1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመንግሥት ቀውስ በጀርመን፤ መንስኤው መዘዞቹና መጪው ምርጫ

ማክሰኞ፣ ኅዳር 3 2017

በFDP ከጥምሩ መንግሥት መውጣት ምክንያት ጀርመን እስከ ሚቀጥለው ምርጫ ባለው የሽግግር ጊዜ የምትመራው በፓርላማው አብላጫ ድምጽ በሌላቸው በSPDና የአረንጓዴዎቹ ፓርቲዎች አናሳ መንግሥት ይሆናል። ምንም እንኳን አናሳው መንግሥት ካለ ተቃዋሚዎች ድጋፍ ሕጎችን ማሳለፍ ባይችልም የመንግሥቱን ስራዎች ግን ማከናወኑን ይቀጥላል

https://p.dw.com/p/4mw7E
Nach Ampel-Aus | Bundespräsident Steinmeier übergibt Entlassungsurkunde an Lindner
ምስል Kay Nietfeld/dpa/picture alliance

የመንግሥት ቀውስ በጀርመን፤መንስኤው መዘዞቹና መጪው ምርጫ

 ያለፈው የጀርመን አጠቃላይ ምርጫ አሸናፊ የጀርመን ሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ SPD፣ ከአረንጓዴዎቹና ከነጻ ዴሞክራቶቹ ፓርቲ በጀርመንኛ ምህጻሩ  FDP ጋር በጎርጎሮሳው ታኅሳስ 2021 ዓመተ ምኅረት ተጣምሮ የመሰረተው መንግሥት ሦስት ዓመት እንኳን ሳይደፍን የዛሬ ሳምንት ፈርሷል። ጥምሩ መንግሥት ሲመሰርት የተለያየ አቋም ያላቸው ሦስቱ ፓርቲዎች አንድ ላይ መዝለቅ መቻላቸው አጠራጣሪና አነጋጋሪም ነበር ። ውሎ አድሮም ይህ ሰበብ ሆኖ የተፈራው ደርሷል። ይህም ዱብ እዳ ሳይሆን ቀድሞም ሲገመት የነበረ በመሆኑ ለብዙዎች እንግዳ አልሆነም። ከመካከላቸው አንዱ ጀርመን የሚኖሩትና የሚሰሩት የፖለቲካ ሳይንስና የሕግ ምሁር ዶክተር ለማ ይፍራሸዋ አንዱ ናቸው።

 የጀርመን ምርጫ ውጤትና የአዲስ መንግሥት ምስረታ ዝግጅት


የSPDው መሪ መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ ቀደም ካሉት ጊዜያት አንስቶ ደጋግመው ሲቃወሙንና ውሳኔዎችን እንዳያልፉ ሲያደርጉ ታግሰናቸው ቆይተናል ካሏቸው የFDP መሪ ከጀርመን የፋይናንስ ሚኒስትር ክርስቲያን ሊንድነርን ጋር መስማማታት ባለመቻላቸው ባለፈው ሳምንት ከስልጣን አባረዋቸዋል። በተለይ በመጨረሻ ያልተስማሙትና ሊንድነርን ከስልጣን ከስልጣን ለመነሳት ያበቃቸው የጎርጎሮሳዊ 2025 የሀገሪቱ በጀት ጉዳይ ነበር። ዶክተር ለማ እንደሚሉት ሾልዝና ሊንድነር የማይስማሙባቸው ሌሎች ጉዳዮችም ነበሩ። ከመካከላቸው ጀርመን ለዩክሬን የምትሰጠው የብዙ ቢሊዮን ዩሮ ድጋፍ እንዲሁም ከኮሮና በኋላ ንረቱ የጨመረው የኑሮ ውድነት ይገኙበታል።  በጀርመኖቹ በዛክሰን አንሀልት እና ቱሪንገን ፌደራዊ ግዛቶች የተካሄደው ምርጫ ውጤትና መዘዙ

 

ሊንደር በተጠራቀመው ተቃውሞና አለመግባባት ባለፈው ሳምንት ከሥልጣን ሲባረሩ መንግስት እንዲፈርስ ምክንያት ሆኗል። ከዚያም መካሄድ ያለበት የፓርላማው የመታመኛ ድምጽና ወቅቱን ያልጠበቀ ምርጫ የሚካሄድበት ቀን ማወዛገቡ ቀጠለ።FDP ከተጣማሪው መንግሥት መውጣቱ የሾልዝ መንግሥት በፓርላማው የነበረውን አብላጫ ድምጽ እንዲያጣ በማድረጉ ከምርጫው በፊት  ሾልዝ የመታመኛ ድምጽ እንዲሰጣቸው ይህም በመጪው ጎርጎሮሳዊው 2025 ዓ.ም. በጥር ወር እንዲሆንና ምርጫው በመጋቢት ወር እንዲካሄድ ማቀዳቸውን አሳውቀው ነበር ሆኖም ፓርላማው የመታመኛ ድምጽን በሳምንታት ውስጥ መስጠት አለበት የሚሉት ተቃዋሚዎች ግፊት ከበረታ በኋላ ሾልዝ ከጥር ይልቅ በታኅሳስ የመታመኛ ድምጹ ቢካሄድ እንደሚስማሙ ባሳወቁ በሁለተኛው ቀን ዛሬ ፓርላማው የመታመኛ ድምጹን በጎርጎሮሳዊው ታኅሳስ 16 ቀን 2024 ዓ.ም. እንዲሰጥ ሾልዝ ጥሪ ያቀርባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅና ምርጫውም በየካቲት 2025 ዓ.ም. እንዲካሄድ መወሰኑ ዛሬ ይፋ ተደርጓል።

