ትግራይ፤ የተቋረጠዉ የምግብ እርዳታ እንዲቀጠል ተጠየቀ
ሰኞ፣ ሰኔ 19 2015በረሃብ ምክንያት የዜጎች ሞት እየቀጠለ መሆኑ በትግራይ የሚገኙ የሃይማኖት አባቶች ገለፁ። የሃይማኖት መሪዎቹ ዓለምአቀፍ የሰብአዊ እርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች እና ሌሎች ግብረሰናይ ተቋማት በትግራይ የሚታየው ግዜ የማይሰጥ ችግር በመገንዘብ የዜጎች ሕይወት ለማትረፍ እንዲሰሩ እና የተቋረጠው የምግብ እርዳታ አቅርቦትን እንዲያስቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የሃይማኖት መሪዎቹ በሰብአዊ እርዳታ ላይ ዘረፋ የፈፀሙ አካላት ለሕግ ሊቀርቡ እንደሚገባም አንስተዋል። ዶቼቬሌ ያነጋገራቸው በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የዓዲግራት ጳጳስ አቡነ ተስፋስላሴ መድህን ጦርነቱ ባስከተለው ከፍተኛ ውድመት እና ሌሎች ምክንያቶች በተለይም በትግራይ በርካታ ህዝብ እርዳታ ፈላጊ ሆኖ ያለ ቢሆንም አሁንም በቂ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ለህዝቡ እንዳልደረሰ ገልፀዋል። ይባስ ብሎ የሰብአዊ አቅርቦቱ መቋረጡ ደግሞ የነበረው ማሕበራዊ ቀውስ እንዲባባስ እንዳደረገው የሃይማኖት መሪው ተናግረዋል።
"በትግራይ ውስጥ ሁሉም ማለት በሚቻል፣ በሌሎች ክልሎች እንዲሁ ተረጂ የነበረ ህዝብ መጥፎ ሁኔታ ላይ ባለበት፥ የረድኤት ዘራፊዎች ለማግኘት ተብሎ ጠቅላይ የእርዳታ አቅርቦት መቆሙ ሕመም፣ ሞትና ከባድ ማሕበራዊ ችግር እያስከተለ ነው" የሚሉት የዓዲግራት ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳስ አቡነ ተስፋስላሴ መድህን " ይህ ከሁለተኛ ወይም ሶስተኛ ወገን ያገኘነው መረጃ አይደለም እየተናገርን ያለነው፣ ከእኛ ጋር እየኖረ ያለህዝብ እየደረሰበት ያለ ችግር እየተመለከትን ነው" ሲሉ አክለዋል።
የካቶሊካዊት ቤተክስርስቲያን መሪው ጨምረውም "ማሕበራዊ ችግሩ ካለው ወደ ከፋ ሁኔታ ሳይሸጋገር፥ ሁሉም በዓለም ያሉ እርዳታ ተቋማት መፍትሔ ማበጀት" እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል። ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጨምሮ ሌሎች የክርስትና እና አስልምና አብያተ እምነቶች ያካተተው የትግራይ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በበኩሉ ተመሳሳይ ጥሪ አስተላልፏል።
የትግራይ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አስተባባሪው መምህር አበበ ገብረእግዚአብሔር የእርዳታ ምግብ የዘረፉ አካላት ከመለየት እና ለሕግ ከማቅረብ ሂደት ጎን ለጎን የተቋረጠው ሰብአዊ እርዳታ እንዲቀጥል ጠይቀዋል። "አንድ ሌባ ለመያዝ ተብሎ የሺዎች ሕይወት ለአደጋ ማጋለጥ አይገባም" ሲሉ መምህር አበበ አክለው ገልፀዋል። እንደዓለም አቀፍ ተቋማት እና የክልሉ አስተዳደር ገለፃ በትግራይ ከአምስት ሚልዮን በላይ ህዝብ እርዳታ ጠባቂ ነው።
ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
አዜብ ታደሰ
ሸዋዬ ለገሠ