በትግራይ በረሃብ ሰዎች እየሞቱ ነው
ሰኞ፣ መስከረም 21 2016ጦርነቱ ካስከተለው ውድመት ያላገገመችው ትግራይ ድርቅ እና ረሃብ ጨምሮ በተለያዩ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ አደጋዎች እየተፈተነች ነው። የትግራይ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ ያሰራጨው መረጃ እንደሚያመለክተው በአሁኑ ወቅት በትግራይ 27 ወረዳዎች በድርቅ የተመቱ ሲሆን፥ ከፍተኛ የውኃ እና የእንስሳት መኖ እጥረትም መከሰቱ ይገልፃል። የክረምቱ ወቅት ዘግይቶ መጀመር እና ቶሎ መቋረጥ፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ በከፍተኛ መጠን የዝናብ እጥረት መከሰት ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ ቢሮው አመክክቷል። ድርቁ የተከሰተው በደቡብ፣ ደቡብ ምሥራቅ እና ምሥራቅ ዞኖች መሆኑ የክልሉ አስተዳደር መረጃ ያመለክታል። በትግራይ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ የኮምኒኬሽን ዳይሬክተሩ አቶ ሚኪኤለ ምሩፅ ለዶቼቬለ እንዳሉት ድርቁ ያሰሰከተላቸው ችግሮች በድርቁ በተጎዱ አካባቢዎች መታየት ጀምሯል።
የዕርዳታ ጅማሮ
በአሁኑ ወቅት ከተከሰተው ድርቅ በተጨማሪ በትግራይ ከፍተኛ የረሃብ አደጋም እየታየ ሲሆን፥ በቅርቡ የትግራይ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮምሽን እንደገለፀው ባለፉት 11 ወራት ከ1,320 በላይ ስዎች በትግራይ በረሃብ ምክንያት ሞተዋል። ዓለም አቀፍ ለጋሾች ያቀርቡ የነበረውን የምግብ ድጋፍ ማቋረጣቸውን ተከትሎ አደጋው እየከፋ መምጣቱን የሚያነሱት በትግራይ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮምሽን የቅድመ ጥንቃቄ እና ፈጣን ምላሽ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ገብረእግዚአብሔር አረጋዊ በረሃብ የሚሞቱ ዜጎች ለመታደግ የትግራይ አስተዳደር ከፌደራሉ መንግሥት ጋር በጋራ እየሠራ መሆኑ እና የፌደራሉ መንግሥት በትግራይ ላሉ እርዳታ ፈላጊዎች ከ126 ሺህ ኩንታል በላይ የሚሆን የምግብ እርዳታ ድጋፍ ማቅረቡን ገልፀዋል። አቶ ገብረእግዚአብሔር «ከሁለት ወር በፊት 31.08 ሺህ ኩንታል የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ወዳሉባቸው 17 ወረዳዎች በቀጥታ አድርሰን ነበር። አሁን ደግሞ በሁለተኛ ዙር ስንዴ፣ ዱቄት፣ ፋፋ፣ ዘይት እና ሌሎች ያለበት በአጠቃላይ 126,415 ኩንታል የምግብ እርዳታ ተመድቦ እህሉ ወደ ትግራይ መግባት ጀምሯል። ይሄም በዋነኛነት ለተፈናቃዮች ነው የሚውለው። ይህ ድጋፍ በአንድ ወር ኮታ ከፍለን ስናየው ለ745 ሺህ እርዳታ ፈላጊ ወገኖች የአንድ ወር ቀለብ ይሆናል። ድጋፉ የሚበረታታ ቢሆንም፥ ካለው የእርዳታ ፈላጊ እና የተፈናቃዮች ቁጥር አንፃር አነስተኛ ነው» ብለዋል።
ዓለም አቀፍ ለጋሾች እጃቸውን እንዲዘረጉ ስለመጠየቁ
ከዚህ በተጨማሪ በትግራይ ያለው ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ ከሚደረግ እንቅስቃሴ በተጨማሪ ዓለም አቀፍ ለጋሾች በትግራይ ለሚገኙ እርዳታ ፈላጊ ዜጎች ያቋረጡት ድጋፍ እንዲቀጥሉ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑ ተገልጿል። «እርዳታ አቅራቢዎች የተቋረጠው ድጋፍ እንዲቀጥሉ መጥራት ብቻ ሳይሆን የሚያስፈልጉ ዝቅተኛ መመዘኛ ለሟሟላት እየሠራን ነው። እነሱም ይህ እየተከታተሉ ነው። በቅርቡ ውሳኔ ያስተላልፋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ይሁንና ቁርጥ ያለ ቀን ማስቀመጥ አይቻልም። በተለይም USAID በሀገር ደረጃ ያቋረጠው የምግብ ነክ ድጋፍ እንዲቀጥል ጥረቶች እየተደረጉ ነው። የሚጀምሩትን ጊዜ በተስፋ እየጠበቅን ነው» ሲሉ አቶ ገብረእግዚአብሔር አረጋዊ ጨምረው ገልፀዋል።
እንደ የትግራይ ክልል ግዚያዊ አስተዳደር መረጃ በትግራይ በአጠቃላይ 2.2 ሚልዮን ተፈናቃዮች ያሉ ሲሆን ለእነዚህ የሚሆን የምግብና ሌሎች ድጋፎች አቅርቦት፥ ከዓለም አቀፍ ለጋሾች ከተቋረጠ ከስምንት ወራት በላይ አልፏል። በዚህም በርካቶች እየሞቱ፣ ለበሽታ እየተጋለጡ መሆኑ ታውቋል።
ሚልዮን ኃይለሥላሴ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሔር
ሽዋዬ ለገሠ