበረሰብ ጋር ያደረጉት ውይይት፣በወቅታዊ የኢትዮጵያ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነበር።
ልዩ ልዑኩ፣በኢትዮጵያ መንግስትና በህወሓት መኻከል ፕሪቶሪያ ላይ ስለተደረሰው የሰላም ስምምነት አፈጻጸምን ጨምሮ፣በሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከኢትዮጵያ አሜሪካውያን ማኀበረሰብ ጋር መክረዋል።
በዚሁ ሕዝባዊ ውይይት ላይ የተሳተፈችው፣የትግራይ አክሽን ኮሚቴ እንዲሁም የአፍሪቃ ቀንድ ሴቶች ህብረት ተባባሪ መሥራችና ፕሬዝደንት ማህብል ገብረመድህን፣ውጤታማ ውይይት ማካሄዳቸውን ለዶይቸ ቨለ በሰጠችው አስተያየት ተናግራለች።
" ውይይቱ በጣም ውጤታማ ነበር።በሎስአንጀለስ አካባቢ የሚገኙ ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔሮች የተወከሉበት ሕዝባዊ ውይይት ነው።ከአቅራቢያውና ከሌሎች ክፍለ ግዛቶች የሄዱ ተሣታፊዎችም ተገኝተዋል።ኢትዮጵያ ጥቂት አሰቃቂ ዓመታትን እንደማሳለፏ መጠን ውይይቱ በኢትዮጵያ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነበር።የውይይቱ ግብ ማኀበረሰቡን በማቀራረብ እርስ በርስ መነጋገር እንዲጀምሩና ሰላምን እንዲያጸኑ ነው።"
የአሜሪካ ዉጭ ጉዳይ ሚንስቴር መስሪያ ቤት፣በተለይም በቀጣናው የአሜሪካ ልዩ ልዑክ አምባሳደርነት ማይክ ሐመር፣በኢትዮጵያ ጉዳዮች ላይ ጉልዕ ተሣትፎ እያደረጉ በመሆናቸው፣ በኢትዮጵያ አሜሪካውያኑ ዘንድ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለማስተናገድም ህዝባዊ ውይይቱ መልካም አጋጣሚ የፈጠረ እንደሆነ ፕሬዚዳንቷ አመልክታለች።
"በውይይቱ የተሳተፉ የማኀበረሰቡ አባላት ዐሳባቸው ተሰሚነት እንዳገኘ ተሰምቷቸዋል።ባለፉት ጥቂት ዓመታት እንዲህ የመደመጡ ዕድል አልነበረም።ተረስተናል የሚል ቁጭት ስለነበር፣ሕዝባዊ ውይይቱ በጣም አስፈላጊ ነበር።በሎስ አንጀለስ አካባቢ የሚኖረው ማኀበረሰብ የመደመጥ አጋጣሚን ያገኘበት ነው።"
በሎስ አንጀለስ የዐማራ ማኀበር ሊቀመንበር ቤተልሔም አየለ በበኩላቸው፣ አምባሳደር ማይክ ሐመር፣ ከዐማራ ማኀበረሰብ ጋር ውይይት ሲያደርጉ የአሁኑ የመጀመሪያቸው እንደሆነ ገልጸው፣የዐማራው ሕዝብ ያለበትን ነባራዊ ሁኔታ እንዲገነዘቡላቸው እንደሚፈልጉ አመልክተዋል።
"እኛ አሁን ከእርሱ ጋር መገናኘት የፈለግነው፣ዐማራው ያለበትን ሁኔታ እንዲገነዘብ ነው።ዘር ማጥፋት የተደረገበትን እንዲያውቅ፣የተፈናቀለውን እንዲያውቅ፣ ግንኙነትን አጠናክረን የሚያወጡት ፖሊሲ ዐማራውን የሚጠቅም እንዲሆን ነው።እኛ እንደ ዐማራ ማኀበር፣እዚህ ሃገር ተቀምጠን የአሜሪካ ፖሊሲ በጣም ተጽዕኖ ያለው ስለሆነና ብዙውን ነገር ሃገሩ ላይ የሚያደርጉት ነገር በዚህ የተመሠረተ ስለሆነ ያንን እንዲያስተካክሉ ለማሳመን ነው።"
የአሜሪካ መንግስት በተለይ የዐማራውን ህዝብ አስመልክቶ የተዛባ ፖሊሲ ይከተላል ያሉት ሊቀመንበሯ፣በዐማራ ሕዝብ ላይ ይፈጻማሉ ያሏቸውን ግድያና ማፈናቀል እያየ ዝምታን መርጧል ሲሉ ወቅሰዋል።
"ዐማራው ለምንድን ዝም የተባለው?ይህ ሁሉ ግፍ ሲደርስበት ችሎ ሰላማዊ የሆነ ሕዝብ፣ጦር ላንሳ ልንገንጠል ያላለ፣የመገንጠል ዐሳብ ያለው ሁፓርቲ የማያስተናግድ፣ ኢትዮጵያን የሚወድ ሕዝብ ነው።ዐማራ ብለን እንደራጅ እንጂ፣በዐማራነት ዐማራ ነን ስለተባልን ስለምንገደል፣ዋናው መዳረሻችን ኢትዮጵያ ናት።"
በመሆኑም፣ይህንን በዐማራው ሕዝብ ይፈጸማል ያሉትን በደልና ግፍ ለማስረዳት፣ከአምባሳደር ሐመር ጋር የተካሄደውን የውይይት መድረክ ማመቻቸታቸውን አስረድተዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመት ያህል የተካሄደውን ደም አፋሳሽ ጦርነት ለማስቆም፣በአፍሪቃ ህብረት ሸምጋይነት ከተካሄደው ድርድር ጀርባ፣አሜሪካ ቁልፍ ሚና ስትጫወት መቆየቷ ይታወቃል።
አምባሳደር ማይክ ሐመርን ጨምሮ፣በቀጣናው የተሰየሙት የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኞችም ወደአካባቢው በተደጋጋሚ በማቅናት፣ተፋላሚ ኀይላቱ ወደ ድርድር ጠረጴዛ እንዲመጡ፣ ብሎም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ የአሜሪካ ተሳትፎ ወሳኝ እንደነበር ይታመናል።
ታሪኩ ሃይሉ
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
ኂሩት መለሰ