1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሱዳን የሰላም ውይይት በጀኔቭ

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 11 2016

የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬሽ ለዚህም ሁለት ምክኒያቶችንይጠቅሳሉ፤ “ አንደኛው የሁለቱ ጀኔራሎች ትግል ለህዝብ ግድ የሌለው የስልጣን ትግል መሆኑ ነው፤ ሁለተኛው በሱዳን ላይ ልዩ ፍላጎትና ጥቅም ያላቸው የውጭ አገሮች ጣልቃ መግባት ነው”ይላሉ።

https://p.dw.com/p/4ja2r
Sudans de-facto-Staatschef al-Burhan
ምስል Sudanesischer Übergangsrat/XinHua/dpa/picture alliance

የሱዳን የሰላም ውይይት በጀኔቭ


16 ወራት የዘለቀውን የሱዳንን የእርስ በእርስ ጦርነት  ለማስቆም ያለመ የሰላም ውይይይት ካለፈው እሮብ ጀምሮ  በጀኔቭ በመካሄድ ላይ ነው።፡ የሰላም ውይይቱን አሜሪካ፣ ከሳውዲ አረቢያና አስተናጋጇ ስዊዘርላንድ ጋር እንዳዘጋጀች የተነገረ ሲሆን፣ የመንግስታቱ ድርትና የአፍሪካ ህብረት፣ ግብጽና የተባበሩት አረብ ኤሚርቶች በታዛቢነት የተገኙበት መሆኑም ታውቋል።
የውይይቱ አላማዎችና የመሳካት እድላቸው
ውይይቱ የተኩስ አቁም ስምምነት ለመድረስ፣ የሰብአዊ እርዳታን ተደራሽ ለማድረግና የተደረሱ ስምምነቶችን ተግባራዊነት ለመቆጣጠር  የሚያስችሉ አሰራሮችን ለመዘርጋት አልሞ የተጠራ እንደሆነ ቢነገርም፤ ዋናዎቹ ተፋላሚዎች በተለይም የሱዳን ጦር ዋና አዛሽ ጀነራል ዓብዱልፈታሕ አልቡርሀን ቡድን በስብሰባው እንደማይገኝ መገለጹ ንግግሩ የሱዳንን ጦርነት በማስቆም በኩል ቢያንስ አሁን ተጨባጭ ውጤት ያስገኛል ተብሎ እንዳይጠበቅ አድርጎታል ። የሌላው ተፋላሚ ቡድን የፈጥኖ ደራሹ ጦር ዋና አዛዥ ጄነራል ሐምዳን ዳጋሎ ሉዕክ ግን በውይይቱ ሲሳተፉ ባይታዩም ለስብሰባው ጀኔቫ መግባቱን ተገልጿል።


የጀኔራል አልቡርሀን ቡድን በስብሰባው ያለመገኘት ምክንያቶች
ጄኔራል ዓልቡርሃን በስብስባው የማይሳተፉት ቀደም ሲል በተደረሱት ስምምነቶች መሰረት የጀነራል ዳጋሎ ሀይሎች በቅድሚያ ከከተሞች መውጣት አለባቸው በማለት እንደሆነ ተነግሯል ።፡ ቀድሞ በሱዳን የብሪታኒይ አምባሳደር የነበሩት ሰር ኒክ ካይ እንደሚሉት ጀነራል አልቡርሀን በውይይቱ ላለመሳተፍ ሌሎችንም ምክንያቶች ያቀርባሉ፤ “ አንደኛው የሱዳን የጦር ሀይሎችና መሪው ጀኔራል አልቡርሀን እራሳቸውን የሱዳን መንግስትና ተወካይ  አድርገው የሚወስዱ በመሆኑ ከጀኔራል ሃምዳን ዳጋሎ ጋር በአቻነት መታየታቸውንና ለስብሰባ መቀመጣቸውን ይቃወማሉ። ሁለተኛ የፈጥኖ ደራሹ ዋና አዛዥ ጀኔራል ሀምዳን ዳጋሎ  ደጋፊ ናት የሚሏት የተባበሩት አረብ ኤሚሪቶች በውይይቱ በታዛቢነት መሳተፏንም ይቃወማሉ”  በማለት አሁን ባለው የውይይት ማእቀፍ የታዛቢዎች ስብጥር ወደፊትም ለውይይት መምጣታቸውን እንደሚጠራጠሩ አስታውቀዋል።
ስብሰባው ግን ሁለቱ ተፈላሚ ወገኖች በሌሉበትም ቢሆን እንደቀጠለና በታዛቢነትና አደራዳሪነት የተሳተፉት ሀይሎች የችግሩን አስከፊነትና ውስብስብነት ላይ በመወያየት አማራጭ ሀሳቦችን እያንሸራሸሩና የሰብአዊ እርዳታ ሊደርስ በሚችልበት ሁኒታ እየመከሩ እንደሆነ ከስብሰባው የወጡ መግለጫዎች ይገልጻሉ።፡

