1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን የምዕራብ አፍሪቃ ፖለቲካ

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 29 2013

የጀርመን ወታደሮች ማሊ ውስጥ፤ ፍልሰት፤ ምጣኔ ሐብት፦ እንደ ምዕራብ አፍሪቃ ሁሉ በአንጌላ ሜርክል ዘመናት ብዙ ትኩረት ያገኘ ቀጠና የለም። ይህ በቀጣዩ አዲሱ መራኄ-መንግሥትም ሊቀጥል ይችላል።

https://p.dw.com/p/3ztaD
Kanzlerin Merkel in Afrika Mali
ምስል picture-alliance/dpa/M. Kappeler

የጀርመን ወታደሮች ማሊ ውስጥ፤ ፍልሰት፤ ምጣኔ ሐብት

ለሞሐመድ ባዞም ቀጠሮው ልዩ ስፍራ የሚሰጠው ነበር። የኒጀር ሪፐብሊክ ርእሰ-ብሔር መራኂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል ፊት በመገኘት ለመሰናበት ሐምሌ ወር ውስጥ ወደ በርሊን አቅንተው ነበር። እዚያም ከስብሰባቸው ቀደም ብለው ባሰሙት ንግግር፦ «የጀርመን ሕዝብ ድጋፍ አድርጎልናል። ኒጀርን ደግፏል። ለቀጠናውም ድጋፍ ሰጥቷል» ሲሉ ተደምጠዋል።  ይህ ድጋፍ ማንም ይመረጥ ማን በቀጣዩ የጀርመን መራኄ-መንግሥትም እንዲቀጥል ይፈለጋል።

በእየ ሳምንቱ በሚባል ኹኔታ ግን ከሣኅል ቀጠና የሚሰማው ደስ አይልም፦ በቡርኪና ፋሶ የሽብር ጥቃት፤ በመዓከላዊ ማሊ የአርብቶ አደሮች እና የአርሶ አደሮች ግጭት፤ በኒጀር መንደሮች ጥቃት እንዲህ ያለው ነገር ጎልቶ ይሰማል። እንደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ ከኾነ ምዕራብ አፍሪቃ ውስጥ በሚገኘው የሣኅል ቀጠና 30 ሚሊዮን ግድም ነዋሪ የሰብአዊ ርዳታ ፈላጊ ነው።

Deutschland Berlin | Treffen Angela Merkel und Mohamed Bazou aus Niger
ምስል Presse- und Kommunikationsdienst der Präsidentschaft von Niger

ስጋት በርሊን ውስጥ

በሣኅል ቀጠና የሚሰማው የቤርሊን ፖለቲከኞችን አስግቷል። በአካባቢው የእስልምና አክራሪዎች ብርታታቸው እያየለ ነው። ቀጠናው የኾነ ጊዜ ወደ ጀርመን መጥተው ጥቃት ሊፈጽሙ የሚችሉ አሸባሪዎች መሸሸጊያ የመኾን ስጋቱም ጨምሯል። የአመጻ እና ግፍ መበራከቱ ብሎም አንዳንድ መንግሥታት ድጋፍ ማድረጋቸው አዳዲስ ፍልሰተኞች ወደ ጀርመን እንዲተሙ ምክንያት ሊሆን ይችላል። 

ያም በመሆኑ የጀርመን ፖለቲካ በቀጠናው ሦስት ጉዳዮች ላይ ያተኩራል። የደኅንነት ጉዳይ፤ ልማት እና ፍልሰትን መታገል ላይ። ለዚያ ደግሞ ግልፁ ማሳያ የጀርመን ወታደሮች ማሊ ውስጥ መገኘታቸው ነው። ወደ 1000 የሚጠጉ የጀርመን ወታደሮች በአውሮጳ ኅብረት የስልጠና ተልእኮ (EUTM) እና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዘርፈ-ብዙ የተቀናጀ ማሊን የማረጋጋት ተልእኮ(MINUSMA)ስር ይካፈላሉ።

ማሊ ውስጥ ያለው ጥቃት ተልዕኮውን ከተግባሩ አላናጠበውም። ናዲያ አዳም ማሊ ዋና ከተማ ባማኮ ውስጥ በሚገኘው የደኅንነት ጥናት ተቋም ባልደረባ ናቸው። የማሊ ወታደሮች ቀጥተኛ ተሳትፎ የጀርመን ድጋፍ ለብቻው የሚያመጣውን ለውጥ ያጠይቃሉ።

