1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የግንቦት 19 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ግንቦት 19 2016

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ዘንድሮ ስምንተኛ ሆኖ ያጠናቀቀው ማንቸስተር ዩናይትድ የዋንጫ ባለ ድሉ ማንቸስተር ሲቲን አሸንፎ የኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫን ወስዷል ። አጓጊ ሆኖ ዛሬ ማታ ስለሚጠናቀቀው በቡንደስሊጋው የመቆየት ወይንም የመሰናበት የመጨረሻ ግጥሚያም ዘገባ ይኖረናል ። የአትሌቲክስ እና የአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ ግጥሚያንም እንቃኛለን ።

https://p.dw.com/p/4gKTx
የባዬር ሌቨርኩሰን አማይ ግራኒት ሻቃ
የባዬር ሌቨርኩሰን አማካይ ተጨዋች ግራኒት ሻቃ ካይዘርስላውተርን 1 ለ0 በፍጻሜው አሸንፈው የወሰዱትን የጀርመን ዋንጫ ከፍ አድርጎምስል Frank Hoermann/SVEN SIMON/picture alliance

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ዘንድሮ ስምንተኛ ደረጃ ይዞ ያጠናቀቀው ማንቸስተር ዩናይትድ  የዋንጫ ባለ ድሉ ማንቸስተር ሲቲን አሸንፎ የኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫን ወስዷል ።  የፕሬሚየር ሊጉ የዋንጫ ተፎካካሪ የነበረው አርሰናል ባዶ እጁን ቀርቷል ። ተከታዩ ሊቨርፑል በዬርገን ክሎፕ ምትክ ሆላንዳዊ አዲስ አሰልጣኝ አስፈርሟል ። ወደ  ጀርመን ቡንደስሊጋ ለመግባት አለያም ከቡንደስሊጋው ለመሰናበት ሁለት ቡድኖች ዛሬ ማታ የሞት ሽረት ፍልሚያ ያደርጋሉ ። በዩጂን ዳይመንድ ሊግ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አሸነፊ ሆነዋል ።

አትሌቲክስ

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ፈረንሣይ ውስጥ ለሚካሄደው የዘንድሮ የፓሪስ 2024 ኦሎምፒክ ለመመረጥ የሚያደርጉት ጥረት ቀጥሎ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ለድል በቅተዋል ። እሁድ፤ ግንቦት 18፣ ቀን 2016 ዓ.ም ሄይዋርድ ፊልድ ውስጥ በተካሄደው የዩጂን ዳይመንድ ሊግ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አሸነፊ ሆነዋል ።

በእሁዱ ውድድር በ1500 ሜትር ሴቶች ርቀት አትሌት ድርቤ ወልተጂ (3:53.75) በመሮጥ 1ኛ ወጥታለች ። 5000 ሜትር ሴቶች ፉክክር ከ7ኛ በስተቀር ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ደረጃ ኢትዮጵያውያን ለድል በመብቃት ተከታትለው ገብተዋል ። በውድድሩም፦ 1ኛ የወጣችው ፅጌ ገብረሰላማ (14:18.76) ናት ። እጅጋየሁ ታዬ (14:.18.92) ተከትላት 2ኛ ስትወጣ፤ ፋሬወይኒ ኃይሉ (14:20.61) የ3ኛ ደረጃ አግኝታለች ። አይናዲስ መብራቱ (14:22.76) 4ኛ፤ ብርቄ ኃየሎም (14:23.71) 5ኛ፤ ሂሩት መሸሻ (14:33.44) 6ኛ እንዲሁም ሰናይት ጌታቸው (14:35.27)8ኛ ወጥተዋል ።በ10,000 ሜትር ሴቶች ፉክክር ጉዳፍ ፀጋይ (29.05.92) 2ኛ ደረጃ አግኝታለች ።

«የታላቁ ቦቆጂ ሩጫ» በሚል የሚጠራው የሩጫ ፉክክር ለሦስተኛ ጊዜ እሁድ ግንቦት 18፣ ቀን 2016 ዓ.ም ተካሂዷል ።
«የታላቁ ቦቆጂ ሩጫ» በሚል የሚጠራው የሩጫ ፉክክር ለሦስተኛ ጊዜ እሁድ ግንቦት 18፣ ቀን 2016 ዓ.ም ተካሂዷል ። ምስል Omna Tadel

«የታላቁ ቦቆጂ ሩጫ» በሚል የሚጠራው የሩጫ ፉክክር ለሦስተኛ ጊዜ እሁድ ግንቦት 18፣ ቀን 2016 ዓ.ም ተካሂዷል ። የኢፌድሪ ቱሪዝም ሚኒስቴር እና «ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ» በጋራ ባዘጋጁት የ12 ኪሎ ሜትር ውድድር ላይ 100 ወንድ እና 50 ሴት አትሌቶች ተካፍለዋል ። ከአዲስ አበባ ጭምር በቆጂ የተገኙ በአጠቃላይ 1500 ተሳታፊዎችም በውድድሩ ላይ ተሳታፊ ነበሩ ።

እግር ኳስ

በእንግሊዝ የኤፍ ኤ ካፕ የፍፃሜ ግጥሚያ ቅዳሜ እለት ማንቸስተር ዩናይትድ ማንቸስተር ሲቲን ሁለት ለአንድ በማሸነፍ ዋንጫውን ወስዷል ። በሚኬል አርቴታ እየሰለጠነ የዘንድሮ ፕሬሚየር ሊግ ዋንጫን ለጥቂት በማንቸስተር ሲቲ ለተነጠቀው አርሰናል ከዳር ተመልካች መሆኑ ለደጋፊዎቹ እጅግ የሚያስቆጭ ነው ። በፕሬሚየር ሊጉ የሚፈለገውን ውጤት ባለማምጣት በብርቱ ለሚተቹት የማንቸስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሐግ ደግሞ ስንብታቸው መሪር እንዳይሆን የማታ ማታ ያስገኙት ዋንጫ መጽናኛቸው ሆኗል ።

ፔፕ ጓርዲዮላ በሚቀጥለው የጨዋታ ዘመን ውላቸው ያበቃል ። ሊቨርፑል በበኩሉ ጀርመናዊው አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ ትናንት አንፊልድ ስታዲየም ውስጥ ስሜታዊ በሆነ መልኩ ተሰናብተዋል ። በወቅቱም እሳቸውን ማን እንደሚተካ በስታዲየሙ ድምፅ ማጉያ ይፋ አድርገዋል ። ሊቨርፑል የአዲሱ አሰልጣኙ ማንነትን ዛሬ በድረ ገጹ በይፋ አረጋግጧል ። ዬርገን ክሎፕን የሚተኩት የቀድሞ ፌዬኖርድ ሮተርዳም አሰልጣኝ የ45 ዓመቱ አርኔ ስሎት መሆናቸው ታውቋል ። የግንቦት 5 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሆላንዳዊው አሰልጣኝ በዘንድሮ የሆላንድ የመጀመሪያ ሊግ ማለትም ኤረዲቪ ቡድናቸው ከፒኤስ ቪ አይንድሆቨን ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ እንዲያጠናቅቅ አስችለዋል። አሰልጣኙ ለምን ያህል ጊዜ ውል በሊቨርፑል እንደፈረሙ ግን ቡድኑ ያለው ነገር የለም ። የባዬር ሌቨርኩሰን አሰልጣኝ ዣቪ አሎንሶ ወደ ቀድሞው ቡድኑ ሊቨርፑል በአሰልጣኝነት ሊመለስ ይችላል የሚል ግምት ነበር ። ሊቨርፑል የአይንትራኅት ፍራንክፉርት ተከላካይ ዊሊያም ፓቾ ላይ ዐይኑን ጥሏል ። የፌዬኖርድ ተከላካይ ዴቪድ ሀንኮንም ለማሰመጣት ፍላጎት እንዳለው ተዘግቧል ።

ፔፕ ጓርዲዮላ የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ዐይናቸውን ጨፍነው ሲስሙ
ፔፕ ጓርዲዮላ ቡድናቸው ማንቸስተር ሲቲ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2023 በፍጻሜው ኢንተር ሚላንን 1 ለ0 ካሸነፈ በኋላ የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ዐይናቸውን ጨፍነው ሲስሙምስል Mark Pain/empics/picture alliance

ሳውዝሐምፕተን ሊድስ ዩናይትድን ትናንት ዌምብሌ ስታዲየም ውስጥ 1 ለ0 አሸንፎ ወደ ፕሬሚየር ሊጉ ተመልሷል ። ሉቶን ታወን፤ በርንሌይ እና ሼፊልድ ዩናይትድ ከፕሬሚየር ሊጉ ተሰናብተዋል ። ከታችኛው ዲቪዚዮን ከሳውዝሐፕተን በተጨማሪ  ላይስተር ሲቲ እና ኢፕስዊች ቀደም ሲል ማለፋቸውን አረጋግጠዋል። ኢፕስዊች ወደ ፕሬሚየር ሊግ የተመለሰው ከ22 ዓመታት በኋላ ነው ።

ከቡንደስሊጋው ላለመውረድ እና ከታችኛው ዲቪዚዮን ለማደግ ብርቱ ፍልሚያ ዛሬ ማታ በዱስልዶርፍ ሜዳ ይኖራል ። ከቡንደስሊጋው 18 ቡድኖች 16ኛ ሆኖ በ33 ነጥብ ያጠናቀቀው ቦሁም በሁለተኛ ዲቪዚዮን የሦስተኛ ደረጃ ይዞ ከጨረሰው ዱስልዶርፍ ጋ ነው የመልስ ግጥሚያውን ዛሬ ማታ የሚያከናውነው ። ባለፈው ሐሙስ ግጥሚያ የሁለተኛ ዲቪዚዮኑ ዱስልዶርፍ የቡንደስሊጋው ቦሁምን ሦስት ለዜሮ በሆነ አስተማማኝ ውጤት ድል አድርጓል ። በደርሶ መልስ ግጥሚያ አሸናፊው የቀጣዩ የቡንደስሊጋ ፉክክክር ተሳታፊ ይሆናል ።

ከቡንደስሊጋው ኮሎኝ እና ዳርምሽታድት ቀድሞውኑ ተሰናብተዋል ። ከታችኛው ዲቪዚዮን ሳንክት ፓውሊ እና ሆልሽታየ‍ን ኪል አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ይዘው የዋናው ቡንደስሊጋ ቀጣይ ተሳታፊነታቸውን አረጋግጠዋል ።    

ባዬር ሌቨርኩሰን በጀርመን ዋንጫ ፉክክር ቅዳሜ እለት ካይዘርላውተርን አንድ ለዜሮ አሸንፎ ዘንድሮ ሁለተኛ ዋንጫውን ወስዷል ። ቀደም ሲል የቡንድስሊጋውን ዋንጫ በእጁ አስገብቷል ።  እስከ ሦስተኛ ቡንደስሊጋ ድረስ ያሉ ቡድኖች በሚጋጠሙበት የጀርመን ዋንጫ ባዬር ሌቨርኩሰን እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ1993 ወዲህ ዋንጫ ሲያነሳ ለሁለተኛ ጊዜ ነው ። ባዬር ሌቨርኩሰን በአንድ የጨዋታ ዘመን ሁለት ዋንጫዎችን መውሰድ ሲችል ደግሞ በታሪኩ ዘንድሮ የመጀመሪያው ነው ። አሰልጣኝ ዣቪ አሎንሶ ሦስተኛ ዋንጫ በአውሮጳሊግ ለማንሳት ያደረገው ግስጋሴ የተገታው በፍፃሜው በአታላንታ ቡድን ነው ። አጠቃላይ ውጤቱ የቀድሞ የሊቨርፑል ድንቅ ተጨዋች ለነበረው ስፔናዊው አሰልጣኝ ዣቪ አሎንሶ ከፍተኛ ብቃቱ የታየበት ነው ።

ባዬር ሌቨርኩሰን በጀርመን ዋንጫ ፉክክር ቅዳሜ እለት ካይዘርላውተርን አንድ ለዜሮ አሸንፎ ዘንድሮ ሁለተኛ ዋንጫውን ወስዷል ።
ባዬር ሌቨርኩሰን በጀርመን ዋንጫ ፉክክር ቅዳሜ እለት ካይዘርላውተርን አንድ ለዜሮ አሸንፎ ዘንድሮ ሁለተኛ ዋንጫውን ወስዷል ። ቀደም ሲል የቡንደስሊጋውን ዋንቻ እንዲህ አንስቶ ነበር ።ምስል Michael Probst/AP Photo/picture alliance

የአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ ግጥሚያ

የፊታችን ቅዳሜ  በአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ  የፍጻሜ የዋንጫ ጨዋታ የጀርመኑ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ከስፔኑ ሪያል ማድሪድ ጋ ይጋጠማል ። ባለፈው የውድድር ዘመን ከቦሩስያ ዶርትሙንድ ወደ ሪያል ማድሪድ በ108 ሚሊዮን ዶላር የተዛወረው የ20 ዓመቱ ጁድ ቤሊንግሀም ጉዳይ የቀድሞ ቡድኑን ሳያሳስብ አልቀረም ። ጁድ ከሪያል ማድሪድ ጋ ሆኖ የዘንድሮ የላሊጋውን ዋንጫ ከማንሳቱም ባሻገር ይኸው ለሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ የቀድሞ ቡድኑን ሊገጥም ወደ ዌብሌይ ስታዲየም ያቀናል ።  የቦሩስያ ዶርትሙንድ ስፖርት ኃላፊ ሠባስቲያን ኬህል ቅዳሜ ዕለት ዌብሌይ ውስጥ ጁድ ቤሊንግሀምን ለማግኘት እንደሚጥሩ ከወዲሁ ዐሳውቀዋል ።  ከዚህ ከቀደም በደንብ የምናውቀው ተጨዋች በመሆኑም እንዴት አድርገን ሜዳ ላይ እንደምንቆጣጠረው እናውቅበታለን ብለዋል ።

አውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው የ64 ዓመቱ የሪያል ማድሪድ አሰልጣኝ  ካርሎ አንቼሎቲ ዋናው ጉዳይ ተጨዋቾቻቸው ሜዳ ውስጥ በጨዋታው ዘና ማለታቸው መሆኑን ተናግረዋል ። በዚህም አለ በዚያ ግን፦ እንግሊዝ ዌምብሌይ ውስጥ በሚኖረው የዋንጫ ጨዋታ ሪያል ማድሪድ እንደሚያሸንፍ በርካቶች ከወዲሁ ገምተዋል ።  በኢንተርኔት በተደረገ ግምገማ ቦሩስያ ዶርትሙንድ አሸንፎ ዋንጫውን ይወስዳል የሚሉ ገማቾች ሪያል ማድሪድ ከሚሉት በሦስት እጥፍ ያንሳሉ ።

የሜዳ ቴኒስ

በሜዳ ቴኒስ ዘመን አይሽሬው ብርቱ ተፎካካሪ ራፋኤል ናዳል በፈረንሳይ ፍጻሜ የመጨረሻው ይሆናል የተባለለትን የመጀመሪያ ዙር የስንብት ጨዋታውን በፈረንሳይ መክፈቻ ከጀርመናዊው አሌክሳንደር ዜቬሬቭ ጋ አከናውኖ ሁለት ጊዜ 6 ለ3 እና 7 ለ6 ተሸንፏል ።

Spanien Madrid | Rafael Nadal
ምስል Oscar J. Barroso/AFP7/picture alliance

ከጥቂት ቀናት በኋላ 38 ዓመት ለሚሞላው ስፔናዊ የስንብት ስነስርዓት እንደማያደርግ ግን የፈረንሳይ ፌዴሬሽን ትናንት ዐስታውቋል። ምክንያቱ ደግሞ፦ የዓለማችን ምርጥ የሜዳ ቴኒስ ተጨዋች ራፋኤል ምናልባትም ከዛሬው ውድድር በኋላ ሌላ ግጥሚያ ላይም ሊሳተፍ ይችላል የሚል ነው ። ራፋኤል ናዳል የፈረንሳይ የሜዳ ቴኒስ ፉክክር ፍጻሜን ለ14 ጊዜያት በማሸነፍ ወደር የማይገኝለት ተጨዋች መሆኑን አስመስክሯል ። በአጠቃላይ የሜዳ ቴኒስ ፉክክር ደግሞ 22 ዋንጫዎችን ማንሳት ችሏል ።

በሜዳ ቴኒስ የፍጻሜ ውድድሮች 24 ዋንጫዎችን በማንሳት ቀዳሚው ሌላኛው የሜዳ ቴኒስ ብርቱ ተፎካካሪ ሠርቢያዊው ኖቫክ ጄኮቪች ዘንድሮ በፈረንሳይ ፉክክር ብዙም እንደማይጠበቅ ተዘግቧል ። ኖቫክ ሦስቱን ዋንጫዎች የወሰደው በፈረንሳይ የፍጻሜ ውድድሮች ነው ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

እሸቴ በቀለ