የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጥቃት የሱዳናዉያኑን ዕልቂት አባብሶታል
ቅዳሜ፣ ጥቅምት 23 2017በሱዳን የፈጥኖ ደራሽ ኃይል በደቡባዊ ምስራቅ ሱዳን በምትገኘው በአልጀዚራ ግዛት ውስጥ በሚገኙ በርካታ አካባቢዎች መጠነ ሰፊ ጥቃት ከፍቷል። ዓለማቀፍ የመገናኛ ብዙኃን የሱዳን የመብት ተሟጋቾች እና ነዋሪዎችን ዋቢ አድርገው እንደዘገቡት ከሆነ ከ120 በላይ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል፤ ሌሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ቆስለዋል። የመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ ኦቻ መረጃ እንደሚያሳየው ጥቃቱን ተከትሎ በግዛቲቱ ከ47 ሺ በላይ ነዋሪዎች ከቀዬአቸው ተፈናቅለዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለሞያዎች በአካባቢው የጦር ወንጀል ስለመፈጸሙ ሪፖርት አድርገዋል።
የከፋ ሰብዓዊ ቀውስ ያስከተለው የሱዳን ግጭት
የሰሞንኛው የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች የተከሰሱበት ዕልቂት አመት ከስምንት ወራት ገደማ ያስቆጠረው የሱዳን የርስ በርስ ጦርነት የተገደሉ ሰዎችን ቁጥር 25 ሺ አድርሶታል ።
የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎችን ወደ ብሄራዊ ጦሩ ለመቀላቀል የተደረገውን ሙከራ ተከትሎ በሁለቱ ጄኔራሎች በጄነራል አብዱል ፈታህ አልቡርሃን እና በጄነራል መሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ እና እነርሱ በሚመሯቸው ኃይሎች መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት ሱዳን በታሪኳ አይታው የማታውቀው ሰብአዊ እና ቁሳዊ ውድመት እንድታስተናግድ አስገድዷታል። ቀውሱ በሃገሪቱ የከፋ ረሃብ በመቀስቀስም ጭምር በዓለማችን ከጋዛ ቀጥሎ አስከፊ ሰብአዊ ቀውስ የተመዘገበበት ምድርም አድርጎታል።
በሱዳን የርስ በርስ ጦርነት ሦስት ሚሊዮን ሰዎች ከሀገር ተሰድደዋል
የሱዳን የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ከጥቂት ቀናት በፊት በአልጀዚራ ግዛት ከፈጸሙት ግድያ በፊት በወታደራዊ አዛዦች መካከል ውጥረት ነግሶ እንደነበር ዘገባዎች ያመለክታሉ ። ባለፈው ጥቅምት 10 ቀን 2017 ዓ/ም የፈጥኖ ደራሽ ቡድን የአንድ ቀጣና ወታደራዊ አዛዥ የነበረው አቡ አቅላ ኪክል እና እርሱ የሚመራቸው ወታደሮች ቡድኑን ከድተው ብሔራዊ ጦሩን መቀላቀላቸው በቡድኑ ውስጥ መከፋፈል ስለመፈጠሩ ማሳያ ነው ተብሎለታል።
የሱዳን ጦርነት፣ የሰላማዊ ሰዎች ፍዳ፣ የኬንያ መሪዎች አንድነት ፍፃሜ
ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ የፈጥኖ ደራሽ ኃይል ወታደሮች የአቡ አቂላ የትውልድ አካባቢ ላይ የብቀላ በትራቸውን ያሳረፉት ። እንደ ታዛቢዎች ገለጻ ከሆነ የቡድኑ ብቀላ አብዛኛውን ሰላማዊ ሰዎችን ዒላማ ያደረገ ነበር ።
