1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመስከረም 14 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ መስከረም 14 2016

ጀርመን ቤርሊን ከተማ ውስጥ ትናንት በተከናወነ የማራቶን ሩጫ ፉክክር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ትእግስት አሰፋ የዓለም ክብረወሰን ሰብራ ለድል በቅታለች ። ከቡሩንዲ ጋር አንድ እኩል የተለያዩት ሉሲዎቹ በአፍሪቃ ሴቶች ዋንጫ ማጣርያ ሁለተኛ ዙር የመልስ ጨዋታቸውንም ማክሰኞ መስከረም 15 ቀን፣ 2016 በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ያደርጋሉ።

https://p.dw.com/p/4WmbS
በቤርሊን ማራቶን ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ትእግስት አሰፋ
በቤርሊን ማራቶን የሩጫ ፉክክር ክብረወሰን የሰበረችው ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ትእግስት አሰፋ የዓለም ክብረወሰን የሰበረችበትን ሰአት ሠሌዳ በፈገግታ ስታመለክትምስል Markus Schreiber/AP/picture alliance

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

ጀርመን ቤርሊን ከተማ ውስጥ ትናንት በተከናወነ የማራቶን ሩጫ ፉክክር ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ትእግስት አሰፋ የዓለም ክብረወሰን ሰብራ ለድል በቅታለች ። በአፍሪቃ የእግር ኳስ የኮንፌዴሬሽን ግጥሚያ ባለፈው ድል የቀናው ባሕርዳር ከነማ የእግር ኳስ ቡድን የፊታችን እሁድ ለመልስ ግጥሚያው ከቱኒዝያው አቻው ጋ ያደርጋል ። በአፍሪቃ የእግር ኳስ ቡድኖች የአሸናፊዎች አሸናፊ ውድድር ቅዱስ ጊዮርጊስ በግብጹ አል አህሊ ትናንት ሽንፈት ገጥሞታል ። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ አርሰናል ነጥብ ሲጥል ሊቨርፑል ተጨማሪ ድል በመቀዳጀት ከመሪው ማንቸስተር ሲቲ ጋር ተጠጋግቷል ። በጀርመን በቡንደስሊጋ ቦሁም የግብ ጎተራ ሆኗል ። 

አትሌቲክስ

ብዙዎች አስደማሚ ሲሉ ዘግበውታል ።  ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ትእግስት አሠፋ ትናንት በጀርመንዋና ከተማ ቤርሊን ያስመዘገበችው ድንቅ ውጤት ። በማራቶን ሩጫ ፉክክር አዲስ ክብረ ወሰን ሆኖ ተመዝግቧል ። በዚህ ርቀት «ታላቋ» የምትባለው ፓውላ ራድክሊፍ እንኳን ያስመዘገበችው በሦስት ደቂቃ ከሰላሳ ሰከንድ ይዘገያል ። እስከ ትናንት ድረስ በኬኒያዊቷ አትሌት ብሪጊድ ኮስጌ ተይዞ ከተሰበረው ክብረወሰንም በሁለት ደቂቃ የተሻሻለ ነው ። 2 ሰአት ከ11 ደቂቃ ከ53 ሰከንድ የአትሌት ትእግስት አሠፋ አዲስ ክብረወሰን ።

ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ትእግስት አሰፋ
በቤርሊን ማራቶን የሩጫ ፉክክር ክብረወሰን ሰብራ ድል የተቀዳጀችው ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ትእግስት አሰፋ ምስል Michael Sohn/AP Photo/picture alliance

ኬንያዊቷ ብሪጊድ ኮስጌ በጎርጎሪዮሱ 2019 በበቺካጎ ማራቶን ይዛ የቆየችው ክብረወሰን (2:14:04)ነበር ። ትዕግስት ውድድሩን በታላቅ ድል ካጠናቀቀች በኋላ በሰጠችው ቃለ ምልልስ፦ «በምወደው ሀገር እና በምወደው ሰው ፊት ለፊት ይህን ክብረወሰን በመስበሬ በጣም ደስ ብሎኛል» ብላለች ።

«አመሠግናለሁ እጅግ በጣም ደስታ ነው የተሰማኝ ደስታዬ ወደር የለውም ይህ እግዚአብሔር የሰጠኝ የጠንካራ ሥራ ውጤት ነው ልምምዴን ያደረግሁት በጣም በስነስርዓት ነው እግዚአብሔር ይመስገን  የምወደው ሀገር እና የምወደው ሰው ፊት ለፊት ይህን ክብረወሰን በመስበሬ በጣም ደስ ብሎኛል በጣም የምወደው ሀገር ነው ቤርሊንን በጣም የምወደው ሀገር ነው እዚህ ሀገር ላይ በመስበሬ ደግሞ ደስታዬን ይበልጥ ከፍ አድርጎታል አመሠግናለሁ »

ከ156 ሃገራት የተውጣጡ 48,000 ሯጮች በተሳተፉበት የትናንቱ የማራቶን ሩጫ ፉክክር ትእግስት በተለይ የቤርሊን ነዋሪዎች ለሰጧት ማበረታቻ እና ድጋፍ ከልብ አመስግናለች ።

«ያው በእውነት ድካሜ ሁሉ እስኪጠፋ ድረስ ነው ያደረጉኝ ። የሕዝቡ ማበረታቻ እና ድጋፍ በጣም ይገርማል ። እኔ በሕይወቴ እንደዚህ ዐላየሁም ። ለብዙ ውድድር ሄጃለሁ ግን እንደዚህ ማበረታቻ ድጋፍ የሚሰጥ ሰው ዐላየሁም ። በእውነት ድካሜ ነው የጠፋው የሕዝቡ ድጋፍ፤ የሕዝቡ ጩኸት፤ የሕዝቡ  ጥሪ የእውነት ብርታት ነው የሆነኝ። አመሠግናለሁ በዚህ አጋጣሚ ። የቤርሊንን ሕዝብ ። በጣም ነው የምወደው ። በጣም ነው ማመስገን የምፈልገው ።»

ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ትእግስት አሰፋ
ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ትእግስት አሰፋ በጀርመን ቤርሊን ማራቶን ድል ከተቀዳጀች በኋላ ምስል Markus Schreiber/AP Photo/picture alliance

የቤርሊን ማራቶን የአትሌት ትእግስት አስደናቂ ድል

በእርግጥም የቤርሊን ከተማ ነዋሪዎች የትናንትና የጎዳና ላይ ድጋፍ እጅግ ከፍተኛ ነበር ። የቤርሊኑ ወኪላችን ይልማ ኃይለ ሚካኤል ቤርሊኖች በድጋፍ አሰጣጣቸው እንኳን አይታሙም ይለናል ።

አትሌት ትእግስት ወደ ማራቶኑ ከመሻገሯ በፊት ገና በታዳጊነቷ በአጭር ርቀት ማለትም 400 እና 800 ሜትር ውድድር ብርቱ ተፎካካሪ ነበረች ። በ17 ዓመቷ በ800 ሜትር ያስመዘገበችው ሰአት በኦሎምፒክ እና በዓለም የሩጫ ፉክክር አሸናፊ ከነበሩት ከዝነኞቹ ደቡብ አፍሪቃዊቷ ካስተር ሴመንያ  እና ኬኒያዊቷ ዩኒስ ጄፕኮዬች ብዙም ያልራቀ ነበር።

ትዕግስት አሰፋ በዓለማችን ከሚከናወኑ ታላላቅ የማራቶን የውድድር መድረኮች አንዱ በሆነው በቤርሊን ማራቶን አዲስ የዓለም ክብረ ወሰን በማስመዝገብ ጭምር ማሸነፏ በቀጣዩ የፓሪስ ኦሎምፒፒክ ውድድር ገና ከወዲሁ ትልቅ ግምት እንዲሰጣት አስችሏል ።