ጀነራል አብዱፈታሕ አልቡርሐን
ጀነራል አብዱፈታሕ አልቡርሐንምስል AFP


የስብሰባው አዘጋጆችና ታዛቢዎች የጋራ መግለጫ
 
በስብሰባው አስተናጋጆችና ታዛቢዎች በጋራ የወጣውና በአሜሪካው  የሱዳን መልክተኛ  ሚስተር ቶም  ፕሪየሎ በ ኤክስ የግል ገጽ ይፋ የሆነው መግለጫ፤ በሱዳን የሰብአዊ እርዳታ እንዲደርስና በሁለቱ ወገኖች ያለው አለመግባባትና ቅራኔ እንዲበርድ እየሰሩ መሆኑን ቢያስታውቁም፤ ሁለቱን ወገኖች አቅርበው ማደራደር ግን እንዳልቻሉ ግልጽ አድረገዋል፡፡ “ ሁለቱም ወይም አንዱ ወገን በሌለበት ሁኒታ ሁለቱን ወገኖች በግምባር ማወያየትና መደራደር አልቻልንም” በማለት ዋና መልክተኛው  ውይይቱ የችግሩን ዋና ተዋናያን  ያላሳተፈ መሆኑን አምነዋል። በዚህም ምክንያት ብዙ ተጠብቆ ከነበረው በጀኔቫ የሱዳን የሰላም ውይይት ብዙ መጠበቅ እንደማይቻል ነው ብዙዎች የሚናገሩት።
 
የሱዳን አውዳሚ ጦርነት አባባሽ ምክንያቶች
 
በሱዳን የርስ በርስ ጦርነት እስከአሁን ከአስር ሚሊዮን ህዝብ በላይ እንደተፈናቀለና አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ ደግም ለገዳይ እረሀብ ተጋልጠው በሞት አፋፍ ላይ መሆናቸውን የመንግስታቱ ድርጅት ልዩ ልዩ ዘርፎች ያሚያወጧቸው ዘገባዎች ያመለክታሉ ። ሆንም ግን ህዝቡን እያጫረሱ ያሉትን የሱዳን ተፋላሚ ሀይሎች ወደ ድርድር ማምጣቱ ቀላል እንዳልሆነ የሚታይ ሲሆን፤  የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬሽ ለዚህም ሁለት ምክኒያቶችንይጠቅሳሉ፤ “ አንደኛው የሁለቱ ጀኔራሎች ትግል ለህዝብ ግድ የሌለው የስልጣን ትግል መሆኑ ነው፤ ሁለተኛው በሱዳን ላይ ልዩ ፍላጎትና ጥቅም ያላቸው የውጭ አገሮች ጣልቃ መግባት ነው” በማለት እነዚህ ነገሮች ባንድ ላይ  የሱዳንን ሰላም እሩቅ ያደረጉት መሆኑን ገልጸዋል።
                      
ገበያው ንጉሴ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር