1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዉይይት፣ የኢትዮጵያዉያን የጋራ ትርክትና የጋራ ትርክት እጦት

እሑድ፣ ኅዳር 23 2016

በተለይ ከአፄ ኃይለ ስላሴ የመጨረሻ የአገዛዝ ዘመኖች ከ1960ዎቹ ጀምሮ ብቅብቅ ያሉ ፖለቲከኞች አንድ የቀድሞ ኢትዮጵያዊ ፖለቲከኛ አሉት እንደተባለዉ ኢትዮጵያዉያን በተለይ ስለፖለቲካ ማህበር ምስረታ ሲያስቡና ሲዘጋጁ ሁለት ሆነዉ ሶስት የፖለቲካ ፓርቲ መመስረት የሚቃጣቸዉ ናቸዉ ይባላሉ።

https://p.dw.com/p/4ZhEq
አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ርዕሰ ከተማ
የአዲስ አበባ ከተማ በከፊል ምስል Seyoum Getu/DW

ዉይይት፣ የኢትዮጵያ የጋራ ትርክትና የጋራ ትርክት እጦት

ለዛሬዉ ዉይይታችን «የኢትዮጵያዉያን የጋራ ትርክትና የጋራ ትርክት  እጦት ተቃርኖ፣ መዘዙና መፍትሔዉ የሚል ጥቅል ርዕስ ሰጥነዋል።

ኢትዮጵያ የረጅም ዘመን ታሪክ፣ ለረጅም ጊዜ የፀና የሐገረ-መንግሥት ሥርዓት፣ የዳበረ ፅሁፍና ባሕል ያላት ሐገር መሆንዋ በተለያዩ አጋጣሚዎች ይተረካል፤ ተፅፏልም።የዚያኑ ያክል ኢትዮጵያዉያን የፖለቲካኞችና  የአካዳሚ ልሒቃን በኢትዮጵያ ታሪክ፣ በሐገረ-መንግስት ምስረታ፣ በፖለቲካ ስርዓቷ   አወቃቀር፣ በቋንቋና ባሕሏ የጋራና አንድነት ላይ አይስማሙ።

እንዲያዉም በተለይ ከአፄ ኃይለ ስላሴ የመጨረሻ የአገዛዝ ዘመኖች ከ1960ዎቹ ጀምሮ ብቅብቅ ያሉ  ፖለቲከኞች አንድ የቀድሞ ኢትዮጵያዊ ፖለቲከኛ አሉት እንደተባለዉ ኢትዮጵያዉያን በተለይ ስለፖለቲካ ማህበር ምስረታ ሲያስቡና ሲዘጋጁ ሁለት ሆነዉ ሶስት የፖለቲካ ፓርቲ መመስረት የሚቃጣቸዉ ናቸዉ ይባላሉ።

የኢትዮጵያዉያን ምሕራን በየአመድረኩ የሚነሱ የትርክት ልዩነቶችን ወይም አለመግባቶችን ለማጥበብ በጥናት ላይ የተመሰረቱ ያሏቸዉን ፅሑፎች ማቅረባቸዉና የልዩነቶችን ምክንያቶች ለማሳወቅና መፍትሔ ለመጠቆም  መሞከራቸዉ አልቀረም።ይሁንና ሙከራዎቹ አንዳዴ የተነጣጠሉ፣ ሌላ ጊዜ በራሳቸዉ በምሁራኑ ዘንድ ልዩነት የሚፈጥሩ ባብዛኛዉ ግን የፖለቲካ ሥልጣን በሚይዙ ኃይላት ዉድቅ ስለሚደረጉ ሙከራዎቹ ከወረቀት ባለፍ ገቢር ሳይሆኑ መክነዋል።

የኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ
አዲስ አበባ ምስል Solomon Muchie/DW

ልዩነቶቹ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናሩ፣ የጎሳና የብሔር መልክና ባሕሪ እየያዙ ሐገሪቱን በየሰበብ አስባቡ የግጭት፣ ዉዝግብና ንትርክ መድረክ አድርገዋታል።በቅርብ አመታት በተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩ ግጭቶች፣ ዉጊያዎችና በዘር ወይም በጎሳ ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች ባንድ ወይም በሌላ መልኩ የአግባቢ ትርክት እጦት፣ የፍትሐዊ ፖለቲካዊና የምጣኔ ሐብታዊ ባለቤትነት ወይም  የክፍፍል ንፍገት ነፀብራቅ መሆናቸዉ በሰፊዉ እየተነገረ ነዉ።

ከታሪክ-እስከ ባንዲራ፣ ከሐገረ መንግስት ምስረታ እስከ ቋንቋና ባሕል የሚደርሰዉ የትርክት ተቃርኖ መሰረታዊዉ ምክንያትን፣ ያስከተለዉ ጉዳትና መፍትሔዉን ባጭሩ እንቃኛለን ሶስት እንግዶች አሉን።

ዶክተር አበባ ፈቃደ---------የሥነ ልቡና ምሑር

አቶ ባይሳ ዋቅወያ----- የሕግ ባለሙያና የቀድሞዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዲፕሎማት

ዶክተር አባድር ኢብራሒም-----በሐርቫርድ ዩኒቨርስቲ የሰብአዊ መብቶች ጥናት ክፍል ተባባሪ ኃላፊ

ነጋሽ መሐመድ