የሱዳኑ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ፍቅራ የተሰኘ የልማት እና ጥናት ጋዜጣ እንደዘገበው፣ የበቀል እርምጃው መጀመሪያ ላይ የተፈጸመው ከግዛቱ ምስራቃዊ ክፍል በቂኪል የትውልድ ስፍራ ነዋሪዎች ላይ ነበር። የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በአካባቢው ለቀናት የቆየ ዘረፋ ሲፈጽም እንደነበረ የአይን ምስክሮች ተናግረዋል።
የቡድኑ አንድ ታጣቂ አንድን ታዳጊ «ሳያድግ ግደለው» እያለ ሲጮህ መመልከቱን የአይን ምስክሮች ተናግረዋል። ነዋሪዎች በጅምላ በከዳተኛነት መፈረጃቸው የጅምላ ጥቃት ሰለባ እንዲሆኑ ማስገደዱንም ነው ዘገባው ያመለከተው።
«እየተተኮሰብን ነው አምልጠን የወጣነው » ሊባኖስ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን
ታጣቂዎቹ በግዛቲቱ ታምቡል በተሰኘች ከተማ ጥቅምት 12 ቀን 2017 በአንድ ቀን 300 ሰዎችን ገደሉ። እንደ ዘገባው ከሆነ ታጣቂዎቹ አንድ ቀን አስቀድመው ሩፋ በተባለች ከተማ ወደ 100 የሚጠጉ ሰዎችን ገድለዋል። አሰቃቂው እርምጃቸው በዚህ ብቻም አላበቃ ሴቶችን እያስገደዱ ደፍረዋል ፤ ሴቶችን ጨምሮ በርካታ ሰዎችን አፍነው ወስደዋል ።
የልማት እና ጥናት ዘጋቢው እንደተመለከተው በቀጣዮቹ ቀናት በግዛቲቱ ከ100 በላይ ከተሞች እና መንደሮችን ወርረው ጥቃታቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል። በወሰዱት የበቀል እርምጃ ያeልረኩት ታጣቂዎቹ በግዛቲቱ ሰሜናዊ እና ማዕከላዊ ግዛቶች በመግፋት ብርቱ ሰብአዊ ጉዳት አድርሰዋል።
በሱዳን መሰል ለሰብአዊነት ያልራሩ ጥቃቶች አዲስ አልነበረም የሚሉት የሱዳን እና የደቡብ ሱዳን ፎረም ሊቀመንበር ማሪና ፒተር በ2 ሺዎቹ መጀመሪያ ላይ በዳርፉር ተመሳሳይ አሰቃቂ ድርጊቶች መፈጸማቸውን ያስታውሳሉ ።
በኢትዮ ሱዳን ድንበር አካባቢ ያሉ ስደተኞች ስሞታ
«በዚያን ጊዜም አስከፊ ጭካኔ ነበር። ሰዎች ተቃጥለዋል፣ ስደተኞች በጥይት ተደብድበዋል፣ ሰላማዊ ዜጎች ተሰቃይተዋል፣ ሴቶች በጅምላ ተደፍረዋል።»
በጭካኔ የተሞላው አስከፊው ድርጊት እንዲፈጸም የአ,ር ኤስ ኤፍ ተዋጊዎች አብዛኞቹ አፍላ ወጣቶች መሆናቸው እና የአደንዛዥ ዕጽ እና በመድሃኒት ተጽዕኖ ስር መሆናቸውን ባለሞያው በምክንያትነት ያነሳሉ ።
«እነዚህ ተዋጊዎች በጣም ወጣት ናቸው ፣ አንዳንዶቹም የሕፃናት ወታደሮች ናቸው፣ እናም መድኃኒቶችን በተለይም በዋናነት ሙሉ በሙሉ የተከለከሉ ሜታሞርፊኖች ነው የሚጠቀሙት»
አር ኤስ ኤፍ በሱዳን እያደረሰ ያለው እልቂት ሀገሪቱን በመቆጣጠር እና ግብርናውን በማሰናከል ላይ ብቻ የሚገታ አይደለም የሚሉት የሱዳን ጀርመን ትብብር የተሰኘ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት አባል የሆኑት አህመድ ኢሳም ይልቁኑ ከወታደራዊ ወደ ሲቪል አስተዳደር እንዲሸጋገር አጥብቆ የሚሻውን የሱዳንን ህዝብ በማስፈራራት ማስቆም ነው ።