በትናንቱ የቤርሊን ማራቶን የሩጫ ውድድር ኬኒያዊቷ  ሼይላ ቼብኪሩር 2:17:49 በመሮጥ ሁለተኛ እንዲሁም ታንዛንያዊቷ ማግዳሌና ሻውሪ 2:18:41 በሆነ ጊዜ ማጠናቀቅ ሦስተኛ ወጥታለች ። ዘይነባ ይመር 4ኛ ፤ ሰንበሬ ተፈሪ 5ኛ ደረጃ አግኝተዋል።

 ትእግስት አሠፋ እና ኤሊውድ ኪፕቾጌ በቤርሊን ማራቶን
በወንዶች የቤርሊን ማራቶን ለ5ኛ ጊዜ ያሸነፈው ኬኒያዊው ኤሊውድ ኪፕቾጌ በሴቶች ርቀት ክብረወሰንሰብራ ካሸነፈችው ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ትእግስት አሠፋ ጋር በቤርሊን ማራቶን ምስል Christoph Soeder/AP

በወንዶች ተመሳሳይ ርቀት ኬኒያዊው ኤሊውድ ኪፕቾጌ የበርሊን ማራቶንን ለአምስተኛ ጊዜ አሸናፊ መሆን ችሏል ። የገዛ ክብረወሰኑን ያሻሽል ይሆናል የሚል ቅድመ ግምት ተሰጥቶት  የነበረው ኬኒያዊ ትናንት ባይሳካለትም የገባበት ሰዓት 2 ሰዓት ከ2 ደቂቃ ከ42 ሰከንድ ሆኖ ተመዝግቧል። እርሱን ተከትሎ ኬናያዊው ቪንሴት ኪፕኬሞይ 2:03:13 በሆነ ጊዜ ሁለተኛ ሲሆን፤ ኢትዮጵያዊው ታደሰ ታከለ በሰከንዶች ልዩነት 2:03:24. በመግባት ሦስተኛ መውጣት ችሏል ።

የሮም ማራቶንን በባዶ እግሩ የሮጠው ሁለተኛው ኢትዮጵያዊ

ሌላኛው ኬኒያዊ ሮናልድ ኮሪር አራተኛ፤ ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ሐፍቱ ተክሉ እና አንዱዓለም ሽፈራው አምስተኛ እና ስድስተኛ ሆነው ተከታትለው ገብተዋል ። ከኋላቸው እነሱን እና ሌሎች ሁለት ኬንያውያን ሯጮችን ተከትሎም ለጀርመን ተሰልፎ የሚሮጠው ትውልደ ኢትዮጵያዊው አትሌት ዓማናል ጴጥሮስ በዘጠነኛ ደረጃ አጠናቋል ። ዓማናል የገባበት ሰአት በጀርመን ሯጮች ደረጃ የጀርመን ክብረወሰን በመሆኑ እጅግ መደሱትን በጀርመንኛ ቋንቋ ገልጿል ።

«2 ሰአት ከ4 ደቂቃ ከ20 ሰከንድ ለመግባት ነበር እቅዱ ። ግን ባስመዘገብሁት ሰአት እጅግ በጣም በጣም ደስተኛ ነኝ ። አሁን የገባሁበት ሰአት በዚህም አለ በዚያ የጀርመን ክብረወሰን ነው ። ያም በመሆኑ ምንም የማማርርበት ምክንያት የለም ። ደስተኛ ነኝ ። ድባቡ ፍጹም የማይታመን ነበር ። እንደዚያ ዐይቼም ዐላውቅም ። ሁሉም ነገር ዐየሩም፣ ድባቡም፤ አሯሯጮቹም  በጣም ጥሩ ነበሩ ። የሕዝቡ ድጋፍ ፤ ሁሉም ነገር የተሳካ ነበር ። በጣም በጣም ደስተኛ ነኝ ።»

ለጀርመን ተሰልፎ የሚሮጠው ዓማናል ጴጥሮስ ትውልዱ በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት ግድም በጦርነት ውስጥ ከነበረችው የትግራይ ክልል ነው ። ወላጅ እናቱ ጀርመን ውስጥ ተገኝተው ውድድሩን መከታተል አለመቻላቸው ቢከፋውም የቀጥታ ሥርጭቱን ግን ከርቀት ቢያንስ በኢንተርኔት እንዲከታተሉ አድርጓል ።  

