የጀርመን ጥምር መንግሥት ሲፈርስ ሀገሪቱ የተጣለባት የብድር ገደብ ሚና ምንድነው?
ረቡዕ፣ ኅዳር 4 2017ጀርመን የካቲት 15 ቀን 2017 ምርጫ ለማካሔድ ወስናለች። ከዚያ በፊት ግን በመጪው ታኅሳስ 7 ቀን 2017 በሥልጣን ላይ የሚገኘው መንግሥት በሀገሪቱ ምክር ቤት የመተማመኛ ድምጽ ይሰጥበታል። ምርጫ ቢካሔድ ክርስቲያን ሜርዝ የሚመሩት የክርስቲያን ዴሞክራቶች ኅብረት (CDU) ከ30 በመቶ በላይ ድምጽ ሊያገኝ እንደሚችል በሀገሪቱ የተካሔዱ የሕዝብ አስተያየት መጠይቆች ያሳያሉ። ቀኝ አክራሪው አማራጭ ለጀርመን (AfD) በሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ጀርመን ምርጫ ለማካሔድ ውሳኔ ላይ ከመድረሷ በፊት ሦስቱ ተጣማሪዎች ማለትም ሶሻል ዴሞክራቶች (SPD)፣ ነጻ ዴሞክራቶች (FDP) እና አረንጓዴዎቹ ባለፈው ሣምንት ረቡዕ ለአስቸኳይ ስብሰባ ተገናኝተው ነበር። ስብሰባው ለሁለት ሰዓታት ብቻ የዘለቀ ነው። የፋይናንስ ሚኒስትር የነበሩት ክርስቲያን ሊንድነር ከታቀደለት ጊዜ አስቀድሞ ምርጫ እንዲካሔድ ምክረ-ሐሳብ አቀረቡ።
መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልስ ምክረ-ሐሳቡን አልተቀበሉም። እንዲያውም የፋይናንስ ሚኒስትራቸውን ከሥልጣን አባረሩ። ከጋዜጠኞች ፊት ቀርበው የሀገሪቱ ፕሬዝደንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር የፋይናንስ ሚኒስትሩን እንዲያሰናብቱ መጠየቃቸውን ይፋ አደረጉ።
የመንግሥት ቀውስ በጀርመን፤ መንስኤው መዘዞቹና መጪው ምርጫ
መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልስ “በጣም ብዙ ጊዜ አስፈላጊ የሆነ ሥምምነት በአደባባይ በተፈጠሩ አለመግባባቶች እና ርዕዮተ ዓለማዊ ጥያቄዎች ተውጦ ቀርቷል። በተደጋጋሚ ፌድራል ሚኒስትር ሊንድነር አግባብነት በሌለው አኳኋን ሕግጋት አግደዋል” ሲሉ ተደምጠዋል።
“ብዙ ጊዜ ከፌድራል መንግሥቱ ይልቅ የራሳቸውን ፓርቲ ፍላጎት እና ጥቅም በሚያስከብር ጥቃቅን ስልቶች ተጠምደዋል” በማለት የፋይናንስ ሚኒስትራቸውን የተቹት ሾልስ “በተደጋጋሚ በእሳቸው ላይ የነበረኝን እምነት ሰብረውታል። በረዥም ድርድር ከደረስንበት የበጀት ሥምምነት ጭምር ራሳቸውን አግልለዋል” በማለት ተናግረዋል።
“ለቀጣይ ትብብር የሚሆን የእምነት መሠረት በመካከላችን የለም” ያሉት መራኄ መንግሥቱ “በዚህ መንገድ ከባድ የመንግሥት ሥራ ማከናወን አይቻልም” በማለት የፋይንስ ሚኒስትራቸውን እንዳባረሩ አስረድተዋል።
የሾልስን ውሳኔ ተከትሎ የሊንድነር ፓርቲ ከትራንስፖርት ሚኒስትሩ ፎልከር ቪሲግ በቀር ተሿሚዎቹን በሙሉ ከመንግሥት ውስጥ አስወጣ። በኃላፊነታቸው ለመቀጠል የወሰኑት ፎልከር ቪሲግ በአንጻሩ ከፓርቲያቸው ለቀቁ።
