1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን የውጭ ፖሊሲ ቅኝት

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 23 2016

የዩክሬን ዋነኛ ደጋፊ አሜሪካን ጨምሮ ሌሎች ምዕራባውያን ሀገሮች ለዩክሬን ወታደራዊ እርዳታ የመስጠት ፍላጎታቸው ተዳክሟል።በዩክሬን ጦርነት የተሳለቸው የምዕራቡ ዓለም ህዝብ ፖለቲከኞች ጦርነቱን በጠረጴዛ ዙርያ በሚካሄድ ድርድር ለማብቃት እንዲያስቡ ግፊት እያደረጉ ነው። አንዳንድ ፖለቲከኞች ግን ድርድር እንዳይካሄድ ጦርነቱም እንዳይቆም ይፈልጋሉ።

https://p.dw.com/p/4amJK
የጀርመንና የብራዚል ልዑካን ምክክር ተሳታፊዎች በጀርመን መራኄ መንግሥት ጽህፈት ቤት
የጀርመንና የብራዚል ልዑካን ምክክር ተሳታፊዎች በጀርመን መራኄ መንግሥት ጽህፈት ቤትምስል Emmanuele Contini/NurPhoto/IMAGO

የጀርመን የውጭ ፖሊሲ ቅኝት

የ2023 ዓ.ም. የጀርመንን የውጭ ፖሊሲ 

ለጀርመን የውጭ ፖሊሲ ጉዳዮች በዝምታ የሚታለፉበት ጊዜ አብቅቷል ሲል ይጀምራል የጎሮርጎሮሳዊውን የ2023 ዓ.ም. የጀርመን ውጭ ፖሊሲን ወደ ኃላ መለስ ብሎ የቃኘውና እና በዚህ ረገድ በአዲሱ ዓመት የሚጠበቀውን የተመለከተው የዶቼቬለ የክሪስቶፍ ሀስልባህ ዘገባ። አሁን በርሊን ለሁለት ጦርነቶች፣ እጅግ እየጨመረ ለመጣው የቻይና ተጽእኖ እና ሽግግር ላይ ያለ ለሚመስለው የዓለም ስርዓት መፍትሄ መፈለግ አለባት ሲል የቀጠለው ዘገባው በተሰናበተው በ2023 የእስራኤል ሀማስ ጦርነት ከጀርመን የውጭ ፖሊሲ ተግዳሮቶች መካከል አንዱ እንደነበር ያወሳል። እንደዘገባው ጦርነቱ ሊያስከትል ይችላል የሚባሉትን አስከፊ መዘዞችን ለመከላከል ጀርመን ሚዛናዊ ለመሆን ትሞክራለች። የጀርመን መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ ጀርመን ፣የእሥራኤል ደኅንነት ከምንም በላይ ትኩረት የምትሰጠው ጉዳይ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል። የዚህ ምክንያትም ከቀድሞው የጀርመን ብሔራዊ ሶሻሊስት ፓርቲ ናዚ ጋር ጀርመንን የሚያገናኛት ያለፈ ታሪኳ መሆንን ገልጸዋል።

ይሁንና ይህ የጀርመን መራኄመንግሥት አቋም የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክን ጀርመን የአውሮጳ ኅብረትና ዩናይትድ ስቴትስ እንዲሁም ሌሎች ሀገራት አሸባሪ ሲሉ ከፈረጁት ከሀማስ  ጋር እስራኤል የምታካሂደውን ጦርነት ከመተቸት አላገዳቸውም። ቤርቦክ ባለፈው ህዳር ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ በዬርዳኖስ ወንዝ ምዕራባዊ ዳርቻ የሚገኙ አይህዱ ሰፋሪዎች በፍልስጤማውያን ላይ የሚሰነዝሩትን ጥቃት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲያወግዙ ጠይቀው ነበር።«የእሥራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ሰፋሪዎቹ የሚያደርሱትን ጥቃት ማውገዝ አለባቸው። ወንጀለኞቹ ክትትል ሊደረግባቸው ይገባል። ይህ ደግሞ ከእስራኤል ደኅንነት ጥቅሞች ጋር የተያያዘ ነው።የዮርዳኖስ ወንዝ ምዕራባዊ ዳርቻን ደኅንነት በሚመለከት እስራኤል በዚያ ያለው ሁኔታ እንዳይባባስ የማረጋገጥ ሃላፊነት አለባት »