«ከጥቂት ዓመታት በፊት በማይታሰብ መልኩ የጀርመን መንግሥት በሣኅል ቀጠና የወታደራዊ ተሳትፎውን ቢያጠናክርም ሀገሪቱ ግን ለወታደሮቿ አደገኛ በሆነው ወታደራዊ ተልእኮ ለመሳተፍ ዝግጁ አይደለችም። ይህ ወታደራዊ ጥቃት ጀርመን ማሊ ውስጥ ባላት ተሳትፎ ጥልቅ የሆነ ለውጥ የማምጣት ዕድሉ አናሳ ነው። ሀገሪቱ ጣልቃ የመግባት ፖሊሲዋን ሙሉ ለሙሉ ከማቋረጥ ያለጥርጥር ታስብበታለች።»

የሚኑስማ (MINUSMA)ተልእኮ የተባበሩት መንግሥታት በዓለም ዙሪያ ካሉት አደገኛ ተልእኮዎች አንዱ ነው። ባለፈው የሰኔ ወር መገባደጃ ላይ 12 የጀርመን ወታደሮች በእስልምና አክራሪዎች ፍንዳታ በከፊል  ከባድ የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል።

ፈረንሳይ ጦሯን ማስወጣት ትሻለች፤ ለጀርመን ተጨማሪ ጫና?

Infografik Karte Bundeswehstützpunkte in Afrika DE

ጀርመን ላይ ጫናው መበርታቱ አይቀርም። የፈረንሳይ ርእሰ-ብሔር ኤማኑዌል ማክሮ በሚቀጥሉት ሦስት ወራት ውስጥ ወደ 2000 የሚጠጉ ወታደሮቻቸውን ከሣኅል ቀጠና ማስወጣት ይሻሉ። የፈረንሳይ ወታደሮች ቦታ ሌላ የአውሮጳ ጦር ተክቶ ሽብርተኝነትን ሊዋጋ በአውሮጳውያኑ ፖለቲከኞች ዘንድ ይፈልጋል። የጀርመን ወታደሮች በዚያ ተሳታፊ አይደሉም። የፀጥታው ኹኔታ እየተባባሰ የሚኼድ ከሆነ ግን ተጨማሪ ወታደሮችን እንዲልክ ለጀርመንም ጥሪ መቅረቡ አይቀርም።

የኢዩቲኤም (EUTM ) የስልጠና ተልእኮ እስካሁን ብዙም ፍሬ አልሰጠም። ጂሃዲስቶችን በመወጋቱ ረገድ የማሊ መንግሥት በቂ ሥንቅና ትጥቅ የለውም። እንዲያውም እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2020 የሀገሪቱ ፕሬዚደንት ኢብራሂም ቦባከር ኬይታ ከሥልጣናቸው ተወግደው በማሊ ጦር በቁጥጥር ስር ውለውም ነበር። የማሊ የደኅንነት ኹኔታ ያሳሰበው የጀርመን ምክር ቤት  በዚህ ዓመት 650 ወታደሮችን ለመላክ ወስኗል።

ሕጋዊ ፍልሰት የበርካቶች ምኞት እንደኾነ ቀጥሏል

የፍልሰተኞች ጉዳይም ወደፊት የጀርመን መንግሥትን ትኩረት የሚሻ ነው። ናይጀሪያ እና ጋና ስደተኞች በብዛት ወደ አውሮጳ የሚፈልሱባቸው ሃገራት ናቸው። ኒጀር ደግሞ ለፍልሰተኞቹ አመቺ መሸጋገሪያ ሀገር። 

ወትሮዉኑም ቢሆን ምዕራብ አፍሪቃ የፍልሰተኞች ጉዳይ ለፖለቲከኞች የሚያስጨንቃቸው ስፍራ ነው።  በርካቶች ከዚያ አካባቢ ወደ አውሮጳ ይፈልሳሉ። ከቅርብ ጊዜ አንስቶ እንኳን በዓመት 150.000 ፍልሰተኞች ወደ ባሕሩ ለማቅናት ኒጀርን መሻገሪያ አድርገዋል።

የጀርመን መንግሥት ሃገራቱ ድንበሮቻቸውን እንዲያጠባብቁ ርዳታ ይሰጣል። ርዳታውም የድንበር ጥበቃዎችን በማሰልጠን አለያም የአገልግሎት መሣሪያዎችን በማቅረብ የሚከወን ነው። ኒጀር ውስጥ የጀርመን መንግሥት ለድንበር ጥበቃ ስድስት ሚሊዮን ዩሮ አፍስሷል። አብዛኛው ድጋፍ የሚላከውም በልማት ርዳታ ስር ነው።

Infografik Karte Migrationsströme von Westafrika nach Europa DE

ጋናዊው የፍልሰተኞች ጉዳይ ባለሞያው ሽቴፋን አዳዌን ተልእኮው ግቡን አልመታም ባይ ናቸው።

«በእርግጥ ፍልሰትን የፀጥታ ችግር ሲያደርጉት እየተመለከትን ነው። የፍልሰት ቁጥጥርን እንዲያጎልብቱ በሚል የአፍሪቃ ሃገራት ላይ ጫናው ሲበረታባቸው ይፋዊ የልማት ድጋፍም መጠቀሚያ ሲሆን  ዐይተናል።  የተነሳበትን ዓላማ የሳተ፤ የአፍሪቃ ሃገራት ግቦችን የተፃረረ ነው።»

ጋናዊው የፍልሰት ጉዳዮች ባለሞያ የጀርመን መንግሥት ሰዎችን በሕጋዊ መንገድ ወደ ጀርመን ለማፍለስ የገባውን ቃልም አጥፏል ሲሉ አያይዘው ተችተዋል።

በቀጠናው የተቆጡ በርካቶች ናቸው።  በአሁኑ ወቅት ወጣቶች ወደ ጀርመን መኼድ እና እዚያ መማር፤ አለያም ገንዘብ የሚያስገኝላቸውን ሥራ መሥራት ይሻሉ። ጋናዊቷ ኤሊፕክሊም አዉኩ ቀጣዩ የጀርመን መራኄ-መንግሥት ይህን የማያስተጓጉል እንዲሆን ትፈልጋለች።

«ቀጣዩ የጀርመን መራኄ-መንግሥት ማን እንደሚሆን ዕናውቃለን? ቀኝ ጽንፍ የረገጠ አለያም እጅግ ወግ አጥባቂ እንደማይኾን ተስፋ አደርጋለሁ። ለሰብአዊነት ግድ የሚሰጠው፤ በዚያም ፍልሰትን በተመለከተ በተገቢ መልኩ ምላሽ መስጠት ይችላሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።»

የጀርመን በቦታው መገኘት አናሳ ነው

የምጣኔ ሐብት ትብብሩም ቢሆን በርካታ ተግዳሮቶች አሉበት። ምንም እንኳን እምቅ አንጡሯ ሐብት እንዳለ ቢነገርም ከፍተኛ የእድገት መጠን ይኖራል የሚል ምክር ቢሰጥም የጀርመን ባለ ሐብቶች ግን ወደ አፍሪቃ ለማቅናት ሲያንገራግሩ ይስተዋላል። ያም በመሆኑ የጀርመን መንግሥት እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ2017 አንስቶ የጀርመን ባለሐብቶች አፍሪቃ ውስጥ ስለሚኖራቸው ዕድል ገለጣ ማድረጉን ተያይዞታል። ባለሐብቶችን ለመሳብ ከሚያደርጋቸው የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ጎን ለጎን «ከአፍሪቃ ጋር ስምምነት» (Compact with Africa) የተሰኘ መነቃቃትንም አስጀምሯል።

Elfenbeinküste Abidjan | Coronavirus | Handelsbeziehungen
ምስል Issouf Sanogo/Getty Images/AFP

ሰባት የምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት በዚህ እንቅስቃሴ ተሳታፊ ናቸው። ሃገራቱ ለባለ ወረቶች ሳቢ ለመሆን ግዴታ ገብተዋል። በአንጻሩ ጀርመን እና ሌሎች አጋሮች መዋዕለ-ንዋይ አፍሳሾችን ያፈላልጋሉ። ይህን አስመልክቶ ከፍተኛ ባለ ሥልጣናት የተሳተፉበት የአፍሪቃ ጉባኤ ቤርሊን ውስጥ በተደጋጋሚ ተደርጓል። ያም ኾኖ ከሌሎች የእስያ ሃገራት እና ከፈረንሳይ አንጻር ጀርመን አፍሪቃ ውስጥ እንቅስቃሴው አነስተኛ ነው።

ዳንኤል ፔልስ/ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