1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሐምሌ 8 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ሐምሌ 8 2016

«ሦስቱ አናብስት» ትናንት የቀያዮቹ አጥርን መስበር አቅቷቸው ጥርስ አልባ ሆነው አምሽተዋል ። የ37 ዓመቱ አጥቂ ሊዮኔል ሜሲ በተጎዳበት የደቡብ አሜሪካው ኮፓ አሜሪካ ፍጻሜ ግጥሚያ አርጀንቲና ኮሎምቢያን አሸነንፋ ዋንጫ ወሰደች ። ከሁለት ሳምንት በታች በቀረው የፓሪስ ኦሎምፒክ የምርጫ ጉዳይ ከኢትዮጵያውያን አትሌቶች አሰልጣኞች ቅሬታ ተሰምቷል ።

https://p.dw.com/p/4iLHy
የዩሮ 2024 ዋንጫን ስፔን እንግሊዝን 2 ለ1 አሸንፋ ወሰደች
የዩሮ 2024 ዋንጫን ስፔን እንግሊዝን 2 ለ1 አሸንፋ ወሰደችምስል Kai Pfaffenbach/REUTERS

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

«ሦስቱ አናብስት» ትናንት የቀያዮቹ አጥርን መስበር አቅቷቸው ጥርስ አልባ ሆነው አምሽተዋል ። እንግሊዞች እጅግ የተማመኑባቸው ጁድ ቤሊንግሀምም ሆነ ሔሪ ኬን ትናንት የስፔን ቀዩ የብረት አጥርን ማለፍ ተስኗቸው ቀርተዋል።  ሦስቱ አናብስት፦ የብዙኃኑ የእንግሊዞች ሕልምን ማሳካት በተሳነባቸው ምሽት ስፔኖች ፈንጥዘዋል ።ስፔንን ለድል ያበቁት ሁለቱ የዘር ሐረጋቸው ከአፍሪቃ የሚመዘዝ ተጨዋቾች  እንደተለመደው በሽቱም ገንነው ወጥተዋል ። ትንታኔ ይኖረናል ። በደቡብ አሜሪካው ኮፓ አሜሪካ ዋንጫ የ37 ዓመቱ አጥቂ ሊዮኔል ሜሲ እያነባ ከሜዳ ቢወጣም፤ ዋንጫውን ሲያነሳ ግን ቦርቋል ። ከሁለት ሳምንት በታች በቀረው የፓሪስ ኦሎምፒክ የምርጫ ጉዳይ ከኢትዮጵያውያን አትሌቶች አሰልጣኞች ቅሬታ ተሰምቷል ። የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ፤ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እና አሰልጣኞችን አነጋግረናል ።

እግር ኳስ

«ዘንድሮ እግር ኳስ ወደ ምንጩ ይመለሳል» ። ይህ ምኞት «ሦስቱ አናብስት» በሚል የሚጠራው የእንግሊዝ ቡድን አብዛኛ ደጋፊዎች ምኞት ነበር ። ነበር ። ከምኞት ግን ሊዘል አልቻለም ።  የእንግሊዝ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን አሰልጣኝ ጋሬት ሳውዝጌት የስፔን ቡድን በፍጻሜውም ሆነ በአጠቃላይ ውድድሩ ምርጥ እንደነበር መስክረዋል ። ምንም እንኳን የሚያሰለጥኑት ቡድናቸው መራር የሽንፈት ጽዋን ቢጨልጥም፤ የስፔን ተጨዋቾችን እጅግ አድንቀው፦ «እንኳን ደስ ያላችሁ» ምኞት አስተላልፈዋል ።  ቡድናቸው ለምን ሽንፈት እንደገጠመውም ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አብራርተዋል ።

«በቡድኑ ተጨዋቾች እጅግ ኮርቻለሁ የተቻላቸውን ጥረዋል ለሀገራቸው ከእዚህ በላይ ምንም ሊያደርጉ አልቻሉም   የተሸነፍነው በተሻለው ቡድን ነው እንዴት ሊሆን ቻለ የሚለውን መገምገሙ ላይ ማተኮር ይሻለናል ግን ደግሞ ጨዋታው አእምሮዬ ውስጥ እጅግ ግልጽ ነው   ቀደም ብዬ እንደተናገርሁት፦ ለእኔ ዛሬ ማታ ቁልፉ ኳስን መቆጣጠር ነበር   በቂ ቁጥጥር አልነበረንም »