ይኸ ጀርመኖች ከሦስቱ ፓርቲዎች ቀለማት ወስደው በትራፊክ መብራት የሰየሙትን ጥምር መንግሥት አፈረሰው። ክርስቲያን ሊንድነር ፓርቲያቸው ከጥምር መንግሥቱ መውጣቱ ከተረጋገጠ በኋላ “ኦላፍ ሾልስ በሀገራችን አዲስ የኤኮኖሚ መነቃቃት እንደሚያስፈልግ መገንዘብ አልቻሉም” በማለት ተችተዋል።
“የዜጎቻችንን ኤኮኖሚያዊ ሥጋቶች ቸል ብለዋል። አሁንም ቢሆን ዜጎች በጀርመን ዳግም እንዲኮሩ መወሰድ የሚገባቸውን አስፈላጊ ውሳኔዎች እየተጠራጠሩ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።
በጀርመን መንግሥት ሲፈርስ በሀገሪቱ ያለፉት 75 ዓመታት ታሪክ የመጀመሪያው ነው። ሾልስ የሚመሩት ጥምር መንግሥት ከመነሾው ስኬታማ እና በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት የነበረው ቢሆንም ፓርቲዎቹ በሚያቀነቅኑት ርዕዮተ ዓለም አንዱ ከሌላው የራቁ በመሆናቸው በመካከላቸው ልዩነት ነበራቸው።
ጥምር መንግሥቱን የነቀነቀ የመጀመሪያው ጥያቄ የተነሳው የኦላፍ ሾልስ መንግሥት ያልተጠቀመበትን ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ ኤኮኖሚያዊ ጫና ማገገሚያ የተመደበ 60 ቢሊዮን ዩሮ ኢንዱስትሪዎችን ለማዘመን እና የከባቢ አየር ለውጥን ለመቋቋም ጥቅም ላይ ለማዋል የያዘውን ዕድቅ የሀገሪቱ ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ባገደበት ወቅት ነው። የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ከጥምር መንግሥቱ በጀት 60 ቢሊዮን (65 ቢሊዮን ዶላር) አጎደለ።
ከዚያ በኋላ ሦስቱ ፓርቲዎች መሥማማት አልሆነላቸውም። በዱስልዱርፍ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰር የሆኑት ሽቴፋን ማርሻል “የጀርመን ጥምር መንግሥት መጨረሻ የሚያስደንቅ ባይሆንም የፈረሰበት ጊዜ ግን አስገራሚ ነው” የሚል ዕምነት አላቸው።
“ባለፉት ሁለት ወራት በሦስቱ ተጣማሪ ፓርቲዎች መካከል ብዙ አለመግባባቶች፣ ውዝግቦች እና ግጭቶች ነበሩ” የሚሉት የፖለቲካ ፕሮፌሰር ለዚህ “የሚፈርስበትን ጊዜ ስንጠብቅ ነበር” በማለት “በመካከላቸው ከቁጥጥር ውጪ የሆነ ልዩነት” እንደነበር ያስረዳሉ።
ሦስቱ ተጣማሪ ፓርቲዎች በሚከተሉት ርዕዮተ ዓለም መሠረታዊ ልዩነት ያላቸው ናቸው። የመሀል ግራ ርዕዮተ ዓለም የሚያቀነቅኑት ሲሻል ዴሞክራቶች እና አረንጓዴዎቹ ለማኅበራዊ ፖሊሲ እና ለከባቢ ጥበቃ ከፍ ያለ ገንዘብ የሚያስፈልገው ጠንካራ መንግሥት እንዲኖር ይሻሉ።
በነጻ ገበያ የሚያምኑት ነጻ ዴሞክራቶች በአንጻሩ አቋማቸው ተቃራኒ ነው። ፓርቲው መንግሥት በልዩ ሁኔታዎች ብቻ በገበያው ጣልቃ የሚገባ እና ጥብቅ የፊስካል ፖሊሲ የሚከተል ሊሆን ይገባል የሚል አቋም አለው። በምረጡኝ ዘመቻ ወቅት የሀገሪቱን በጀት ለማመጣጠን እና በጀርመን ሕገ መንግሥት የተደነገገውን የብድር ገደብ ለማክበር ቃል ገብቷል።
የጀርመን ሕገ-መንግሥታዊ የብድር ገደብ ምንድነው?
