1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን ውህደት 29ኛ ዓመት

ማክሰኞ፣ መስከረም 20 2012

በምሥራቅ ጀርመን ከውህደቱ 29 ዓመት በኋላ አሁንም ቅሬታዎች ይሰማሉ።ምክንያቱ ህዝቡ ቃል የተገባለት አለመተግበሩ እና ይጠብቅ የነበረውንም አለማግኘቱ ነው።ይህም ባስከተለው አለመርካትና በሥራ እጥነት ወጣቶች ወደ ምዕራብ ጀርመን ይሰደዳሉ።በአንዳንድ የቀድሞ ምሥራቅ ጀርመን መንደሮች የወጣቱ ቁጥር ተመናምኗል።ይህም ለቀኝ ጽንፈኞች ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሯል

https://p.dw.com/p/3Qarn
Deutschland Berlin Tag der deutschen Einheit 1990
ምስል Imago/Gueffroy

የምሥራቅ ጀርመኖች ቅሬታ

ምሥራቅ እና ምዕራብ ጀርመን ከተዋሀዱ በዚህ ሳምንት ሐሙስ 29ኛ ዓመታቸውን ይደፍናሉ።ብዙ ጠቃሚ ውጤቶችን ያስገኘው የጀርመን ውህደት ሊፈታ ያልቻላቸው ችግሮችም አሉ።የዛሬው አውሮጳ እና ጀርመን ዝግጅታችን ትኩረት ነው። ዝግጅቱ ከውህደቱ በኋላ ጎልቶ የወጣውን የውጭ ዜጎች ጥላቻ ለማስቀረት የበኩላቸውን ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያዊን አስተያየትና ልምድም አካቷል።

በጀርመን ታሪክ ልዩ ስፍራ ይዟል፤በዓለም አቀፍ ደረጃም አርአያነቱ የጎላ ነው፤የዛሬ 29 ዓመት እውን የሆነው የምሥራቅና ምዕራብ ጀርመን ውህደት።ጀርመናውያንን ብቻ ሳይሆን ዓለምን ያስደሰተው እና ያስደነቀው የሁለቱ ጀርመኖች ውህደት ብዙ ውጤቶችን አስገኝቷል። ውህደቱ የጀርመን ኤኮኖሚ ከአውሮጳ የአንደኝነቱን ደረጃ እንዲይዝ አስተዋጽኦ አድርጓል።ይሁን እና ከ30 ዓመታት በኋላ ዛሬም በቀድሞዋ የምሥራቅ ጀርመን ግዛቶች ልዩ ልዩ ኤኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ችግሮች አልተፈቱም።ይህም የአብዛኛዎቹ የምሥራቅ ጀርመን ነዋሪዎች ቅሬታ ነው።በቅርቡ ይፋ የተደረገ በውህደት ላይ ያተኮረ  ዓመታዊ ዘገባ ላይ እንደተገለጸው ውህደቱን እንደ ስኬት የሚወስዱ ቢኖሩም አብዛኛዎቹ የምሥራቅ ጀርመን ነዋሪዎች ሁለተኛ ዜጋ እንደሆኑ ያህል ነው የሚሰማቸው።ምሥራቅ ጀርመኖች አሁንም ከምዕራብ ጀርመኖች ጋር መስተካከል ባለመቻላቸው የተረሱ የተዘነጉ ያህል ይሰማቸዋል።

Deutschland Brandenburger-Tor 1990
ምስል imago/F. Berger

ዶክተር መኮንን ሽፈራው«ባብል ኤ ፋው የተባለ»ዋና ጽሕፈት ቤቱ በርሊን የሚገኝ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት መሥራችና ሃላፊ ናቸው።የዛሬ 40 ዓመት ከፍተኛ ትምሕርታቸውን ለመከታተል ጀርመን የመጡት ዶክተር መኮንን ከውህደቱ በኋላ የመሰረቱት ይኽው ድርጅት ያኔ የተባባሰውን ዘረኝነት መቋቋም በሚያስችል ሥራ ላይ ነው የተሰማራው። ዶክተር መኮንን  ዛክሰን በተባለው ፌደራዊ ክፍለ ሃገር ስር በምትገኘው በላይፕሲሽ ከተማ ውስጥ ባለው በላይፕሲሽ ዩኒቨርስቲ ነው ከፍተኛ ትምሕርታቸውን የተከታተሉት። የዶክትሬት መመረቂያ ጽሁፋቸውን በማጠናቀቅ ላይ ሳሉ ነበር ሁለቱ ጀርመኖች የተዋሃዱት። ጋዜጠኝነት ያጠኑት ዶክተር መኮንን በተማሩበት በምሥራቅ ጀርመን ከውህደቱ 30 ዓመት በኋላ አሁንም ቅሬታዎች ይሰማሉ።ምክንያቱ ርሳቸው እንደሚሉት ህዝቡ ቃል የተገባለት አለመተግበሩ እና ይጠብቅ የነበረውንም አለማግኘቱ ነው።ይህም ባስከተለው አለመርካት እና በሥራ እጥነት ምክንያት ወጣቶች ወደ ምዕራብ ጀርመን ይሰደዳሉ።በዚህ ሰበብ በአሁኑ ጊዜ በአንዳንድ የቀድሞ ምሥራቅ ጀርመን መንደሮች የወጣት ቁጥር ተመናምኗል።ይህም የውጭ ዜጎችን ለሚጠሉ  ቀኝ ጽንፈኛ ፓርቲዎች ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሯል እንደ ዶክተር መኮንን።እነዚህ ፓርቲዎች ይህን ተጠቅመው ጥላቻ እየነዙ በምሥራቁ ክፍል ዘረኝነትን ለማስፋፋት ተጠቅመውበታል።የውጭ ዜጋ ሥራህን ቀማህ፣አገርህን ወረረ ጥቅምህን ወሰደብህ እያሉ በመቀስቀስ የፖለቲካ መጠቀሚያም እያደረጉት ነው።ቀኝ ጽንፈኛ ፓርቲዎች ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በምሥራቅ ጀርመን በሚካሄዱ ምርጫዎች ከፍተና ድምጽ እያሸነፉ ነው።።ባለፈው አጠቃላይ ምርጫም በፌደራል ጀርመን ፓርላማ ከፍተኛውን የተቃዋሚዎች መቀመጫ የያዘው ቀኝ ጽንፈኛ ፓርቲ ነው።ዶክተር መኮንን እንደሚሉት ህዝቡ ለቀኝ ጽንፈኞች ድምጹን የሚሰጥበት ምክንያት ግልጽ ነው።

25 Jahre Deutsche Einheit
ምስል picture-alliance/dpa/P. Kneffel

ያም ሲባል ግን በምሥራቅ ጀርመን ምንም የተለወጠ ነገር የለም ማለት አይደለም እንደ ዶክተር መኮንን ።ዶክተር መኮንን  ጀርመን ትምሕርት ላይ እያሉ ቤተሰብ በመመስረታቸው ምክንያት ትምሕርታቸውን ከጨረሱ በኋላ ወሃገራቸው አልተመለሱም።ጋዜጠኝነት ያጠኑት ዶክተር መኮንን በሙያቸው በቴሌቭዢን ጣባይ ለተወሰነ ጊዜ ከሰሩ በኋላ ነበር የያኔውን ባቢሎን በአሁኑ መጠሪያው ደግሞ ባብል ኤፋውን የመሰረቱት።ከውህደቱ በኋላ ቀድሞ ብዙም ጎልተው ይወጡ ያልነበሩ ዘረኝነትን የመሳሰሉ ችግሮች መታየት መጀመራቸው አሁን ለተሰማሩበት ሥራ መነሻ ምክንያት ሆኗቸዋል።ዶክተር መኮንን ሽፈራው ለበርካታ ዓመታት በኖሩባት በጀርመን ዘረኝነት በመታገልና ከህብረተሰቡም ጋር ተቀራርቦ ለመኖር ባከናወኑት ሥራ በጎርጎሮሳዊው 2010 ዓም የጀርመን የውህደት ሜዳሊያ በመራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ተሸልመዋል። የጀርመን ውህደት 29ኛ ዓመት ሲከበር ውህደቱ ካስገኛቸው ጥቅሞች ጋር በውህደቱ እውን ይሆናሉ ተብለው ያልተሳኩትም እየተነሱ ነው።ከሁሉም በላይ ግን አርዓያነቱ ጎልቶ እየተወሳ ነው።
ኂሩት መለሰ 

Anti Rassismus Engagement im Berliner Problembezirk Marzahn
ምስል DW/Yilma Hinz

አዜብ ታደሰ