የጀርመን መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ እስራኤልን በጎበኙበት ወቅት ከእሥራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ነታንያሁ ጋር
የጀርመን መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ እስራኤልን በጎበኙበት ወቅት ከእሥራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ነታንያሁ ጋር ምስል Michael Kappeler/dpa/picture alliance

የሁለት መንግሥታት መፍትሔ ምንድን ነው?


ጀርመን ከዚህ ሌላ ከጋዛው ጦርነት በኋላ መካከለኛው ምሥራቅ እንዴት መሆን እንዳለባት በሚካሄዱ ውይይቶች ላይም ትካፈላለች። እንደ አውሮጳ ኅብረት እና የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ሁሉ ጀርመንም ለእሥራኤልና ለፍልስጤማውያን ግጭት ለሁለት መንግሥታት መፍትሔ የቆመች ሀገር ናት። ቤርቦክ ስለ ወደፊትዋ ጋዛ ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሃላፊነት አስፈላጊነትን አንስተው ነበር።«ደኅንነትን ለማረጋገጥ ዓለም አቀፍ ሃላፊነት ያስፈልጋል። ይህን በአውሮጳ ከተካሄዱት የባልካን አሰከፊ ጦርነቶች እናውቃለን።በዚያ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ችግሩን የመከላከል ሃላፊነት ወስዶ ነበር። ምክንያቱም በነዚህን መሰል እጅግ ዘግናኝ ወንጀሎች በተፈጸሙባቸው ሁኔታዎች ፣በአካባቢው የሚገኙ ግጭቱ ተካፋዮች ፈጽሞ ምንም መተማመን የላቸውም ። እዚያም(ጋዛም) ይሄን ነው የማየው ።»  የጀርመን የምዕራብ አፍሪቃ ፖለቲካ
ለእስራኤል ፍልስጤማውያን ግጭት ሁለቱ መንግሥታት ጎን ለጎን በስምምነት የሚኖሩበት መፍትሄ ቀደም ካሉት ዓመታት ጀምሮ የተቀመጠ አማራጭ ነው። ይሁንና ከፀረ ሽብር ፕሮጀክት ዓለምአቀፍ ድርጅት የመካከለኛው ምሥራቅ ጉዳዮች አዋቂ ሀንስ ያኮብ ሺንድለር ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ እንዳሉት ይህ መፍትሄ  አሁን አጠያያቂ ሆኗል። 
«በአሁኑ ጊዜ የሁለት መንግሥታት መፍትሄ አሁን በሚፈጸሙት ድርጊቶችና  ባለፉት ሀያ ዓመታትም በሆነው በጣም ሩቅና ፣ግልጽ እንዳልሆነ በእርግጠኝነት ታውቋል። ግን ከሁለት መንግሥታት መፍትሄ ውጭ ሌላ ምን መፍትሄሔ አለ?»ይህን ጥያቄ ያነሱት ሺንድለር የጀርመን ፌደራል መንግስት ይህ ግብ እንዲሳካ ጥረቱን እንዲቀጥል መክረዋል። 

የአውሮጳን የደኅንነት ስሜት ያጠፋው የሩስያ ጥቃት 

በየካቲት 2022 ዓ.ም. ሩስያ በዩክሬን እንዳካሄደቸው ወረራ በቅርብ አሥርት ዓመታት ውስጥ የጀርመንንና የአውሮጳን ዲፕሎማቶች የተፈታተነ ጉዳይ የለም ማለት ይቻላል። ጀርመን ከሌሎች ምዕራባውያን ሀገራት ጋር ለዩክሬን መጠነ ሰፊ ወታደራዊ  እርዳታዎችን ትሰጣለች ። ሆኖም ጦርነቱ ከተጀመረ ሁለት ዓመት የተጠጋው ቢሆንም ዩክሬን ሩስያ በኃይል የያዘቻቸውን መሬቶች ለማስመለስ ያደረገችው ሙከራ ያን ያህል ውጤት አላስገኘም።  በአሁኑ ጊዜ ዋነኛዋን የዩክሬን ደጋፊ ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ ሌሎች ምዕራባውያን ሀገሮች ለዩክሬን ወታደራዊ እርዳታ የመስጠት ፍላጎታቸው ተዳክሟል። በዚህ ዓመት በዩናይትድስቴትስ በሚካሄደው ምርጫ እጩ ተወዳዳሪ ይሆናሉ ተብለው የሚጠበቁት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከተመረጡ ዋሽንግተን ለዩክሬን የምትሰጠውን ድጋፍ በእጅጉ ትቀንሳለች ተብሎ ይጠበቃል።

 ለዩክሬኑ ጦርነት መፍትሔው ድርድር ወይስ ወታደራዊ ዘመቻ

በዩክሬን ጦርነት የተሳለቸው የምዕራቡ ዓለም ህዝብ ፖለቲከኞች ጦርነቱን በጠረጴዛ ዙርያ በሚካሄድ ድርድር ለማብቃት እንዲያስቡ ግፊት እያደረጉ ነው። ከጀርመኑ የሀለ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ዮሐንስ ቫርቪክ ይህ በዚያም ሆነ በዚህ የማይቀር መሆኑን ያምናሉ።«ሩስያ የጦርነቱ አሸናፊ ሳትሆን ሊሳኩ ይችላሉ ተብለው የሚታሰቡ መፍትሔዎችን ማሰብ አለብን። ከዚሁ ጋርም እኛም የበኩላችንን ሰጥቶ መቀበል አበክረን ማሰብ ይኖርብናል። ግን እንደሚመስለኝ ከተኩስ አቁም እና ከዚያ በኋላ በዩክሬን ስለሚካሄዱ የግዛት ለውጦች፣ አስቸጋሪ ዲፕሎማሲያዊ ድርድሮች ስለ ዩክሬን ገለልተኝነት፤እነዚህ ሁሉ የጠረጳዛ ዙሪያው ድርድር አካል መሆን አለባቸው። ይህም ከነገ ይልቅ ዛሬ ነው መሆን ያለበት።»
ይሁንና ከዶቼቬለ የዩክሬን ክፍል ባልደረባ ሮማን ጎንቻሬንኮ እንደሚለው ለሰላም መሬት መስጠትን መሠረት ያደረገው መፍትሔ በዩክሬን በኩል ተቀባይነት የማግኘት እድል አይኖረውም። ድርድር እንዳይካሄድ ጦርነቱም እንዳይቆም የምዕራቡ ዓለም ለዩክሬን የሚሰጠው ወታደራዊ ድጋፍም እንዲቀጥል የሚፈልጉ የጀርመን ፖለቲከኞችም አሉ። 

በ2023 መገባደጃ በሩስያ የሚሳይል ጥቃት ክፉኛ የተጎዳ ሆቴል
በ2023 መገባደጃ በሩስያ የሚሳይል ጥቃት ክፉኛ የተጎዳ ሆቴልምስል Vyacheslav Madiyevskyy/Ukrinform/abaca/picture alliance