«የቀጥታ ሥርጭቱን እናቴ እንድትከታተለው አድርጌያለሁ ። ሩጫውን ተመልክታለች ። እዚህ መምጣታ ባለመቻሏ ግን ከፍቶኛል ። በዚህም አለ በዚያ ባለፉት ሁለት ዓመት ከመንፈቅ ጦርነት ነበር ።  እሷም በጦርነት ቀጣና ትግራይ ውስጥ ነበረች ። ያኔ ላያትም ልደውልላትም አልችልም ነበር ። ያ በጣም የሚያሳዝን ነበር ። ግን ደግሞ አሁንም ቢሆን ጦርነት ቢኖርም እጅግ ቢከፋኝም ቢያንስ በሳምንት አንድ ጊዜ በስልክ ስለማገኛት ግን ደስተ ነኝ ። »

በቤርሊን ማራቶን ዓማናል ጴጥሮስ
በቤርሊን ማራቶን 9ኛ ደረጃ ይዞ ያጠናቀቀው ትውልደ ኢትዮጵያዊ የጀርመን ሯጭ ዓማናል ጴጥሮስ የገባሁበት ሰአት የጀርመን ክብረወሰን ነው ። ያም በመሆኑ ደስተኛ መሆኑን ገልጿል ።ምስል Roland Weihrauch/dpa/picture alliance

የመስከረም 7 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ከዓማናል በተጨማሪ ለጀርመን ተሰልፈው ትናንት ከተወዳደሩ ሯጮች መካከል፦ ሌላኛው ትውልደ ኤርትራዊ ጀርመናዊ ሯጭ ሣሙኤል ፍትዊ 18ኛ እንዲሁም ሔንድሪክ ፕፋይፈር 20ኛ ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል ።

እግር ኳስ

ባለፈው ዐርብ ቡሩንዲ አቅንተው አንድ እኩል የተለያዩት የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን (ሉሲዎቹ) ዛሬ ረፋድ ላይ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ልምምዳቸውን አከናውነዋል ። በአፍሪቃ ሴቶች ዋንጫ ማጣርያ ሁለተኛ ዙር የመልስ ጨዋታቸውንም  ከነገ በስትያ ማክሰኞ መስከረም 15 ቀን፣ 2016 በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ያደርጋሉ። ለሉሲዎቹ ከወዲሁ መልካም ውጤት እንመኛለን ።

ለአፍሪቃ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ከሳምንት በፊት ከቱኒዝያው ክለብ አፍሪቃ ጋርተ ተጫውቶ 2 ለ 0  ያሸነፈው የኢትዮጵያው የባሕር ዳር ከነማ ቡድን የመልሱን ጨዋታ የፊታችን እሁድ ያደርጋል ።  አበበ ቢቂላ ስታዲየም ውስጥ የመጀመሪያ ጨዋታውን ማሸነፉ ወደ ቀጣይ ዙር የማለፍ እድሉን እጅግ አለምልሟል ።  ባህርዳር ከነማ ከእሁዱ ጨዋታ በኋላ በሚኖረው ውጤት የቱኒዝያውን ቡድን የሚጥል ከሆነ በአፍሪቃ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳታፊ ይሆናል ።

በአፍሪቃ ሻምፒዮንስ ሊግ ሁለተኛ ዙር ማጣሪያ ጨዋታደግሞ ወደ ግብጽ አቅንቶ የነበረው የኢትዮጵያው ቅዱስ ጊዮርጊስ  ቡድን በአል አህሊ  የ3 ለ0 ሽንፈት ገጥሞታል ። ትናንት ምሽት ካይሮ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ውስጥ ቀደም ሲል ከተፈቀደው የዐሥር ሺህ ታዳሚ በተለየ 30 ሺህ ታዳሚ እንዲገባ መፈቀዱ ተዘግቧል ። የመልሱ ጨዋታ የፊታችን ዐርብ ይከናወናል ።