በእርግጥም አሰልጣኙ እንደጠቆሙት፦ ብዙ የተባለለት ጁድ ቤሊንግሀምም ሆነ አጥቂው ሔሪ ኬን አለያም በክንፍ በኩል የተከላካዮች ጭንቅ በመሆን የሚታወቀው ቡካዮ ሳካ እንግሊዝን ሊታደጉ አልቻሉም ።

በአንጻሩ ስፔን እንግሊዝን ትናንት 2 ለ1 ስታሸንፍ፦ «ቀዩው» በሚል የሚጠራው የስፔን ቡድንን ለድል ያበቁት ሁለት ወሳኝ ተጨዋቾች በመላው ዓለም የስፖርት አፍቃሪያን ዘንድ መነጋገሪያ ሆነዋል ።  ሁለቱ ቤተሰቦቻቸው ከአፍሪቃ የሆኑ ተጨዋቾች በእርግጥም የምሽቱ ከዋክብት ነበሩ ። ላሚን ያማል እና ኒኮ ዊሊያምስ ። ላሚን ከኢኳቶሪያል ጊኒ እና ሞሮኮ ወላጆች ነው የተወለደው ። ሌላኛው የስፔን ድንቅ፦ ኒኮ ዊሊያምስ ደግሞ የተወለደው አሰቃቂውን የሰሐራ በረሃ አቋርጠው ስፔን አዲስ ሕይወት ከጀመሩ ጋናውያን ቤተሰቦች ነው ።

 ላሚን ያማል እና ኒኮ ዊሊያምስ
የስፔን ቡድንን ለድል ካበቁት ወሳን ተጨዋቾች መካከል ሁለቱ በመላው ዓለም የስፖርት አፍቃሪያን ዘንድ መነጋገሪያ ሆነዋል ።  ሁለቱ ቤተሰቦቻቸው ከአፍሪቃ የሆኑ ተጨዋቾች በእርግጥም የምሽቱ ከዋክብት ነበሩ ። ላሚን ያማል እና ኒኮ ዊሊያምስ ምስል Andre Weening/Orange Pictures/Imago Images

ያም ብቻ አይደለም ግቦቹም ሆኑ የአውሮጳ ዋንጫ ድሉ ለሁለቱም ተጨዋቾች የልደት ቀን ስጦታ ሆኖም ነው የቀረበው ማለት ይቻላል ። ላሚን ያማል 17ኛ የልደት ቀኑን ባከበረ በነጋታው ስፔን እንግሊዝን 2 ለ1 አሸንፋ ለአውሮጳ ዋንጫ ድል እንድትበቃ አስችሏል ። ቀዳሚዋን ግብ በ47ኛው ደቂቃ ላይ ኒኮ ዊሊያምስ እንዲያስቆጥር አመቻችቶ የሰጠው ይኸው በዩሮ ታሪክ ትንሹ ተጨዋች ላሚን ነው ። ቀዳሚዋን ግብ ያስቆጠረው ኒኮ ዊሊያምስ 22ኛ የልደት በዓሉን ያከበረው ከዋንጫ ጨዋታው ሁለት ቀን ቀደም ብሎ ዓርብ ዕለት ነበር ።

ሌላው አስደማሚ ነገር፦ ላሚን ያማል የዛሬ 17 ዓመት ጨቅላ ሳለ ቤተሰቦቹ በደረሳቸው የእጣ አጋጣሚ ላሚን ከሊዮኔል ሜሲ ጋ ፎቶ እንዲነሳ መደረጉ ነው ። የያኔው ባለ ረጅም ፀጉሩ የ20 ዓመቱ ወጣት ሊዮኔል ሜሲ እና የወራቶች እድሜ ብቻ የነበረው ጨቅላው ላሚን ያማል እጅግ ተደስተው ሲስቁ ይታያል፥ በዚያ ታሪካዊ ፎቶ ላይ ። ሁለቱን የዛሬ 17 ዓመታት እንዲህ ያስፈገጋቸው ፥ ከ17 ዓመታት ወዲህም በተመሳሳይ ቀን ይደገማል ብሎ ማን አሰበ? የሊዮኔል ሜሲ አርጀንቲና ኮሎምቢያን በፍጻሜው አንድ ለዜሮ ድል አድርጋ የደቡብ አሜሪካውን ኮፓ አሜሪካ ዋንጫ ትናንት አንስታለች ። እነ ላሚን ያማልም ትናንት መላ ስፔንን አስፈንጥዘዋል፤ በዋንጫ ድል ።

