የፀጥታ ስጋት የፈጠረው ግጭት በጉጂ ዞን
ዓርብ፣ ሐምሌ 7 2015ከምስራቅ ቦረና ዞን ምስረታ ጋር ተያይዞ በነጌሌ ቦረና ከተማ ዙሪያ በአቅራቢያው በሚገኘው ጎሮ ዶላ ወረዳ አከባቢ አሁንም ለአከባቢው ጸጥታ ስጋት የሆነው አለመግባባት መቀጠሉ ነው የሚነገረው፡፡ በተለይም ሰኞ ለማክሰኞ አጥቢያ በዚሁ ወረዳ ኪሊዌ በምትባል ስፍራ ተሸከርካሪዎች መቃጠላቸውን ተከትሎ ለአከባቢው ፀጥታ ሌላው የራስ ምታት ሆኗል ነው የተባለው፡፡ ለደህንነታቸው ሲባል ስሜ ይቆይ ብለው አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የጎሮ ዶላ ነዋሪ በዚህ ሳምንት ለተፈጠረው የፀጥታ መደፍረስ ምክኒት ነው ያሉትን ሲያስረዱ፤ “በዚህ ሳምንት ከጎሮዶላ አመራሮችን ስብሰባ ብለው ወደ ነጌሌ ጠርተው ነበር፡፡ በዚያው በምን ምክኒያት እንደሆነ ባናውቅም አሰሩዋቸው፡፡ የወረዳው ህዝብ ይህን ሲሰማ 30 ኪ.ሜ ወደ ነጌለ ተጉዘው እንዲፈቱ ጠየቀ፡፡ የህዝቡ ጥያቄ እነዚህ አመራሮች የህዝብ ፍላጎትን መሰረት አድርገው የሚሰሩ ናቸው የሚል ነበር፡፡ ይሁንና የጸጥታ ሃይሎች ወዲያው መጥተው የሃይል እርምጃ በመውሰዳቸው ከዚያን ቀን ጀምሮ በርካታ ወጣቶች ወደ ከተማ ሳይሆን ወደ ጫካ ነው የገቡት” ብለዋል፡፡
እንደ ነዋሪው አስተያየት በእለቱ ከአዶላ ወዩ ወደ ነጌሌ ከተማ ሲጓዙ የነበሩ ሁለት ተሽከርካሪዎችም ተቃጥለዋል፡፡ “ሁለት ተሽከርካሪዎች መንግድ ላይ ተቃጥለዋል፡፡ በርግጥ ማን እንዳቃጠላቸው እኔ አላውቅም፡፡ በወረዳው አሁን እንቅስቃሴ ተገድቧል፡፡ በእየለቱ መንገድ ይዘጋል፡፡ የፀጥታ ሃይሎች እየዞሩ መንገድ ቢያስከፍቱም ወጣቱ ምን ሰዓት መንገዱን እንደሚዘጋ አታይም፡፡”
እኚህ አስተያየት ሰጪ ከአዲስ ዞን አወቃቀር ጋር ተያይዞ ህዝቡ ላለፉት አራት ወራት ቅሬታውን በተለያየ መልክ ሲገልጽ እንደነበር አስረድተዋልም፡፡
እንደ ሌላው ነዋሪ አስተያየት ደግሞ በወረዳው ቅሬታውን የማሳየት እንቅስቃሴ የተጀመረው ባለፈው ሰኞ እና ማክሰኞ በአዳማ የተካሄደው የጨፌ ኦሮሚ መደበኛ ጉባኤ ከመጀመሩም አስቀድሞ ነው፡፡ “የጎሮ ዶላ ወረዳ ምክር ቤት በጉጂ ዞን ስር ነው የምንተዳደረው ብለው ለጨፌ ኦሮሚያ አስቀድሞ ደብዳቤ ጽፎ ነበር፡፡ ግን ምላሽ አላገኙም፡፡”
ይህ ሁኔታ በአከባቢው ውጥረት በመፍጠሩ እንቅስቃሴዎች ክፉኛ ተገድበዋል ነው ያሉት፡፡ “ሾፌሮችና የተሸከርካሪ ባለንብረቶች አሁን ይፈራሉ፡፡ መንግስት መንገድ እንዲያስከፍትም ይጠይቃሉ፡፡
የጸጥታ ሃይሎች ደግሞ ሲመጡ ህዝቡን መንግድ ላይ አያገኙም፡፡ የመንግስት ሰራተኛም ሳይቀር ሂደቱን ተቃውመው ወደ ጫካ ገብተዋል፡፡”