የጀርመን ፕሬዝዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር የጀርመን ጥምር መንግሥት ከፈረሰ በኋላ የFDPውን መሪና የፋይናንስ ሚኒስትሩን ክርስቲያን ሊንድነርን ሲያሰናብቱ
የጀርመን ፕሬዝዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር የጀርመን ጥምር መንግሥት ከፈረሰ በኋላ የFDPውን መሪና የፋይናንስ ሚኒስትሩን ክርስቲያን ሊንድነርን ሲያሰናብቱምስል Lisi Niesner/REUTERS


ታዲያ ሾልዝ በታኅሳስ የፓርላማውን የመታመኛ ድምጽ ያገኙ ይሆን ?ካላገኙስ ምንድነው የሚጠበቀው?በመጪው ምርጫስ የትኛዎቹ ፓርቲዎች የማሸነፍ እድል ይኖራቸዋል። የአንጋፋዎቹ ፓርቲዎች እጣ ፈንታስ ምን ሊሆን ይችላል? እነዚህ በዚህ ወቅት ላይ ደጋግመው የሚነሱና የተለያዩ ግምቶችም የሚሰጡባቸው ጥያቄዎች ናቸው።ሆኖም በነሐሴና መስከረም በተካሄዱት የአካባቢ ምርጫዎች አብላጫ ድምጾች ያገኙት ቀኝ ጽንፈኛው« አማራጭ ለጀርመን ፓርቲ»ና «ዛራ ቫግንክኔሽት ኅብረት» የተባለው በቅርቡ የተቋቋመው የግራ ጽንፍ አቋም እንዳለው የሚነገረው ፓርቲ በምርጫው ብዙ ድምጽ ያገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል። በፌደራል መንግሥት ምስረታ ላይ በተለይ «አማራጭ ለጀርመን» ሊጣመር የሚችልበት እድል ላይኖረው እንደሚችል ነው የሚገመተው።

የጀርመን መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝአ አርዴ ለተባለው የጀርመን ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ቃለ ምልልስ ሲሰጡ
የጀርመን መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝአ አርዴ ለተባለው የጀርመን ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ቃለ ምልልስ ሲሰጡምስል Carsten Koall/dpa/picture alliance


በFDP ከጥምሩ መንግሥት መውጣት ምክንያት ሀገሪቱ እስከ ሚቀጥለው ምርጫ ባለው የሽግግር ጊዜ የምትመራው በፓርላማው አብላጫ ድምጽ በሌላቸው በSPDና የአረንጓዴዎቹ ፓርቲዎች አናሳ መንግሥት ይሆናል። ምንም እንኳን አናሳው መንግሥት ካለ ተቃዋሚዎች ድጋፍ ሕጎችን ማሳለፍ ባይችልም የመንግሥቱን ስራዎች ግን ያከናውናል። ይህም SPDና አረንጓዴዎቹ ሾልዝን ከሊንድነር ጋር ያላስማማቸውና ሊንድነርን እስከ ማባረር ያደረሳቸውን የጎርጎሮሳዊውን 2025 ዓም በጀት በሚመለከት ሊያግዛቸው ይችላል ተብሎ ይታሰባል። 

የጀርመን መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝና ሾልዝ  ያባረሩዋቸው የነጻ ዴሞክራቶቹ ፓርቲ መሪ ክርስቲያን ሊንድነር
የጀርመን መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝና ሾልዝ ያባረሩዋቸው የነጻ ዴሞክራቶቹ ፓርቲ መሪ ክርስቲያን ሊንድነር ምስል Chris Emil Janßen/IMAGO


ሾልዝ ከ4 ሳምንታት በኋላ የፓርላማውን የመታመኛ ድምጽ ካላገኙ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ፓርላማውን እንዲበትኑ ይጠይቃሉ። ምርጫውም ከ60 ቀናት በኋላ ይካሄዳል። ለዚህ ዓይነቱ ዐውድ የተዘጋጁ የሚመስሉት ፕሬዝዳንት ሽታይንማየር ጥምሩ መንግሥት በፈረሰ በማግስቱ ለFDP መሪና ለፓርቲው አባላት ሚኒስትሮች የስንብት ደብዳቤ ከመስጠታቸው በፊት ፣ ያልተረጋጋው የፖለቲካ ሁኔታ በሀገር ውስጥ ፣ በአውሮጳና በዓለም  ብዙዎችን የሚያሳስብ ጉዳይ መሆኑንም ገልጸው ጊዜው የግጭት አለመሆኑን ጠቁመዋል። ይልቁንም ሁሉም ተግዳሮቱን የመቋቋም ሃላፊነቱን እንዲወጣ አሳስበው ነበር። 

የብራንድንበርጉ አካባቢያዊ ምርጫ ውጤትና አንድምታው
«አሁኑ ጊዜ የታክቲክ እና ግጭት አይደለም። ጊዜ የምክንያታዊነት እና የኃላፊነት ነው። እያንዳንዱ ሀላፊነት ይወስዳል ብዬ እጠብቃለሁ። በኃላፊነት ላይ ያሉ ሁሉ የገጠመንን ተግዳሮት እንደሚቋቋሙ እጠብቃለሁ። ሀገራችን የተረጋጋ ብዙሃን እና አቅም ያለው መንግሥት ትፈልጋለች።»

ኂሩት መለሰ

እሸቴ በቀለ