ቻይና ከቀድሞ የበለጠ አስጊ ሆና ትታያለች   

ሌላው የጀርመን የውጭ ፖሊሲ ፈተና ከቻይና ጋር ያላት ግንኙነት ነው። የቻይናና የጀርመን ግንኙነቶች ከ2005 እስከ 2021 ከዘለቀው የመራኂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል የስልጣን ዘመን በኋላ ብዙ ተለውጧል። በሜርክል የሥልጣን ዘመን የጀርመን መንግሥት ቻይናን በንግድ ፖሊሲ ጥቅም ረገድ በጥንቃቄ ነበር የያዘው። በንጽጽር ሲታይ ጀርመንን የሚመራው የሶሻል ዴሞክራቶቹ የSPD የአረንጓዴዎቹ እና የነጻ ዴሞክራቶቹ ፓርቲ FDP መንግሥት ቻይናን ለጀርመንና ለአውሮጳ ኅብረት አጋር፣ ተፎካካሪና ስልታዊ ተቀናቃኝ ነው የሚላት።የጀርመን ዓለም ዓቀፍ ሚና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በርሊን የቻይናን ተቀናቃኝነት በእጅጉ ታጎላለች። የጀርመን መንግሥት ቻይና ታይዋንን እንደ ተገንጣይ ግዛት ማየቷ እና ሩስያ በዩክሬን ጦርነት በምታካሂድበት ወቅት ቻይና ከሩስያ ጋር የቅርብ ግንኙነት መፍጠሯ የጀርመንን መንግሥት ያሳስበዋል። 

ቻይና የኤኮኖሚ አጋር ወይስ ጠላት?

ቻይና ከጎርጎሮሳዊው 2016 ዓመተ ምኅረት አንስቶ  እጅግ ጠቃሚ የጀርመን የንግድ አጋር ናት።ለዚህም ነው የጀርመን መንግሥት የቻይና ፖሊሲ ሁለቱን ኤኮኖሚዎች ማለያየት ላይ የማያተኩረው።ከዚያ ይልቅ ጀርመን በቻይና ኤኮኖሚ ላይ ብቻ ጥገኛ መሆንዋን ለመቀነስ ማድረግ በሚገባት ላይ ነው ጥረቷ ።  
ጀርመን እሴቶቿን መሠረት ባደረገው የውጭ ፖሊሲዋ ቻይናን ለመውቀስ ብትሞክርም ከቻይና በኩል ግን ጠንካራ አጸፋ መልስ ነው የሚሰጣት። ባለፈው ሚያዚያ የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክ ቻይና ሰብዓዊ መብቶችን እንድታከብር ጥሪ ሲያቀርቡ የያኔው የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሺን ጋንግ ከምንም በላይ ቻይና የምዕራቡ ዓለም አስተማሪ አያስፈልጋትም ሲሉ መልስ ሰጥተዋል። አንዳንድ አስተያየት ሰጭዎች ምዕራቡ ዓለም ጫና ውስጥ በወደቀበት በዚህ ወቅት ላይ ምዕራባውያን እሴቶቻቸው እንዲከበሩ መላልሰው መጠየቃቸው ጠላቶቻቸውን ስለሚያበዛ ደግሞ ደጋግሞ ከማንሳት ይልቅ ጥቅሞቻቸው ላይ ቢያተኩሩ የሚል ሃሳብ ያቀርባሉ። ይሁንና የጀርመን የውጭ ጉዳዮች ምክር ቤት ባልደረባ ሄኒንግ ሆፍ በዚህ አይስማሙም። 
« ሩስያና ቻይናን ለመሳሰሉ አስቸጋሪ ለሚባሉ አጋሮች የኛን እሴቶች ማንሳት አንችልም የሚለው ያረጀ ክርክር ጊዜው ያለፈበት ነው።የፌደራል መንግሥት በአሁኑ ሁኔታው ጀርመን ለነዚህ እሴቶች እንደምትቆም ግልጽ ማድረጓ በጣም ጥሩ ስራ ነው።ሜርክልን ለመተካት የሚወዳደሩት እጩዎች የውጭ ፖሊሲ  በኔ አመለካከት መንግሥት እነዚህ የእሴቶችና የጥቅሞች ጉዳዬች መሆናቸውን በግልጽ በማስቀመጥ አለመግባባቶቹን መወጣት ችሏል። ግን በሩስያ ላይ እንደተደረገው እነዚህን እሴቶች ካላነሳን ይህ አደገኛ መዘዞችን ማስከተሉ አይቀርም። ይህም በዩክሬን እየታየ ነው። »   

የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክ ከቻይናው ውጭ ጉዲይ ሚኒስትር ሺን ጋንግ ጋር በበርሊን
የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክ ከቻይናው ውጭ ጉዲይ ሚኒስትር ሺን ጋንግ ጋር በበርሊንምስል Thomas Trutschel/photothek/picture alliance

የአጋሮች ፍለጋ  


የዩክሬኑ ጦርነት ለጀርመን መንግሥት ትምሕርት ሰጥቷል ይላሉ ሆፍ ። ይኽውም በሩስያ ላይ ማዕቀብ ለመጣል  ከዓለም ድጋፍ ለማግኘት በተደረገው ሙከራ በርካታ ያደጉና በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ለጥያቄው ጀርባቸውን መስጠታቸው  ነው። ሆፍ እንዳሉት ከምዕራቡ ዓለም ጋር ተሰልፈው የነበሩ ህንድና ብራዚልን የመሳሰሉ ሀገራት በመቀየር ያለ በሚመስለው የዓለም ስርዓት አዳዲስ ሰፋ ያለ የመንቀሳቀስ ነጻነት በማግኘታቸው ለአንዱ ያለመወገን ነጻነታቸውን እየተጠቀሙ ነው። ሆኖም የሾልዝ መንግሥት እነዚህን ሀገራት ቀርቦ ሃሳባቸውን ለማወቅ መሞከሩ ጠንካራ ጎኑ ነው። «የጀርመን መንግሥት ያደረገው ምንድነው እነዚህን ሀገራት ማለትም ህንድንና ብራዚልን በመቅረብ በእኩል ደረጃ በሚካሄድ ውይይት ጉዳዩን ይበልጥ ግልጽ ማድረግ ነው። ይህ እስካሁን በመስፋፋት ላይ ያለው የጀርመን የውጭ ፖሊሲ ነው። በርሊን አሁን በትክክለኛው መስመር ላይ ናት።»

የብራዚሉ ፕሬዝዳንት ሉላ ደ ሲልቫና የጀርመን መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ
የብራዚሉ ፕሬዝዳንት ሉላ ደ ሲልቫና የጀርመን መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝምስል Kay Nietfeld/dpa/picture alliance


ከአውሮጳ ቀዳሚዋ ከዓለም ደግሞ አራተኛዋ የኤኮኖሚዋ አንቀሳቃሽ ጀርመን በዓለም አቀፍ ደረጃb ከዩናይትድ ስቴትስና ከአውሮፓ ኅብረት ያላነሰ ተጨማሪ ሚናዎችን ትጫወታለች ተብሎ ይጠበቃል። ኮርበር የተባለው ድርጅት ባካሄደው ጥናት ላይ ከተሳተፉ ሰዎች 54 በመቶው ግን በተለይ የጀርመን ተሳትፎ በዓለም አቀፍ ቀውሶች መገደብ አለበት ብለዋል።38 በመቶው ብቻ የጀርመን ተሳትፎ እንዲጨምር ይፈልጋሉ። 71 በመቶው ደግሞ ጀርመን በአውሮጳ የወታደራዊ መሪነት ሚና እንዲኖራት አይሹም ።ጀርመን ግን ከምንም በላይ ዓለም ከፖለቲካ ነውጥ እንድታርፍ ትፈልጋለች።  

ክሪስቶፍ ሀስልባህ

ኂሩት መለሰ