አህመድ ኢሳም በሰላማዊ ሰዎች ላይ እየደረሰ ላለው እዕልቂት የብሄራዊ ጦሩንም ተጠያቂ ያደርጋሉ ። ጦሩ በተለይ ለሰላማዊ ሰዎች ከለላ ከመስጠት ይልቅ ለጥቃት እንዲጋለጥ አድርጓል በማለት ይተቻሉ ። ጦርነት የሚሸሸው ህዝብ ጥበቃ አይደረግለትም ፤ ይልቁኑ የአየር ኃይልን ጨምሮ የታጠቀውን ከሰላማዊ ሰው የማይለዩ ከባድ መሳሪያዎችን በመጠቀም ጭምር የህዝቡ ዕልቂት እንዲባባስ ጭምር ምክንያት ሆኗል ይላሉ ።
የሱዳን ግጭት በኢትዮጵያ የስደተኞችን ቀውስ አባብሷል
« ሠራዊቱ በዋናነት የአየር ኃይሉን ይጠቀማል። ነገር ግን ይህ ትክክለኛ የጦር መሣሪያ የታጠቀ ባለመሆኑ በሚያደርሰው ጥቃት ምክንያት በርካታ ሰላማዊ ሰዎች ይሞታሉ። በአጠቃላይ ሠራዊቱ በተለይም ጦርነቱን ለሶስተኛ ወገን ለመስጠት እየሞከረ እንደሆነ ይሰማኛል። በዚህ ላይ ምንም ልምድ ለሌላቸው ሰላማዊ ዜጎች፤ ስለዚህ ለእነዚህ ጭፍጨፋዎች ቢያንስ በከፊል ተጠያቂው ሠራዊቱ ነው”
ግጭት ጦርነቱን በቅርበት የሚከታተሉት ማሪና ፒተርም የጦርነቱ መገታት ተስፋ አልባነትን ተመልክተዋል።
የሱዳን የሰላም ውይይት በጀኔቭ
«በጦርነቱ ውስጥ ብዙ ቡድኖች እየተሳተፉ ነው። ከሁለቱም ወገኖች የሚዋጉ የጎሳ ሚሊሻዎች ከተቋቋሙ ቆይተዋል፣ ከቀድሞው አምባገነን ኦማር አልበሽር አካባቢም እስላማዊ ሚሊሻዎችን እያየን ነው፣ ስለዚህ ጦርነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ግራ የሚያጋባ እና የማብቃት እድሉ እየቀነሰ ይሄዳል»
ኢንተርናሽናል ክራይሲስ ግሩፕ (ICG)ም ጦርነቱ ሊቆም ስለሚችልበት ሁኔታ ብዙም ተስፋ የለውም። ጦርነቱ በተለይ ወደ ምስራቅ ሊዛመት እንደሚችል ቡድኑ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ባደረገው ትንታኔ አስታውቋል። እንደ ኢትዮጵያ፣ ቻድ እና መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ያሉ የጎረቤት ሀገራት አማፂ ቡድኖች በግጭቱ ውስጥ ላሉት ወገኖች የሚያደርጉትን ድጋፍ ከፍ ሊያደርጉ እንደሚችሉም ይታመናል።
ስደተኞች ወደ ኢትዮ ሱዳን ድንበር መንቀሳቀሳቸው
ተፋላሚ ኃይላት ግችቱን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ዕድላቸውን እያመነመኑ እንደሆነ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚታዩ ተጨባጭ ሁኔታዎች ያመለክታሉ። በሽምግልና ሂደት እና አሸማጋዮች ላይም ጥሬጣሬ እንዳለው አይ ሲ ጂ ጠቅሷል። በዚህ ላይ የግጭቱ አካላት አንዳንድ ጊዜ ከሩሲያ እና ከአረብ ሀገራት ከፍተኛ የውጭ ድጋፍ እያገኙ መሆኑ እየታየ ነው። ክልላዊ እና አለም አቀፍ ተዋናዮች አሁንም ሁለቱን ተፋላሚዎች መደገፋቸውን አላቆሙም ። ይህ ደግሞ ጦርነቱ ከመቆም ይልቅ የበለጠ እንዲራዘም እና የሱዳናዉያንን ሰቆቃ ማስቀጠሉ አይቀርም ።
ታምራት ዲንሳ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር