1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጀርመን ወደ ካቡል የጠረዘቻቸው የአፍጋኒስታን ስደተኞችና የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ተቃውሞ

ዓርብ፣ ነሐሴ 24 2016

የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመፈጸም የሚከሰሰው ታሊባን ወደሚያስተዳድራት አፍጋኒስታን ስደተኞቹን የማባረሩን እርምጃ አምነስቲ ኢንተርናሽናልን የመሳሰሉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በጥብቅ ተቃውመዋል። አምነስቲ በተለይ ጥረዛው በመጪው እሁድ በጀርመን የሚካሄደውን አካባቢያዊ ምርጫ ታሳቢ ያደረገና ዓለም አቀፍ ሕግጋትን የሚጥስም ነው ሲል ከሷል።

https://p.dw.com/p/4k74N
Abschiebungen
ምስል Michael Kappeler/dpa/pictrue alliance

ጀርመን ዛሬ ወደ ካቡል የጠረዘቻቸው የአፍጋኒስታን ስደተኞችና የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ተቃውሞ

ጀርመን 28 የአፍጋኒስታን ስደተኞችን ዛሬ ወደ ሀገራቸው ጠረዘች። የዛሬው ጥረዛ ታሊባን በአፍጋኒስታን ሥልጣን ከያዘ ከዛሬ ሦስት ዓመት ወዲህ የመጀመሪያው መሆኑ ተገልጿል። የጀርመን መንግሥት ቃል አቀባይ ሽቴፈን ሄበሽትራይት  ወደ ሀገራቸው የተባረሩትን 28 ንአፍጋናውያን የተፈረደባቸው ወንጀለኞች ናቸው ሲሉ ከመናገር ውጭ የፈጸሙት ወንጀል ምን እንደሆነ በግልጽ አለመናገራቸው ተዘግቧል። ሆኖም የጀርመን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ናንሲ ፌዘር እርምጃው ለጀርመን የደኅንነት ጉዳይ ነው ብለዋል።የተገን ጠያቂዎች ጥረዛ በጀርመን  

ምንም እንኳን ቃል አቀባዩ አፍጋናውያኑን ወደ ሀገራቸው ማባረሩ  ከወራት በፊት አንስቶ የታሰበበትና ሲሰራበትም የቆየ ጉዳይ መሆኑን ቢናገሩም እርምጃው የተወሰደው ግን  አንድ ሶሪያዊ ስደተኛ በምዕራብ ጀርመንዋ በዞሊንገን ከተማ በፈጸመው የስልት ጥቃት የሰዎች ሕይወት ባጠፋና ባቆሰለ በሳምንቱ ነው።በጥቃቱ የተገደሉትን ሦስት ሰዎችና የቆሰሉትንም የማሰብና ቤተሰቦቻቸውንም የማጽናናት ስነ ስርዓት ዛሬ ምሽት በከተማይቱ ይካሂዷል።

አፍጋናውያን ስደተኞች ወደ ካቡል ሲወሰድ
አፍጋናዊ ስደተኛ ወደ ካቡል ሲወሰድምስል picture alliance/dpa

አዲሱ የአውሮጳ ኅብረት የስደተኞች አቀባበል ስምምነትና ተቃውሞው

የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመፈጸም የሚከሰሰው ታሊባን ወደሚያስተዳድራት አፍጋኒስታን ስደተኞቹን የማባረሩን እርምጃ አምነስቲ ኢንተርናሽናልን የመሳሰሉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በጥብቅ ተቃውመዋል። ስደተኞች ከጀርመን ወደ አፍጋኒስታን መጠረዛቸውን በጥብቅ የተቃወመው  አምነስቲ በተለይ ጥረዛው በመጪው እሁድ በጀርመን የሚካሄደውን አካባቢያዊ ምርጫ ታሳቢ ያደረገና ዓለም አቀፍ ሕግጋትን የሚጥስም ነው ሲል ከሷል። በሀገሪቱ የሚያነጋግረው የፍልሰት ጉዳይ በመጪው እሁድ በምስራቅ ጀርመን በሚካሄደው አካባቢያዊ ምርጫ ቁልፍ ሚና ይጫወታል ተብሎ ይጠበቃል። ስለዛሬው ጥረዛና ተያዝዥ ጉዳዮች የበርሊኑን ነዋሪ ይልማ ኃይለ ሚካኤልን በስልክ አነጋግረነዋል።
ይልማ ኃይለ ሚካኤል 
ኂሩት መለሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