ጀርመን በምትመራበት “መሠረታዊ ሕግ” ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት (GDP) ከ0.35 በመቶ በላይ እንዳትበደር ገደብ ተጥሎባታል። ባለፈው ዓመት የጀርመን አጠቃላይ ሀገራዊ ምርት (GDP) 4.128 ትሪሊዮን ዩሮ ነበር። በዚህ መሠረት ጀርመን መበደር የሚፈቀድላት 14.4 ቢሊዮን ዩሮ ገደማ ነው።
ገደቡ ሥራ ላይ የዋለው የሀገሪቱን ዕዳ የመቆጣጠር ፍላጎት የነበራቸው መራኂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ሥላጣን ላይ ሳሉ ነው። ገደቡ የዓለም የፋይናንስ ቀውስ በተከሰተበት ወቅት በከፍተኛ መጠን የጨመረውን የጀርመን የዕዳ ጫና ለመቀነስ አገልግሏል።
ከመንግሥት ቁጥጥር ውጪ የሆነ እና በሀገሪቱ የፋይናንስ አቅም ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል ተፈጥሯዊ አደጋ ሲያጋጥም ወይም ያልተለመደ አስቸኳይ ጉዳይ ሲኖር የተጣለው ገደብ ሊነሳ እንደሚችል የጀርመን መሠረታዊ ሕግ ይፈቅዳል።
ከዚህ ቀደም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በተከሰተበት ወቅት እና የዩክሬን ጦርነት ሲቀሰቀስ ይኸ ገደብ ተነስቶ ያውቃል። የጀርመን መሠረተ-ልማት አንገብጋቢ ጥገና ይሻል የሚል አቋም ያላቸው ገደቡ በድጋሚ ሊነሳ ወይም ፈጽሞ እንዲሰረዝ ይፈልጋሉ። መከራከሪያቸው ገደቡ ቢነሳ ጠቃሚ በሆኑ ስልታዊ ዘርፎች የሚደረግ መዋዕለ-ንዋይ ኤኮኖሚያዊ ዕድገት ያበረታታል የሚል ነው።
ሌሎች ጀርመን የምትከተለው ጥብቅ የፊስካል ፖሊሲ ለሀገሪቱ የረዥም ጊዜ ተዓማኒነት እና የገበያ እምነት ቁልፍ ነው በሚል ገደቡ እንዳይነሳ ይከራከራሉ። በዚህ መንገድ ጀርመን ስትበደር ባንኮች የሚስከፍሉት ወለድ ዝቅተኛ ሆኖ እንዲቆይ ያደርጋል። የገደቡ ደጋፊዎች እንደሚሉት የመንግሥት ካዝና የሚገጥሙትን ሥጋቶች በመቀነስ የግል መዋዕለ-ነዋይን ያበረታታል።
የጀርመኑ የክርስቲያን ዲሞክራቲክ ኅብረት በአውሮጳ ምርጫ ከፍተኛ ድምፅን አገኘ
መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልስን ጨምሮ ሶሻል ዴሞክራቶች እና አረንጓዴዎቹ የጀርመንን ኤኮኖሚ ለማነቃቃት እና አጀንዳዎቻቸውን ለማስፈጸም የብድር ገደቡ እንዲነሳ ፍላጎት ነበራቸው። የፋይናንስ ሚኒስትሩ በቀጥታ በሕገ መንግሥቱ የተካተተውን የዕዳ ገደብ የማንሳት ሥልጣን የላቸውም። ሥልጣኑ ቡንደስታግ ተብሎ ለሚጠራው የጀርመን የታችኛው ምክር ቤት የተሰጠ ነው። ሊንድነር እንደ ፋይናንስ ሚኒስትርነታቸው የነበራቸው ኃላፊነት የሀገሪቱን የበጀት ረቂቅ በምክር ቤቱ ድምጽ እንዲሰጥበት ማቅረብ ነበር። ክርስቲያን ሊንድነር ፈቃደኛ አልነበሩም።
