ዘላቂ መፍትኄ የሚሻው የፀጥታ ስጋት በኦሮሚያ ክልል
እሑድ፣ ኅዳር 4 2015ኢትዮጵያ በተለይ ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ ደም አፋሳሽ ግጭቶች እና ጦርነቶች ተደጋግመውባታል። የሰላም እና የደኅንነት ኹኔታው ከትግራይ ክልል ባሻገር አንድ ጊዜ ኦሮሚያ ክልል፤ ሌላ ጊዜ አማራ እና ቤንሻንጉል እንዲሁም አፋር ክልሎች ውስጥ ሲደፈርስ መልሶም ሲዳፈን አሁን ያለንበት ላይ ደርሰናል። ከዚህ ቀደም ጋምቤላ እና ቤንሻንጉል ክልሎች ውስጥ በተደጋጋሚ ሲስተዋል የነበረው የፀጥታ መደፍረስ ጋብ ያለ ቢመስልም አልፎ አልፎ ጥቃቶች እና ግድያዎች ግን ይስተዋላሉ።
ከሰሞኑ በኢትዮጵያ የፌዴራል መንግሥት እና በሕወሓት መካከል የሰላም ስምምነት ተደርሷል። ይኼን በርካቶች በበጎ ጎኑ መቀበላቸውን እየገለጹ ነው። ሆኖም በመላ ሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ሌሎች ግጭቶች ባሉባቸው አካባቢዎችም ሰላማዊ መፍትኄ እንዲፈለግ ተደጋጋሚ ጥሪ ይሰማል። በተለይ በኦሮሚያ ክልል ያለው የፀጥታ ችግር ከሰሞኑ ተባብሶ ቀጥሏል። በክልሉ በመንግሥት እና በታጣቂዎች መካከልም ውጊያ እንደቀጠለም ይነገራል። የወለጋ የፀጥታ ኹኔታ አፋጣኝ መፍትኄ እንደሚሻ ብዙዎች እየወተወቱ ነው።
በነቀምቴ በኩል ወደ ጊምቢ፣ መንዲና አሶሳ የሚወስደው የመጓጓዣ አገልግሎት መቋረጡ ተዘግቧል። በአካባቢዎቹ መሠረታዊ አገልግሎቶች ከተቋረጡም ከሳምንት በላይ ተቆጥሯል። ሰዎች በታጣቂዎች ይገደላሉ፤ ይታፈናሉ ሰቅጣጭ የሆኑ ኢሰብአዊ ድርጊቶች እንደሚፈጸሙም ነዋሪዎች ይናገራሉ። በኦሮሚያ ክልል የፀጥታ እና ደኅንነት ስጋቱ አሁንም እንዳለ ይነገራል። በክልሉ የተባባሰው የፀጥታ ችግር ተፈትቶ በክልሉ ብሎም በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ምን መደረግ ይኖርበታል? የእንወያይ መሰናዶ ዐቢይ ትኩረትነው።
በውይይቱ ሦስት እንግዶች ተሳታፊ ኾነዋል።
ሙሉ ውይይቱን በድምፅ ማጫወቻው መከታተል ይቻላል።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ነጋሽ መሐመድ