1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኦሮሚያ ክልል አለመረጋጋት እና የዜጎች ሰቆቃ

ማክሰኞ፣ ኅዳር 13 2015

በኦሮሚያ ክልል እየተስፋፋ ላለው ግጨት አስቸኳይ እልባት እንዲፈለግ ተጠየቀ። አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ (DW)የሰጡት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) እና የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) አመራሮች በክልሉ ሰላምን ለማስፈን ዋነኛው ኃላፊነት ያለበት መንግስት የኅብረተሰቡን ደኅንነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን እንዲወጣም ጠይቀዋል።

https://p.dw.com/p/4JuJq
Äthiopien | Oromiya Region
ምስል G. Fischer/blickwinkel/picture alliance

ለግጨቱ አስቸኳይ እልባት እንዲፈለግ ተጠየቀ

በኦሮሚያ ክልል እየተስፋፋ ላለው ግጨት አስቸኳይ እልባት እንዲፈለግ ተጠየቀ። አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ (DW)የሰጡት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) እና የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) አመራሮች በክልሉ ሰላምን ለማስፈን ዋነኛው ኃላፊነት ያለበት መንግስት የኅብረተሰቡን ደኅንነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን እንዲወጣም ጠይቀዋል። በተለይም የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ ለሚስተዋለው አለመረጋጋት ዋነኛው ተጠያቂ መንግስት ነው ብሏልም። 

 የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አሁን ላይ በኦሮሚያ በተለይም በምእራብ ኦሮሚያ ምስራቅ ወለጋ እና ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞኖች ውስጥ የሚካሄዱ የተስፋፉ ግጭቶች ያሳስቡኛል ብሎ ባወጣው መግለጫ፤ ሰላማዊ ህዝብ በግፍ ከቀዬያቸው እየተፈናቀሉና እየተገደሉ መሆኑን ያትታል፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ህይወት በከንቱ እየጠፉ ነው ያለው ኦነግ የንብረት ዘረፋ እና የእለት ተእለት መፈናቀሉም ከፍቷል ነው ያለው፡፡

ዘላቂ መፍትኄ የሚሻው የፀጥታ ስጋት በኦሮሚያ ክልል

ፓርቲው በመግለጫው እንዳብራራው ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ኅዳር 6 እና ሐሙስ ኅዳር 8 በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ጃርደጋ ጃርቴ ወረዳ የአሊቦ ከተማ እና በምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ የኪረሙ ከተማ በመንግስት የፀጥታ ሃይሎች እና ፋኖ ባሏቸው አካላት መውደማቸውን ተከትሎ የአከባቢው ማህበረሰብ ወደ ጫካ ጭምር መሰደዱን ጠቃቅሷልም፡፡ 
በርግጥ በኦሮሚያ ውስጥ ላለፉት ጥቂት ዓመታት ለተፈጠረው አለመረጋጋት የተለያዩ አካላት ዓላማቸውና ስማቸው የተለያዩትን አካላት ተጠያቂ ያደርጋሉ፡፡

መንግስት ክልሉን በተለይም በምዕራቡ አቅጣጫ መረጋጋት የነሳው ሸነ ያለውና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጠራው አካል መሆኑን በማስረዳት በተለያዩ ጊዜያት ወታደራዊ እልባት እንደሚሰጠው አሳውቋል፡፡ በአከባቢው በተደጋጋሚ የተፈናቀሉ በተለይም የአማራ ተወላጆችም ይህንኑን ታጣቂ ቡድን ሲወቅሱ በአከባቢው በተደጋጋሚ ተጠቅተው የሚፈናቀሉ የኦሮሞ ተወላጆች በፊናቸው ፋኖ እና የአማራ ታጣቂ ያሏቸውን አካላት ተጠያቂ ያደርጋሉ፡፡

Äthiopien IDPs in der Region Amhara
በኦሮሚያ ክልል ግጭት ተፈናቃዮች በከፊልምስል Alemenw Mekonnen/DW

ወለጋ ዞን ኪራሙ ወረዳ ከ 50 በላይ ሰዎች ተገደሉ

በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ቃል አቀባይ አቶ ለሚ ገመቹ ግን በዚህ ላይ የተለየ አስተያየት ነው የሰጡት፡፡ “መንግስት ለተፈጠረው አለመረጋጋት ቀዳሚው ተጠያቂ ነው” በማለትም ወቀሳቸውን መንግስት ላይ ሰንዝረዋል፡፡   በኦሮሚያ በሰፊው የሚንቀሳቀሰው ሌላኛው ተቀናቃኝ የፖለቲካ ድርጅት የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) ውስጥ በከፍተኛ ኃላፊነት የሚያገለግሉና የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ሙላቱ ገመቹ በፊናቸው አሁን ላይ በኦሮሚያ ውስጥ እየተስተዋለ ያለው ሁኔታ ከየትኛውም ጊዜ የከፋና አሳሳቢ ነው ይሉታል፡፡ 

ፖለቲከኞቹ ለተንሰራፋው የኦሮሚያ ግጭት ዘላቂ መፍትሄ ነው ያሉትን ሲያስቀምጡም፡ “ተፋላሚ ሃይላትን ለጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት ማምጣት ብቸኛ አማራጭ ነው” ይላሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ “የጎላ ሃላፊነትና አቅሙም ያለው መንግስት ነው” ብለዋል፡፡  

በኦሮሚያ በጸጥታ ኃይሎች ጥቃት ተፈጽሟል ስለመባሉ

ስለጉዳዩ በመንግስት በኩል ሃሳብ አስተያየት ለማስተናገድ ለኦሮሚያ ክልል ፀጥታና አስተዳደር እና ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊዎች እንዲሁም ለፌዴራል መንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስቴር ኃላፊዎች ብንደውልም ምላሻቸውን ማግኘት ለዛሬ አልሰመረልንም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ባለፈው ሳምንት ስለ ኦሮሚያ አለመረጋጋት እልባት ተጠይቀው ግን ሰላም የመንግስታቸው ቀዳሚ ዓላማ ቢሆንም ሸነ ካሉት ታጣቂ ቡድን ጋር ለድርድር መቀመጥ የሚያስችል መንገድ አለመኖሩንና በዚህ ላይ የተለየ የመንግስት አቅጣጫ አለመቀመጡን ፍንጭ ሰጥተው ነበር፡፡

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