የሊቨርፑል አጥቂ ሞሐመድ ሳላህ
የሊቨርፑል አጥቂ ሞሐመድ ሳላህ በዎልቨርሀምፕተን ተጨዋቾች መሀልምስል David Blunsden/Action Plus/picture alliance

ፕሬሚየር ሊግ

የጳጉሜ 6 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የስፖርት ዘገባበእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያ ትናንት  ሼፊልድ ዩናይትድ በሜዳው አስደንጋጭ ሽንፈት አስተናግዷል።  በኒውካስትል ዩናይትድ ቡድን የ8 ለ0 ሽንፈት ገጥሞታል። ብራይተን በርመስን 3 ለ 1 አሸንፏል ። ሊቨርፑል ዌስትሀም ዩናይትድን 3 ለ1 ሲረታ አርሰናል ከቶትንሀም ሆትስፐር ጋር ሁለት እኩል ተለያይቷል ። ቸልሲ ቅዳሜ ዕለት ዳግም ሽንፈት አስተናግዷል ። በአስቶን ቪላ በሜዳው 1 ለ0 ተሸንፏል ። ማንቸስተር ዩናይትድ በርንሌይን በሜዳው 1 ለ0 አሸንፎታል። 46ኛው ደቂቃ ላይ ሮድሪን በቀይ ካርድ ከሜዳው ያጣው ማንቸስተር ሲቲ ኖቲንግሀም ፎረስትን 2 ለ0 ማሸነፍ ችሏል ። ግቦቹን በ7ኛው እና 14ኛው ደቂቃዎች ላይ ያስቆጠሩት ፊል ፎዴደን እና ኧርሊን ሆላንድ ናቸው ።

ቡንደስሊጋ

በጀርመን ቡንደስሊጋ፦ አይንትራኅት ፍራንክፉርት ከፍራይቡርግ ያለምንም ግብ ተለያይተዋል ። ባዬርን ሌቨርኩሰን ሐይደንሀይምን 4 ለ1 ረትቷል ። ቅዳሜ ዕለት በነበሩ ጨዋታዎች፦ ባዬርን ሙይንሽን ቦሁምን 7 ለ0 ድል አድርጓል ። ቦሩስያ ዶርትሙንድ ቮልፍስቡርግን 1 ለ0 አሸንፏል ። ኮሎኝ በቬርደር ብሬመን የ2 ለ1 ሽንፈት ገጥሞታል።  ሆፈንሀይም ዑኒዮን ቤርሊንን 2 ለ0 ሲያሸንፍ ፤ ላይፕትሲሽ ቦሩሲያ ሞይንሽንግላድባኅን በጠበበ የግብ ልዩነት 1 ለ0 አሸንፏል ። ማይንትስ በአውግስቡርግ የ2 ለ1 እንዲሁም ዳርምሽታድት በሽቱትጋርት የ3 ለ1 ሽንፈት አስተናግደዋል ።

 ፍራይቡርግ ከቦሩስያ ዶርትሙንድ ጋር
በጀርመን ቡንደስሊጋ ፍራይቡርግ ከቦሩስያ ዶርትሙንድ ጋ ሲጫወት፤ ኳስ ፍራይቡርግ መረብን ነክታምስል Tom Weller/picture alliance/dpa

አዲሱ የጀርመን ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ

ከተደጋጋሚ ሽንፈት በኋላ በተባረሩት ዲተር ሐንሲ ፍሊክ ምትክ የተሾሙት አዲሱ የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ዩሊያን ናግልስማን ውጤታማ ሊሆኑ እንደሚችሉ በርካቶች ገምተዋል ። የጀርመን እግር ኳስ ፌዴሬሽን የቀድሞው ኃላፊ ዖሊቨር ቢርሆፍ አዲሱ አሰልጣኝ ዩሊያን ናግልስማ፦ «ከጀርመን ጥቂት ምርጥ አሰልጣኞች አንዱ ናቸው» ሲሉ አሞግሰዋል ። የ37 ዓመቱ አሰልጣኝ የሀገራቸው ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን ከገባበት አጣብቂኝ እንዲያወጡ ይጠበቅባቸዋል ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር