የጀርመን ውህደት 33ተኛ ዓመት
ማክሰኞ፣ መስከረም 22 2016የጀርመን ውህደት 33ተኛ ዓመት ዛሬ በመላ ጀርመን ተከብሮ ውሏል።እለቱ በዋነኛነት በሰሜን ጀርመንዋ በሀምቡርግ ከተማ የሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት በተገኙበት ታስቧል። 33 ዓመታት ያስቆጠረው ውህደት ለበአጠቃላይ ለሀገሪቱ ብዙ ጥቅሞችን ያስገኘ ቢሆንም ፍጹም እንዳይደለ ይነገራል። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ኮምኒስት ምሥራቅ ጀርመንና የጀርመን ፌደራል ሪፐብሊክ ወይም (ምዕራብ ጀርመን) ተብላ በጎርጎሮሳዊው 1945 ለሁለት የተከፈለችው ጀርመን የበርሊን ግንብ ፈርሶ አንድ ከሆነች ዘንድሮ 33 ዓመት ተቆጠረ።ጀርመን በጎርጎሮሳዊው ጥቅምት 3 ቀን 990 በይፋ የተዋሀደችበትን 33ተኛ ዓመት ዛሬ በተለይ በሰሜናዊ ጀርመንዋ ከተማ በሀምቡርግ የጀርመን መራሄ መንግስትን ጨምሮ የሀገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተገኙበት በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ተከብሯል። የጀርመን ላዕላይ ምክር ቤት በጀርመንኛው አጠራር ቡንደስራት የወቅቱ ፕሬዝዳንት በሆነችው በሀምቡርግ ይፋዊ አከባበሩ የተጀመረው በከተማዋ በሚገኘው የቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የተለያዩ ሃይማኖቶች እና የህብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች መልዕክት ባስተላለፉበት ስነ ስርዓት ነበር።
ከዚህ ሌላ የወደብ ከተማዋ መስህብ በሆነውና በኤልበ ወንዝ ላይ በተሰራው ኤልብፊልሀርሞኒ በተባለው የረቂቅ ሙዚቃ ኮንሰርት አዳራሽ ዋነኛዎቹ የጀርመን ፖለቲከኞች እና የፌደራል ግዛቶች ጠቅላይ ሚኒስትሮች የተገኙበት እለቱን የተመለከቱ ንግግሮች የተደረጉበት ስነ ስርዓትም ተካሂዷል። ከትናንት አንስቶ በሀምቡርግ መከበር በጀመረው በዓል ላይ ለመካፈል በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ከተማይቱ ጎርፈዋል። ጀርመን መልሳ አንድ የሆነችበት 33 ተኛ ዓመት በሚከበርበት በዚህ ወቅት ላይ ውህደቱ አንድ ለሆነችው ጀርመን ያስገኘው ፖለቲካዊ ኤኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጥቅሞች ይዘከራሉ። በአንጻሩ እንደ ቀደሙት ዓመታት ከውህደቱ በኋላ በምሥራቅና በምዕራብ ጀርመን መካከል የሚታዩ ልዩነቶችም ይነሳሉ። የጀርመን ውህደትና የምሥራቅ ጀርመን ነዋሪዎች ቅሬታ ውህደቱን በተመለከተ በቅርቡ ይፋ የተደረገ ዘገባ ግን አሁንም በምዕራብና በምሥራቅ ጀርመን ልዩነቶች መኖራቸውን ያመለክታል። ዘገባው ምሥራቅና ምዕራብ ጀርመንን አንድ ከሚያደርጓቸው ይልቅ የሚለያይዋቸው ያመዝናሉ ይላል። የጀርመን መንግሥት ደግሞ ውህደቱ ባለፉት 33 ዓመታት ብዙ አጥጋቢ ውጤቶችን ማስገኘቱን ይናገራል። ሆኖም የምሥራቁም የምዕራብ ጀርመንም የእድገት ደረጃ የተስተካከለ እንዲሆን መሰራት እንዳለበት ያምናል። በዚህ ጉዳይ ላይ ዶቼቬለ ያነጋገራቸው የፌደራል መንግሥቱ የምሥራቅ ጀርመን ኮሚሽነር ካርስተን ሽናይደር በአሁኑ ጊዜ በምሥራቅ ጀርመን የተመዘገበውን የኤኮኖሚ እምርታ አወድሰዋል። ኮሚሽነሩ በጀርመን ፖለቲካዊው ውህደት መሳካቱን ገልጸው አሁንም ምዕራብና ምሥራቅ ጀርመንን የሚለዩ መስመሮች መኖራቸውን ግን አልሸሸጉም
«ይህ በማንኛውም መልኩ ፖለቲካዊ ጉዳይ ነው። ፍጹም ባይሆንም ውኅደቱ ተጠናቋል። ሀገሪቱ በጣም የተለያየች ናት። ከሰሜን ባህር አንስቶ እስከ ባቫርያው የአልፕስ ተራሮች ቅርጿ በጣም ይለያያል። ፓለቲካዊ አመለካከቶችም እንበል የቀድሞ ልምዶችም በርግጥ በምሥራቅ ጀርመን ከተቀረው የሪፐብሊኩ ክፍል ይለያል። ይህ ግን በአጠቃላይ የሀገሪቱ ውብትና ብዘሀነት ነው። ይህን ልምድም ለምሳሌ እንደ ምሥራቅ ጀርመን በፈላጭ ቆራጭ መንግሥት ለተሰቃዩት ለማዕከላዊና ለምሥራቅ አውሮጳ ሀገራት መጠቀም ይቻላል። »
ከከውህደቱ በኊላ የምሥራቅ ጀርመን ማለትም የቀድሞዋ የጀርመን ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ነዋሪዎች ከምዕራብ ጀርመን ጋር ሲነጻጸር የምናገኘው ደሞዝም ሆነ የጡረታ ክፍያ ዝቅተኛ ነው በማለት ሲያማርሩ ቆይተዋል። ሽናይደር ለዶቼቬለ እንደተናገሩት በተለይ የጡረታ ክፍያ በመላ ጀርመን በ2023 ዓም ተስተካክሏል። ይህም ከዋነኛዎቹ ስኬቶች ውስጥ አንዱ ነው ብለዋል ሆኖም አሁንም በደሞዝና በሀብት መጠን ልዩነቶች መኖራቸውን ሽናይደር አምነዋል። በጎርጎሮሳዊው 2020 በምዕራብ ጀርመን አማካዩ ዓመታዊ የደሞዝ መጠን ከምሥራቅ ጀርመን ጋር ሲነጻጸር ከ12 ሺህ ዩሮ ወይም 12 ሺህ 670 ዶላር በላይ ነበር።የጀርመን ፌደራል ባንክ ባወጣው መረጃ መሠረት በምዕራብ ጀርመን ግዛቶች አማካይ የገንዘብ ቁጠባ ከምሥራቅ ጀርመን ጋር ሲነጻጸር በሦስት እጥፍ የላቀ ነው። ለዚህ መፍትሄው ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው የምሥራቅ ጀርመንን ኤኮኖሚም ማሳደግ መሆኑን የተናገሩት ሽናይደር መንግሥታቸው በምሥራቅ ጀርመን የተለያዩ ኢንዱስትሪዎችን በመትከል ላይ መሆኑን አስረድተዋል።ምሥራቅ ጀርመን ከበርሊን ግንብ መፍረስ በኋላ
«አዎ አሁንም ማኅበራዊው ስርዓት ተመሳሳይ ነው። ሕጋዊ መብቶችም ተመሳሳይ ናቸው። እስካሁን ያደረግነው በተለይ የመዋቅር ድጋፍ የመሠረተ ልማትና የባቡር መስመር ግንባታ እገዛ ነው። አውራ ጎዳናዎች በሙሉ እጅግ በጣም ጥሩ ተደርገው ተሰርተዋል። አሁን ደግሞ የከፍተኛ ቴክኖሎጂ ኩባንያዎችን ልናቋቋም ነው። በጋራ ስምምነት የሚቋቋሙት እነዚህ ኩባንያዎች የደሞዝ ልዩነትን የሚያጠብ የተሻለ ደሞዝ ይከፍላሉ።ይህ ሲሆን ሰዎች በመሠረቱ ሁለተኛ ደረጃ እንደተሰጣቸው ሆኖ አይሰማቸውም። ሆኖም ይህ ግን ከፖለቲካው እውነታ የተለየ ነው። ምክንያቱም እያንዳንዱን የፌደራል መንግሥት ምርጫ ማን መራሄ መንግሥት ይሁን አይሁን የሚለውን በአብላጫ ድምጽ የሚወስኑት ምሥራቅ ጀርመኖች ናቸው። »
የዩናይትድ ስቴትሱ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ኢንቴል ፣30 ቢሊዮን ዶላር የሚወርትበት የኮምፕዩተር ቺፕስ ኩባንያ በዛክሰን አንሀልትዋ ፌደራዊ ግዛት ዋና ከተማ ማግድቡርግ ለመስራት አቅዷል።በሽናይደር አገላለጽ የምሥራቅ ጀርመን ከተሞች በሚቀጥሉት 10 ዓመታት በተለይ በኢንዱስትሪ እና በስራ ፈጠራ ረገድ ወደፊት የመራመድ እድላቸው የሰፋ ነው።ይሁንና የፌደራል ስታትስቲክ መስሪያ ቤት ባወጣው መረጃ መሠረት በምሥራቅ ጀርመን መስራት በሚቻልበት እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ቁጥር በሚቀጥሉት አስር ዓመታት እየቀነሰ እንደሚሄድ ይገመታል። መስሪያ ቤቱ እንዳለው በጎርጎሮሳዊው 2022 መጨረሻ እድሜያቸው ከ18 እስከ 64 የሚደርስ 51.4 ሚሊዮን ሰዎች በመላ ጀርመን ይገኛሉ። ከመካከላቸው 7.2 ሚሊዮኑ ብቻ ናቸው በቀድሞው የምሥራቅ ጀርመን ግዛቶች የሚኖሩት።ይህ ግን በርሊንን አይጨምርም።እንደ መስሪያ ቤቱ ትንበያ በሚቀጥሉት ሁለት አሥርት ዓመታት ቀደም ሲል በተጠቀሰው የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገቡት ቁጥር ከ560 ሺህ እስከ 1.2 ሚሊዮን ድረስ ዝቅ ሊል ይችላል። በጎርጎሮሳዊው 1970 ደግሞ ቁጥራቸው በ2.1 ሚሊዮን ይቀንሳል ተብሎ ይጠበቃል። በጀርመን በዚህ እድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሰዎች ቁጥር የሚቀንሰው በምዕራብ ጀርመንም ነው እንደ መረጃው ። የጀርመን ውህደት እና ውጤቱሆኖም በምዕራብ ጀርመን የቁጥሩ ማነስ ያን ያህል አሳሳቢ አይደለም ተብሏል። ለዚህ በምክንያትነት የተጠቀሰው ወደ አካባቢው በብዛት የሚገባው ስደተኛ ጉድለቱን ሊሸፍን ይችላል ተብሎ መታሰቡ ነው።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በምሥራቅ ጀርመን ህዝቡ ለቀኝ ጽንፈኛ ፓርቲዎች የሚሰጠው ድጋፍ እየጨመረ መሄድ አነጋጋሪ ከሆኑት ጉዳዮች መካከል ነው። በተለይም ከተቋቋመ አስር ዓመት ላስቆጠረው ጸረ-የውጭ ዜጎች አቋም ላለው «አማራጭ ለጀርመን» ለተባለው ቀኝ ጽንፈኛ ፓርቲ የምሥራቅ ጀርመን ህዝብ የሚሰጠው ድጋፍ ከምን ጊዜውም በላይ እያደገ መሆኑን አሳስቧል። በቅርቡ የላይፕዚሽ ዩኒቨርስቲ ባካሄደው ጥናት ከምስራቅ ጀርመን ህዝብ 60 በመቶው በሀገሪቱ የሚገኙ የውጭ ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ ነው የሚል አስተሳሰብ አላቸው። ሽናይደር እንደሚሉት ግን ምሥራቅ ጀርመን ውስጥ አካታችነት እና ብዝሀነትከቀድሞው ከፍ ብሏል። እንደ ምሳሌም በምሥራቅ ጀርመንዋ ከተማ ኤርፉርት የውጭ ዜጎች ቁጥር ከአስር ዓመት በፊት ሁለት በመቶ የነበረ አሁን ወደ 18 በመቶ አድጓል። ያም ሆኖ በምሥራቅ ጀርመን በውጭ ዜጎች የቆዳ ቀለማቸው በተለየው ሰዎች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ይደርሳሉ።ታዲያ የፌደራል መንግሥቱ የተለያዩ ዝርያ ያላቸውን እነዚህን ሰዎች እንዴት ከጥቃት መከላከል አስቧል የሚል ጥያቄ ከዶቼቬለ ለሽናይደር ቀርቦላቸው ነበር።ይህን መልሰዋል።
«ማናቸውንም ኃይል መጠቀም ተቀባይነት የለውም ።ይህን ያደረገም ይከሰሳል።በይፋ ለፍርድ ይቀርባል። ይህ የሚደረገው ደግሞ በምስራቅም በምዕራብ ጀርመንም ነው። ይህን መሰሉ ጥቃት በምሥራቅ ጀርመን ብቻ እንደተፈጸመ አላየውም።ይህ ድርጊት የተፈጸመበት ግዛት ባለሥልጣናት ጣልቃ መግባትና ድርጊቱንም ወዲያውኑ ማውገዝ አለባቸው።»የጀርመን ውህደት 30ኛ ዓመት
በሽናይደር እምነት ፖለቲካዊ መፍትሄዎች ብቻ የህዝቡን ቅሬታዎች ማስቀረት አይችሉም።ከዚያ ይልቅ ማኅበረሰቡ በራሱ በጉዳዩ ላይ ፍላጎት እንዲኖረው መጣር እና እርስ በርስም ለመቀራርብ ቢሞክር የተሻለ ውጤት ይገኛል ብለዋል። በጀርመን ዓላማ ባለው መዋቅራዊ ፖሊሲ የፌደራል መንግሥቱ በምሥራቅ ጀርመን ኢንቬስትመንት እንዲስፋፋ ማድረጉን አውራ ጎዳናዎች መገንባታቸውን ዘመናዊ መሠረተ ልማቶች እና የቴሌኮምኒሽን ቴክኖሎጂ መዘርጋታቸውን ጠቅሰዋል። በሂደት ይስተካከላሉ ተብለው ከሚጠበቁት እንከኖቹ ጋር የጀርመን ውህደት ለብዙ ሀገራት እንደ አርአያ ሊወሰድ የሚችል መሆኑን ነው የጀርመን ፌደራል መንግሥት የምሥራቅ ጀርመን ኮሚሽነር ካርስተን ሽናይደር ያተናገሩት
«ሌሎች ሀገራት ሁሉንም በተመሳሳይ ደረጃ የሚያስቀምጥ ሚዛን እንደሌላቸው በጣም እርግጠኛ ነኝ። ይህም ሀገሪቱን ያስተሳስራል። ይህም ወደ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ መረጋጋትን ያስከትላል። ለ40 ዓመታት የሶሻሊዝም ስርዓት የነበረ ቢሆንም ብዙ ለውጦች ታይተዋል። አሳሳቢ የሆነው የኤኮኖሚው ሁኔታ ደግሞ ደግሞ ከዓመት ዓመት እየቀነሰ በመሄድ ላይ ነው።»
ኂሩት መለሰ
ሸዋዬ ለገሠ