የኦሮምያ ግጭት፤ «ሰላማዊ ሰው ይገደላል ፤ጫናው ከፍተኛ ስለሆነ የሚናገር ሰው የለም»
ሰኞ፣ የካቲት 18 2016
ግጭት የከፋባቸው የደቡብ ምዕራብ ሸዋ አራት ወረዳዎች
ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይገለጽ ጠይቀው አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ ነዋሪ በኦሮሚያ በተለይም በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ውስጥ በሚገኙ አራት ወረዳዎች የሚዲያ አይን የተነፈገው አስከፊ ግጭት በእየለቱ የሰላማዊ ዜጎችን ኑሮን ፈታኝ ከማድረግም አልፎ ህይወትን የሚቀጥፍ ነው ይላሉ፡፡
“በተለይም አራት ወረዳዎች፤ ተሌ፣ በቾ፣ ሰዴን ሶዶ እና ሶዶ ዳጪ በሚባሉ ወረዳዎች በየጊዜው በሚፈጠረው ግጭት ሰው ያልቃል፡፡ ግን ምንም አይነት የሚዲያ ሽፋን እያገኘ አይደለም፡፡ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት በሌሊት ስንቀሳቀሱ እገታ በመፈጸም ከመንግስት ጋር ናችሁ ይላል፤ ቀን ደግሞ የመንግስት ጦር ከታጣቂዎቹ ጋር ትሰራላችሁ በሚል ከፍተኘ በመሃል ህዝቡ ተሰቃይቷል” ብለዋል፡፡በኦሮምያ ክልል ለዓመታት ለዘለቀው ግጭትና ግድያ ኃላፊነቱን ማን ይወሰድ?
አስተያየት ሰጪው እንደሚሉት የማያቋርጠው ግጭት በየጊዜው አለ፡፡ “በየጊዜው ሰላማዊ ሰው ይገደላል፡፡ ግን በሁለቱም በኩል ያለው ጫና ከፍተኛ ስለሆነ ህን አውጥቶ የሚናገር ሰው የለም፡፡ ስጋቱ ስለሚያይል ህዝቡ ምንም አይነግርህም፡፡ በዚህ አከባቢ ሁለት ዓመት በሆነው ግጭት ስምንት አስር እና ከዚያ በላይ ቁጥር ያለው ሰላማዊ ሰው በተደጋጋሚ ይገደላል” ነው ያሉት፡፡
የግጭቱ ኢኮኖሚያዊ ጫና
ግጭቱ ነጋዴዎችን አፈናቅሎ አከባቢዎቹን ለኢኮኖሚ መዳሸቅም ዳርጎታል ነው የተባለው፡፡ “በዚህ አከባቢ ካሉ ከተሞች ነጋዴው ተሰዷል፡፡ ገበሬውም ሌት ቀኑን የሚያሳልፈው በመሸበር ነው፡፡ አሁን ከሰሞኑ እንኳ በቶሌ ወረዳ በምትገኘው አቤቤ ከተማ ከባድ ውጊያ ነበር፡፡ በዚህ ደግሞ ከታጠቁ አካላት በተጨማሪ ሲቪሎችም ሰለባ ሆነዋል” ሲሉም አስተያየት ሰጪው የግጭቱ ዳፋ ለሰላማዊ ዜጎች እንደተረፈ አስረድተዋል፡፡
በዚህ ዞን አንዱ ታጣቂ ሌላውን ለማደን በሚያደርግበት ጥረት ውስጥ ሰላማዊ ነዋሪዎችን ሌላኛውን ወገኝ በመደገፍ በመጠርጠር ቤቶችን እስከ ማቃጠል እና የተለያዩ ድብደባዎችን ዜጎች ላይ ማድረስም እንደሚስተዋል አስተያየት ሰጪው አመልክተዋል፡፡ በዚህ ረገድ ደግሞ እንደ ወጣት ዋጋ የሚከፍል የማህበረሰብ አካል እንደሌለ ነው የተጠቆመው፡፡ “ወጣቱ በሰላማዊ መንገድ የሚኖር ወጣት በተለይ አሁን ላይ እንኖራለን የሚለው ተስፋው መንምኗል” ሲሉ የግጭቱ ዳፋ በከፋ መልኩ ወጣቱ ላይ ጫናው እንደሚበረታም አልሸሸጉም፡፡
ሌላው የቱሉ ቦሎ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አስተያየት ሰጪ ደግሞ አሁን አሁን በዚህ አከባቢ አንጻራዊ መረጋጋት ብታይም በሌሎች ወረዳዎች አሁንም ድረስ አለመረጋጋቱ የፈጠረው ቀውስ ስለመቀጠሉ አስረድተዋል፡፡ “ባለፈው ተሸከርካሪዎች ከተቃጠሉ በኋላ እኛ ጋ አንጻራዊ ሰላም አለ፡፡ ከኛ ትንሽ ራቅ በሚሉ ቶሌ እና ሶዶ ወረዳዎች ላይ ግን አሁንም ድረስ ግጭቱ አለ” ብለውናል፡፡
የኦሮምያዉ ግድያ በሰብዓዊነት ላይ የተፈፀመ ወንጀል ተባለ
ግጭቱ ያስከተለው ማህበራዊ ቀውስ
ከምስረቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ ሃሳባቸውን የሰጡ አስተያየት ሰጪም በነሱ አከባቢ አሁን ላይ አንጻራዊ የሆነ ሰላም ብሰፍንም መንገዶች ተከፍተው አስፈላጊውን ማህበራዊ አገልግሎት ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ ማግኘት ግን አዳጋች እንደሆነ ቀጥሏል፡፡ “አሁን ህዝቡ እርቅ ፈጥሮ አንድ ገቢያ እየዋልን ሰላም ተመልሶልናል፡፡ አከባቢው ላይም የመከላከያ ሰራዊቱ ስለሚንቀሳቀስ ለሰላሙ የሚሰጋ ነገር የለም፡፡ ግን ከዚህ ክምንኖርበት ሀሮ ከምትባል አከባቢ ወጥተን ሌላ ቦታ ህክምናም ሆነ ማንኛውም ማህበራዊ አገልግሎት ለማግኘት ከባድ የሆነ የጸጥታ ስጋት አለ፡፡ ወደ ጎጃምና ሌሎች አከባቢም መንገዶች አልተከፈቱም” ብለዋል፡፡በምስራቅ ወለጋ የታጣቂዎች ጥቃት
ዶይቼ ቬለ ስለ ክልሉ አሁናዊ ሁኔታ እና ይስተዋላል ስለተባሉ የጸጥታ ችግሮቹ ከኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ እና ከክልሉ ጸጥታ እና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊዎች ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ለዛሬ አልሰመረም፡፡ ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ባወጣው ዘገባ በኦሮሚያ ግጭት የሚሳተፉ ሁሉም አካላት “ሲቪል ሰዎች ላይ ሆን ተብሎ እና በተስፋፋ ሁኔታ ከሕግ ውጪ ግድያዎች” መፈጸማቸውን ማሳወቁ ይታወሳል። የኮሚሽኑ ምርመራ የመንግሥት የጸጥታ አስከባሪዎች እና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ብርቱ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እንደፈጸሙ ነበር ያሳወቀው።
ስዩም ጌቱ
ኂሩት መለሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