ባለ ረጅም ፀጉሩ ወጣት ሊዮኔል ሜሲ ከጨቅላው ላሚኔ ያማል
ባለ ረጅም ፀጉሩ ወጣት ሊዮኔል ሜሲ ከጨቅላው ላሚኔ ያማል ጋር ። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2007 የባርሴሎናውን ኮከብ ለማግኘት በተደረገ እጣ የላሚኔ ያማል ወላጆች አሸንፈው ነበር ከሊዮኔል ሜሲ ጋ ፎቶ የተነሱት ። አሁን ላሚኔ ያማልም ሆነ ሊዮኔል ሜሲ ሁለቱም በየአኅጉራቸው ሃገራቸውን ለድል አብቅተዋል ።ምስል Joan Monfort/AP Photo/picture alliance

አርጀንቲና የደቡብ አሜሪካ (ኮፓ አሜሪካ) ዋንጫን አሸነፈች

አርጀንቲና የደቡብ አሜሪካ (ኮፓ አሜሪካ) ዋንጫን ለ16ኛ ጊዜ አሸንፋ በማንሳት ክብረ ወሰን ሰብራለች። አርጀንቲና እሁድ ዕለት በፍጻሜው 1 ለ0 ያሸነፈችው ኮሎምቢያን ነው ። ለአርጀንቲና በሦስት ያለፈውን የዓለም ዋንጫ እና የማሸነፊያዋን ብቸኛ ግብ ያስቆጠረው ላውታሮ ማርቲኔዝ ነው ። በሺህዎች የሚቆጠሩ ቲኬት የሌላቸው ደጋፊዎች ወደ ስታዲየሙ ካልገባን በማለታቸው፦ ጨዋታው ለአንድ ሰአት ግድም ዘግይቶ ነበር የጀመረው ።

የዓለማችን ምርጡ የእግር ኳስ ተጨዋች ሊዮኔል ሜሲ የመጨረሻው ይሆናል የተባለለት የትናንቱ የፍጻሜ ግጥሚያ ላይ በጉዳት እስከ መጨረሺያው ባለመጫወቱ በእንባ ተውጦ ታይቷል ። የስምንት ጊዜ የዓለማችን ምርጥ የእግር ኳስ ተጨዋች ተብሎ በባሎን ዲዮር የተመረጠው የ37 ዓመቱ ሊዮኔል ሜሲ ከኮሎምቢያ ጋ በነበረው ግጥሚያ 36ኛው ደቂቃ ላይ ጉልበቱ ላይ ጉዳት ደርሶበት ነበር ። 65ኛው ደቂቃ ላይ ግን ኳሷን ተክትሎ አንድም ተጨዋች ሳይነካው ከኮሎምቢያው አጥቂ ሉዊስ ዲያዝ አጠገብ ወድቋል ።  ወዲያውም እያነከሰ፤ በእንባ ተውጦ ከሜዳ ወጥቷል ። ተቀያሪ ወንበር ላይ ሆኖም ፊቱን በሁለት እጆቹ መዳፍ ከልሎ እየተንሰቀሰቀ ሲያለቅስ ነበር ። ምናልባትም ይህ ለብሔራዊ ቡድኑ የመጨረሻው ጨዋታ ሊሆን ይችላል ተብሏል ። ለሌላኛው አርጀንቲናዊ የ36 ዓመቱ አንኼል ዲ ማሪያ ግን የትናንቱ የፍጻሜ ግጥሚያ የመጨረሻው ነበር ።

አርጀንቲና የደቡብ አሜሪካ (ኮፓ አሜሪካ) ዋንጫን አሸነፈች
አርጀንቲና የደቡብ አሜሪካ (ኮፓ አሜሪካ) ዋንጫን አሸነፈችምስል Charly Triballeau/AFP via Getty Images

በአርጀንቲና ሽንፈት የገጠማት ኮሎምቢያ ለሁለተኛ ጊዜ የኮፓ አሜሪካ ዋንጫን ለማንሳት የነበራት ሕልም በእነ ሊዮኔል ሜሲ መክኗል ። የኮሎምቢያ የትናንቱ ሽንፈት ከሁለት ዓመት ከመንፈቅ ግድም ወዲህ የመጀመሪያው ሆኖ ተመዝግቧል ። ኮሎምቢያ ሽንፈት የገጠማት እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በየካቲት 2022 በአርጀንቲና ነበር ። ቀጣይ የማጣሪያ ጨዋታ በመስከረም ወር የሚጠብቃት ኮሎምቢያ በ2026ቱ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያም ከምድቧ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች ። 

በጀርመን አስተናጋጅነት የተካሄደው የአውሮጳ እግር ኳስ ጨዋታ በአጓጊነቱ ቀጥሎ ትናንት በስፔን ድል ተጠናቋል ። ለዋንጫ ሲጠበቁ የነበሩት ጣሊያኖች ባልተጠበቀ መልኩ ሩብ ፍጻሜ እንኳ ሳይገቡ ተሰናብተዋል ። ጀርመን ግስጋሴው በስፔን ተገትቷል ። ፈረንሳይ እና ኔዘርላንዶች ወደ ኋላ ይቀራሉ ብሎ ማን ገመተ? እንግሊዝ ዘንድሮም ጫፍ ደርሳ፤ ሁለተኛ ደረጃ ይዛ ቀርታለች ። ተጨዋቾቿም ሆኑ ደጋፊዎቿ ዋንጫውን የጎሪጥ ዕያየዩ ዘንድሮም ለሁለተኛ ጊዜ አቀርቅረው ተመልሰዋል ። በቀጣይ ሁለተኛ ደርሰው ይቀራሉ ወይንስ ይሳካላቸው ዕሆን? ወይንስ ደግሞ ሌላ ታሪክ ይጻፍ ይሆን?

በዩሮ 2024 ፍጻሜ ስፔኖች ሲቦርቁ፤ እንግሊዞች አንገት ደፍተዋል
በዩሮ 2024 ፍጻሜ ስፔኖች ሲቦርቁ፤ እንግሊዞች አንገት ደፍተዋልምስል Allstar Picture Library Ltd/Sportsphoto/Imago Images

አትሌቲክስ 

የፓሪስ  ኦሎምፒክ ሊጀመር ከሁለት ሳምንት በታች ይቀረዋል ። በኢትዮጵያውያን አትሌቶች ምርጫ ግን ከወዲሁ ውዝግብ ተነስቷል ። የአንዳንድ አትሌቶች አሰልጣኞች መመረጥ የነበረባቸው አትሌቶች አለአግባብ ከተሳታፊነታቸው እንዲወጡ ተደርገዋል ሲሉ ቅሬታ አሰምተዋል ። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን 12 የምርጫ መስፈርቶች ያሉት የማራቶን ምርጫ  የተኪያሄደው በመስፈርቱ ነው ብሏል።  የስታዲየም ውስጥ ተፎካካሪ አትሌቶች ደግሞ በሚኒማ ሳይሆን ምርጫው ከ2023 እስከ 2024 ድረስ የዓለም አትሌቲክስ ባስቀመጠው መስፈርት ውጤታቸው ታይቶ ነው የተመረጡት ሲል አክሏል።  የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ በበኩሉ ከፓሪስ ኦሎምፒክ ምርጫ ጋ በተያያዘ በትናንትናው ዕለት መግለጫ መስጠቱት ጠቁሟል ። ከዚህ በኋላም ከተለያዩ መገናኛ አውታሮች በተናጠል ለሚቀርቡ ጥያቄዎች መልስ የማይሰጥ መሆኑን ለፓሪስ ወኪላችን ሐይማኖት ጥሩነህ ዐሳውቋል ።  #DWSports 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