በጎሮዶላ ወረዳ የትምህርትና ጤና አገልግሎት ተቋርጧል
ቅዳሜ፣ መስከረም 5 2016በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ቦረና ስር በቅርቡ ተከልሎ የዞን መዋቅሩን በተቃወመው ጎሮ ዶላ ወረዳ የትምህርት እና ጤና አገልግሎት መቋረጡ ተነግሯል፡፡ነዋሪዎች በቅሬታቸው የጤና አገልግሎት በወረዳው ሙሉ በሙሉ መቋረጥ ክፉኛ እንዳስመረራቸው ነው የገለጹት፡፡እስካሁን የተማሪዎች ምዝገባ በወረዳው አለመከወኑም ተብራርቷል፡፡
የትምህርት መቋረጥ
“በጎሮ ዶላ ወረዳ ውስጥ ወደ 80 ትምህርት ቤቶች አሉ፡፡ አሁን ተማሪዎች የትምህርት ቤት መመዝገቢያ ጊዜያቸው ነበር፡፡ ግን እስካሁን አንድም ወደ ትምህርት ቤት በማምራት የተመዘገበ ተማሪ የለም፡፡” በቅርቡ ኦሮሚያ ክልልመጋቢት ወር 2015 ዓ.ም. ላይ ምስራቅ ቦረና የተሰኘ አዲስ የዞን መዋቅር ከጉጂ፣ ቦረና እና ባሌ ዞኖች በተውጣጡ ወረዳዎች ማዋቀሩን ተከትሎ በጎጂ ዞን ስር መተዳደር አለብን በሚል ተቃውሞ ከተነሳባቸው ወረዳዎች አንዱ በሆነው ጎሮዶላ ወረዳ እልባት ያላገኘውን አለመረጋጋት ተከትሎ የተማሪዎች ምዝገባ አለመጀመር አሳስቦናል ያሉ ወላጅ የሰጡን አስተያየት ነበር፡፡
ለደህንነታቸው ሲባል ስሜ አይጠቀስ ያሉን እኚህ አስተያየት ሰጪ እንደሚሉት በወረዳው የትምህርት ዝግጅት እስከ አሁን አልተጀመረም። ምክንያት ሲጠቅሱም “አንደኛ የወረዳው ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊን ጨምሮ በርካታ አመራሮች እስር ቤት ናቸው፡፡ መምህራንም በተፈጠረው አለመረጋጋት ደመወዝ እንኳ ስላልተከፈላቸው እና በርካታ የወረዳው መዋቅር ከስራ ውጪ መሆን ችግሩን እንድንጋፈጥ ዳርጎናል፡፡ አሁን ስጋታችን ልጆቻችንን ወደ ሌላ አከባቢ ወስደን እንዳናስተምር እንኳ መልቀቂያውን እንዴት እናገኝ የሚል ነው፡፡ ችግሩ መፍትሄ ይሻል፡፡”
ሌላው ሰባት ልጆችን አስተምራለሁ ያሉን በወረዳው የሃርቀሎ ከተማ ነዋሪ፤ “በጎሮዶላ ወረዳ አሁን ምንም አይነት የትምህርት አገልግሎት ዝግጅት የለም፡፡ አሁን ምዝገባ የሚጠናቀቅበት ወቅት ነበር፡፡ ግን አንድም ተማሪ አልተመዘገበም። ይህም የሆነው ከዞን መዋቅር ተቃውሞ ጋር ተያይዞ ሰራተኛ ወደ መስሪያ ቤቱ እየሄደ አይደለም፡፡ ይህ ችግር ለወራት እየቀጠለ ነው፡፡ ለመምህራን ደመወዝ አልተከፈለም፡፡ 81ዱም ትምህርት ቤቶች ከስራ ውጪ ናቸው፡፡ ይህ እንደማህበረሰብ ለትልቅ ችግር ዳርጎናል፡፡”
ነዋሪዎቹ ችግር ነው ብለው ለሚያነሱት ቅሬታ አስተያየት እና ማብራሪያ እንዲሰጡን ለአከባቢው ባለስልጣናት በተለይም ለጎሮዶላ ወረዳ አስተዳዳሪ እና ለምስራቅ ቦረና ዞን ምክትል አስተዳዳሪ እንዲሁም በተለያዩ መዋቅር ላይ ላሉ ኃላፊዎች ደውለን ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልሰመረም፡፡
ስማቸው እንዳይገለጽ ጠይቀው አስተያየታቸውን ያጋሩን አንድ የወረዳው ትምህርት ባለሙያ ግን፤ “የነበረን ዝግጅት መልካም የነበረ ቢሆንም አሁን ከዞን መዋቅር ጥያቄው ጋር በተያያዘ መምህራንና ተማሪዎች እንዲሁም ማህበረሰቡ ባጠቃላይ ጥያቄያችንን መንግስት በአግባቡ ሊመልስልን ይገባል በማለታቸው ምዝገባም ሆነ ምንም አይነት የትምህርት ዝግጅት የለም ።” ብለዋል፡፡
የጤና አገልግሎት መቋረጥ
ነዋሪዎቹ ከጤና አገልግሎት አሰጣጥ ጋርም ክፉኛ መፈተናቸውን ያነሳሉ፡፡ “በወረዳው ያሉ አምስቱም ጤና ጣቢዎች ዝግ ናቸው፡፡ ወላድ እናት ለጤና እክል እየተዳረገች ነው፤ እንደ ስኳር ያሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ያላቸው ሰዎችም ለችግር ተዳርገዋል። ምንም የጤና አገልግሎት የለም ፡፡ ሰሞኑን የጤና አገልግሎት በማጣታቸው ሶስት ወላድ እናቶች ሞተዋል፡፡ መድሃኒትም ተገዝቶ ወደ ወረዳው ስለማይመጣ ችግር ነው፡፡ እንደ ማህበረሰብ ፈታኝ የጤና አገልግሎት ችግር ውስጥ ነን፡፡”
አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ ጠይቀው አስተያየት የሰጡን የወረዳው የጤና ባለሙያ እንደሚሉትም የመዋቅር ውዝግቡን ተከትሎ በተነሳው አለመረጋጋት አሁን በወረዳው የጤና አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ተቋርጧል፡፡ “እንደ ወረዳው ያሉን አምስቱም ጤና ጣቢዎች አገልግሎት አይሰጡም፡፡ ለዚህ ደግሞ አንደኛው ችግሩ መድሃኒት የለም፡፡ ሌላው ለባለሙያዎች ደመወዝ እየተከፈለ አይደለም፡፡ ይህ ችግር በጤናው ዘርፍ የእናቶች በወሊድ የመሞት ችግር ከማስከተሉም በተጨማሪ፤ ክትትል የሚያስፈልጋቸው በሽታዎችን የሚከታተሉ ሰዎችን ለአስከፊ ችግር ዳርጓል፡፡ ይህ ችግር የነበረብን የጸጥታ ችግር ላይ በመዋቅር ውዝግቡ የተፈጠረ ነው፡፡”
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት መጋቢት 20 ቀን 2015 ዓ.ም. ምስራቅ ቦረና በሚል አዲስ መዋቅር መፍጠሩን ተከትሎ በተለይም በጉጂ ዞን ለህይወት መጥፋት እና ንብረት ውድመት ምክንያት የሆነ ተቃውሞ መነሳቱ አይዘነጋም፡፡ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ከዚህ ቀደም ስለችግሩ ተጠይቀው ``አዲሱ መዋቅር የተፈለገው ለጸጥታ ጥያቄዎች እልባት ለመስጠትና ልማትን ለማቀላጠፍ በመሆኑ ውሳኔው የማይቀለበስ ነው`` ማለታቸው አይዘነጋም፡፡
ስዩም ጌቱ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር