ስፔንን ለድል ያበቁት የዘር ሐረጋቸው ከአፍሪቃ የሚመዘዝ ተጨዋቾች
ሰኞ፣ ሐምሌ 8 2016ሁለቱም ከድሉ ዋዜማና 2 ቀን በፊት ልደታቸውን አክብረው ነበር
ስፔን በትናንትናው ዕለት እንግሊዝን በአውሮጳ እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ 2 ለ1 ድል ነስታ ስትቦርቅ ፥ የዘር ሐረጋቸው ከአፍሪቃ ከሚመዘዝ ቤተሰብ የተወለዱ ሁለት ተጨዋቾች ታላቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል ። ላሚን ያማል እና ኒኮ ዊሊያምስ ። ላሚን ከኢኳቶሪያል ጊኒ እና ሞሮኮ ወላጆች ነው የተወለደው ። ሌላኛው የስፔን ድንቅ፦ ኒኮ ዊሊያምስ ደግሞ የተወለደው አሰቃቂውን የሰሐራ በረሃ አቋርጠው ስፔን አዲስ ሕይወት ከጀመሩ ጋናውያን ቤተሰቦች ነው ።
ላሚን ያማል እና ኒኮ ዊሊያምስ
ያም ብቻ አይደለም ግቦቹም ሆኑ የአውሮጳ ዋንጫ ድሉ ለሁለቱም ተጨዋቾች የልደት ቀን ስጦታ ሆኖም ነው የቀረበው ማለት ይቻላል ። ላሚን ያማል 17ኛ የልደት ቀኑን ባከበረ በነጋታው ስፔን እንግሊዝን 2 ለ1 አሸንፋ ለአውሮጳ ዋንጫ ድል እንድትበቃ አስችሏል ። ቀዳሚዋን ግብ በ47ኛው ደቂቃ ላይ ኒኮ ዊሊያምስ እንዲያስቆጥር አመቻችቶ የሰጠው ይኸው በዩሮ ታሪክ ትንሹ ተጨዋች ላሚን ነው ። ቀዳሚዋን ግብ ያስቆጠረው ኒኮ ዊሊያምስ 22ኛ የልደት በዓሉን ያከበረው ከዋንጫ ጨዋታው ሁለት ቀን ቀደም ብሎ ዓርብ ዕለት ነበር ።
ላሚን ያማል ከሊዮኔል ሜሲ ጋ ፎቶ
ሌላው አስደማሚ ነገር፦ ላሚን ያማል የዛሬ 17 ዓመት ጨቅላ ሳለ ቤተሰቦቹ በደረሳቸው የእጣ አጋጣሚ ላሚን ከሊዮኔል ሜሲ ጋ ፎቶ እንዲነሳ መደረጉ ነው ። የያኔው ባለ ረጅም ፀጉሩ የ20 ዓመቱ ወጣት ሊዮኔል ሜሲ እና ጨቅላው ላሚኔ ያማል እጅግ ተደስተው ሲስቁ ይታያል በፎቶው ። የሊዮኔል ሜሲ አርጀንቲና የደቡብ አሜሪካውን ኮፓ አሜሪካ ዋንጫ ትናንት አንስታለች ። እነ ላሚን ያማል ደግሞ ትናንት ። ሁለቱን የዛሬ 17 ዓመታት እንዲህ ያስፈገጋቸው ከ17 ዓመታት ወዲህም በተመሳሳይ ቀን ይደገማል ብሎ ማን አሰበ? #DWSports
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ታምራት ዲንሳ