ጥምር መንግሥቱ ከፈረሰ በኋላ ባወጡት መግለጫ “መራኄ መንግሥቱ በስተመጨረሻ የፌድራል መንግሥት የተጣለበትን የብድር ገደብ እንዳነሳ ጠይቀውኛል። ቢሮ ስረከብ ከፈጸምኩት ቃለ መሐላ ስለሚቃረን በዚህ መስማማት አልቻልኩም” ሲሉ ከሰዋል። የብድር ገደቡን የማንሳት እና ያለማንሳት ጉዳይ ግን ሊንድነር እንዳሉት በቃለ መሐላቸው የተካተተ አልነበረም።
በሙኒክ ፌድራላዊ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰሯ ያዝሚን ሪድል “ሦስቱ ተጣማሪዎች በተለያዩ አንኳር የፖለቲካ ጉዳዮች በጣም ይለያያሉ። በኤኮኖሚ ረገድ ሊበራል ፓርቲ እና ሶሻል ዴሞክራቶች አንዳቸው ከሌላው በጣም የተራራቁ ናቸው። ይኸ ደግሞ እንዴት ገንዘብ መውጣት አለበት? ለማን እንስጥ? በየትኛው ዘርፍ ወጪ እንቆጥብ? በሚሉ ጉዳዮች ላይ በእርግጠኝነት ችግር ይፈጥራል” በማለት አስረድተዋል።
“የሦስት ፓርቲዎች ጥምር መንግሥት ኖሮን አያውቅም” የሚሉት ያዝሚን ሪድል “ዳግም መመረጥ እና በሚቀጥለው ዓመት ጥሩ ድምጽ ማግኘት በሚፈልጉ ሦስት አጋሮች መካከል ሥምምነት መፍጠር ሁልጊዜም ከባድ ነው” ሲሉ ፈተናውን ያብራራሉ።
በተሰናባቹ ክርስቲያን ሊንድለር ምትክ ዮርግ ኩኪስ የጀርመን የፋይናንስ ሚኒስትር ሆነው ተሾመዋል። አዲሱ ተሿሚ የ2025 የጀርመን ፌድራል መንግሥት በጀት አጠቃላይ ምርጫ ከመካሔዱ በፊት እንደማይጸድቅ ተናግረዋል። ለ2025 ጊዜያዊ በጀት እንደሚዘጋጅ የገለጹት ዮርግ ኩኪስ መንግሥት ሁሉንም አስፈላጊ ወጪዎች እንደሚያወጣ እና ቃልኪዳኖቹን እንደሚፈጽም ቢናገሩም አዳዲስ ዕቅዶች ግን እንደሚዘገዩ አስታውቀዋል።
የጀርመን መንግሥት ቀውስ ውስጥ የተዘፈቀው በአሜሪካ ዶናልድ ትራምፕ ተፎካካሪያቸው ካማላ ሐሪስን አሸንፈው ወደ ዋይት ሐውስ መመለሳቸው በተረጋገጠበት ሣምንት ነው። ትራምፕ በምረጡኝ ዘመቻቸው አሜሪካ ከውጪ በምትሸምታቸው ሸቀጦች ላይ ከ10 እስከ 20 በመቶ ታሪፍ ሊጥሉ እንደሚችሉ አስታውቀዋል። ይኸ የጀርመን አምራቾችን በእጅጉ የሚያሳስብ ሆኗል።
ትራምፕ እንዳሉት እስከ 20 በመቶ የሚደርስ ታሪፍ ቢጥሉ እና የአውሮፓ ኅብረት ተመጣጣኝ እርምጃ ቢወስድ የቀጠናው ኤኮኖሚ በ1.3% ሊቀንስ እንደሚችል የጀርመን የኤኮኖሚ ኢንስቲትዩት ይፋ ማድረጉን ሬውተርስ ዘግቧል።
እሸቴ በቀለ