ስማቸው እና ኃላፊነታቸው እንዳይገለጽ ጠይቀው አስተያየታቸውን የሰጡን የጎሮዶላ ወረዳ የመንግስት ሰራተኛ በፊናቸው፤ አሁናዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴ በአካባቢው ከዚህ በፊትም ለነበረው የጸጥታ ችግር ሌላው ራስ ምታትእንዳይሆን ያሰጋል ነው የሚሉት፡፡ “በጎሮ ዶላ አሁን አስከፊ የጸጥታ ችግር ነው ያለው፡፡ ተቃውሞን ያስከተለው የአዲሱ ዞን መዋቅርን ተከትሎ የወረዳ ካቢኔን የሚያወያይ አካል ወደዚህ ብላክም ካቢኔው ህዝብ ያልተቀበለውን ለማስፈጸም እንቸገራለን በማለታቸው፤ መንግስት አንዴ ተወስኗል በሚል እየገፋበት ነው፡፡ አሁን ስጋቶች አሉ፡፡ ገልገሎ ኦዶ የተባሉ የጎሮዶላ ወረዳ አስተዳዳሪ በነጌሌ መታሰራቸውን ተከትሎ ውጥረት ነግሷል፡፡ እስር ማንገላታቱ እየከፋ ነው፡፡ ካቢኔ ሳይቀር አሁን ሰው ከከተማ ወደ ጫካ ገብተዋል ያሰጋል፡፡”
በዚህ አከባቢ ስለተነሳው ውዝግብ ማብራሪያ እንዲሰጡን ለአዲሱ ዞን ምስራቅ ቦረና ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ታጁራ ኦዳ ደጋግመን ብንደውልም ስብሰባ ላይ መሆናቸውን ገልጸው ስልካቸውን ዘግተዋል፡፡ ሰኞ በተካሄደው የጨፌ ኦሮሚያ ጉባኤ ላይ አንድ የምክር ቤቱ አባል የህዝቡ ጥያቄ ከዚህ አንጻር ሁለት ነው “አንደኛው ለ21 ዓመታት የጉጂ ዞን ከተማ ሆና ያገለገለችው ነጌሌ በዚያው እንዲቀጥልና ሁለተኛው የጎሮ ዶላ ህዝብ በጉጂ ስር እንተዳደር እያሉ ስለሆነ ጉዳይ ብታይ” ሲሉ ነበር ጥያቄያቸውን ያቀረቡት፡፡ የጨፌው አባል ውዝግብ እያስነሳ ያለው ይህ ጉዳይ ዳግም ብታይና ጥናት ብደረግ የሚል ምክረሃሳብም ሰጥተው ነበር፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ መልስ ሰጥተው የነበሩት በጨፌ የመንግስት ተጠሪ አቶ ፍቃዱ ተሰማ በዚህ አከባቢ የአዲስ ዞን መዋቅር ያስፈለገበት አንደኛው ምክኒያት የኦሮሞን ህዝብ አንድነት ለማጠናከር ነው ብለዋል፡፡ “ሁሉም ኦሮሞ ቦረና፣ ጉጂ፣ አርሲ አንድ ሆነው በጋራ የሚያስተዳድሩት፤ ባህል ማንነታቸውን በማሳደግ የሚመጣውን ልማት በጋራ የሚቋደሱበት እንጂ አንዱ ሌላውን የሚገፋበት፤ ከአንዱ ተወስዶ ለሌላ የሚሰጥ ነገር እንዳልሆነ ምክር ቤቱ ብረዳ መልካም ነው፡፡'' አሉ አቶ ፍቀቃዱ፡፡ አቶ ፍቃዱ በአከባቢው ያለውን የፀጥታ ችግር መፍታትም ዞኑ የተዋቀረበት ሌላኛው ዓለማ መሆኑንም አስረድተው ነበር፡፡
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በዚህ ኣመት መጋቢት ወር አጋማሽ ከቦረና፣ ባሌ እና ጉጂ ዞኖች የተወሰኑ ወረዳዎችን አቀናጅቶ ምስራቅ ቦረና የሚል ዞን መመስረቱ ይታወሳል፡፡ ይህን ተከትሎ ግን በተለይም ከጉጂ ዞን የተነሳው ተቃውሞ አሁንም ስጋት ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ይህ አዲስ የዞን መዋቅር ከቦረና ዞን ሞያሌ፣ ጉቺ እና ዋጪሌ ወረዳዎችን እንዲሁም ሞያሌ ከተማን፤ ከጉጂ ዞን ሊባን፣ ጉሚ ኤልደሎ፣ ጎሮዶላ ወረዳዎች እና ነጌሌ ከተማን፤ እንዲሁም ከባሌ ዞን መዳወላቡ፣ ኦቦርሶ እና ሃራና ቡሉቅ ወረዳዎችን ያካተተ መሆኑም ተገልጾ ነበር፡፡ አስቀድሞ የጉጂ ዞን መቀመጫ ሆኖ ለዓመታት ያገለገለውና ሙግት ሲነሳበት የነበረው ነጌሌ ከተማ በአዲሱ መዋቅር የምስራቅ ቦረና ርዕሰ ከተማ ሆኗል፡፡ በአዲሱ መዋቅር መሰረት የጉጂ ዞን ርእሰ ከተማ ደግሞ ወደ አዶና ሬዴ ከተማ ተዘዋውሯል፡፡
ሥዩም ጌቱ
እሸቴ በቀለ
ነጋሽ መሐመድ